Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮሪያ ዘማቾች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ ብርድ ልብሶችና የገንዘብ ድጋፍ...

የኮሪያ ዘማቾች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ ብርድ ልብሶችና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገላቸው

ቀን:

በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ‹‹ኤልጂ›› የተባለው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ የሠራተኛ ማኅበር በሕይወት ለሚገኙ 75 የኮሪያ ዘማቾች በነፍስ ወከፍ 10,700 ብር እና 1.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ በኤሌክትሪክ ኃይል ሙቀት የሚያመነጩ ብርድ ልብሶች (ኤሌክትሪክ ሂቲንግ ማት) ድጋፍ አደረገላቸው፡፡

እያንዳንዱ የኤሌክትሪክ ብርድ ልብስ አንድ ሜትር ከዘጠና ሳንቲም ሲሆን የጎን ስፋቱ ደግሞ ዘጠና ሳንቲ ሜትር ነው፡፡ በውስጡም ማብሪያና ማጥፊያ፣ ዲጂታል መቆጣጠሪያም የተገጠመለት የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶለታል፡፡

በቅዝቃዜ ጊዜ መስመሩን ከኤሌክትሪክ ሶኬት ጋር በማገናኘትና ማብሪያ ማጥፊያውን በመጫን የኤሌክትሪክ መስመሩ ኃይል በማስተላለፍ ሙቀት ያመነጫል፡፡ ዲጂታል መቆጣጠሪያው ደግሞ የተሠራጨው ሙቀት ከተወሰነው መጠን ወይም ጣሪያ በላይ ከፍ እንዳይል ይቆጣጠራል፡፡

የሙቀት መጠኑ ከአንድ እስከ አምስት ሲሆን፣ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን አንድ ሆኖ፣ ከዚያም እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ መጠኑን ወደ ሁለትና ሦስት ከፍ ሲል ደግሞ ወደ አራት እንዲያሻቀቅብ ማድረግ ይቻላል፡፡ ጣሪያው ደግሞ አምስት ቁጥር ነው፡፡ ሙቀት መጠኑን እያየ ከፍ ዝቅ የሚያደርገው ዲጂታል መቆጣጠሪያው ነው፡፡

ይህንኑ የኤሌክትሪክ ብርድ ልብስ አለጋ ላይ በተዘረጋው ፍራሽ ላይ በማንጠፍ አለበለዚያ በተነጠፈው ልብስ ላይ አንሶላ ደርቦ መተኛት እንደሚቻል ከባለሙያዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ሁሉም ዘማቾች በስማቸው በከፈቱት የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገቢ የተደረገላቸው ሲሆን ስምንት ዘማቾች በተለይ በኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ግቢ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው አንዳንድ የኤሌክትሪክ ሂቲንግ ማት ተቀብለዋል፡፡ ለቀሩት ዘማቾችም ማኅበሩ በየአድራሻቸው እንዲላክላቸው ተደርጓል፡፡

የኤልጂ ኩባንያ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ሁዋን ያንግ የሠራተኛው ማኅበር ለኮሪያ ዘማቾች ቤተሰቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የጀመረውንም ድጋፍ ሳያቋርጥ አሁን ደግሞ የኤሌክትሪክ ብርድ ልብስ መደገፉን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ድጋፍ ለማድረግ ያነሳሳው ዘማቾቹ እርጅና እንደተጫጫቸውና በአንጻሩ ደግሞ ቅዝቃዜው እየበረታ መምጣቱን በመረዳትና ቅዝቃዜውን ተቋቁመው ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ የተጠቀሰውን ድጋፍ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ነው ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረሙስቀል ‹‹የተደረገው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ለተደረገልንም ድጋፍ እናመሰግናለን፤›› ብለዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ከፑስ በስተቀር ሁሉም ወደቦቿ በወራሪ ጠላት እጅ ሥር በነበሩበት ዘመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹ሁሉም ዓይኖች ወደ ፑሳ ይዙሩ›› የሚል መመሪያና ለዚህም ዕውን መሆን አባል አገሮች ወታደሮቻቸውን እንዲያዘምቱ ጥሪ ማስተላለፉን ገልጸው የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ችግር የሌለባቸው አገሮች እ.ኤ.አ. በ1950 የፀጥታ ኃይሎቻቸውን ወደ ሥፍራው እንዳዘመቱ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጥሪው ዘግይቶ ቢደርሳትም በ1951፣ 6037 ወታደሮቿን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እንዳዘመተች፣ ወታደሮቹም በየማያውቁት አገር፣ አካባቢ፣ የመሬት ገጽታ ግርታውን ወዲያውኑ በመቋቋም ራሳቸውን ከአካባቢው ጋር ማላመዱ ጊዜ እንዳልፈጀባቸው ነው የገለጹት፡፡

በዚህም የተነሳ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ፍልሚያ ውስጥ ገብተው በወራሪ ጠላት ላይ አይቀጡ ቅጣት በማሳረፍ ለደቡብ ኮርያ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ፣ በዚህም ውስጥ 122 ወታደሮች እንደተሰዉ፣ 637 አካል ጉዳተኛ እንደሆኑና በጠላት እጅ የተማረኩ እንደሌሉ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከ5,900 በላይ የሚሆኑ ወታደሮቿ በድል አድራጊነት ወደ ውዲቷ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ፣ ከተመለሱትም የኮሪያ ዘማቾች መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ 75 ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ፣ ከቤት የማይወጡ የመንቀሳቀስ አቅማቸው እየተዳከመ የመጣ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፡፡

ማኅበሩን ለልጆቻችሁ ወይም ለልጅ ልጆቻችሁ ታወርሳላችሁ እየተባለ ይወራል፣ ምናልባት ይህ ጉዳይ ካልተሳካ የማኅበሩ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል ብለው ያሰባሉ? ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሎኔል እስጢፋኖስ ሲመልሱ፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ከሲቪል ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተን ‹እኛ ለምታስረክቡት አካል እንነግራችኋለን› የሚል መልስ ሰጥተውናል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ለየትኛው አካልና መቼ እንደሚያስረክቡ እንዳልተገለጸላቸው፣ ይህም ሆኖ ግን መልሱን በተስፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑና መልስ እስካላገኙ ድረስ ደጋግመው ከመጠየቅ ወደኋላ እንደማይሉ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...