- የዋሊያዎቹ አጥቂ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል
በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ የምድቡን ጨዋታ ከማድረጉ አስቀድሞ ለአቋም መለኪያ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ይገጥማል፡፡
ዋሊያዎቹ የምድባቸውን ሦስተኛና አራተኛ ጨዋታዎች የሚያደርጉ ሲሆን፣ ለቅድመ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ የሩዋንዳ አቻቸውን እሑድ መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚገጥሙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ጨዋታውን ከጊኒ አቻው ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ያከናውናል።
የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ዝግጅቱን ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረው የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አጥቂ አቡበከር ናስር ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገም ባለመቻሉ ከዋሊያዎቹ ስብስብ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። አቡበከር ከሁለት ወራት በፊት ክለቡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከኦርላንዶ ፓይሬትስ ጋር በነበረው ጨዋታ በቁርጭምጭሚቱ ላይ አጋጥሞት በነበረው ጉዳት ሙሉ በሙሉ ማገገም ባለመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በምትኩም የኢትዮጵያ መድን አጥቂ የሆነውና በቻን ውድድር ላይ የብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ኪቲካ ጀማ ጥሪ እንደተደረገለት ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በማጣሪያው ምድብ አራት ከግብፅ፣ ከማላዊና ከጊኒ ጋር የተደለደለች ሲሆን፣ የምድቧን የመጀመርያ ጨዋታ በማላዊ 2 ለ1 ስትረታ፣ በሁለተኛው ምድብ ጨዋታ የግብፅ አቻዋን 2 ለ0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ዋሊያዎቹ ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ወደ በአይቮሪኮስት ለሚያደርጉት ጉዞ ውሳኝነት እንዳለው ዕሙን ነው፡፡
ከሁለት ጨዋታ 3 ነጥብና 1 የግብ ልዩነት በመያዝ ምድቡን በመምራት ላይ ትገኛለች።
ብሔራዊ ቡድኑ ከወራት በፊት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ሲከናወን በነበረው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ውድድር ላይ የተካፈለ ቢሆንም፣ ከምድቡ ሳያልፍ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ በውድድሩ ላይ የነበረውን ደካማ እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ ለተመዘገበው ውጤት የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ይረዳው ዘንድ፣ በቻን ውድድር ላይ የታዩ ክፍተቶችን አርሞ ከምድቡ ማለፍ የሚችልበት አጋጣሚን መጠቀም እንደሚገባው እየተገለጸ ይገኛል፡፡
አሠልጣኝ ውበቱ ብሔራዊ ቡድኑ ለካሜሮኑ አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ እያከናወነ ባለበት ወቅት፣ የአሠልጣኝነት መንበሩን ከአሠልጣኝ አብርሃም መብራሃቱ ላይ ከተረከቡ በኋላ በካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ፣ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ፣ እንዲሁም በቻን ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኑን መምራት ችለዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአገር ውስጥ በተለያዩ ሊጎች እየተጫወቱ ለሚገኙ ለበርካታ ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሠልጣኙ አዳዲስ ተጫዋቾችና በብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በሊጉ ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል፣ ቡድኑ ወጥ የሆነ አቋም እንዲኖረው እየሠሩ እንደሚገኙ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
በአንፃሩ የዋሊያዎቹ ስብስብ ከዚህ ቀደም ከነበረው እንቅስቃሴ በቁጥር አንፃር የተሻለ ቢመስልም፣ በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚሠራቸው ስህተቶች ዋጋ ሲያስከፍለው ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ ዋሊያዎቹ በካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ላይ በምድብ አንድ ጨዋታ በተከላካይ የተሠራ ስህተት፣ እንዲሁም በአልጄሪያው የቻን ውድድር በግብ ጠባቂ የተሠራው ስህተት ብሔራዊ ቡድኑን ከምድቡ ማለፍ እንዲሳነው ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚስተዋለው ተደጋጋሚ ስህተት ምክንያት አሠልጣኙን ለትችት መዳረጉ አልቀረም፡፡ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድቡን በበላይነት እየመራ የሚገኘው የዋሊያዎቹ ስብስብ፣ ደረጃውን አስጠብቆ ወደ አይቮሪኮስት የሚያደርገውን ጉዞ ለማረጋገጥ ስህተቱን አርሞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
የካፍን መሥፈርት ያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ፣ በአገር ውስጥ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳታከናውን የታገደችው ኢትዮጵያ፣ ብሔራዊ ቡድኗ የማጣሪያ ጨዋታውን በአገር ውስጥ ካከናወነ ሁለት ዓመታትን ተሻግረዋል፡፡ በአገር ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙት ስታዲየሞች ግንባታቸው መጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ደጅ በመጥናት ጨዋታዎችን ለማድረግ ተገደዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ከካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ደጅ እየጠኑ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ እንደሚገኘ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ለውድድር ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲሁም በውድድሮች ላይ ለመሳተፍ መንግሥትን የገንዘብ ድጋፍ ሲጠይቅ ከርሟል፡፡
ምንም እንኳ በአገሪቱ ያሉት ስታዲየሞች እየተገነቡና እየታደሱ ቢገኙም፣ መጠናቀቅ ያለመቻላቸው ሚስጥር የበጀት እጥረት እንደሆነ ይነሳል፡፡ በአንፃሩ ብሔራዊ ቡድኑ ከአገር ውጪ ዝግጅት ለማድረግ እንዲሁም በውድድር ላይ ለመካፈል ከመንግሥት የሚጠይቀውን የገንዘብ ድጋፍ ለምን የስታዲየሞቹ ግንባታ ላይ አውሎ ማፍጠን አልተቻለም? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡