- የሐዋሳ፣ አዳማና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ አቅርበዋል
- የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተከትሎ አክሲዮን ማኅበሩ ቅድመ ይግባኝ ጠይቋል
በድሬዳዋ ሲከናወን የቆየው የቤቲኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በዝናብ ምክንያት መቋረጡን ተከትሎ፣ ቀጣዩን መርሐ ግብር ለማስቀጠል ስታዲየም ፍለጋ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የሊጉን 17ኛ ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ሐዋሳና ኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ቢያስተናግድም፣ በከተማዋ በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ ምክንያት ቀጣዩን የሳምንቱ ጨዋታ ማድረግ እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስታውቃል፡፡
በዚህም ምክንያት የ2015 ዓ.ም. የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ኛ ሳምንት ሊካሄዱ የነበሩ ቀሪ ጨዋታዎች ለሌላ ተስተካካይ መርሐ ግብር መዘዋወራቸውን አክሲዮን ማኅበሩ ገልጿል፡፡
በመርሐ ግብሩ መሠረት ቀጣይ የሳምንቱ ጨዋታዎችን ለማድረግ ቢታሰብም፣ በከተማዋ በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ ሜዳው በመበላሸቱና በቀላሉ ሊያገግም ባለመቻሉ አወዳዳሪው አካል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ቀሪ የከተማው የመጨረሻ ጨዋታዎች መሰረዙን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ውድድሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተቋርጦ በተመረጠ ቦታ መካሄዱ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከ18ኛው ሳምንት በኋላ ባለው ወቅት በተስተካካይ መርሐ ግብር ይስተናገዳሉ ተብሏል፡፡
በድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ሊደረጉ መርሐ ግብር የወጣላቸው ጨዋታዎች፣ መቻል ከአዳማ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በቀጣይ በተስተካካይ መርሐ ግብር እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡
ቀጣይ መርሐ ግብሮችን ለማስተናገድ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዳማ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት የአክሲዮን ማኅበሩ የግምገማ ቡድን ወደ አዳማና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ማቅናታቸው ተሰምቷል፡፡
የግምገማ ቡድኑ ቀጣዩን የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር የሚያስተናግደውን ከተማ ለይተው ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን ይፋ እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአይቮሪኮስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት መጀመሩን ተከትሎ ሊጉ የሚቋረጥ ሲሆን፣ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን ከሚጀምርበት አሥር ቀናት አስቀድሞ እንዲሁም የማጣሪያ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ አምስት ቀናት፣ በአጠቃላይ ለ15 ቀናት እንደሚቋረጥ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ጨዋታውን ከጊኒ አቻው ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ካከናወነ በኋላ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. አክሲዮን ማኅበሩ ይፋ በሚያደርገው ስታዲየም የሊጉ 18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ35 ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ፣ ባህር ዳርና መድን በ30 ነጥብ በግብ ተበላልጠው ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ይከተላሉ፡፡ ሐዋሳ ከተማ በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አርባ ምንጭ ከተማ በ18 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ አትዮ ኤሌክትሪክ በ8 ነጥብ 15ኛ እንዲሁም ዘንድሮ ወደ ሊጉ ያደገው ለገጣፎ ለገዳዲ በ6 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ውስጥ እየታተሩ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል የኢትጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ከለገጣፎ ለገዳዲ እግር ኳስ ክለብ ጋር ተያይዞ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ይገባኝ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል፡፡
የለገጣፎ ለገዳዲ እግር ኳስ ክለብ ክስ ማቅረቡን በመጠቀስ የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ዓርብ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአክሲዮን ማኅበሩ ማቀረቡን ተገልጿል፡፡ ይህን ተከትሎም ማክሰኞ መጋቢት 5 ቀን በዲሲፕሊን መመርያው አንቀጽ 98 በተመለከተ መሠረት የኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበሩ በ16 ነጥቦች ላይ ቅድመ ይግባኝ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማስገባቱን አስታውቋል፡፡