Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፈጽሟል በተባለው የሕግ ስህተት የግማሽ ቢሊዮን ብር ክስ ቀረበበት

ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፈጽሟል በተባለው የሕግ ስህተት የግማሽ ቢሊዮን ብር ክስ ቀረበበት

ቀን:

  • ተቋማት ዝግ የሚሆኑባቸው ቀናትን አስታኮ የተሰጠው ብይን በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ መሠረት በተፈጸመ የሕግ ስህተት፣ ግምቱ 500,000,000 ብር የሆነ ይዞታ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል በሚል ክስ ቀረበ፡፡

ጉዳት እንደደረሰበት በመግለጽና በአዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 48 ድንጋጌ መሠረት፣ ውሳኔው እንዲከለስለት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረበው፣ ፋና ቦሌ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ ባቀረበው ክስ እንዳብራራው፣ ማኅበሩ በአዋጅ ቁጥር 985/2009 የተቋቋመ ነው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ክልል ውስጥ የሚገኙ ማዕከላት በተለምዶ 17/19 (መለያ ቁጥር AA 000060305208) እና 17/23 (መለያ ቁጥር AA000060305433) ተብለው የሚጠሩ የዕለት ተዕለት የፍጆታ ዕቃዎችን ለማኅበረሰቡ የሚያቀርቡና ከ3,000 በላይ አባላት የሚሠሩበትና የሚተዳደሩበት ማዕከል ነው፡፡

ማዕከሉ ለበርካታ የአካባቢውና ከተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ለሚመጡ ነዋሪዎች፣ ለውጭ አገር ዜጎች፣ ለወጣቶች፣ ለአዛውንቶች፣ የእግር ኳስ፣ የቴኒስና ሌሎች ስፖርቶች ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምግብ አቅርቦት (በተመጣጣነኝ ዋጋ) የመጠጥ፣ የስቲምና የአዳራሽ ኪራይ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ማኅበሩ በክሱ አብራርቷል፡፡ ይዞታዎቹን ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ እየሠራባቸው እንደነበርና ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደንብ ቁጥር 46/2004 መሠረት በይዞታነት ተላልፈውለት የራሱ በማድረግ እየሠራበት መሆኑንም ማኅበሩ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ክስ ላይ አብራርቷል፡፡

ይዞታውን ይዞ እያስተዳደረ መሆኑን በሰነዶች ጭምር የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ይዞታዎቹ ‹‹ኤምደብሊውኤስ ትሬዲንግና በቀለ ለገሠና አረጉ አበበ›› ለተባሉ ግለሰቦች ለአፓርትመንት፣ ለሞልና ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ እንዲውሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ ማስተላለፉን በመግለጽ፣ ማኅበሩ ስለሀብቶቹ እንዲያስረክብ ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በደብዳቤ እንዳሳወቀው በክሱ ጠቅሷል፡፡

ማኅበሩ ደብዳቤ እንደደርሰው በቦሌ ክፍለ ከተማና ወረዳ 03 መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤትንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

የማኅበሩ አባላት እንዳይሰበስቡና በማዕከላቱ እንዳይገኙ ተደርጎ፣ የቦታ ልኬትና የንብረት ግምት ሥራ በማካሄድ፣ ተከሳሾቹ ‹‹መሬት ለግለሰቦች ስለሚተላለፍበት ሁኔታ ተደንግጎ የሚገኘውን አዋጅ ቁጥር 719 (10)›› በመተላለፍ ተከሳሾች ማሟላት የሚገባቸውን ሳያሟሉ ቀጥታ ወደ ካሳ ግመታ በመግባት፣ በአዋጅ ቁጥር 1161 (7/1) እና ደንብ ቁጥር 472 (8)ን በመተላለፍ፣ ማኅበሩ ማግኘት የሚገባውን የቅድሚያ ዕድል እንዲያጣ በማድረጋቸው ሁከት ስለተፈተጸመበት ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምለት፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149 (1) ድንጋጌ መሠረት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን በክሱ አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከማኅበሩ የቀረበለትን ክስ ተመልክቶና ተከሳሾች ምላሽ እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ፣ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ‹‹ጉዳዩን የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የለኝም፤›› በማለት፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 254 (2) ድንጋጌ መሠረት መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

በመሆኑም የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 መሬት ልማት አስተዳደር ጽሕፈት በዕለቱ ለማኅበሩ በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፣ ማዕከሎቹን በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲያስረክበው ማኅበሩን ጠይቋል፡፡ ማኅበሩ በዕለቱ ይግባኝ ማለት ወይም አዲስ ክስ ማቅረብ ባለመቻሉና በቀጣይ ቀናትም ተቋማት ዝግ የሚሆኑበት ቅዳሜና እሑድ በመሆናቸው፣ የቀበሌ አስተዳደሩ በማግሥቱ ‹‹ካቢኔው ወስኖላቸዋል›› የተባሉት ድርጅትና ግለሰቦች በማዕከሉ ላይ የግንባታ ሥራ መጀመራቸውን የማኅበሩ አባላት አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥረ 205 ድንጋጌ መሠረት በቃለ መሃላ አረጋግጦ ክስ ላቀረበበት ፍርድ ቤት የዕግድ አቤቱታ አቅርቦ እየተጠባበቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ማዕከሉ በአዋጅ ቁጥር 729/2004 አንቀጽ (10) መሠረት በሕግ ጥበቃ ሊደረግለት ቢገባም፣ ገና የዕግድ ትዕዛዝ እንዳልተሰጠው ጠቁሞ፣ በአጠቃላይ አዋጁ ቁጥር 1183/2012፣ 729/2004 እና 1161/2011 ድንጋጌዎችንና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን ደንብ ቁጥር 472 ድንጋጌዎችን የጣሰ መሆኑንም ማኅበሩ በክሱ ጠቅሷል፡፡

አስተዳደሩ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር አንቀጽ 401 (1) ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ የተፈጸመ በመሆኑ፣ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የወሰነው ውሳኔ (ካቢኔው) ፉርሽ ሆኖ ይዞታውን የያዙት ባለሀብቶችን እንዲያስለቅቅለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...