Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ፣ የሰሜኑን ጦርነት ለመቋጨት ይረዳል ተብሎ የሚታመንበትን ውይይት ከፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትና ከትግራይ ክልል ተወካዮች ጋር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ቂምና ቁርሾ እንዲሽርም የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ተቀርፆ ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ለሰላም ይበጃሉ የሚባሉ ተግባራት እየተከናወኑ ባሉበት በዚህ ጊዜ ዜጎች ለዓመታት የኖሩበት ጎጆ እየፈረሰ ሕገወጥ ተብለው መፈናቀላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ባለቤቶችና ሾፌሮች በጊዜያዊ ዕግድ ስም ሥራቸውን እንዲያቆሙ መደረጋቸውን፣ በጦርነትም ሆነ በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖች በአግባቡ ዕርዳታ እየደረሳቸው አለመሆኑን፣ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ መኖርም ሆነ መሥራት አዳጋች መሆኑንና የመሳሰሉ እሮሮዎች በየቀኑ ይሰማሉ፡፡  ዜጎች ሰላምና ደኅንነታቸው ተቃውሶ የመንግሥት ያለህ እያሉ ሲጮሁ መፍትሔ መፈለግ ያለበት መንግሥት ነው፡፡

ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት፣ ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማከናወንና ነፃነታቸው ተጥብቆ እንዲኖሩ የሕግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ የሠፈሩት የዜጎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶችም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በሕግ ከተደነገገው ውጪ ዜጎች ነፃነታቸውን አያጡም፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወርቃማ ቃላት የሠፈሩት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን ወርቃማ የሕግ ትዕዛዛት እየተላለፉ ዜጎችን የሚደበድቡ፣ የሚዘርፉ፣ የሚገድሉ፣ ከመኖሪያም ሆነ ከሥራ ገበታቸው የሚያፈናቅሉ አሉ፡፡ እነዚህ በሕግ አደብ የማይገዙ ከሆነ የሕግ የበላይነት አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍነው ዜጎች በነፃነት መኖር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

አንድ ዜጋ በነፃነት ካልኖረ፣ የመሰለውን ሐሳብ ካላራመደ፣ የሚፈልገውን በነፃነት ካልመረጠ፣ በአመለካከቱ ምክንያት የሚደበደብ፣ የሚታሰርና የሚንገላታ ከሆነ፣ ከሥራና ከመኖሪያ ቀዬው ከተፈናቀለ እሪታውና ጩኸቱ ይቀጥላል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ፖሊሲዎችና ሕጎች ዝግጅቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በውክልና ተሳታፊ ካልሆነ፣ በሥልጣን የሚባልጉ ሹማምንት የሚፈነጩበት ከሆነ፣ በየደረሰበት ጉቦ እየተጠየቀ የሚንገላታ ከሆነ፣ የመደራጀት መብቱ ከተገደበ፣ በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች ከሆነና ምሬቱ ጣሪያ ከነካ ጩኸቱ የትም ድረስ ይሰማል፡፡ እነዚህን ችግሮች ፈር አስይዞ አገር ማስተዳደር የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ ሰብዓዊ መብትን ለማክበርና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ አሁንም ብዙ መንገድ የሚቀር ከሆነ ያሳዝናል፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ አገሩ ስትለማ እየራበውም ቢሆን ይታገሳል፡፡ ነገን ተስፋ ያደርጋል፡፡ በእብሪተኞችና በጥጋበኞች ምክንያት ግን በገዛ አገሩ ባይተዋር ተደርጎ ሲጎሳቆል ቁጣው ይቀሰቀሳል፡፡ መብቱ ሲረገጥና ሲንገላታ፣ ሲታሰርና ሲሰደድ፣ በገቢው ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ ሳይኖር በየቀኑ በሚጨምረው ዋጋ ምክንያት የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶት የሚቀምሰው ሲያጣ ጩኸቱ ወደ አመፅ ይለወጣል፡፡ ሰሞኑን በምግብ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው ከአቅም በላይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ የመንግሥትን ልዩ ዕርምጃ ይፈልጋል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን በሕግ ዋስትና ያገኙባቸውን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ማጣጣም የሚችሉት፣ አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ስምምነቶችና ሰነዶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ሲተረጎሙና ተፈጻሚ ሲሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መብቱን የሚጠይቅ ዜጋ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ አቤቱታ ሲያቀርብ፣ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት አሠራር ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለመንግሥት የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎች ወደ ሁከትና ብጥብጥ ተቀይረው፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጠፍ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም እንዲሁ፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር መሠረት የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታትና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አሉ፡፡ መላ አገሪቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በፌዴራል መንግሥት ሲመሩ፣ የክልል ጉዳዮችም በክልል መንግሥታት ሥር ይጠቃለላሉ፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የክልል ሕገ መንግሥቶች ዜጎች በሕግ የበላይነት ሥር እንዲተዳደሩ ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ በርካታ ችግሮች ናቸው ያሉት፡፡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሾቻቸው ሥልጡንነት እየጎደላቸው ዜጎች በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት እየተሰማቸው ነው፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) በአገራቸው ልማት ተሳታፊ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎ በዓይነትም በመጠንም መጨመር ሲገባው፣ ዓይንህን አልይ የሚል ዓይነት የፍረጃ ፖለቲካ ተገቢ አይደለም፡፡ ዳያስፖራው በምልዓት ተንቀሳቅሶ በአገሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ እንዲያደርግ መንግሥት ኃላፊነት አለበት፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ይዞ ዳያስፖራው የአገሩ የልማት አጋር ይሆን ዘንድ፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊፈጠር ይገባል፡፡ ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር ሊኖረው የሚገባ ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ ይገንባ፡፡ ፖለቲካው ውስጥ ያለ ጋሬጣ እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ ዳያስፖራው በአመለካከቱ ምክንያት መገለል የለበትም፡፡ በብርታታቸውና በአርዓያነታቸው የሚጠቀሱ የዳያስፖራ አባላት እየተወደሱ፣ ሌሎች ለአገራቸው በተለያዩ መስኮች አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ እንዲበረታቱ ይደረግ፡፡ በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ በሌሎች ልዩነቶች ሳቢያ ሳይገደቡ፣ ለእናት አገራቸው ተጠቃሽ የሆኑ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የቁርጥ ቀን የዳያስፖራ አባላት እንዳሉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የዳያስፖራውና የአገሩ ትስስር በዚህ መንፈስ መጠናከር ሲገባው፣ ጋሬጣ ፈጣሪ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ ልዩነትን ማክበር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ልዩነት በጠላትነት የመፈራረጅና የመጨካከን መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የታየውን የአገሪቱን የፖለቲካ አካሄድ ለሚመረምር ልዩነትን ማቻቻል ወይም በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ባለመቻል ብቻ በርካታ ዜጎች ለሞት፣ ለሥቃይና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በዚህ ዘመን ልዩነትን ይዞ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እየተቻለ መወነጃጀልና በጥላቻ መገፋፋት ከፍቷል፡፡ ራስን አነሳስቶ ግማሽ መንገድ በመጓዝ ከተፎካካሪ ጋር ለመነጋገር ከመሞከር ይልቅ፣ በሩንና መስኮቱን በመቀርቀር አትድረስብኝ ማለት ቀላልና ተራ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የጽንፈኝነት የብሔር ፖለቲካ በመጦዙ ደግሞ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚለው ፍረጃ የከፋ ጠላትነትን እያስፋፋ፣ የጋራ ማንነት የሆነውን ኢትዮጵያዊነት እየተገዳደረ ነው፡፡ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ካልተደረገለት ነገሮች እየከበዱ ይሄዳሉ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...