Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግሥት ለደረሰው ጉዳት በመንግሥት ላይ ክስ ተመሠረተ

በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግሥት ለደረሰው ጉዳት በመንግሥት ላይ ክስ ተመሠረተ

ቀን:

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግሥት በሻሸመኔና በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለደረሰው ጉዳት፣ መንግሥትን ተጠያቂ ያደረገ ክስ መመሥረቱን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ሦስት ክሶችን (Strategic Litigation Cases) አዘጋጅቶ፣ ጉዳዮቹን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረቡን ገልጿል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ጉዳዮችን አጣርቶ ለፍትሕ አካላት በማቅረብ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ድርጅቱ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱና ዋናው መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

በዚህ ረገድ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል ያሏቸውን በአጠቃላይ አራት ክሶችን ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን፣ የድርጅቱ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሕግ ባለሙያው አቶ በላቸው ግርማ አስረድተዋል፡፡

ሥልታዊ ሙግት (Strategic Litigation) መንግሥት ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀር በፍርድ ቤት ግዴታውን እንዲወጣ የሚደረግበት ሒደት መሆኑን ያስረዱት አቶ በላቸው፣ በአራት ጉዳዮች ድርጅታቸው በመንግሥት ላይ ክስ መመሥረቱን አመልክተዋል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም የለገጣፎ አካባቢ ነዋሪዎችን ቤት መፍረስ የተመለከተ ክስ አቅርበናል፡፡ አሁን ደግሞ በሴቶች ላይ በሥራ ቦታ የሚፈጸም ወሲባዊ ትንኮሳን የሚከላከል ሕግና ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚጠይቅ አቤቱት አቅርበናል፡፡ በአዲስ አበባ በጎዳና የሚኖሩ ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል የሚያስችል ሕግና ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚጠይቅ አቤቱታ አቅርበናል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከሰኔ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሉ ቀናት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁከት፣ ብጥብጥና ግድያዎችን በተመለከተ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚጠይቅ ክስ መሥርተናል፤›› በማለት ነው የመሠረቷቸውን የክስ ዝርዝሮች ያብራሩት፡፡

የሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በሻሸመኔና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ ሪፖርቶችን፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ማቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡ መንግሥት ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ በእነዚህ ሪፖርቶች ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸውንም አስታውሰዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በተናጠል ጥቂት ሰዎች በግድያ ወንጀሎች ከመጠየቃቸው ባለፈ፣ ብጥብጥና ግድያውን የመራው አካል ተጠያቂ አልተደረገም፡፡ ጉዳቱን ማስቀረት ካልተቻለም መቀነስ እየተቻለ ይህ አልተደረገም፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ የተነሳ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ በኦሮማያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በፌዴራል መንግሥትና በዓቃቤ ሕግ ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ክስ መመሥረቱን ጠቁመዋል፡፡

ከሃጫሉ ግድያ ጋር ከተያያዘው ክስ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ መንግሥት መጠለያ ሊሰጣቸው ሲገባ፣ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በመጣ ቁጥር የሚያሳድዳቸውና የሚያፍሳቸው የጎዳና ተዳዳሪዎችን የተመለከተ ክስም መቅረቡን አመልክተዋል፡፡ በኢንዲስትሪ ፓርኮች በሰፊው ይፈጸማል የሚባለውን የፆታና የወሲብ ጥቃት ለሕግ መቅረቡንም አውስተዋል፡፡ እነዚህ ክሶችም እስከ ዘጠኝ ወራት የፈጀ ጥናት፣ ውይይትና መረጃ ማሰባሰብ ተካሂዶባቸው እንደቀረቡ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ከዚህ ቀደም ተቋሙ ያቀረበው የአንዳንድ ክልሎች ሕገ መንግሥቶች አድሏዊና ኢሕገ መንግሥታዊ ናቸው የሚል አቤቱታ፣ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በመታየት ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...