የአፍሪካ አገሮችን የፋይናንስ አጠቃላይ ሁኔታ በማጥናት ይፋ የሚያደርገው አብሳ አፍሪካ ፋይናንሺያል ማርኬትስ ኢንዴክስ፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2022 ጥናት ከተደረገባቸው 26 የአፍሪካ አገሮች የመጨረሻ ግርጌ ላይ እንደምትገኝ አመላከተ፡፡
በ26 የአፍሪካ አገሮች የሚገኘውን የፋይናንስ ዘርፍ (ገበያ) ግልጽነትና ሳቢነትን የመዘነው የአብሳ ግሩፕና ዘ ኦፊሻል ሞኒተሪና ፋይናንሺያል ኢንስቲትዩሽን ፎረም (OMFIF) ጥናት፣ የአገሮችን ያለፈው ዓመት የፋይናንስ ሁኔታን ለመመልከት አርባ አመላካች ያላቸውን ስድስት የመገምገሚያ መሥፈርቶችን መሠረት በማድረግ ደረጃ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
የአገሮች የፋይናንስ ገበያ አድማስ ምን ያህል የሰፋ ነው? አገሮች የሚያቀርቧቸው የፋይናንስ አገልግሎቶች ምን ያህል አማራጮች ብዙ ናቸው? ስብጥሮቹስ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው? ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ያላቸው አመቺነትና የማስገኘት አቅም አላቸው ወይ? በሚለው ላይ ከተገመገሙት 26 አፍሪካ አገሮች፣ ከመቶ አሥር ነጥብ የተሰጣት ኢትዮጵያ በዝርዝር የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በሌላ በኩል ከውጭ ምንዛሪ አንፃር አስፈላጊ ለሆነው ገቢ ምርት ምን ያህል በቂ ክምችት ይገኛል? በአገር ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ልውውጥ፣ ወጥነት ያለው የልውውጥ ተመንስ ምን ይመስላል? የሚለው ሲመዘን እንዲሁ ዝቅተኛ ነጥብ ከተሰጣቸው ሦስት አገሮች ተርታ አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች፡፡
የተረጋጋ የፋይናንስ፣ የታክስና የሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን አስመልክቶ በተደረገው ግምገማ ከ26 አገሮች በመጨረሻ ደረጃ ላይ የሰፈረችው ኢትዮጵያ፣ በተለይም የዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝና የሪፖርት ደረጃዎች አጠቃቀምና የፋይናንስ መረጃዎችን በማጠናከር ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የአገሮች ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለመመዘን በቀረቡት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ)፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ብድር፣ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ውሳኔዎች ነጥቦች ከመጨረሻዎቹ ሦስት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ሆና ተቀምጣለች፡፡
ከሕግ ደረጃዎች ተፈጻሚነት አንፃር ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ተጠቅሶ፣ ነገር ግን በተደረገው ዝርዝር ውጤት ኢትዮጵያ በመጨረሻ ላይ ከተዘረዘሩ አራት አገሮች ውስጥ አንዷ መሆኗን ጥናቱ ያሳያል፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪሺየስ፣ ናይጄሪያ ይፋ በተደረገው የ26 አገሮች ዝርዝር ውስጥ በቅደም ተከተል የተሻለ ውጤት ያገኙ አገሮች ሆነዋል፡፡ ኡጋንዳ፣ ናሚቢያና ኬንያ እንዲሁ ተግባራዊ ያደረጓቸው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ከቀዳሚዎች አገሮች ዝርዝር ውስጥ እንዲቀመጡ እንዳደረጋቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡
በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት በአፍሪካ አገሮች ላይ የተደረጉ ዓበይት የፋይናንስ ሁነቶችን የዘረዘረው ሪፖርቱ፣ ለአብነትም ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የጀመረቻቸው እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎች ይገኝበታል፡፡
በሩሲያና በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ የተፈጠረው የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት መዛባት ሌላው ጉዳይ ሆኖ ሲጠቀስ፣ በተለይ የካፒታል ማሸሽና ከፍተኛ ዕዳ የመክፈል ጫና፣ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2022 በአይኤምኤፍ ብድር የመክፈል አቅማቸው ሥጋት ላይ ያሉ አገሮች በሚል ከዘረዘራቸው ስምንት የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አስታውሷል፡፡