Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት አመራሮችን አንደሚያነጋግሩ ተገለጸ

አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት አመራሮችን አንደሚያነጋግሩ ተገለጸ

ቀን:

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሰክሬታሪ (ሚኒስትር) አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚያደርጉት የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከሌሎች ፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ከሕወሓት አመራሮች ጋርም ተገናኝተው እንደሚወያዩ ተገለጸ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሞሊ ፊ፣ አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝትን አስመልክቶ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ብሊንከን የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት አመራሮችን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

‹‹ሴክሬታሪ ብሊንከን ወደ መቀሌ ባይጓዙም ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከትግራይ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ እንደሚገናኙ ይጠበቃል፤›› ሲሉ ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የኤርትራ ጦር ከትግራይ ለቆ ስለሚወጣበት ሁኔታ ይወያዩ እንደሆነ የተጠየቁት የአፍሪካ ረዳት ኃላፊዋ ሞሊ ፊ፣ ከዚህ በፊትም ቢሆን አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በነበራቸው ግንኙነት፣  የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ ደጋግመው ያነሱ እንደነበር በመጀመሪያ መታወስ አለበት ብለዋል። 

በትግራይ የነበረው ጦርነት መቆሙና አብዛኛው የኤርትራ ጦርም መውጣቱን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የአፍሪካ ዩኒየን የቁጥጥር፣ ክትትልና ማረጋገጫ ሥርዓት አረጋግጧል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በግጭት ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ሁሉ አስፈላጊ የሆነ የሰብዓዊ ዕርዳታ መቅረቡንና በከፍተኛ ሁኔታ ተቋርጦ የነበረው አገልግሎትም ለክልሉ እንደገና መቅረብ መጀመሩንም አሜሪካ ትገነዘባለች ሲሉ አክለዋል።

‹‹ስለዚህ የኤርትራ ጦር ከአካባቢው እንደወጣ እንገነዘባለን፡፡ ቢሆንም ግን ስለዚህ ጉዳይ መወያየታችንን እንቀጥላለን፤›› ሲሉ ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት የአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት ቀድሞ ወደ ነበረበት መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ እንደሆነ የተጠየቁት የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ኃላፊዋ በሰጡት ምላሽ፣ በዚህ ጉብኝት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ መደበኛ ሁኔታ ይገባል የሚለውን ሐረግ ለመጠቀም እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

‹‹እኛ ማድረግ የምንፈልገው ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማደስ ነው። በታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ አጋርነት እንዳለን ይታወቃል። ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ዕድገት ትልቅ ሚና ተጫውታለች፣ እንዲሁም በምትገኝበት ቀጣና ውስጥም በኃላፊነት ጠቃሚ ሚና ነበራት። ስለዚህ ከኢትዮጵያ ስፋትና ተፅዕኖ እንዲሁም አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ካላት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ጋር የሚመጣጠን አጋርነት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲኖረን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል።

‹‹ነገር ግን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስና ወደፊት ለመውሰድ፣ የቅርቡን ግጭት ጨምሮ አገሪቱን ለብዙ አሥርት ዓመታት ወደ ኋላ የመለሰውን አጠቃላይ የብሔር ግጭት አዙሪት ለመስበር የሚረዱ ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ በኩል ሲተገበሩ ማየት እንፈልጋለን፤›› ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማት ግጭት እጅግ አደገኛና በሁሉም ወገኖች አሰቃቂ ግፍና በደል የተፈጸመበት ሲሆን፣ በዚህ ላይ የገጠማት ድርቅ ሲታከልበት ደግሞ የአገሪቱን መረጋጋትና ኢኮኖሚዋን በእጅጉ የሚረብሽ እንደሚሆን ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ግን አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ፣ ጦርነቱን በሰላም ስምምነት ለማስቆም የተሳተፉትን ሁሉንም አካላት ዕውቅና ለመስጠትና ለኢትዮጵያ አዎንታዊ አዲስ አቅጣጫን በማጎልበት ረገድ አሜሪካ ስለሚኖራት ሚና ለመነጋገር መሆኑን የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ኃላፊዋ ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...