Friday, March 31, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉየሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና  የታዩ  ለውጦች በኢትዮጰያ ፦ ከተመረጡ የአበባ እርሻዎች...

የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና  የታዩ  ለውጦች በኢትዮጰያ ፦ ከተመረጡ የአበባ እርሻዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

Published on

- Advertisment -

የሴት ሰራተኞች የራ ሁኔታ እና  የታዩ  ለውጦች በኢትዮጰያ ፦ ከተመረጡ የአበባ እርሻዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.) ካለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት በላይ ጀምሮ በዜጎች ማህበራዊ ህይወትና ምጣኔ ብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የምርምር ስራዎችን  እያከናወነ ይገኛል፡፡ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በተለያዩ የአገራችን  ማህበራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ መድረኮችን በማዘጋጀትና ውጤታማ የፖሊሲ ትግበራና አዳዲስ አማራጭ አቅጣጫዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳየት  ጥሩ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኝ   መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

ኤፍኤስኤስ እየተከናወኑ የሚገኙ የጥናት ውጤቶችን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ለህብረተሰቡ በሰፊው እንዲደርስ ከሚጠቀምባቸው   መንገዶች አንዱ   የህትመት ውጤቶች  ጋዜጦች  ሲሆኑ  በዚህ አምድም በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በሚካሄዱ የምርምር ስራዎች ላይ የተመሰረቱ የጥናት ውጤቶች አንዱ የሆነውንና  በርካታ አንጋፋ ተመራማሪዎች የተሳተፉበትንና   ለፖሊሲ አውጭዎች በርካታ ምክረ ሀሳቦችን ያካተተውን‹‹የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና የታዩ ለውጦች በኢትዮጲያ፤ ጨርቃ-ጨርቅ አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ የአበባ እርሻዎች  እና በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ በሚል ርእስ የተካሄደባቸውን ጥናቶች  በዚህ ዓመድ በተከታታይ ያቅርባል፡፡

  1. መግቢያ

በተቀሩት የዓለም አገራት እንደሚታወቀው በኢትዮጲያ ሴቶች በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያላቸው ሚና  የሚታየው  እንደ ሚስት እና እንደ እናት ባለ የማህበራዊ ተሳትፎ ነው፡፡ በሃገራችን ከ85 በመቶ የሚሆነው የሴቶች  ቁጥር የሚገኘው በገጠሩ የሃገሪቱ ክፍል ሲሆን በአብዛኛው በግብርናና ግብርና መር በሆኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ነው፡፡

እንደ የዓለም ባንክ  የ 2021 የዕድገት አመልካች መረጃ መሰረት በሃገራችን ኢትዮጵያ የሴቶች የስራ ተሳትፎ ( Female Labor Force) ከጠቅላላው   የስራ ሀይል (total labor force) 46.31 በመቶ ይሆናል፡፡

ባለፉት ዓመታት ውሰጥ መንግሰት አየተከተለ ባለው ጉልበት-መር የኢንዱስትሪ  የፖሊሲ አቅጣጫዎች  የውጪ ንግድ ቀላልና መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱሰትሪዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በማድረጉ ምክንያት የሰት ሰራተኞች ተሳትፎ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከእነዚህ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ውሰጥ  የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ አንዱ ነው፡፡

በሃገራችን ኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብታዊ እድገት ውስጥ የአበባ እርሻው ኢንዱስትሪ እየተጫወተ ያለው ሚና በእጅጉ የጎላ ነው ።  ምንም እንኳ ዘርፉ በሌሎች ሴክተሮች እንደታየው  የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የተለያዩ  ችግሮችን ያለፈ ቢሆንም በአጠቃላይ  የአገሪቱን የወጪ ንግድ  በማነቃቃትና ብሄራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሻሻል አንፃር እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ጉልህ ቦታ ይይዛል። በተጨማሪም  በሀገሪቱ የሚታየውን  የሥራ አጥነት ችግር በማቃለል በኩል እያደረገ  ያለው አስተዋጽኦ   በተለይም በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ወይም ምንም ዓይነት ቅድሚያ የሙያ ስልጠና ለሌላቸው ወጣት ሴቶች የሥራ እድል በመፍጠር አጠቃላይ አገራዊውን የምጣኔ ኃብት ሁኔታ እያገዘ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ) በቅርቡ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ  የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን አማካኝነት በኢትዮጲያ በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ ጨርቃ-ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ እና የአበባ እርሻዎች የተሰማሩ ሴት ሰራተኞች ተከትሎ አጠቃላይ የዳሰሳ  ጥናት አካሂዷል፡፡  የጥናቱ ውጤቶች እንደሚያሳዩት፤ ሴቶች ዝርፉ  ባስገኘላቸው የስራ እድሎች  ደመወዝተኛ በመሆንና ገቢ በማግኘት   ኑሮአቸውን እየመሩ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር በሚበዛባቸው እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ሀገራት የአበባ እርሻዎችም ሆኑ፤ የመስተንግዶ ኢንዱትሪ እንዲሁም የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች እየፈጠሩ የሚገኘው  የስራ እድል  አበረታች ነው፡፡

ይህ ጽሁፍ ከእነዚህ ዘርፎች አንዱ በሆነው የአበባ ምርት   የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ ፤ የታዩ  ለውጦችና ተሞክሮዎችን  በሃገራችን ኢትዮጰያ ላይ ያለውን ነባራዊ  ሁኔታ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

  1. የስራ አድልን ማመቻቸትን በተመለከተ

ይህ ጥናት እንዳመለከተው ካለፉት ሁለት ዓስርተ ዓመታት ጀምሮ በሃገራችን   የአበባ አምራች ኢንዱሰትሪ  ቁጥር ከ አንደ መቶ ሃያ በላይ ደርሰዋል። ይህ እድገት በኢንደሰትሪው  የእሴት ትስስር ሂደት  ውስጥ ለሴቶች ሰፊ የስራ  ዕድሎችን በመፍጠር የዘርፉን ዘጠና  በመቶ  በሴቶች እንዲሸፈን ለማድረግ አስችሏል፡፡ በተለይም፣ ጥናቱ በተደረገበት የአበባ ምርት ኢንዱሰትሪከሚገኙ 1500  ሠራተኞች መካከል 1050 የሚሆኑት  ሴት ሰራተኞች ሲሆኑ፣ በሌላው ተመሳሳይ የአበባ ኢንዱሰትሪ  ከሚገኙ 500  ሠራተኞች መካከል 250 ሴት ሰራተኞች መሆናቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ከእነዚህ የአበባ ምርት ኢዱሰትሪ  ሴት ሰራተኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ አመቺ ባልሆኑ የቀን ሥራ፣ በጎዳና አነስተኛ ንግድ፣ በቤት ውስጥ ሰራተኝነት፣ በምግብና መጠጥ መስተንግዶና በመሳሰሉት የስራ ዋስትና አስተማማኝነታቸው ዝቅተኛ በሆኑ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው  የነበሩ ናቸው፡፡

  1. የስራ ዋሰትና

ከፍተኛ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሴት ሰራተኞች (92.0%) በእጃቸው የሥራ ኮንትራት ውል   ጥናቱ ማመላከቱም የሰራተኞቹን የስራ   ዋስትናና የህግ ከለላ እንደአሏቸው አመላካች ከመሆኑም በላይ በራስ የመተማመንና ተስፋን የመሰነቅ፤ የአጭርና  የረጅም ጊዜ የስራ የትምህርትና የቤተሰብ ዕቅድን      የመተለምን ስነ ልቦና  እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል፡፡  

ምንም እንኳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴት ሰራተኞች በህጋዊ መንገድ በኮንትራት ውል የተቀጠሩ ከሴት ሰራተኞቹ መካከል 38 በመቶ የሚጠጉት ሥራቸውን የማጣት ስጋት እንዳላቸው በተለያየ ደረጃ ያመለከቱ ሲሆን 62 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሥራቸውን የማጣት ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌላቸው  ጥናቱ ያመላክታል፡፡።  ይህም በዘርፉ እየታዩ   ካሉ ለውጦች ውስጥ እንደ አንዱና ዋና ሆኖ  የሚጠቀስ  ነው፡፡  ለዚህም ምክንያቱ ዘርፉ በፈጠረው  የሥራ እድል ምክንያት የሴቶችን የገቢ አቅም በማጐልበት የግለሰብ እና የቤተሰብን ድህነት ለመቀነስ ከማገዝ ባሻገር የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ እድገት መጠን እንዲሻሻል የበኩሉን ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የአበባው ምርት  ኢንቨስትመንት እያበረከተ ላለው አገራዊ የምጣኔ ኃብት እድገት በዘርፉ የተሰማሩት ወጣት ሴቶች ሚናም ከፍተኛ መሆኑም ይጠቀሳል። ሆኖም ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ ጅማሬዎች  ተግዳሮቶችና ከችግሮች ነጻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሰማሩበት በዚህ ዘርፍ አያሌ ተግዳሮቶችና ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል።  ከእነዚህ ችግሮች መካከልም አንዱ ዝቅተኛ ወርሃዊ ክፍያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሴቶች ዝቅተኛ ችሎታን በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ምደባ ይህም ዝቅተኛ ክፍያን ማስከተሉ፣ አስጊ የሥራ ሁኔታዎች፣ ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት፣ የጉልበት ብዝበዛ እና የሴቶች የቤት ውስጥ የሥራ ጫና መጨመር በዘርፉ ጐልተው የሚታዩ ችግሮች ናቸው።

በአበባ እርሻ እና ሎሎች ዘርፎችም ለሴት ላብ አደሮች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጋዊ እና የፖሊሲ ምላሾች ውሱንነት፣ በዘርፉ ሴቶች የሚገኙበትን ሁኔታ የከፋ የሚያደርጉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ጥናቱ አረጋግጧል።

 

  1. ተግዳሮቶች

4.1 ለሴት ላብ አደሮች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጋዊ እና የፖሊሲ ምላሾች ውሱንነት

4.1.1  ክፍያና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ውሱንነት

በኢትዮጵያ የዝቅተኛ የደሞዝ ፖሊሲዎች ባይኖሩም፥ በአበባ ምርት  ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሴት ተቀጣሪዎች ክፍያ ባለፉት አመታት ማሻሻያ ተደርጐበታል።ለምሳሌ በተመረጡት ሁለት ድርጅቶች የሴት ሰራተኞችን አሓዛዊ ገቢ   አማካይ የመነሻ ደመወዛቸው 1050 ብር የሚጠጋ ሲሆን ጥናቱ በተካሄደበት ወቅቱ አማካይ ደመወዛቸው ደግሞ 1842 ብር ነበር። ከዚህ እንደምንረዳው የደመወዝ ማሻሻያ የታየ መሆኑን   ቢያመለክትም በአገሪቱ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ያለመረጋጋት እና የኑሮ ውድነት ሴት ሰራተኞች በድህነት ውስጥ  እንዲቆዩ እያደረጋቸው ይገኛል።

በተጨማሪም በጥናቱ እነደ ተጠቆመው  ሴት ሰራተኞች ክፍያቸውንም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በጋራ ድርድር የመወሰን መብት የሌላቸው ሲሆን ከሚያገኙት ወርሃዊ ክፍያ ውስጥ  80 በመቶ የሚሆነው የሚውለው ለምግብ እና ለመጠለያ በመሆኑም  ምክንያት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚ ንብረቶችን ማፍራት ተስኗቸዋል።

4.2 የክህሎት አቅም ውስንነትና ዝቅተኛ ውክልና በውሳኔ ሰጭነት ደረጃ፡ –

ዘርፉ በተለያየ መልኩ የሴት ሠራተኞች አቅምና ክህሎት ለማሻሻል ሚና እየተጫወተ መሆኑን  በተካሄደው ጥናት የታየ ሲሆን  በዚህም ሴቶች የአመራር ቦታን የመያዝ፣ በውሳኔ ሰጪነት እና በአበባ እርሻ የምርት ሂደት ውስጥ የመሳተፍ አቅም ባለፉት አመታት እያደገ መጥቷል። የአመራር ቦታ ላይ የተቀመጡ ሴቶች እጅ 20 በመቶ ገደማ ደርሷል። በዚህ ምክንያትም፣ በእርሻ ሥራ ሂደትም ሆነ በሥራ አስፈጻሚነት ውስጥ ሴት ሠራተኞች ተሳትፎ ከአመት አመት እያደገ መምጣቱ  የሴት ሰራተኞችን አቅም በማሳደግ ረገድ እየተጫወተ ያለውን ሚና ያሳያል።

 

ሆኖም ግን ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር አሁንም የአቅም ውስንነቱ ጎልቶ ይስተዋላል።  ቁልፍ የሥራ አመራርን በመሳሰሉ ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው የሥራ መደቦች በአብዛኛው በወንዶች የተያዙ ከመሆናቸውም በላይ   አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በዝቅተኛ የሥራ ደረጃዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

ለዚህም ምክንያቱ የሴት ሠራተኞችን አቅም በማጐልበት በአመራር እና በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ እንዲሳተፉ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተለይቶ የሚታወቅ ጠንካራ መርሃ‑ግብር አለመኖሩ ና ሴቶችን ለማብቃት የሚያግዙ ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ስርአቶች አለመኖራቸውን ጥናቱ ያሳያል። 

  • ኮቪድ 19 በሴት ሰራተኞች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው አለም ያስከተለው መጠነ-ሰፊ ቀውስ በተለይ ሴቶችን ይበልጡኑ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እንዲጋፈጡ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ወረርሽኙ በአበባ እርሻዎች ምርት፣ ሽያጭ እና ገቢ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ፣ ቀደም ሲል በዘርፉ ውስጥ የነበሩትን ጫናዎች እና ውስብስብ ችግሮች አባብሶት ታይቷል፡፡ በሃገራችንና  በሌሎች የአለም ክፍሎች የተጣሉት ከቤት መውጣትን የሚከለክሉ ገደቦች ለአበባ ገበያ የነበረውን ፍላጐት በመቀነሱ የተነሳ የዘርፉ ምርት እንዲያሽቆለቁል  እና ለኪሳራ እንዲዳረግ ምክንያት ሆኗል።

የአበባ እርሻዎቹ፥ ወረርሽኙ ያስከተለውን ቀውስ ለማቅለል በሚል አግባብ ካላቸው የመንግስት አካላት እና ከሠራተኞቹ ከራሳቸው ጋር በቅርብ በመነጋገር የፊት ማስኮችን ማቅረብ፣ እጅ መታጠብን ማበረታታት እና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ እንዲሁም የእጅ ፅዳት መጠበቂያ ማቅረብን የመሳሰሉትን በምርት ቦታዎች አካባቢዎች እንዲገኙና በተገቢው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በምርት ሥርዓቶቹ እና ሴት ሰራተኞችን ዙሬያ ከተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ውስጥ የአበባ የእርሻ ሥራ አመራሩ በአንድ ጊዜ ሥራ ላይ የሚገኙ ሴት ሰራተኞችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል የፈረቃ ሥራ ስርዓትን ዘርግቷል። 

  1. ምን ይደረግ?

5.1 በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ዘርፍ ዝቅተኛ የክፍያ መጠን መወሰን

አሁን በአበባ እርሻ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ክፍያ ሁኔታ ለማሻሻል በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ዘርፍ ዝቅተኛ የክፍያ መጠን መወሰን አንዱና ዋነኛው  ጉዳይ ነው ።  ምክንያቱም አስካሁን ድህ ጥናት ይፋ እሰከሆነበት ድረስ በአገሪቱ  ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ገደቦችን መወሰንን በተመለከተ ተጨባጭ እርምጃዎች ባለመወሰዱ    የሴቶችን ተገቢውን ክፍያና  ጥቅማ ጥቅሞች ተገድቦ እዲቆይ አድርጎታል ፡፡ በመሆኑም ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ገደቦችን መወሰን ይገባል። ይህ ውሳኔ የሴቶች ሠራተኞችን መብቶች ከማክበር እና ከማጠናከር እንዲሁም ኑሮዋቸው ከማሻሻል አኳያ መቃኘት እንዳለበትን የጥናቱ ምክረ ሀሳብ ይጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር (EHPEA) የክላስተር (cluster-based) የክፍያ ስርዓቶችን ከማስተዋወቅ ረገድ ያደረገው ጥረት በስፋት ሊተገበር እና ለሌሎች ዘርፎችም እንደ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡።

5.2 በአበባ እርሻዎች ወስጥ ለሴት ሰራተኞች የሚሰጡ ስልጠናዎች እና እድገቶች ማጠናከር  

እነደሚታወቀው ማንኛውም ዓይነት ልማት እና እድገት የሚጀምረው የሰው ሃይል ካፒታል በመገንባት ነው። የሴት ሰራተኞችን አቅምና ክህሎች ለማሻሻል ደግሞ  የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስርዓቶችን መዘርጋት ያስፈልጋል ፡፡ አሰሪዎች  ትርፋቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከክህሎትም ሆነ ከገንዘብ ረገድ የሠራተኞቻቸው ብቃት እጅጉን ሲሻሻል እነደመሆኑ መጠን  መደበኛ ስልጠና እና ትምህርት ከፍተኛ ኢንቬስትመንቶችን የሚጠይቁ ይሁኑ እንጂ፣ አነስተኛ በሆነ ወጪ ከሥራ ጋር ተያይዘው (on job Training ) የሚሰጡ ስልጠናዎችን በመንደፍ፣ አዲስ ተቀጣሪዎችን እውቀት ለማሳደግ እና በእርሻው ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ መርዳት ይቻላል። በመሆኑም ይህንን መሰል ስልጠና ቀጣይነት ባለው መልኩ ቢዘጋጅ፣ ሴት ሰራተኞች መብቶቻቸውን እና ኃላፊነቶቻቸውን ለማስከበር የሚያስችላቸውን አቅም ያጐለብትላቸዋል።

  • የሥራ ቦታ ደህንነት ማሻሻል

የሥራ ቦታ ደህንነት ደንቦችን በተመለከተ በጥናቱ እንደተስተዋለው በዚህ ረገድ የተወሰኑ ጥረቶች ይኑሩ እንጂ፣ ይበልጥ ትኩረት በሚሹ  ቦታዎች ላይ የክትትል እና የቁጥጥር መመሪያዎች፣ ተቋማዊ የደንብ ማስከበሪያ ስርዓቶች እንዲሁም በየጊዜው የሚደረጉ የጤና ምርመራዎች የሠራተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊነታቸው የጐላ በመሆኑየሥራ ቦታ ደህንነት ደንቦች በሥራ አስፈጻሚዎችም ሆነ በሠራተኞች በራሳቸው ያለ ልዩነት በጥብቅ መከበር አለባቸው፡፡ ሊከበሩ እንደሚገባ ጥናቱ ያስገነዝባል፡፡

በዚህ ረገድ በእርሻዎቹ ውስጥ የሚገኙት የሠራተኞች ማህበራት፣ ደህንነታቸው የተጠበቁ የሥራ ቦታዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ እና የሴት ሰራተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ ከአሰሪዎች ጋር በጣምራ መስራት ይኖረባቸዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የአበባ እርሻዎችን የጤና መድህን ዋስትናን ለሰራተኞቻቸው ማስተዋወቅ እንደሚኖርባቸውና የኣበባ እርሻዎች እራሳቸውን አዳዲስ የጤና መድህን በመግዛት ሴት ሰራተኞቻቸውን ማበረታታት የሚስችል ፖሊሲዎችን መተግበር አለባቸው ፡፡

5.4 በኢትዮጵያ የአበባ እርሻዎች የሥርዓተ ጾታዊ አቅም ማጐልበቻ ማዕከላትን ማጠናከር

የሴት ሰራተኞችን ሁለንተናዊ መብቶች ማስጠበቅ ይቻል ዘንድ በየኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ውስጥ በጠንካራ ሁኔታ የታነፁ የሥርዓተ‑ ፆታ ማዕከላት እነዲመሰረቱ ቢደረግ  በእርሻዎቹ የተጠናከሩ ሥርዓተ‑ፆታዊ ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችሉ ማሻሻያዎች በሴት ሰራተኞች እና በሥራ አመራሩ መካከል የሚኖረውን ትብብር ለማፋጠን እንዲሁም የሴት ሰራተኞችን የተለዩ ፍላጐቶች ለመረዳት እገዛ ያደርጋል። ማዕከሉ እርሻዎቹ ከሚገኙባቸው የከተማውና እና የክልል መስተዳድሮች ጋር ከሚገኙ የሥራ እና የክህሎት ማዳበሪያ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ጋር በቅርበት መሥራት ያስችላቸዋል፡፡።

የሥርዓተ ፆታ ማዕከሉ ከዚህ ሌላ ከጤና፣ ከቤተሰብ እቅድ፣ ከኤችአይቪ/ኤድስ መኮንኖች እና ከትዳር የምክር አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በጣምራ በመሥራት የሰራተኛ ሴቶችን ችግሮች ለመፍታት ፡ በተለመደ መልኩ አንድ የሥርዓተ‑ጾታ ጉዳዮች ተጠሪ ግለሰብ እዲኖር መደረጉ  አጥጋቢ ለውጥ  እንደማያመጣ ካለፉት አመታት ተሞክሮዎች በግልጽ ማየት ይቻላል።

በሥርዓተ‑ጾታዊ አቅም ማጐልበቻ ማዕከላቱ፣ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሴት ሠራተኞችጾታዊ ጥቃት፣ የወሲብ ትንኮሳ ወይም መድልዎ በደረሰባቸው ጊዜ ሁሉ ሊመክሯቸው የሚችሉ የሕግ አማካሪ እና ከፍተኛ ባለሞያ እንዲኖራቸው ማድረግ  እነኚህን ሥርዓቶች በአጠቃላይ በአበባ እርሻዎች ወስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ ለማሻሻልና በእርሻዎቹ ውስጥና ውጪ ለድርጅቱም ሆነ ለሰራተኛው ኑሮ ዘለቄታዊነት እና መልካም ስም አስፈላጊ መሆናቸውንም በኤፍኤስኤስ የተካሄደው ጥናት ምክረ-ሃሳብ አሰቀምጧል፡፡

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14 ቀን 2015 ዓም በህገወጥ መንገድ...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር ፕሬዚደንት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ አባላቱ የተከበሩ ተብለው የሚጠሩት በምክንያት...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል መንግሥታት...

ተመሳሳይ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ተጠሪ የሆኑ ንዑሳን...

በዚህ የየቅዱስ ፓትሪክ መታሰቢያ ቀን አየርላንድ የታሪኳን ሶስት ወሳኝ ወቅቶች መለስ ብላ ትመለከታለች

አየርላንድ እጅግ ከፍ ባለ ሁኔታ የምታከብረው የቅዱስ ፓትሪክ ቀን በሚውልበት መጋቢት 8 (እ.ኤ.አ. ማርች...

የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ ፦  በተመረጡ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.) የፖሊሲ ፍሬ ሐሳቦች የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ ፦ ...