Thursday, November 30, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉየሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ ፦  በተመረጡ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች...

የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ ፦  በተመረጡ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

Published on

- Advertisment -

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.)

የፖሊሲ ፍሬ ሐሳቦች

የሴት ራተኞች ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ   በተመረጡ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.) ካለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት ጀምሮ በዜጎች ማህበራዊ ህይወትና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በተለያዩ የአገራችን ማህበራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ መድረኮችን በማዘጋጀትና ውጤታማ የፖሊሲ ትግበራና አዳዲስ አማራጭ አቅጣጫዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳየት ጥሩ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

በኤፍኤስኤስ እየተከናወኑ የሚገኙ የጥናት ውጤቶችን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ለህብረተሰቡ በሰፊው እንዲደርስ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የህትመት ውጤቶች ጋዜጦች ሲሆኑ በዚህ አምድም በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በሚካሄዱ የምርምር ስራዎች ላይ የተመሰረቱ የጥናት ውጤቶች አንዱ የሆነውንና በርካታ አንጋፋ ተመራማሪዎች የተሳተፉበትንና ለፖሊሲ አውጭዎች በርካታ ምክረ ሀሳቦችን ያካተተውን ‹‹የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና የታዩ ለውጦች በኢትዮጲያ፤ ጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ የአበባእርሻዎች እና በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ በሚል ርእስ የተካሄደባቸውን ጥናቶች በዚህ ዓምድ በተከታታይ ማቅረብ መጀመሩን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ሶስተኛውን  የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ፡ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ተሞክሮዎች   በሚል ርእስ የተካሄደው ጥናት ቀርቧል፡፡

  1. መግቢያ

ስራ አጥነት የኢትዮጵያ ከተሞች የኢከኖሚ ችግር ሆኖ ለብዙ ጊዜ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም በማእከላዊ ስታትስቲካል ኤጀንሲ የተሰራው የከተማ ስራ እና ስራ አጥነት የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው የከተማ ስራ አጥነት 18.7 በመቶ ደርሷል፡፡ የጥናት ዳሰሳው ስራ መስራት ከሚችሉ ሴቶች መሃል 26.1 በመቶው ስራ አጥ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ምንም እንኳን በኢ-መደበኛ ሴክተር ውስጥ ሴቶች (24 በመቶ) ከወንዶች (10 በመቶ) ጋር ሲወዳደር ተሳትፏቸው በልጦ ቢታይም በቅርብ ጊዜያት ሴቶች መደበኛ ሴክተሩን በተሸለ ሁኔታ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር በተለይም ደግሞ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱሰትሪ ለወጣቱ ስራ የሚፈጥር ተደርጎ ይታያል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሰራሽ መነሻ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም ቃጫዎችን እና ከልብስ እና አልባሳት ጋር የሚዛመዱ መጣጥፎችን የማምረት ሃላፊነት ያለው መጠነ ሰፊ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያጠቃልላል ፡፡ምንም እንኳን በኢኮኖሚ ረገድ ብዙውን ጊዜ ከጫማ ኢንዱስትሪ ጋር ይመደባል ፣ ከቴክኒካዊ እይታ አንፃር እንደ መሰረታዊ ሽክርክሪት ፣ ጥልፍ (ምንጣፎችን ማሰር) ፣ ሹራብ ፣ የጨርቅ ማቅለሚያ ፣ ጨርቃ ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻን በመሰረታዊነት የተለያዩ ሂደቶችን ያጠቃልላል ፡፡በአሁኑ ወቅት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው በዓለም ላይ በዋናነት በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሥራ ስምሪት ከሚያመነጩት ውስጥ አንዱ ነው፡: እያደገ በመጣው በዚሁ ዘርፍ በሃገራችን  80 በመቶ የሚሆነውን የስራ ቦታ የሚይዙት ሴቶች ናቸው ፡፡

 ኢትዮጵያ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ እንዳላት መታወቁን ተከትሎ   ይህንን የ የኢንዱስትሪ ዘርፍ  በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦውን ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጥናቶችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች  ያመለክታሉ ።ምንም እንኳን የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ሴክተር ለሴቶች የስራ እድል እያመቻቸ ቢገኝም በተለይም አነሰተኛ  ክህሎቶች በሚፈልጉ የስራ ዘርፎች ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ ሴቶች የፆታ መድሎ፣ ያልተመጣጠነ ክፍያ እንዲሁም ደህንነት የጎደለው የስራ ከባቢ እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ሲገጥሟቸው ይታያል፡፡

የዚህ ጥናት ዋነኛ ዓላማ   የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና የታዩ ለውጦች በኢትዮጲያ ጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ  በመመልከት  የማህበራዊ እና ስነ-ሕዝብ ባህሪያትን፥ የመደራደር አቅምን፥ ገቢን፥ ጥቅማጥቅሞችን እና የሴት ሰራተኞችንየሥራ ሁኔታ በመገምገም በዘርፉ የሚገኙ ተግዳሮቶችን በመለየት  መፍትሔ  የሚሆኑ ምክረ ኃሻቦችን ማቅረብ ነው ::

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ) በቅርቡ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ  የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን አማካኝነት በኢትዮጲያ በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ ጨርቃ-ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ እና የአበባ እርሻዎች የተሰማሩ ሴት ሰራተኞች ተከትሎ አጠቃላይ የዳሰሳ  ጥናት አካሂዶል፡፡  የጥናቱ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ዘርፉ  ባስገኘላቸው የስራ እድሎች  ደመወዝተኛ በመሆንና ገቢ በማግኘት   ኑሮአቸውን እየመሩ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር በሚበዛባቸው እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ሀገራት የአበባ እርሻዎችም ሆኑ፤ የመስተንግዶ ኢንዱትሪ እንዲሁም የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች እየፈጠሩ የሚገኘው  የስራ እድል  አበረታች ናቸው፡፡

ይህ ጽሁፍ ከእነዚህ ዘርፎች አንዱ በሆነው ጨርቃ-ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ ፤ የታዩ  ለውጦችና ተሞክሮዎችን በመዳሰስ  በሃገራችን ኢትዮጰያ ላይ ያለውን ነባራዊ  ሁኔታ በመዳሰስ ለፖሊሲ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ ሃሰቦችን አቅርቧል፡፡

  1. ጥናቱ ምንን ያመለክታል ?

2.1 በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሰሩ የሴት ተቀጣሪዎች ሁኔታ

ለጥናቱ በተመረጡ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ሲቀጠሩ 1280.86 ብር ያገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በአማካይ 2066 ብር በወር ይከፈላቸዋል፡፡ በአዲስ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች በአመት የደመወዝ  ጭማሪ በአማካይ 2.67 ሲሆን በጥቃቅንና መካከለና አልባሳት ኢንተርራይዝ 2.77 በመቶ ነበር፡፡ በፋብሪካዎቹ ውስጥ ለሴቶች የሚካፈለው ደመወዝ  ሰራተኞቹ ያላቸውን የመሰረታዊ ፍላጎቶች ወጪ በቅጡ አይሸፍንም፡፡ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየናረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ተባብሷል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች በቂ ያለመከፈል ሁኔታን ከመቅረፍ አንፃር በመንግስት በኩል አስፈላጊው ጥረት ሲደረግ አይታይም፡፡ እንደውም መንግስት ኢትዮጵያ ከአለም ሀገራት በጣም ዝቅተኛ ደምዎዝ ተከፋይ የጨርቃ መርቅ እና አልባሳት ፋብሪካ ሰራተኞች ያሉባት ሀገር መሆኗን በኩራት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ሲናገር ይታያል፡፡ ይህንን በተመለከተ ከመንግስት በኩል አነስተኛ ክፍያን አለመወሰኑ እንደአንድ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የተሸሻለው የአሰሪና ሠራተና ጉዳይ አዋጅ አናስተኛ ደመወዝ  የሀገሪቷን የኢኮኖሚ እድገት ባገናዘበ መልኩ እንዲያይ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የደመወዝ  ቦርድ አሁንም አልተቋቋመም፡፡

2.2 በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ ያለው የጤና እና የስራ ቦታ ደህንነት ሁኔታ

በጥናቱ የተሳተፉ ሰራተኞ ከባድ የሆነ በስራ ምክንያት የደረሰባቸው ጉዳት የለም፡፡ ሪፖርት የተደረጉት ጥቂት በስራ ምክንያት የደረሱ አደጋዎች በመርፌ የመወጋት አደጋ እና ከዛ ጋር የተያያዘ እነፌክሽን ናቸው፡፡ በስራ ምክንያት አደጋ በሚደርስ ጊዜ እና ቀላል ሲሆን ፋብሪካዎቹ በስራ ቦታ ባላቸው የመጀመሪያ ጊዜ አደጋ እረዳታ መስጫ ቁሳቁሶች ይጠቀማሉ ነገር ግን አደጋው የከፋ ከሆነ ሰራተኞቹ ወደ ጤና ማእከላት ሄደው ይታከማሉ፡፡ ፋብሪካዎቹም የራሳቸው የሆነ የጤና ማእከላት ስለሌላቸው የሰራተኞቹን የመጓጓዣ እና የመታከሚያ ወጪ ይሸፍናሉ፡፡

በስራ ምክንያት ከሚደርሱ አደጋዎች ውጪ የፋብሪካዎቹ ስራ በሴት ሰራተኞች ላይ የተለያዩ የጤና ስጋቶች እንደሚጥል ሰራተኞቹ ይናገራሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሴት ሰራተኞች ለሰዓታት ቆመው ከመስራታቸው ጋር በተገናኘ እግራቸው እንደሚያብጥ እንዲሁም ኩላሊታቸውን እንደሚታመሙ ይናገራሉ፡፡

የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ የሠራተኞችን የጤና ኢንሹራንስ የማግኘት መብት አይደነግግም፡፡ አዋጁ የሚያጠቃልለው በስራ ላይ የሚከሰት አደጋን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ የ20 አመት የጤና እቅድ ሁሉም ዜጋ የጤና አገልግሎትን ያለምንም ችግር እንዲያገኝ እየሰራ ስለሆነ በፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሠራተኞችም በዚህ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  1. ተግዳሮቶች

በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች የሚያገኙት ጥቅም እና የሚገጠሟቸው ተግዳሮቶች  በጥናቱ ተካተዋል፡፡

በጥናቱ ውስጥ የተሳተፉ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎች ለሴቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸው ጠቀሜታ አለው፡፡ 32 በመቶ የሚሆኑት በዳሰሳ ጥናት የተሳተፉ ሴቶች በፋብሪካዎቹ ውስጥ ከመቀጠራቸው በፊት ስራ ያልነበራቸው በመሆናቸው በመቀጠራቸው ገቢ ለማግኘት ችለዋል፡፡ ነገር ግን ሰራተኞቹ እንደሚናገሩት የሚያገኙት ገቢ የዕለት ተዕለት ወጪያቸውን በተገቢ መልኩ አይሸፍንላቸውም፡፡

ጥቂት ፋብሪካዎች ከደመወዝ ውጪ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞችን ለሰራተኞቻቸው ያቀርባሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የምግብ፣ ማበረታቻ ክፍያ እንዲሁም የመጓጓዣ ወጪን መሸፈን የተጠቀሱ ናቸው፡፡ የተወሰኑት ፋብሪካዎች እነዚህን ጥቅማ ጥቅሞች ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ገቢ መቀነስ ምክንያት አቋርጠዋል፡፡ ከነዚህ ጥቅማ ጥቅሞች በተጨማሪ ሴት ሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን ያገኛሉ፡፡ በተለይም ልብስ ስፌትን በስራ ላይ የመሰልጠን እድል ይመቻችላቸዋል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች ብዙ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል፡፡ ሴቶቹ ሪፖርት ያደረጓቸው ፆታዊ ጥቃቶች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አንድም የፋብሪካ አመራሮች እንደሚሉት ፆታዊ ጥቃት የሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የማያዳግም ቅጣት ስለሚጣልባቸው ሊሆን ይችላል አልያም የተወሰኑት ቁልፍ ሰጪዎች እንዳሉት ፆታዊ ጥቃት ሲፈፀምባቸው ሴቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ችግሩን ለበላዮቻቸው አያሳውቁም፡፡

ለመጓጓዣ የሚከፍሉት ከፍተኛ ክፍያ እና መፀዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ የተፈቀደላቸው ውስን ሰአት ሌሎች ሴት ሰራተኞች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ሰራተኞቹ ጤናቸውን እንዲሁም ምርታማነታቸውን እንደሚፈታተኑት ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ወደቤታቸው ሲሄዱም የቤት ስራ እንዲሰሩ ማህበረሰቡ ስለሚጠብቅባቸው ከፋብሪካ ስራቸው በተጨማሪ የማብሰል የማፅዳት እንዲሁም ቤተሰባቸውን የመንከባከብ ሚናቸው በፋብሪካ ውስጥ ያላቸውን ስራ በትክክል እንዳይሰሩ በዛም ምክንያት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የቤት ሀላፊነታቸው ፋብሪካ በሚሰሩ ሴቶች ላይ ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ አይገኙም፡፡ ብዙዎቹ የአመራር ሚና ያላቸው ሴቶች ከመስመር ተቆጣጣሪነት ሲያልፉ አይታይም፡፡ በተጨማሪም በሰራተኛ መሀበራት ውስጥ የአመራር ሚና ስለማይጫወቱ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ባሉ ድርድሮች ላይ ተፅዕኖዋቸው ውስን ነው፡፡ ለጥናቱ መረጃ በተሰበሰበባቸው ፋብሪካዎች ደግሞ የሰራተኛ ማህበራት ከነአካቴው ባለመኖራቸው ምክንያት የሰራተኛና አሰሪ ድርድሮች አይታወቁም፡፡

  1. ምን ይደረግ ?

በኢትዮጵያ በፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሴቶችን ሁኔታ ለማሻሻል ያለሙ ብዛት ያላቸው የህግ እና ፖሊሲ ሰነዶች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የትምህርት እና ጤና ፖሊሲዎች የሴት ሰራተኞችን ሁኔታ ሴቶች ወደ ትምህርት እንዲሄዱ በማበረታታት እና አጠቃላይ የጤና ሽፋን እንዲያገኙ ይሰራሉ፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁም እንዲሁ የሴቶች ሰራተኞችን የስራ ሁኔታ ለማሻሻል ያለሙ በዛ ያሉ አንቀፆችን ይይዛል፡፡ ከአንቀፆቹ ውስጥ የስራ ሁኔታ መቆጣጠርን፣ የሰራተኛ ማህበራትን ማቋቋምን እንዲሁም አነስተኛ ደመወዝን የሚመለከቱ ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም ከመንግስት በኩል ባለ የአቅም እና ቁርጠኝነት ማነስ ምክንያት አላማቸውን ሲመቱ አይታዩም፡፡

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሴክተር ውስጥ ብዙ ሴቶች ተቀጥረው ይገኛሉ፡፡ ይህም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን ከፍተኛ ስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በሴክተሩ ተቀጥረዉ የሚሰሩ ሴቶች በህይወታቸው ውስጥ እርባና ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ለማስቻል ከተፈለገ ሴቶቹ በስራ ቦታ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የስርዓተ-ፆታ ፍላጎቶችን ባገናዘበ መልኩ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የሴት ሰራተኞችን የስራ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ በተለይም መንግስት እና ፋብሪካዎች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡

ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን የጥናቱ ውጤቶች ተከትሎ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምክረ-ሃሳቦች አቅርቧል፡፡

  • የሰራተኛ ማህበራት እንዲቋቋሙ ድጋፍ ማድረግ እና ለሚቋቋሙት ማህበራት ድጋፍ ማድረግ

ምንም እንኳን የሰራተኛ ማህበራት የሰራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች  በማህበራት አልተደራጁም፡፡ በመሆኑም በየኢንድስትሪዎቹ ሰራተኛ ማህበራት መቋቋም ያለባቸው ሲሆን የሚቋቋሙትም ማህበራት የሰራተኞችን የስራ ሁኔታ እንዲሻሻል ብሎም ኢንድስትሪው ላይ የተሻለ የስራ ግንኙነት እንዲስፍን መደራደር አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽንም ማህበራት በየኢንድስትሪዎቹ እንዲቋቋሙ የማስተባበር ግድታውን በአፋጣኝ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ በተጫማሪም ኮንፌዴሬሽኑ ለማህበር አባላት የስራተኛ መብትን ለማስጠበቅ የሚረዱ ስልጠናዎችን ሊያዘጋጅ ይገባል።

  • መዋቅሮችን ማጠናከር፡-

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ስርአተ-ፆታ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ጽ/ቤቶች በፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞችን ሁኔታ በተሻለ መልኩ እንዲከታተሉ በገንዘብ እና በሰው አቅም መጠናከር አለባቸው፡፡ በተጨማሪም  በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ደረጃም ቢሆን ስረዓተ-ፆታ ላይ አትኩረው የሚሰሩ ተወካዮች ተመልመለው ከስረዓተ-ፆታ ጋር የተገናኙና በየጊዜው የሚታቀዱ ፕሮግራሞችን እንዲያስተባብሩ ሊድርግ ይገባል፡፡

  • የሰራተኞች ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የተደነገጉ ደንቦችንና መመሪያዎች ማስፈፀም ፦

በመካከለኛ አልባሳት ኢንተርራይዝ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ ደህንነታችውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት የስራ ድህንንትን የመቆጣጠር ስራን ባልተማከለ መልኩ በክ/ከተማ አልያም በወረዳ ደረጃ እንዲሰራ ለማድርግ አቅጣጫ ያስቀመጠ ቢሆንም፤ ክታች ያሉት የመንግስት አደረጃጅቶች በቂ የስው ሀይል እና ሌሎች ግብዓቶች የሚያንሳቸው በመሆኑ የጨርቅና አልባሳት ኢንትርፕራይዞቹ በቂ ክትትልና ቁጥጥር አይደረግባችውም። ስልሆነም ያሉትን አደራጃጅቶች የሚያስፈልጋችውን ግብዓት በማሟሟላት የስራተኛ ደህንነትን ለማስጠበቅ የተደነገጉ ደንቦችን እንዲተገበሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  • አነስተኛ ደመወዝን መወሰን እና ለሰራተኞች የመኖሪያ ቦታ ማመቻቸት፡-

እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2011 በታወጀው የኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ላይ በተመልከተው መሰረት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ከስራተኞች፤ ከቀጣሪዎች፤ ከሰራተኛ ማህበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት የደመወዝ  ቦርድ ለማቋቋም አፋጣኝ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም፣ በአዲስ ኢንዱስትሪ መንደር የሚገኙ ፋብሪካዎች የሴት ሰራተኞቻቸውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የመኖሪያ ቦታ የማመቻቸት ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡

  • የሴት ሰራተኞን አቅም መገንባት፡-

መንግስት ከሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር የሰራተኞች መብቶችን በተመለከተ ስልጠናዎችን፣ ውይይቶችን እንዲሁም የልምድ ልውውጦችን ቢያዘጋጅ፡፡ በተጨማሪም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁንና ሌሎች ተዛማጅ ህጎችን ለሴት ሰራተኞ እንዲገነዘቡት በመስጠት የማብቃት እና ሴት ሰራተኞች መብታቸውን እንዲጠይቁ የማስቻል ስራ መስራት አስፈላጊ ነው፡፡

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለተከበረው ምክር ቤት ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት የሚነሱ ጥያቄዎችን እየተቀበሉ ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው]

ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ነገር ከምን እንደደረሰ ቢያብራሩልን? ምንድነው ይፋ ያደረገው? ጥያቄውን ትንሽ...

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ ነዋሪዋ ወጣት፣ ባለፈው ሳምንት ለሦስት...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች ውስጥ ሲሚንቶ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ እምለው” ዓምድ ላይ፣ “ብሔር ተኮር...

ተመሳሳይ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ መደበኛ እና ድንገተኛ ጠቅላላ...

ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን

በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡም ሆነ ከገቡ በኋላ በጥሩ ውጤት ተመርቀው ለቁም ነገር የሚበቁ ሴት ተማሪዎች...

Unlocking Sustainable Change: The Dalberg Approach to Impact-driven Innovation

Dalberg Advisors, a global impact consultancy committed to building a more inclusive and sustainable...