Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሞት ጋር የተጋፈጡት የቦረና አርብቶ አደሮች

ከሞት ጋር የተጋፈጡት የቦረና አርብቶ አደሮች

ቀን:

  • ‹‹200 ከብቶች የቀረችኝ አንድ ብትሆንም ድምጿን መስማት ብቻ ዕፎይታ ይፈጥርልኛል››

በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ዳስ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጃተሚ ሶራ፣ የዛሬን አያድርገውና በነበሯቸው 200 ከብቶች ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ ተብለው አሥር ልጆቻቸውንም ሳይቸገሩ ማሳደጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ ግን የነበረውን እንዳልነበረ እንዳደረገባቸው የሚናገሩት አቶ ጃተሚ፣ ድርቁ ከመከሰቱ በፊት 200 ከብቶቻቸው ውኃ ለማግኘት በየቀኑ ሦስት ሰዓታት የሚወስድ መንገድ በመጓዝ እንደሚደክሙ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ ልፋታቸው መና ቢቀርም አሁን ሁሉም ከብቶቻቸው አልቀው አንድ ላም ብቻ ቀርታቸዋለች፡፡ ወተት የማይነጥፍበት ቤታቸውም ጉሮሮን የሚያርስ ውኃ ናፍቆታል፡፡ የቀረችው ላምም ብትሆን በሰዎች ዕገዛ የምትንቀሳቀስ በመሆኗ እንዳለች አትቆጠርም ይላሉ፡፡ 

‹‹ከነበሩኝ 200 ከብቶች የቀረችኝ አንድ ብትሆንም ድምጿን መስማት ብቻ ዕፎይታንና ተስፋ ይፈጥርልኛል፤›› ሲሉ አቶ ጃተሚ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

አቶ ጃተሚና ልጆቻቸው ይኖሩበት ከነበረው መቶ አርባ ከሚባለው የገጠር ቀበሌ ለቀው ወደ ዳስ ወረዳ ቀቀሎ ሀሮ ኡርጌ ቀበሌ ተሰደዋል፡፡፡ ከዚህ ቀደም እንግዳ ለመቀበል እጃቸውን የሚዘረጉት የዞኑ ነዋሪዎችም ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡  እንደ አቶ ጃተሚ ሁሉ በቀቀሎ ሀሮ ኡርጌ የተፈናቃዮች መንደር የሚኖሩት የቦረና አርብቶ አደሮች የከብቶቻቸው ዕጣ እንዳይደርስባቸው፣ የልጆቻቸውንና የራሳቸውን እስትንፋስ ማቆየት ላይ ማተኮራቸውን አስረድተዋል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመንደሩ  ከአራት ቀበሌዎች የተሰባሰቡ ከ300 በላይ አባወራዎች መኖራቸውን፣ ሁሉም ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት የመንግሥትና የግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ድጋፍ የሚጠባበቁ ናቸው ብለዋል፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች መተዳደሪያቸውና ለመኖራቸው ወሳኝ የሆኑት ከብቶቻቸውን በሙሉ ማጣታቸውንና ለእነሱም ሁኔታው አሥጊ መሆኑን ገልጸው፣ በመንግሥትና በሌሎች ተቋማት የሚደርሳቸው የዕለት ጉርስ በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ያሉበት ችግር በአፋጣኝ ዕልባት ካላገኘም ለሕይወታቸው ሥጋት መፍጠሩን በፍርኃት ይናገራሉ፡፡

በመንግሥትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አማካይነት በሳምንት ሁለት ቦቴ ውኃ የሚቀርብ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ ለአንድ አባወራ አሥር ሊትር ውኃ ብቻ ይደርሰዋል ብለዋል። በመሆኑም የሚቀርበው ውኃ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ ሕይወት ከማስቀጠል ውጪ ጉሮሮ የሚያረሰርስ አይደለም ይላሉ፡፡ አቶ ጃተማና ቤተሰባቸው በደጉ ጊዜ በቀን ሦስቴ ቤተሰባቸውን ይመግቡ እንደ ነበር፣ አሁን ግን ጊዜው የጨከነ በመሆኑ ከተገኘ በቀን አንድ ጊዜ አንዳንዴም ፆማቸውን እንደሚያድሩ ይናገራሉ፡፡ በመንግሥት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በከፍተኛ የምግብ ዕጦት ለተጋለጡት ብቻ መሆኑን፣ ከቅርብ ሳምንታትም በፊትም ኬር ኢትዮጵያ ከተሰኘ ድርጅት 150 ኪሎ ግራም ስንዴ በሦስት ወራት ልዩነት እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጃተማም ሆኑ ሌሎች የመንደሩ ነዋሪዎች በተስፋ መቁረጥና በቁዘማ ጊዜያቸውን ይገፋሉ። የቤተሰቦቻቸውን ጎሮሮ የሚያረጥብ ውኃና የሚቀመስ ምግብ ማግኘት የዘወትር ፀሎታቸው ከሆነ መክረሙን ይናገራሉ። በመንደሩ በከፍተኛ ሁኔታ በምግብ ዕጦት ሳቢያ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያቅታቸው ሰዎች ቁጥራቸው በርከት ያለ እንደሆነ ለመታዘብ ተችሏል፡፡

በቅርቡም የተወሰኑ የመንደሩ ነዋሪዎች በከባድ የምግብ ዕጦት ምክንያት ወደ ሕክምና እንደሄዱ የሚገልጹት አቶ ጃተማ፣ መንግሥት በዘላቂነት መፍትሔ ካላበጀ ከዚህ የከፋ ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹ተስፋ ያደረግነው ዋቃን ብቻ ነው፡፡ ሰዎች የሚረዱንም ቢሆን የዋቃ ፈቃድ ሲሆን ነው፡፡ የፈጣሪ ምሕረት እንዲበዛልን መፀለይ ብቻ አማራጫችን ነው፤›› ሲሉ አቶ ጃተማ ዕንባ በተሞላ ዓይናቸው ስለገጠማቸው መከራ ተናግረዋል፡፡

የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማቆየት በማለት ይኖሩበት ከነበረው መንደር ወደ ቀቀሎ ሀሮ ኡርጌ ነቅለው ከመጡ ወራት ያስቆጠሩት አቶ ጉዮ ጃርሶ በቡከላቸው፣ ድርቁ ከመከሰቱ በፊት ሰባት የቀንድ ከብቶች እንደ ነበሯቸውና ነገር ግን ሁሉም ከብቶቻቸው ዓይናቸው እያየ ማለቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ የቤተሰቦቻቸውና የእሳቸውን ሕይወት ለማስቀጠል ወደ መንደሩ ከሚመጣው የቦቴ ውኃ በሳምንት አሥር ሊትር እንደሚደርሳቸው፣ አንድ አባዋራ ከሚያስተዳድረው በርከት ያለ የቤተሰብ ቁጥር አንፃር በሳምንት የሚያገኘው አሥር ሊትር ውኃ ከንፈር ከማርጠብ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው አቶ ጉዮ ይናገራሉ፡፡

ቀዬአቸውን ለቀው አሁን በሚገኙበት መንደር የገጠማቸው ትልቁ ችግር ደግሞ የምግብ ዕጦት መሆኑን የተናገሩት አቶ ጉዮ፣ ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ ካላገኙ እነሱም ከብቶቻቸው ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸው በከፍተኛ ሥጋት ገልጸዋል። የሕክምና አገልግሎት በአቅራቢያቸው አለመኖር ሌላኛው ትልቁ ችግር መሆኑን፣ በሳምንት አንዴ በሚቆመው ገበያ ቀን ብቻ ትራንስፖርት እንደሚያገኙ አክለዋል፡፡

የታመሙ ሰዎችን ወደ ከተማ (ዳስ ወረዳ) ለማሳከም በሳምንት አንዴ የሚቆመውን የገበያ ቀን እንደሚጠብቁ፣ አስቸኳይ ሕመም የገጠማቸውና ፋታ ያጡት ደግሞ ደርሶ መልስ ስድስት መቶ ብር አውጥተው በሞተር ብስክሌት ወደ ሕክምና እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡ እንደ አቶ ጉዮ ገለጻ፣ በመንደሩ በድርቁ ብዙ ሰዎች መሞታቸውን እንደሚሰሙ ገልጸው፣ በገጠማቸው የምግብ ዕጦት ምክንያት በርካቶች በመታመማቸው ሌላው የመንደሩ ራስ ምታት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

‹‹በመንደሩ እንደ እኔ ያሉ አቅመ ደካሞች ከሞቱ ረሃብ እንደገደላቸው በስፋት ይወራል፤›› ሲሉ አቶ ጉዮ አስረድተዋል፡፡ በድርቁ ሳቢያ ከብቶቻቸው አንድ በአንድ በመሞታቸው ልባቸውን ቢያዝንም፣ የእሳቸው እኩያ የሆኑ የመንደሩ ጓደኞቻቸው መሞታቸውን እየሰሙ መሆኑ ደግሞ ከትካዜ አልፎ ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራሉ፡፡  ሪፖርተር ከመንደሩ ነዋሪዎች እንደሰማው፣ በከፍተኛ የምግብ ዕጦት መንቀሳቀስ አቅቷቸው ወደ ወረዳ ጤና ጣቢያ ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሚጓዙ ነፍሰ ጡር እናቶችና ሕፃናት ተበራክተዋል።

የቦረና ዞን መቀመጫ ከሆነችው ያቤሎ ከተማ ዳስ ወረዳ ለመድረስ ከ160 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይጠይቃል፡፡  ወትሮም ቢሆን ወደ ቦረና ሲቃረቡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ለዓይን የሚማርኩት የቦረና ብርቅዬ ከብቶች መንገዱን በማቋረጥ ጭምር ጉዞ ያዘገዩ ነበር። ዛሬ ግን እነዚያ የቦረና ከብቶችን በመንገዱ ግራና ቀኝ ማየት ብርቅ ነው።

ወትሮም ቢሆን የቦረና ፀጋዎች ሲወሱ በሁሉም ዘንድ የሚጠቀሱት የቀንድ ከብቶች ዛሬ ተፈጥሮ ጨክናባቸዋለች፡፡ በመስኮቹ መቦረቅ ካቆሙም መቆየታቸውን የአካባቢው ገጽታ ያሳብቃል፡፡ አካባቢው ለመጣ እንግዳ ሁሉ በወተት መቀበል የማይታክቱት የቦረና አርብቶ አደሮች፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የራሳቸውን ሕይወት ለማቆየት መቸገራቸውን ጓዳዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡

የቦረና ነዋሪዎች ከብቶቻቸው አልቀውባቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማስቀጠል ብቻ የሚሆን፣ ጉሮሯቸውን ማርጠቢያ ውኃ ፍለጋ ከወዲያ ወዲህ የሚመላለሱ ተሽከርካሪዎችን በዓይናቸው ሲያማትሩና ሲማፀኑ ይስተዋላሉ። እንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ከወደቁም ከርመዋል፡፡ 

ሕፃናት፣ እናቶች፣ አባቶችና ወጣቶች ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙስ በመያዝ የውኃ ጥማቸውን ለማርካትና እስትንፋሳቸውን ለማቆየት እጃቸውን ሲዘረጉ ማየት የዘወትር ተግባራቸው መሆኑን ለማየት ተችሏል፡፡ በውኃ ጥምና በግጦሽ ዕጦት ሰውነታቸው ተዝለፍልፎ እግራቸውን ለማንሳት አቅም ያጠራቸውን ከብቶች በየመንደሩና አልፎ አልፎም በዋና መንገዶች መሀል ወድቀው ሞታቸውን ሲጠባበቁ ማየት ቅስም የሚሰበር፣ ግን ደግሞ ከቦረና ሰማይ ሥር ለሚኖሩት አርብቶ አደሮች የሚጋፈጡት ሀቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ 

በመንገዱ በስተቀኝና በስተግራ ድርቁ ጨክኖ እስከ ወዲያኛው የሸኛቸው ከብቶች አፅም በቅርብ ርቀት ይስተዋላል።  ሞት ያንዣበባቸውና እየተሽቀዳደማቸው የሚገኙ ከብቶች ዛሬን ለመሰንበት ፌስታል ሳይቀር ያገኙትን ባዕድ ነገር ለመብላት ሲታገሉ ማየት ለቦረና ምድር አዲስ አይመስልም፡፡

በዚህ የጉዞ ማሳረጊያ የሆነችው በጭቃና በሸራ በተወጠሩ አነስተኛ ቤቶች የታጀበችዋ ቀቀሎ ሃሮ ኡርጌ የተፈናቃዮች መንደር ናት፡፡ በመንደሯ ከተለያዩ ቀበሌዎች ከተሰባሰቡት አባዎራዎች መሀል ደግሞ የአሥር ልጆች አባት ይገኙበታል፡፡ 

አቶ ሱሌማን ባሊሳ ከሚኖሩበት ቀዬ ተሰደው ወደ ቀቀሎ ሀሮ ኡርጌ መኖር ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ከ50 በላይ ከብቶች ባለፀጋ የነበሩት አቶ ሱሌማን፣ ከእነዚያ ውስጥ በሕይወት የቆዩላቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ የቀሩትም የሚያገኙት መኖ በቂ ባለመሆኑ በሕይወት ለማሰንበት በሰው አቅም የሚነሱ ናቸው፡፡ ከበራፋቸው ንቅንቅ ለማይሉት የአቶ ሱሌማን ከብቶች፣ ከቤተሰቦቻቸው ተርፎ በቂ መኖ ለመሸመት እጅ እንዳጠራቸው ያስረዳሉ፡፡ የአቶ ሱሌማን ዕጣ የገጠማቸው የመንደሩ ነዋሪዎች በመንግሥትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዕገዛ ካልተጠናከረላቸው የከብቶቻቸው ዕጣ ወደ እነሱ እንደማይደርስ ምንም መተማመኛ የላቸውም፡፡

በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገሩት የመንደሯ ነዋሪዎች፣  ሕይወታቸው በመኖር ባለመኖር መሀል ሆኗል ይላሉ፡፡ እንደ ወትሮው የአካባቢው ሰዎች ወተትና ሥጋ ስለማያገኙ ለሕመም እንደሚጋለጡ፣ ከምግብ ዕጦት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ወረርሽኝ ሞታቸውን እንዳያፋጥነው በሥጋት ይናገራሉ፡፡

በምግብ ዕጦትና በተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ተደራርበው ከአልጋ ለመነሳትና ለመንቀሳቀስ የተገደቡ አቅመ ደካሞች በርካቶች ናቸውም ይላሉ፡፡ አቶ ሱሌይማን የቀሯቸውን ከብቶች ለማቆየት ከግብረ ሰናይ ድርጅት ካገኙት 150 ኪሎ ግራም ዕርዳታ ገሚሱን ሸጠው መኖ እየገዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

በመንደሯ ሪፖርተር ያነጋራቸው ነዋሪዎች በየቤቱ በራፍ ሞት እየተሽቀዳደማቸው ያሉ ከብቶቻቸውን ለመሸጥ ገበያ ቢወጡ እንኳ ከ1,500 ብር በላይ እንደማያወጡ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድምፃቸውን መስማት የቀድሞውን የአኗኗር ዘይቤ ስለሚያስታውሳቸውና ተስፋ ስለሚሰጣቸው፣ በቀሩት ከብቶች ማነስ አንዳልተከፉ ያስረዳሉ፡፡

የቦረና ዞን ዳስ ወረዳ ቀቀሎ ሀሮ ኡርጌ ቀበሌ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኙኬ ቦሩ እንደሚሉት፣ በመንደሯ የተጎዱ ዜጎችን ማሰባሰብ ከተጀመረ 13 ወራት ሆነዋል፡፡ በቀበሌው ትልቁ ችግር ምግብና የውኃ እጥረት መሆኑን፣ ወረዳውም በሳምንት አራት ጊዜ በቦቴ ውኃ እያቀረበ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ ቀበሌዎች በተሰባሰቡት 370 አባወራዎች ሥር ከ2,000 በላይ ቤተሰቦች እንደሚኖሩ አቶ ኙኬ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በመንግሥት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ የምግብ ዕጦት ላጋጠማቸው እንደሆነ የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ አቅመ ደካሞች፣ ሕፃናትና ነፍሰ ጡሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፕላን ኢንተርናሽናል ግበረ ሰናይ ድርጅት አማካይነት ለእያንዳንዱ አባወራ 4,500 ብር እንደተሰጠ፣ ኬር ኢትዮጵያ የተባለ ሌላ ግብረ ሰናይ ድርጅት ደግሞ ስንዴ ማቅረቡን፣ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ ሌላው ችግር ብለው የገለጹት በመንደሩ የቀሩት ከብቶች በሕይወት ማቆየት መሆኑን፣ ተፈናቃዮቹ ከብቶቻቸው አልቆባቸዋል ተብሎ ስለተነገረ እስካሁን ምንም ዓይነት የከብት መኖ እንዳላገኙ ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ሊመንበሩ እንደገለጹት፣ የመንደሩን ችግር በሚዲያዎች አማካይነት የሚመለከታቸው የበላይ አካላት ችግራችን እንዲያውቁ እየጮሁ ቢሆንም፣ በሚጮሁት ልክና ባለው የሕዝብ ቁጥር ልክ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተር ከመንደሩ ነዋሪዎች በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ቢሰማም፣ ሊቀመንበሩ አቶ ኙኬ ግን ይህንን አስተባብለዋል።

አቶ ኙኬ እንደሚሉት፣ በቀበሌው በምግብ ዕጦት ሳቢያ አንድም የሞተ ሰው የለም። ይሁን እንጂ በከፍተኛ የምግብ ዕጦት ሳቢያ ወደ ሕክምና የተላኩ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና አቅመ ደካሞች መኖራቸውን አልካዱም፡፡ በመንደሩ ሕይወታቸው ያለፉት ከብቶች ሥጋ የሌላቸው በመሆናቸው ሥጋ በል የዱር እንስሳት እንኳ ለምግብነት አይጠቀሟቸውም ሲሉ ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡

ለመንደሩ ዕርዳታ እየተሰጠ ያለው አንዳንዶች በምግብ ዕጦት አቅማቸው ከደከመ በኋላ መሆኑን፣ ችግሩን ማቃለልና መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ በቀበሌው ያለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ብቻ መሆኑን፣ ያለው ክፍልም አንድ ስለሆነ ለሁሉም ማድረስ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ በድርቅ ሳቢያ ከተቋቁሙት 20 የተፈናቃዮች መንደር ውስጥ አንዱ በቦረና ዞን ድቡልቅ ወረዳ የሚገኘው ነው፡፡ የመኪና ድምፅ ሲሰሙ የዕለት ጉርስ የሚመጣላቸው እየመሳላቸው ወደ ሰሙት ድምፅ የሚኮለኮሉ እናቶች፣ አባቶችና ሕፃናት ቁጥራቸው በጣም በርካታ ነው፡፡ 

ከመንደሩ ነዋሪዎች መካከል በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገኙት አንድ እናት ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ቀበኔ ጉዮ ከመዳች አነስተኛ ቀበሌ ወረዳ ዱቡልቅ ወረዳ በሚገኘው መጠለያ ኑሮዋቸውን ከጀመሩ 12 ወራት ሆኗቸዋል፡፡ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ቀበኔ እንደ ወትሮው የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማስቀጠል ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ልጆቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት የግድ ጆሮዋቸው የዕርዳታ አቅራቢ መኪናዎችን ድምፅ ለመስማት ንቁ መሆን አለባቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ ቀበኔ ሁሉ የመንደሩ እናቶች ልጆቻቸውን በቀን አንዴ መመገብ ፈተና እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡ አምስቱም ልጆቻቸው ድርቁ ባስከተለው ችግር ትምህርታቸውን ትተው በድቡሉቅ ወረዳ በሚገኘው መጠለያ ለመክተም መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡ በመጠለያው የመማር ዕድል ያገኙት ሦስቱ ልጆቻቸው መሆናቸውን፣ የተቀሩት ልጆች ለማስተማር የትምህርት ቤቱ አቅም እንደማይፈቅድ ገልጸዋል፡፡ በደጉ ዘመን የወ/ሮዋ ከብቶች ብዛት 25 ቢሆንም፣ በድርቁ በግጦሽ መሬትና የውኃ ዕጦት ሳቢያ ሁሉም አልቀውባቸዋል፡፡

የመንደሩ ነዋሪዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኙ እንባ ያቀረረው በዓይናቸው ያስታውቃል፡፡ በተለይ እንደ ቀበኔ ያሉት ሴት አርብቶ አደሮች ሕይወታቸውን ከድጡ ወደ ማጡ ያደረገባቸው ድርቅ፣ የቤተሰቦቻቸውን እስትንፋስ ለማቆየት የመኪና ድምፅ በተጠንቀቅ መስማት ግንባር ቀደሙ ሥራቸው ነው፡፡ የዕለት ጉርስ ብርቅ የሆነባቸው ወ/ሮ ቀበኔና የመንደሩ ነዋሪዎች፣ ድርቁ ከብቶቻቸውን ጨርሶ ወደ ሰዎች ሕይወት እንዳይዞር ተጨማሪና ዘላቂ ዕገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ፡፡ ውኃ ለማግኘት ለቀናት የሚጠብቁት ወ/ሮ ቀበኔና የመንደሩ ነዋሪዎች፣ በቦቴ የሚመጣውም ውኃ ካለው ሕዝብ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡ 

በዝናብ የሚታወቀው የቦረና ከብቶች ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው፣ አሁን እነዚህ ሁሉ ከብቶች ታሪክ ሆነው መቅረታቸውን አስረድተዋል፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች ትልቁ ችግር የነፍስ ማቆያ ምግብና ውኃ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ቀበኔ፣ መንግሥት ትውልዱን (ልጆቻቸውን) እንዲታደግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አቶ ጎዳና ቁንጮራ የድቡልቅ የተፈናቃዮች መንደር ኃላፊ ናቸው፡፡ መንደሩ ከተመሠረተ 13 ወራት እንደሆነው፣ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ በመንደሩ ከ9,000 በላይ አባወራዎች ይኖሩበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተፈናቃዮች የሚያስተናግደው ይህ መንደር፣ በከፍተኛ ሁኔታ ዜጎች ስለሚጎርፉ የሚቀርበው ዕርዳታ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ አሁን ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚገኘው ዕርዳታ የሕዝቡን ሕይወት ለማስቀጠል መሆኑን፣ ከመንደሩ ነዋሪዎች ብዛት አኳያ የሚቀርበው ዕርዳታ በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመንደሩ በቀን አምስት የቦቴ ውኃ የሚቀርብ ቢሆንም፣ የሚመጣው ውኃ ለሕዝብ ሲከፋፈል ለአንድ ቤተሰብ በሊትር አምስትና ከዚያ በታች የሚከፋፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የመንደሩ ትልቁ ችግር ትምህርት ቤቶች እጥረት መሆኑን ገልጸው፣ ትምህርት ፈላጊው ከተመዘገቡ 2,000 ተማሪዎች ውስጥ 50ዎቹ ብቻ ዕድሉን አግኝተዋል ብለዋል፡፡ በትምህርት ሰዓት ልጆች በምግብ ዕጦት ምክንያት ራሳቸውን የሚስቱ መኖራቸውን የሚገልጹት፣ የፕላን ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል ፕሮግራም ማናጀር አቶ መኰንን ዲልቦ ናቸው፡፡

ከቦረና ዞን በተጨማሪ ምዕራብ ጉጂ (ምሥራቅ ቦረና) ከባሌ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎችና ምሥራቅ ሐረርጌ ጥቂት ወረዳዎች በድርቅ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ባለፉት አምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ያላገኙ አካባቢዎች ወይም ለሦስት ዓመታት ዝናብ ያላገኙ ቦታዎች በመሆናቸው፣ ድርቁ ለሰዎችም ሕይወትም ሥጋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የቦረና ዞንና አካባቢው ነዋሪዎች ሕይወታቸው የተመሠረተው በከብቶች ላይ መሆኑን፣ በድርቁ ሳቢያ ከብቶቻቸው በመሞታቸው በገጠራማ አካባቢዎች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩት ነዋሪዎች ወደ ወረዳው ከተሞች ዙሪያ መሰደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ቦረና ዞን 1.7 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖሩበት ገልጸው፣ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ደግሞ ከ800,000 በላይ ዜጎች ናቸው ብለዋል፡፡ በዞኑ 20 የተፈናቃዮች መንደሮች መኖራቸውን፣ የመንደሮቹ ትልቁ ራስ ምታት ውኃና ምግብ እጥረት መሆኑን አቶ መኰንን ተናግረዋል፡፡ በድርቁ ምክንያት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን፣ ትምህርት በመቋረጡ ያለ ዕድሜ ያገቡ ልጃገረዶች በዞኑ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አምስት በመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶች ያለ ዕድሜያቸው ማግባታቸውን፣ ከዚህ ቀደም በሴቶች ላይ የሚደርስ አስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደማይሰማ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ጥናት እንደሚያስፈልገው በመግለጽ በአካባቢው የሚደርሳቸው መረጃ ዋቢ አድርገው የተናገሩት አቶ መኰንን፣ ድርቁ ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ሳቢያ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን አስድተዋል፡፡

ይህም የሆነበትን ምክንያት ያስረዱት አቶ መኰንን፣ ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ባህልና ወግ ለመጠበቅ እንደተቸገረ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ሦስት ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ መሆናቸውን፣ በተለይም በቦረና ዞን 13 ወረዳዎች የሚኖሩ ከ800,000 በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

የቦረና ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ አምስት የበልግ ወቅቶች 3.6 ሚሊዮን የቤት እንስሳት ሞተዋል። ድርቁ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትሏል ብቻ ሳይሆን፣ በአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

 የጋዮ አርብቶ አደር ዴቭት ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር መሰለ ሥዩም አያኖ፣ ‹‹ውኃ ስትጠይቁ ወተት ሊሰጧችሁ የሚችሉ አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች፣ በዝናብ መጥፋትና ከብቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ሥቃይ ሲደርስባቸው ማየት በጣም ያሳዝናል፤›› ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን፣ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

እንዳለመታደል ሆኖ በዚህ ቀውስ ሴቶችና ልጃገረዶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዱ፣ እናቶች የልጆቻቸውን እስትንፋስ ለማሰንበት እየታገሉ ነውና ልጃገረዶች ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጽሙ እየተገደዱ ወይም ትምህርታቸውን እያቋረጡ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል።

‹‹ይህ ሁኔታ  በመቀጠሉ በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ በሚደርስባቸው የጥቃት መጠን መጨመር ተስተውሏል። ቤተሰቦች ምግብና ውኃ ለማግኘት እየታገሉ እንደሚገኙ፣ ይህን ችግር ለመፍታት አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰዳችንና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ነው›› ይላል።

አስቸኳይ ዕርዳታ  በስፋት ካልቀረበ እየተንሰራፋ ያለው የድርቅ አደጋ ሕፃናትን፣ ልጃገረዶችንና ቤተሰቦቻቸውን እንዳይጎዳ መከላከል አይቻልም ሲሉ የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሙዳሰር ሲዲኪ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሐፈት ቤት በቅርቡ ባወጠው ሪፖርት፣ የቦረና ዞን ለስድስተኛ ጊዜ ዝናብ እንደማያገኝና እስከ የካቲት መጨረሻና መጋቢት ድረስ በርካቶች ለረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ በድርቅና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አስቸኳይ የምግብና ዕርዳታ ለማቅረብ 3.34 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን በሁሉም አካባቢዎች የተሰጠው ዕርዳታ መጠን መድረስ ካለበት በታች ወይም 48 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...