Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የሥራ መደራረብና የፋይናንስ እጥረት ማነቆ እንደሆኑበት አስታወቀ

ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የሥራ መደራረብና የፋይናንስ እጥረት ማነቆ እንደሆኑበት አስታወቀ

ቀን:

  • በቀረቡ ጥቆማዎች የተከሰሱ ሰዎች ከአንድ ሺሕ በላይ መሆናቸው ተገልጿል

የፌዴራል መንግሥት በአገር ደረጃ እየተንሰራፋ እንደመጣና የአገር ደኅንነት ሥጋት ደቅኗል ያለውን የሙስና ድርጊት ለመቀነስ በኅዳር 2015 ዓ.ም. ያቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ፣ ሥራውን በሚጠበቅበት ልክ ለማከናወን የሥራ መደራረብ፣ የሰው ኃይልና የፋይናንስ እጥረት ተግዳሮት እንደሆነበት አስታወቀ፡፡

በአገር ላይ የደኅንነት ተግዳሮትና ሥጋት እንደሆነ የመንግሥት የበላይ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ የሚገልጹትን የተደራጀ ሌብነትና ሙስና ለመታገል፣ በጊዜያዊነት የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አማካይነት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅነነት አገልግሉት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመሥገን ጥሩነህና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በኮሚቴው ተካተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌደራልና የክልል የፀረ ሙስና ኮሚቴዎች ‹‹አገራዊ ጥምረት ለላቀ የፀረ ሙስና ትግል›› በሚል መሪ ቃል፣ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀ የጋራ መድረክ ተወያይተዋል፡፡

በመድረኩ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ለአፈጻጸሙ ገጠመኝ ካላቸው ተግዳሮች መካከል፣ ኮሚቴው በተለያዩ ተቋማት በመወከሉ ሥራውን በፍጥነት ለመሥራት አለመቻል፣ የጥቆማ ማነስ፣ በተራጀ መንገድ የሚዲያ ቅስቀሳ አለመኖር፣ የማኅበረሰቡ ተሳታፊ አነሳ መሆን፣ የሥራ መደራረብ፣ የሰው ኃይል ችግርና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል፡፡

ለአብነት ያህል ተሽከርካሪ፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖችና የመሳሰሉት የግብዓት እጥረቶች የተዘረዘሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም የምርመራ መዘግየት፣ የሰነድ ማስረጃ አለመግኘት፣ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ እጥረትና የመሳሰሉ ችግሮች ተካተዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተርና የብሔራዊ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ተመሥገን ጥሩነህ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ ሙስና ረቂቅ የወንጀል ድርጊት መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ ድርጊት በዋናነት ‹‹በዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በንዋየ ፍቅር በታወሩ ደላሎች፣ በባለሀብቶችና በመንግሥት ሠራተኞች ያልተቀደሰ ትስስር የሚፈጸም በመሆኑ፣ ይህንን ትስስር በመቆራረጥ የአገርን ሀብት መታደግ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ሙስናን ለአገር ሥጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሠራ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኮሚቴው ከተቋቋመ ወዲህ 750 ጥቆማዎች በፌደራል ደረጃ የተገኙ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካከል በተደረገው ማጣራት በ179 ጥቆማዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በ81 ጥቆማዎች የክስ መዝገብ መደራጀቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ክስ ውስጥ የተከሳሽ ሰዎች ብዛት 640 መድረሱን፣ ለኮሚቴው ቀርበው የማጣራት ሥራ ከተሠራባቸው ውስጥ እስካሁን ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ሀብት ላይ ጉዳት እንደደረሰና 225,885 ካሬ ሜትር መሬት ደግሞ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፀረ ሙስና ኮሚቴዎች ከቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ በአማራ 540፣ በኦሮሚያ 204፣ በአዲስ አበባ 204፣ በሶማሌ 417፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 102፣ በቤንሻኒጉል ጉሙዝ 70፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 72፣ በሐረር 38፣ በሲዳማ 80፣ በጋምቤላ 13 እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 15 ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በፌደራል ደረጃም ሆነ በክልሎች በአመዛኙ ከሕዝብ ጥቆማ የቀረበባቸው አካባቢዎች ከመሬት ካሳ ክፍያ፣ ከመንግሥት ቤት፣ ከፋይናንስና ገቢዎች፣ ከግዥና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ሥልጣንን በመጠቀም ገንዘብ ከመቀበል፣ ከመሬት ወረራ፣ ከመንግሥት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር፣ ምንጩ ካልታወቀ ሀብትና ንብረት ማፍራት፣ ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የመንግሥት ገቢን ከመሰወር ጋር የሚገናኙ ይገኙበታል፡፡

በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ፀረ ሙስና ኮሚቴ ምርመራ ከተደረገባቸው የጥቆማ መዛግብት ውስጥ ምርመራቸው ተጠናቆ የተደራጁት መዛግብት ከፌደራል 81፣ ከአማራ 134፣ ከኦሮሚያ 197፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 7፣ ከደቡብ 4፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ 8፣ ከሐረሪ 8፣ ከሲዳማ 44፣ ከጋምቤላ 6፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ 98 ይገኙበታል፡፡

ይሁን እንጂ ምርመራ በተጠናቀቀባቸው መዝገቦች ክስ የተመሠረባቸው መዝገቦች በፌደራል 65፣ በአማራ 4፣ በኦሮሚያ በ136፣ በደቡብ 3፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 2፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 1፣ በሶማሌ 124፣ በሐረሪ 8፣ በሲዳማ 30፣ በጋምቤላ 1፣ በአዲስ አበባ 2 መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ በፌደራልና በክልሎች በደረሰ ጥቆማ ክስ የተመሠረተባቸው መዝገቦች 391 መሆናቸውን፣ የተከሳሽ ሰዎች ብዛት ደግሞ 1,067 መድረሱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...