Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኦሮሚያ አምስት ዞኖች ለአርሶ አደሮች የቀረቡ ኮምባይነሮች አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው ቅሬታ አስነሳ

በኦሮሚያ አምስት ዞኖች ለአርሶ አደሮች የቀረቡ ኮምባይነሮች አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

  • ለ77 ኮምባይነሮች ግዥ ከ362 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል
  • ሃያ ኮምባይነሮች በባንክ ተወርሰዋል

በኦሮሚያ ክልል አምስት ዞኖች ለሞዴል አርሶ አደሮች የቀረቡ ኮምባይነሮች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ምክንያት፣ ለችግር መጋለጣቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች አስታወቁ፡፡

በክልሉ በሚገኙ አምስት አካባቢዎች ማለትም ከምዕራብ አርሲ፣ ከአሰላ ዙሪያ፣ ከባሌ፣ ከምሥራቅ ሸዋና ከሐረርጌ ዞኖች የተውጣጡ ሞዴል ተብለው የተመረጡ አርሶ አደሮች፣ ‹‹ጆንዲር ሲ120›› የተሰኘ ኮምባይነር በግዥ መልክ ቢቀርብላቸውም፣ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ብልሽት በማጋጠሙ አገልግሎት ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

መስከረም 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ዘመናዊ ኮምባይነር ግዥ እንዲፈጸምላቸው የተነገራቸው 77 አርሶ አደሮች፣ ቅድመ ክፍያ 30 በመቶ 1.4 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉና ቀሪው 70 በመቶ 3.3 ሚሊዮን ብር በባንክ ተሸፍኖ፣ በአምስት ዓመት 1.8 ሚሊዮን ብር ወለድ ጨምሮ ክፍያው እንዲፈጽሙ ታስቦ ማሽኖችን መረከባቸውን፣ የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ በአጠቃላይ ለ77 ኮምባይነሮች ግዥ ከ362 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አክሏል፡፡

ከአምስቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 77 አርሶ አደሮች ኮምባይነሩን ተረክበው ወደ ሥራ ቢገቡም፣ ኮምባይነሮቹ ከ30 ደቂቃ በላይ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ ብልሽት እየገጠማቸው ለጥገና ጋራዥ እየገቡ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ያወሳሉ፡፡

ለአርሶ አደሮቹ ከቀረቡት 77 ኮምባይነሮች መካከል 65 ያህሉ ለጥገና ወደ ጋራዥ ቢገቡም፣ ብልሽታቸው ተመሳሳይ የሆነና የጥራት ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

‹‹መጀመሪያ የተነገረን ጥራት ያላቸውና ዘመናዊ የአሜሪካ ኮምባይነሮች እንደሚቀርቡልን ነበር፡፡ በአንፃሩ ሁሉም ማሽኖች በተመሳሳይ ችግር ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጡን አልቻሉም፤›› ሲልም አብራርቷል፡፡

አርሶ አደሮቹ አሥር አባላት ያሉት ኮሚቴ በማዋቀር በኮምባይነሮቹ ላይ ጥናት እንዲደረግባቸው መደረጉ ተገልጿል፡፡ ስላለባቸው ብልሽት በባለሙያ ጥናት ከተደረገባቸው በኋላ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን በዝርዝር በሪፖርት መልክ የቀረበ በመሆኑ፣ ለክልሉ መንግሥት ግብርና ቢሮ ሪፖርቱ መቅረቡም ታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት በባሌ፣ በምዕራብ አርሲና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች የሚገኙ 67 ኮምባይነሮችን በአካል በመገኘት የእያንዳንዳቸው ብልሽት መታየቱም ተጠቁሟል፡፡

‹‹የኮምባይነር ባለቤቶችን፣ የማሽኖቹ ኦፕሬተሮችን፣ የአካባቢ ነዋሪዎችን፣ እንዲሁም አርሶ አደሮችን ጭምር በማነጋገር የጽሑፍና የፎቶ ማረጋገጫዎችን ይዘናል፤›› በማለት ኮሚቴው ሒደቱን ገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ የ56 ኮምባይነሮችን የአገልግሎት ሰዓት (Engine Hour or Drum Hour) የተመለከተ መሆኑን፣ ማሽኖቹ በሰዓት ከፍተኛው 2,798.5 ሰዓታት ሲሠሩ፣ ዝቅተኛው 1,168.63 ሰዓታት፣ እንዲሁም መካከለኛው 1,806.3 ሰዓታት ብቻ ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ማሽኖቹ እህል ማጨድ (Cutting System)፣ እህል መውቃት (Threshing system)፣ እህልን ከገለባ መለየት (Separation)፣ እህሉን ማፅዳት (Cleaning System) መሠረታዊ አገልግሎቶች የመስጠት ችግር እንዳለባቸው መረጋገጡ ተነግሯል፡፡

ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ መፍትሔ ለማግኘት ለክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ በአካልና በጽሑፍ ለማቅረብ ቢቻልም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

ማሽኖቹ ለአርሶ አደሮቹ ከባንክ በተመቻቸላቸው ብድር አማካይነት መቅረባቸውን፣ ከባንኮች ቀሪ ክፍያን በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበባቸው እንደሆነም አክሏል፡፡  

የባንክ ወለድን ጨምሮ በአምስት ዓመታት ስድስት ሚሊዮን ብር ክፍያ የሚጠበቅባቸው ባለንብረቶቹ፣ ከ77 ኮምባይነሮች መካከል 20 ኮምባይነሮች በወቅቱ ክፍያ ባለመፈጸማቸው በባንክ መወረሳቸው ታውቋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ለኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን የሚገልጹት ባለንብረቶቹ፣ አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ቢናገሩም፣ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ግን ኮምባይነሮቹ ጥገና እንደተደረገላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ብልሽት የገጠማቸው ኮምባይነሮች በመኖራቸው ከአርሶ አደሮቹ ጋር ከተወያየን በኋላ ከአስመጪዎቹ ጋር ተነጋግረን፣ ባለሙያዎች ከውጭ መጥተው ጥገና እንዲደረግላቸው አድርገናል፤›› ሲሉ አቶ ጌቱ ገልጸዋል፡፡

ኮምባይነሮቹ ጥራት የሌላቸው በመሆናቸውና አርሶ አደሮቹም ሠርተው ከባንክ የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ስላልቻሉ፣ የክልሉ መንግሥት ተተኪ ማሽኖችን አስመጥቶ ሠርተው ከዕዳ ነፃ የሚሆኑበትን መፍትሔ ሊያበጅ እንደሚገባ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የመጨረሻ መፍትሔ ለማግኘት ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ስለሁኔታው የሚያስረዳ ደብዳቤ መግባቱን አስታውሶ፣ ምንም ዓይነት ምላሽ አለመገኘቱንም ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...