ባንኮች በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ለተሰማሩና ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡
በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለልማት የወሰዱትን መሬት ከመመንጠር አንስቶ ማሽኖችን ተከራይቶ ለማስገባት፣ በሔክታር ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደሚጠይቅ፣ ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሻ ቦታ የሚወስዱ መንገዶችን መገንባት ሌላው የሚጠበቅባቸው ተግባር ስለሆነ የባንኮች ድጋፍ ያስፈልግቸዋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፍራፍሬና አትክልት ሽያጭ አክሲዮን ማኅበር (ኢትፍሩት) ከሚያሠራጨው የሙዝ ተክል 70 በመቶውን የሚያቀርበው የዳኜ ዳባ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ድርጅት ባለቤት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር አድናቆት ለቸሩት በብላቴና በዓባያ አካባቢዎች በጠቅላላው በ3,500 ሔክታር ላይ ለተንጣለለው የአቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬ የእርሻ ልማት የትኛውም ባንክ ብድር አላቀረበላቸውም፡፡
የፋይናንስ ተቋማት እውነተኛ አገልግሎት ሰጪዎች መሆናቸው ሊመዘኑ ከሚችሉባቸው መሥፈርቶች ውስጥ ደንበኞቻቸውን ቀርበው በማየት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማቅረብ ዋነኛው ተግባር ነው የሚሉት አቶ ዳኜ፣ በተለይ በእርሻ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፉ ለአገር የሚሰጠውን ጥቅም ማገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ሰፋፊ እርሻ እንዲገቡ ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ዳኜ አክለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች አማካይነት ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸርና የፍሎሪካልቸር ኤግዚቢሽን፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
በኤግዚቢሽኑ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ እያመረቱ እንደሚገኙ ያስተዋወቁ ባለሀብቶች እንደገለጹት፣ በትልልቅ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ዘርፉ ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ በፋይናንስ ተቋማትና በሌሎች የመንግሥት ቢሮዎች ደጅ በመጥናት ማሳለፍ እንደማይችሉና በዚህ ዙሪያ ያሉ ችግሮቻቸው ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንትና የአግሮ ኢኮኖሚ ተመራማሪ መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ከምርት ባህሪው አንፃር ዓመቱን በሙሉ ለሚሠራው የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት አስፈላጊ የሆነውን ውኃ ለማግኘት ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የግብዓት ወጪዎች አሉ፡፡ ተወዳዳሪ የኤክስፖርት ምርት ለማምረት ከተፈለገ ደግሞ ከላይ የተገለጹትን ወጪዎች ለመሸፈን፣ በተለይ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አክለዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ግብርናን ዘንግተውታል የሚሉት መንግሥቱ (ፕሮፌሰር)፣ ሥጋት ስላለባቸው ለሌላው ዘርፍ እንደሚያደሉ በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለውን ግብርና መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡
የግል ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ በመንግሥት ሥር ያሉትም የፋይናንስ ተቋማት በግብርናው ዘርፍ ላይ አልገቡም ማለት ይቻላል ሲሉ የገለጹት መንግሥቱ (ፕሮፌሰር)፣ ስለሆነም የራሱ የሆነ የፖሊሲ ማዕቀፍ ኖሮት የፋይናንስ ተቋማት የብድር ሥርዓታቸውን አሻሽለው፣ ለአብነትም ከሚያበድሩት ላይ የተወሰነው ድርሻ ለግብርና ማድረግ አለባቸው የሚል ግፊት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
ፍራፍሬን ወደ ውጭ ለመላክ ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ቀዝቃዛ ኮንቴይነር አንዱ ሲሆን፣ ለዚህም ራሱን የቻለ ፋይናንስ እንደሚያስፈልግና ከባለሀብቶች በተጨማሪ መንግሥት እየተስፋፋ ለመጣው የፍራፍሬ ምርት ኤክስፖርት ተፈላጊ የሆነውን ቀዝቃዛ ኮንቴይነርና ተሽከርካሪ ሊያቀርብ ይገባል ተብሏል፡፡
ከብላቴና ከዓባያ አካባቢዎች በተጨማሪ በጉራጌ ዞን በሁለት ሺሕ ሔክታር ላይ የፍራፍሬና ለዘይት ምርት ግብዓት የሆነውን የሱፍ አበባ ተክል እያለሙ እንደሆነ፣ በተጨማሪም ስምንት ሺሕ ሔክታር የማስፋፊያ መሬት መጠየቃቸውን የተናገሩት አቶ ዳኜ፣ በአጠቃላይ አሥር ሺሕ ሔክታሩን ለማልማት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚጠይቅና ቢያንስ ሁለት ሺሕ ሔክታር በራሳቸው ወጪ ለመሸፈን ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
ለዘይት ፋብሪካዎች ዋነኛ ግብይት የሆነውን የሱፍ አበባ በሰፊ እርሻ ላይ የማባዛት ሥራ እያከናወኑ እንደሆኑ ያስረዱት አቶ ዳኜ፣ ይህም ለገበሬው እንደሚዳረስ ተናግረዋል፡፡ የሱፍ አበባ በሔክታር 42 ኩንታል የሚገኝበት መሆኑን፣ ከአንዱ ኩንታል 42 ሊትር ዘይት የሚገኝበት ስለሆነ ለገበሬዎች ከፍተኛ ጥቅም የሚያመጣ መሆኑን ባለሀብቱ ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪ በጂቡቲና በሶማሌላንድ የፍራፍሬ ምርታቸውን እንደሚያቀርቡ የሚናገሩት ባለሀብቱ፣ በአዲስ አበባ በየዕለቱ እስከ አምስት ተሽከርካሪዎች የፍራፍሬ ምርት በቅናሽ ዋጋ ቢያስረክቡም የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ላይ ሰፊ ሥራ ባለመሠራቱ በኪሎ 28 ብር የሚያስረክቡት ሙዝ ገበያ ውስጥ 60 ብር እንደሚሸጥ ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ባለሀብቶች የሚሸጡበት ቦታ ቢያገኙ ምርቶቻቸውን በርካሽ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡