Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዕግድ የተጣለባቸው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ

ዕግድ የተጣለባቸው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአዲስ አበባ ከተማ የባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪዎች ከየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እንዳይሰጡ በመደረጋቸው፣ አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡

የከተማዋ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ‹‹አትሠሩም›› ብሎ ማገዱ ‹‹ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሮብናል›› ሲሉ አሽከርካሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪ ባለትዳርና የልጅ አባት መሆኑን ገልጾ፣ በድንገት ሥራ ታቆማለህ መባሉ ቤተሰቡን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ድርጊት መሆኑን ገልጿል፡፡

የዕለት ምግብ ፍጆታን ጨምሮ ነዳጅና ሌሎች ወጪዎችን በማሟላት በቀን 200 ብር በመቆጠብ፣ የቤት ኪራይና ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ይሠራ እንደነበር ተናግሯል፡፡

‹‹ከቀን ወደ ቀን እየከበደ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ደፋ ቀና በምንልበት ወቅት፣ ይህንን መሰል ዕገዳ መጣሉ ችግሩን ከዚህ የከፋ የሚያደርግ ይሆናል፤›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ‹‹ለልጄና ለባለቤቴ የማቀርብላቸውን ሳስብ ይጨንቀኛል፤›› ያለው ወጣቱ አሽከርካሪ፣ ሥራ ከማቆሙ በፊትም ቢሆን አንዳንድ ሕግ አስከባሪዎች ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው በእሱና በሌሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርሱባቸው እንደነበር ተናግሯል፡፡

‹‹እየሠራን ቤተሰብ ለመምራት እንኳን ባልቻልንበት ሁኔታ መሥራት አትችሉም መባላችን፣ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎብናል፤›› ሲል ሌላው የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪ ወጣት ተናግሯል፡፡

ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ተቀጥሮ እየሠራ በሚያገኘው ገቢ ብቻ መሆኑን ተናግሮ፣ ሰሞኑን በተደረገው ክልከላ ንብረቱን ለባለቤቱ መመለሱንና ሥራ ፈትቶ መቀመጡን አክሏል፡፡

እየታየ ካለው የኑሮ ውድነት ላይ ሥራ አጥነት ተጨምሮበት ነገሩን የበለጠ ያባብሰዋል እንጂ ሌላ ፋይዳ የለውም ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ክልከላው የአንድን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የብዙ ቤተሰቦችን ኑሮ ሊያመሰቃቅል የሚችል ውሳኔ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ከ3‚000 ሺሕ እስከ 4‚000 ሺሕ ብር በማውጣትና በሕጋዊ መንገድ በመደራጀት እንደ ማንኛውም ሥራ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድን በማሟላት የሚሠሩ ዜጎችን ከሥራ ማገድ፣ አግባብነት የሌለው ውሳኔ ነው ሲሉ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል፡፡

ዜጎችን ካለ በቂ ምክንያት ከሥራ ማፈናቀል የሥራ አጦችን ቁጥር ከመጨመሩም በላይ፣ ችግሩ ብዙዎችን ወደ ጎዳና የሚያወጣና ለሌሎች አላስፈላጊ ነገሮች ሊያጋልጥ የሚችል ነው ሲሉ ሥጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ችግራቸው ተመሳሳይ እንደሆነ የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፣ ንብረታቸውን ከአዲስ አበባ ውጪ ወስደው ሠርተው ለመኖር ጭምር መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡

መሄድ ከፈለጋችሁ ንብረታችሁን ትታችሁ ከተማዋን ለቃችሁ መውጣት ትችላላችሁ እየተባሉ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

‹‹ሠርተን ከማደር ውጪ ሌላ ነገር አናውቅም›› የሚሉት አሽከርካሪዎች በብሔርም ሆነ በፖለቲካ ልዩነት ሳይኖራቸው በሚሠሩበት ሁኔታ አንዳንድ የትራፊክ ፖሊሶች፣ ነገሩን ከፖለቲካና ከብሔር ጋር ለማያያዝ ሲሞክሩ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ለምን ሥራ እንዳቆሙና ክልከላውስ እስከ መቼ ነው የሚሉትን፣ እንዲሁም የተገልጋዮች ዕጣ ፈንታ ምንድነው ለሚሉት ጥያቄዎች ከአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ፣ ጉዳዩ ቢሮውን እንደማይመለከተው የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የተማ አስተዳደሩ በቂ ምላሽና ማብራሪያ እንደሰጠበት ገልጸው፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ማብራሪያ ስለባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያለው ነገር የለም፡፡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸውና የተወሰኑት በወንጀል ድርጊቶች ላይ በመሰማራት፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች የቅሬታ ምንጭ በመሆናቸው ነው ሲል የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ማብራሪያ ገልጿል፡፡

በዚህም አገልግሎቱን ሥርዓት ለማስያዝ የአሠራር ማስተካከያ እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ይህም ተግባራዊ እስከሚሆን በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አገልግሎቱ እንዲቆም መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎች ተገልጋዮች የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተመሠረቱ እንደ ሰሚት፣ ጀሞና ሌሎች አዳዲስ አካባቢዎች በተለይም ጧትና ማታ በትራንስፖርት ዕጦት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

አስፋልት ላልሆኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ትልቁን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት እነዚሁ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን የሚናገሩት ተገልጋዮቹ፣ ክልከላው ከተደረገ ወዲህ ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ መጉላላትና እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በሰጠው ማብራሪያ፣ የተሽከርካሪዎቹን ከሥራ መውጣት ተከትሎ በነዋሪዎቹ ላይ የትራንስፖርት ጫና እንዳይኖር ሌሎች አማራጮች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብሏል፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠበት የከፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል ያሉት አሽከርካሪዎች፣ ችግር የሚፈጥሩና ሌላ ዓላማ አላቸው ያላቸውን ግለሰቦች በመለየት በሰላማዊ መንገድ ሥራቸውን የሚሠሩት ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ውሳኔው የሥራ አጦችን ቁጥር ለመጨመር፣ ለዘረፋና ለግድያ የሚዘጋጁ ወጣቶችን ለማፍራት በር ከፋች ነው ሲሉ ተገልጋዮችም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...