- በፓርኩ ገና ሙሉ ለሙሉ ጥናት ሳይደረግ 51 ብርቅዬ የዱር እንስሳት በድርቅ ሞተዋል ተብሏል
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከብቶቻቸው ያለቁባቸው ሰዎች ለከፋ የምግብ ችግር በመጋለጣቸው፣ በዞኑ በሚገኘው ቦረና ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በሕገወጥ አደን መሰማራታቸውን የኦሮሚያ ክልል የዱር እንስሳት ድርጅት አስታወቀ፡፡
በዞኑ ዝናብ ለአምስት ወቅቶች ባለመዝነቡ ሳቢያ ነዋሪዎቹ የከፋ የምግብ ችግር ስለገጠማቸው በፓርኩ የሚገኙ ሳር በል እንስሳትን በሕገወጥ መንገድ ለማደን መገደዳቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል የዱር እንስሳት ድርጅት የዱር እንስሳት ፓርኮችና ኢኮ ቱሪዝም ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኑርጀማል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹በፓርኩ ውስጥ በሕገወጥ አደን ተሰማርተው የተያዙ ሰዎች አሉ፡፡ የታደኑ እንስሳት ውጤቶችም ተይዘዋል፤›› ያሉት አቶ መሐመድ፣ ‹‹ይህም የሆነው በድርቁ ሳቢያ ከብቶቻቸው ያለቁባቸው ሰዎች የዱር እንስሳቱን ለምግብነት ስለሚፈልጓቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በፓርኩ ከሚገኙ እንስሳት መካከል ድክድክ በመባል የምትታወቅ እንሰሳን በሕገወጥ አደን መገደሏንና ለአደን የተሰማሩ ሰዎች መያዛቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እስካሁን በዱር እንስሳት አደን ተሰማርቶ እንደማያውቅ ጠቅሰው፣ በድርቁ ሳቢያ የተጀመረው ሕገወጥ አደን በወቅቱ መፍትሔ ካልተሰጠው ድርጊቱ ሊስፋፋ እንደሚችል ሥጋታቸውን አስረድተዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ለምን በሕገወጥ አደን እንደተሰማሩ ሲጠየቁ፣ ‹‹ስንራብ ታዲያ ምን እናድረግ? ከብቶቻችንን እንኳ ለምግብነት እንዳንጠቀም በድርቁ ሞተው አልቀዋል፡፡ ልጆቻችንን ጨምሮ ምን እንብላ?›› እንደሚሉ ገልጸዋል፡፡
በዱር እንስሳት ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ አደን በዚህ አጋጣሚ እንዳይስፋፋ ሥጋት ያደረባቸው ዳይሬክተሩ፣ በምግብ ችግር ወደ ሕገወጥ አደን የተሰማሩ ሰዎች ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን 200 ኩንታል ዕርዳታ እንዳቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ማኅበረሰቡ በድርቁ ምክንያት ከብቱን በማጣቱ የዱር እንስሳት ሥጋ መብላት ጀምሯል፤›› ያሉት አቶ መሐመድ፣ ለዱር እንስሳቱ ግን በቂ ባይሆንም ሳርና ውኃ እየቀረበላቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት ተሰደው እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ የዱር እንስሳቱ እስካሁን ከብሔራዊ ፓርኩ እንዳልወጡ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ ግን በነዋሪዎች ላይ የተደቀነው የምግብ ችግር ስለሚጨምር በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት ጉዳትም በተመሳሳይ ሊከፋ እንደሚችል ሥጋት ማሳደሩ ተብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል ዳይሬክተሩ ለሪፖርተር ያስረዱት፣ በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በፓርኩ ውስጥ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት እየሞቱ መሆናቸውን ነው፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በፓርኩ ውስጥ 51 የዱር እንስሳት ሞተው መገኘታቸውን፣ ከእነዚህም መካከል 41 ያህሉ የሜዳ አህያ እንደሆኑ፣ ቀሪዎቹ አሥር ደግሞ ሳላ የሚል መጠሪያ ያላቸው እንስሳት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በብሔራዊ ፓርኩ የሚገኙ ቁጥራቸው ገና በውል ያልታወቀ ከርከሮዎች በውኃና በግጦሽ ሳር እጥረት መሞታቸውን፣ እንደ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ የቆላ አጋዘን፣ ሳላና ሌሎች በዓለም የማይገኙ ነገር ግን በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኙ የወፍ ዝርያዎች አደጋ ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በፓርኩ ስንት እንስሳት እንደሞቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተጠና፣ 51 የዱር እንስሳት መሞታቸው የታወቀው እንዲሁ በአጋጣሚ በመገኘታቸው መሆኑን ያብራሩት አቶ መሐመድ፣ በፓርኩ ጥናት ሲደረግ በድርቅ ምክንያት የሞቱ እንስሳት ብዛት ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ለተከታታይ አምስት ጊዜያት የዝናብ ወቅት በመቋረጡ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በከፋ ረሃብ ውስጥ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
በቦረና ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ አምስት ብሎኮች ሲኖሩት፣ ብሔራዊ ፓርክ ተብሎ ከመቋቋሙ በፊት የያቤሎ የእንስሳት መጠለያ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ በ2002 ዓ.ም. በብሔራዊ ፓርክነት የተቋቋመ ሲሆን፣ 3,132 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡