Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኦርቶዶክስ ከክስ በፊት ጊዜያዊ ዕግድ የጠየቀችባቸው ሕገወጥ ተሿሚ ግለሰቦች ስሟንና ዓርማዋን እንዳይጠቀሙ...

ኦርቶዶክስ ከክስ በፊት ጊዜያዊ ዕግድ የጠየቀችባቸው ሕገወጥ ተሿሚ ግለሰቦች ስሟንና ዓርማዋን እንዳይጠቀሙ ታገዱ

ቀን:

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በሚል ከክስ በፊት ጊዜያዊ ዕግድ ከጠየቀችባቸው ግለሰቦች ከሦስቱ ‹‹አባቶች›› በስተቀር፣ የተቀሩት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዓርማንና ስም እንዳይጠቀሙ ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

 የቤተ ክርስቲያኗ የጠበቆች ቡድኑ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የዋለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ችሎት በመዝገብ ቁጥር 300652 ሲካሄድ የነበረው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶበት ዕልባት እንዳገኘ ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የጠበቆች ቡድኑ እንዳስታወቀው፣ ከሦስቱ ‹‹አባቶች›› በስተቀር 26ቱ ግለሰቦች እስከ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ብቻ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሏትን ይዞታዎች፣ አገረ ስብከት፣ ገዳማትና አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናትና ንብረቶቿን፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ መገልገያዎቿን እንዳይጠቀሙ፣ ወደ ቅጥሯ እንዳይገቡ፣ ንብረቶቿን እንዳይወስዱ፣ እንዳይገለገሉ፣ ዓርማዋንና ስሟን ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋህዶ›› የሚለው የወል የእምነት መጠሪያ ስለሆነ እሱን ሳይጨመር የዕግድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡  

በተለያዩ አካባቢዎች ተሹመናል የሚሉት ግለሰቦች፣ የአመልካችን ቤተ ክርስቲያን ለመውረርና ለመንጠቅ በመሞከራቸው ‹‹የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል ይኼ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል›› ያለው የጠበቆች ቡድን፣ በመዝገብ ቁጥር 300652 ሲካሄድ በነበረው ክርክር ቤተ ክርስቲያን የሦስት ወር የጊዜ ገደብ አግኝታ ክስ ለመመሥረትና ለማዘጋጀት በሚል የተከፈተ እንደነበር አስታውቋል፡፡

 ከ25ቱ ተጠሪዎች አብዛኛዎቹ ጣልቃ ገብተው አቤቱታ አቅርበው ዕግድ ሊሰጥ አይገባም በማለት ጠበቃ ልከው መከራከራቸውንና መቃወሚያ (አስተያየት) እንዲሰጡ ተጠይቀው እንደተፈቀደላቸው ተገልጿል፡፡

በፍርድ ቤቱ ከቀረቡ መቃወሚያዎች፣ ‹‹አመልካች ይህን ክስ የማቅረብ ሰውነት የላትም፣ እንደ ሃይማኖት ተቋም ስላልተመዘገበች ጉዳዩ የደረሰው በምዕመንና አገልጋዮች ላይ ስለሆነ እነሱን ወክላ ይህን ክስ ማቅረብ አትችልም፣ ጉዳዩ የተከሰተው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ እስከሆነ ድረስ የፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ ሊታይ አይገባም›› የሚል መቃወሚያ ቀርቧል መባሉ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም በእርቅ ያለቀ ጉዳይ በዚህ ፍርድ ቤት ሊታይ አይገባም የሚል መከራከሪያ ቀርቧል ተብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱም በውሳኔው፣ ቤተ ክርስቲያን ክስ የመክሰስ (የማቅረብ) መብት ሥልጣን እንዳላት፣ ሌሎችንም ወክላ ለምዕመናንና አገልጋዮችም ክስ ማቅረብ ትችላለች መባሉን ያስታወቀው የጠበቆች ቡድን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተደረገ ዕርቅ ስላለ የሚለው ጉዳይ በሁለት መንገድ እንደታየ አስታውቋል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ የመግባቢያ ሐሳብ በሚል እንጂ እንደ ውል ተፈርሞበት የሚፀና አይደለም በሚል የቀረበውን ክርክር ፍርድ ቤቱ በመደገፍ እርቅ ሳይሆን የመግባቢያ ሰነድ እንዳለ ተቀብሏል ያለው የጠበቆች ቡድኑ፣ በሦስቱ ተከሳሾች ላይ (በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎስና አባ ዜና ማርቆስ) ዕግድ እንደማይሰጥ መወሰኑን፣ ነገር ግን አጠቃላይ ከተራ ቁጥር 4 እስከ 25 የተጠቀሱትና ተሹመናል የሚሉት አባቶች እንዲሁም ጠበቃ ኃይለ ሚካኤል ግን ፍርድ ቤቱ እርቅ አለ ለማለት የሚያስችል ነገር አላገኘም በማለት መቃወሚያቸውን ውድቅ አድርጓል ሲል አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቤተ ክርስቲያን በጠበቆች ኮሚቴ አማካይነት ያቀረበቻቸው አብዛኞቹ ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ከተጠየቀባቸው ጉዳዮች ውስጥ አብዛኞቹ በጊዜያዊ ዕግድ የሚታዩ አይደሉም ብሎ፣ በተለየ ሁኔታ ግን የንብረት መብትን በተመለከተ የቀረበውን ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስትያናት፣ ገዳማት ወዘተ መብት እንዳላት በመቀበል ዕግድ መሰጠቱ በመግለጫው ተዳሷል፡፡

 በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎስና አባ ዜና ማርቆስ ሲቀሩ ከተራ ቁጥር 4 እስከ 25 የተዘረዘሩትና ተሹመናል የሚሉት አባቶች እንዳይገቡ እንዳይደርሱ ዕግድ የተሰጠ ሲሆን፣ ዕግዱ ከተሰጠስ ለምን ያህል ጊዜ ይሆናል? በሚል በተያዘው ጭብጥ ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ወር በሚል የጠየቀች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ አንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን ይበቃችኋል በሚል ወስኗል ተብሏል፡፡

 ዕግዱም የሚቆጠረው የመጀመርያው ዕግድ ከተሰጠበት የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀመሮ ስለሚሆንና የሚጠናቀቀውም የጠበቆች ቡድንና አመልካች ቤተ ክርስቲያን ክሳቸውን ማቅረብ ያለባቸው ከመጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እንደሆነ ውሳኔ ተሰጥቷል መባሉን በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

ዕግዱ ፀንቶ እስከሚቆይበት መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም.  ድረስ የተወገዙት አባላት ኢትዮጵያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ገዳማትና የቤተ ክርስቲያኗ ንብረቶች ጋር መገኘት እንደማይችሉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...