Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበግብፅ በኩል ስለህዳሴው ግድብ የሚንፀባረቀው አቋም ኋላቀርና ለዘመኑ የማይመጥን መሆኑን የውጭ ጉዳይ...

በግብፅ በኩል ስለህዳሴው ግድብ የሚንፀባረቀው አቋም ኋላቀርና ለዘመኑ የማይመጥን መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

ቀን:

  • የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል

ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የታላቁ የህዳሴ ግድብና በአጠቃላይ የዓባይ ወንዝን በተመለከተ በአንዳንድ ግብፃውያን ‹‹የሚንፀባረቀው አቋም ኋላቀር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለዘመኑ የማይመጥን ነው›› ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) ለጋዜጠኞች በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፣ ከሰሞኑ በግብፅ ካይሮ በተካሄደው 159ኛው የዓረብ ሊግ ስበሳባ ላይ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ አገራቸው በህዳሴው ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ግር ላላት አለመግባባት ለዓረብ ሊግ አገሮች ያቀረቡትን የድጋፍ ጥሪ አጣጥለውታል፡፡

‹‹የዓረብ ሊግ አፍሪካዊ በሆነ ውኃ ላይ እንዲህ ዓይነት ውይይት እንዲኖር መፍቀድ አልነበረበትም፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹እኛ እየበላን ሌላው ሰው ይራብ ማለት ተገቢ አስተያየት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከጥቂት ቀናት በፊት በግብፅ በተካሄደው የዓረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ሳሚ ሻኩሪ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ አስገዳጅ የሕግ ስምምነት ሳትፈጽም የውኃ ሙሌት እንዳታካሂድ የዓረብ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለ ምንም ውል የምታደርገው እንቅስቃሴ በግብፅ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ፣ ሁሉም የዓረብ አገሮች ለዓረብ ሕዝቦች ጥቅም ሲሉ በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዓረብ አገሮች የጋራ የሆነ ትብብር በማድረግ በአገሮቹ ላይ የሚደርሱ የደኅንነት ሥጋቶች ላይ የጋራ መልስ መስጠት አለባቸው ማለታቸውን፣ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡

  የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ንግግር አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት መለስ (አምባሳደር)፣ ‹‹ሳሚ ሽኩሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ሐሳብ ሲሰጡ እንዳልነበረ፣ በዚህም የተነሳ በእኛ በኩል የነበረው ዕሳቤ ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ አቋማቸው መሬት ላይ ካለው ሀቅና እውነት ጋር ታርቋል የሚል ዕምነት ነበረ፤›› ብለዋል፡፡

  ይሁን አንጂ ከህዳሴው ግድብ ጋር የተገናኘ እንዲህ ዓይነት መግለጫ ለመስጠት የሚያስገድድ፣ ደረት የሚያስደቃና ፀጉር የሚያስነጭ ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር እንደሌለ ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን ግንባታ በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው፣ ጉዳዩ አፍሪካዊ በመሆኑ አፍሪካዊ መፍትሔ ይፈልጋል የሚል የቆየ አቋም እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ 65 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ብርሃን የለውም፣ ጨለማ ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ ብርሃን ሲኖር ከትምህርትና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ይገናኛል፡፡ ስለዚህ ይህ አቋም እኔ እየበላሁ እናንተ በጠኔ እለቁ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፣ ብቸኛው መንገድ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን ዓለም አቀፍ ጉዳይ ለማድረግ መሞከር ብዙም የማያዋጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በመጪው ረቡዕና ሐሙስ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስትሩ ከኒጀር ቀጥሎ በሚያደርጉት ጉብኝት በአዲስ አበባ የፌደራል መንግሥት ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር በፕሪቶሪያ ያደረገውን ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት ሲያደርጉ፣ እንዲሁም ከሰብዓዊ የዕርዳታ ድርጅቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

መለስ (አምሳደር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...