Sunday, March 3, 2024

ታሪክን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ግጭት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር እንደ ዓምና ካቻምናው ሁሉ የታሪክ ሽኩቻ የፖለቲካውን መድረክ ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ ፒያሳ በሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ከተፈጠረው፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን ከተረፈው የፀጥታ ኃይሎችና የዓድዋ በዓል አክባሪዎች ግርግር ባለፈ ታሪክን ተንተርሶ ይደረግ የነበረው የቃላት ጦርነት በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወትሮም ትልቅ ቦታ የያዘው በታሪክ ላይ የሚደረገው አተካሮ ሙቀቱና ግለቱ ጨምሮ መቀጠሉን እንጂ አለመብረዱን፣ የዘንድሮ ዓድዋ ድል አከባበር አረጋግጦ እንዳለፈ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

የጋራ ታሪክ ለአገረ መንግሥት ምሥረታና አብሮ መዝለቅ ዋስትና ቢሆን ኖሮ፣ ህንድና ፓኪስታን ባልተከፋፈሉ ነበር ይላሉ የህንድን ታሪክ የሚያወሱ ጸሐፍት፡፡ ማህተመ ጋንዲና መሀመድ ዓሊ ጂና ሁለቱም ከጉጃራት ግዛት የወጡ ጉጃራቲ ተናጋሪዎች ነበሩ፡፡ ወዲህ ደግሞ ሁለቱም እንግሊዝ ለንደን ሄደው ሕግ ያጠኑ ምሁራን ነበሩ፡፡ ህንድ ነፃነቷን ልትቀዳጅ በዋዜማው እ.ኤ.አ. በ1944 ተገናኙ፡፡ ለሦስት ሳምንታት እልህ አስጨራሽ ክርክርና ምክክር አደረጉ፡፡

የሙስሊም ሊግ ፓርቲ መሪ ዓሊ ጂና በነፃይቱ ህንድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን እንደሚሰጠው ቃል ተገባለት፡፡ የአገሪቱን ሩብ ያህል ሕዝብ የሚሸፍኑት የህንድ ሙስሊሞች ነፃነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ የራሳችንን አገር እንመሥርት ይል ነበር ይህ ፓርቲ፡፡ ሂንዱዎች በበዙበት አገር ብንኖር እንዋጣለን የሚል ነበር የእነ ዓሊ ጂና ሥጋት፡፡ ማህተመ ጋንዲ ይህ ሁሉ እንደማይሆን ሊያግባባው ሞከረ፡፡ ነፃይቱ ህንድ ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባት አገር መሆኗን ቃል ገባለት፡፡  

በህንድ ጥላ ሥር እንኑር፣ አይሆንም የራሳችን አገር ይኑረን የሚለው ክርክር ሁለቱን ወገኖች ማግባባት ባለመቻሉ ከባድ ቀውስ አስከተለ፡፡ በካልካታ ግዛት የደረሰው የሙስሊሞችና የሂንዱዎች ግጭት የአምስት ሺሕ ሰዎች ሕይወት ነጠቀ፣ ከ20 ሺሕ በላይ የሚሆኑትን ተፈናቃይ አደረገ፡፡ ግጭቱ በመላው ህንድም የበቀል ጥቃትና ተከታታይ ግጭት አስከተለ፡፡ 

በሮሀላል ኔሩ የሚመራው ኮንግረስ ፓርቲና የእነ ዓሊ ጂና ሙስሊም ሊግ በመጨረሻ ህንድን መቃረጥ ላይ ተስማሙ፡፡ የነፁት አገር የተባለችው ሙስሊሞች ብቻቸውን የሚኖሩባት ፓኪስታን ተመሠረተች፡፡ ዓለም አይቶት የማያውቀው የሕዝቦች መፈናቀልና ስደት ከህንድ ወደ ፓኪስታን ተከሰተ፡፡ ከህንድ ወደ ፓኪስታን ሙስሊሞች ግልብጥ ብለው መፍለስ ሲጀምሩ፣ በፓኪስታን ይኖሩ የነበሩ ሂንዱዎች ደግሞ ወደ ህንድ በስፋት መመለስ ጀመሩ፡፡ በሁለቱም አቅጣጫ ወደ አሥር ሚሊዮን ሕዝቦች ተሰደዋል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ስደት ደግሞ መንገድ ላይ በታጣቂዎች፣ በሽፍቶችና በበሽታ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች አልቀዋል፡፡

ህንድና ፓኪስታን ይህን የታሪክ እጥፋት ለማለፍ የተገደዱት የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ ልሂቃን በጋራ የሚያኖር ታሪክም ሆነ የጋራ ማንነት፣ ባህልና እሴት የለንም በሚል የፖለቲካ ሥጋት በመካከላቸው በመፈጠሩ ነው፡፡ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው አዲስ አገሮች ሠሩ፡፡ ነገር ግን በጉርብትና በሰላም መኖር አቃታቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1947 ሁለቱ አገሮች ነፃ መሆናቸውን እንዳወጁ የካሽሚር ጦርነት ፈነዳ፡፡ እነሆ እስከ ዛሬም በካሽሚር ጉዳይ ህንድና ፓኪስታን ሲገዳደሉ ይኖራሉ፡፡ ሁለቱ አገሮች ነፃነታቸውን አውጀው በራሳቸው መንገድ መንጎድ ቢቀጥሉም፣ በሂንዱና በሙስሊሞች መካከል ያለው ተቃርኖና ግጭት ግን ዛሬም ህንድን የሚንጥ ችግር እንደሆነ ነው ያለው፡፡

ህንድና ፓኪስታን አንድ መሆን አልበጀንም ቢሉም ተለያይተውም ግን ሰላም አላገኙም ይላሉ የታሪክ ጸሐፍት፡፡ ረዥም የአገረ መንግሥት ወይም ጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪክ ያለው ታላቁ የህንድ ግዛት አንድ ሆኖም ተከፋፍሎም በሰላም መኖር ያቃተው ደግሞ፣ ታሪክን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ ቁርቁዝ የተነሳ መሆኑን ጸሐፍት ለዓለም በምሳሌነት ያስቀምጡታል፡፡ ታላቁ ጥያቄ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከዚህ መሰሉ የታሪክ ክስተት ምን ይማራሉ የሚለው ይመስላል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከርዕዮተ ዓለም፣ ከፖሊሲም ሆነ ከፕሮግራም በላይ የታሪክ ጉዳይ መግዘፉ የተለመደ ሆኗል፡፡ የአገርን ዕጣ ፈንታ ይቀይራል ተብሎ ከሚረቀቅና ከሚተገበር ግዙፍ የልማት ዕቅድ ይልቅ ያለፈ ዘመን ትውስታ ሰፊ የፖለቲካ ክርክር ሊፈጥር ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የታሪክ ሁነት፣ የታሪክ አተረጓጎም፣ የታሪክ ባለቤትነትም ሆነ የታሪክ ስነዳና አተራረክ በሙሉ የፖለቲካ ቁርሾ ምንጭ ሲሆኑ መታየቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በታሪክ ገጠመኞች፣ በታሪክ ሰዎች፣ በታሪክ ጀግኖችና ባለፉ ትውስታዎች በፖለቲካው ገበያ እምብዛም ውስጥ መስማማት የለም፡፡ ይህ ታሪክን አንዱና ዋና ማጠንጠኛ ያደረገ የፖለቲካ ባህል ደግሞ መነሻው ብዙ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ ታሪክ ፖለቲካ ሊሠራበት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካው በሸፍጥ የተሞላ እስከሆነ ታሪክን ለሸፍጡ ሊጠቀም ይችላል ይላሉ፡፡ ትክክለኛ ፖለቲካ ከሆነም ደግሞ የተጣመመውን ታሪክ በማቃናት የፖለቲካ ሥራ ሊሠራበት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

‹‹የእኔ ያልሆነውን ታሪክ ያንተ ነበር ወይም የአንተ ነው ሲሉኝ እኔ ይከፋኛል፡፡ አንድ ጊዜ ተደርጓል ሆኗል ብሎ የታሪክ አጋጣሚን በተጣመመና በተጋነነ ሁኔታ ማቅረብ አግባብ አይሆንም፡፡ ለዚህ ነው ታሪክን መልሶ የመከለስ ጉዳይ በፖለቲካው ውስጥ ጥያቄ ሆኖ የሚፈጠረው፡፡ ለምሳሌ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን  ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ ድል በኋላ ሁሉም በእኩል ደረጃ የድሉን ጣዕም ማጣጣም አልቻሉም፡፡ ድሉን የቀሙና የድሉ ባለቤት ተብለው በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ የሆኑ አሉ፡፡ ሌሎች ግን ከድሉ ምንም ያልተጠቀሙና ተረስተው የቀሩ አሉ፡፡ ዓድዋ የእኔ አይደለም ወይም ምንም አልተጠቀምኩም ብለው ሲናገሩ ግን ምን ችግር ገጠማቸው ተብሎ ሲጠየቅ ሳይሆን፣ ወደ ማንቋሸሽና ወደ ጥላቻ ሲገባ ነው የሚታየው፤›› በማለት ታሪክ በምን መንገድ የፖለቲካ ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኀን ግን፣ ታሪክን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ግጭት በኢትዮጵያ መነሻው ሌላ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹የአገር ምሥረታ ሒደትን እንደ ዘላቂ የቅራኔ ምንጭ በመቁጠር ‘የጨቋኝ ተጨቋኝ’ ትርክትን የሚያቀነቅኑ የታሪክ ምርኮኞች ታሪክን ትምህርት ቤት ከማድረግ ይልቅ፣ ፍርድ ቤት በማድረጋቸው ነው ታሪክ የፖለቲካ ቅራኔና ግጭት ምንጭ የሆነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ በእሳቸው እምነት እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓላት አወዛጋቢ የሆኑት፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግም ሆነ በኦሕዴድ/ብልፅግና ዘመን አፄ ምኒልክን የተቃርኖ ማዕከል የማድረግ ፖለቲካ ጎልቶ በመታየቱ ነው፡፡

‹‹የአንድ ዘውግ ታሪክ ተነጥሎ ሲጻፍ፣ ታሪኩ ከፖለቲካና ከባህል ጥቅም ጋር ተያይዞ እንዲቀርብ በመደረጉ የታሪክ አጻጻፉ በአገር ደረጃ ማኅበራዊ ማንነትና አንድነትን ከመገንባት ይልቅ ልዩነትን፣ ብሎም የተበዳይነትንና የተጠቂነትን ስሜት የሚያሸክም አቀራረብ ይታይበታል፡፡ የታሪክ ቁጭት ፈጠራው በስሜት ለሚናጠው የዘውግ ፖለቲካ ግብዓት በመሆን፣ ለልሂቃኑ የሥልጣን መወጣጫ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሆኖም አካሄዱ ለብዙኃኑ ማኅበረሰብ አብሮነት ጠንቅ በመሆኑ አገራዊ ኪሳራው አመዝኗል›› በማለት ነው ታሪክ የልዩነት ፖለቲካ ማትረፊያ መደረጉን አቶ ሙሉዓለም የሚተቹት፡፡    

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ሹመት ሺሻይ (ኤመራተስ ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ታሪክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መፋለሚያ ወደ መሆን የገባው በቅኝ ገዥዎችና በውጭ የታሪክ ጸሐፍት ተፅዕኖ መሆኑን ነው የሚያሰምሩበት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረርና ለመቀራመት ያሰፈሰፉ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች የኢትዮጵያን ጥንታዊ አገረ መንግሥትነት የሚክድ ታሪክ ሲጽፉ ነበር፡፡ ወራሪው ጣሊያንን ጨምሮ በርካቶች የኢትዮጵያን አገረ መንግሥትነት ሊቀበሉት አልፈለጉም፡፡ ይህን የተዋሱት አብዮተኞችና ፖለቲከኞች በተለይ የብሔር ነፃ አውጪ ቡድኖች ያን የተውሶ ታሪክ ይዘው ነው እስከ ዛሬ የቀሩት፤›› በማለት ምንጩን ይናገራሉ፡፡

ቀደም ሲል የተመሠረተውን አገር ታሪክ አለመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ የአገረ መንግሥቱን መሠረት ማናጋትና ማፍረስ የራስን አገር ለመገንባት ያግዛል በሚል ዕሳቤ ነው የተዛባ የታሪክ ትርክትን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የተጀመረው በማለትም ሹመት (ፕሮፌሰር) ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የውዝግብ ምንጭ የሆኑ የታሪክ አጀንዳዎችና አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የ150 ዓመት ዕድሜ ያላት ትናንት የተፈጠረች አገር ናት የሚለውን የታሪክ ድምዳሜ ባለፉት 30 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የፖለቲካ ኃይል ወደ ሕዝብ ለማስረፅ ብዙ ሲደክም ታይቷል፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የ3,000 ዓመታትና ከዚያም በላይ የሆነ ጥንታዊ የታሪክ መሠረት ያላት አገር ናት የሚሉ ኃይሎችም በራሳቸው መንገድ ይህን የታሪክ ብይን ለማስቀጠል ሲተጉ ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት አገረ መንግሥት ሆና ቆማ የነበረች ቢሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ ተነጣጥላ ቆይታ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍል ዘመን መሸጋገሪያ ላይ ዳግም የተዋሀደች አገር እንጂ፣ የጋራ ታሪክ ያልነበራት አገር አለመሆኗን የሚከራከሩ አሉ፡፡

ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ጥንታዊ ታሪክ ባለቤት ናት የሚለውን ትርክት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከቱ ሲኖሩ፣ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ይህን በሚመለከት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ ነው የሚለውን ለመመለስ፣ ኢትዮጵያ የተመሠረተችበትን ጊዜ ወደኋላ ተመልሶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረችም፡፡ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አለች፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ባለቤቶች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ባለቤቶች አልነበሩም፡፡ ደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍልም ኢትዮጵያ ተብሎ ነው የዛሬዋ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው፡፡ እነ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና ተክለ ጊዮርጊስ ደቡባዊውን ኢትዮጵያ ብዙም አያውቁትም፡፡ አንድ ለማድረግ ቢፈልጉም የሰሜኑን ኢትዮጵያ እንጂ የደቡባዊውን ኢትዮጵያ ክፍል አይደለም፡፡

‹‹የጥንታዊት ኢትዮጵያን ታሪክን ለሁሉም ማላበስ ትክክል አይመጣም፡፡ ለምሳሌ ዛሬ የአክሱም ሐውልት ወይም የላሊበላ ቅርስ የኢትዮጵያ ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ለደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የአንተ ነው ሲባል ትንሽ ይጎረብጣል፡፡ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍልም የታሪክ ሀብት አለ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ባለቤት እንዲሆን ብዙ መሥራት ይፈልጋል፡፡ የታሪክ ሀብቱን ማጣጣም ብቻ ሳይሆን፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የልጆቻችን ልትሆን ትችላለች የሚል ምኞት ሊኖራቸው ይገባል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የአቶ ጥሩነህን ሐሳብ የሚቃረኑት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ግን፣ ‹‹ባሳለፍናቸው ሦስት አሠርት ዓመታት ጉዟችን የታሪክ ጉዳይ እጅግ አወዛጋቢ ሊሆን የቻለው፣ አገዛዙ ለኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ በጎ ዕይታ የሌለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክና ትውልድ በተቃርኖ አጀንዳ እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ የአገረ መንግሥቱን ቅቡልነት ፈተና ውስጥ ጥሎታል፡፡ ዛሬ በልሂቃን ደረጃ ኢትዮጵያ የምትወከልባቸው ምልክቶች እንደ ሰንደቅ ዓላማ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ የታሪክ አረዳዶች፣ ባህል፣ ልማዶችና የመሳሰሉት ላይ እንኳ ሆን ተብሎ የወል ስምምነቶች እንዳይፈጠሩ ተደርጓል፡፡ ታሪክና ትውልድ ለዘውግ ፖለቲካ ማቀጣጣያ በዋለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ህልውና ቀጣይነት ዋስትና አጥቷል፡፡ በታሪክ ፖለቲካ የተነሳ መጠፋፋትን ያረገዘ ብሔራዊ አደጋ ከፊት ለፊታችን  ተደቅኗል፤›› ሲሉ ነው ታሪክን ማጠንጠኛው ያደረገ ፖለቲካ አገሪቱን ወዴት እየወሰዳት እንደሆነ ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል ይህንኑ ሥጋት የሚጋሩት ‹‹የጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማነወር የተጀመረው ለፖለቲካ ዓላማ ነው›› የሚሉት ሹመት (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ‹‹ነባሩን አፍርሶ ድጋሚ ሌላ ታሪክ ለመሥራት መነሳት ሌላ ዙር እልቂት መጋበዝ›› መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹የጋራ ታሪክ እንዳንፈጥር ያደረጉን ወገኖች የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡ ቅኝ ገዥዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያን በግጭትና በብጥብጥ አዙሪት ለመክተት ብዙ አጀንዳ አቀብለዋል፡፡ ከጎጥ፣ ከዋሻና ከጫካ ኑሮ ወጥተው በአንድ ተሰባስበው ራሳቸውን ከውጭ ጥቃት ያልተከላከሉ አገሮች የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው በሌላ አገር ሆኖ የማያውቅ ትልቅ ችግር አገሪቱን ላለፉት 30 ዓመታት የሚገዛው አገሪቱ እንድትፈርስ የሚፈልግ ኃይል መሆኑ ነው፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው የሚል ኃይል ነው አገር የመራው፡፡ ስለዚህ አገሪቱን የሚያፈርሱ ታሪኮች ሲፈበረኩም ሆነ ዘመቻዎች ሲካሄዱ ለማስቆምና ለመዳኘት አይፈልግም፡፡ በዚህ የተነሳ በኢትዮጵያ ታሪክን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ቁርሾ ጎልቶ ይታያል፤›› በማለት ነው የታሪክ ምሁሩ የሚናገሩት፡፡  

በታይም መጽሔት “India’s Divider in Chief” በሚል ርዕስ ተነባቢ ጽሑፍ በአንድ ወቅት ያስነበበው አቲሽ ታዚር ራሱ በህንድ እየተዘዋወረ የተረከው “In Search of India’s Soul” በተባለው የብሩኖ ሩሶ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ፣ የታሪክ ፖለቲካ ህንድን ወደ አስከፊ የፖለቲካ ውዝግብ እየከተታት መሆኑን ያስመለክታል፡፡ ሂንዱትቫ የሚል ወግ አጥባቂ የሂንዱ ብሔረተኝነት ፖለቲካን የሚያቀነቅነው የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ቢጄፒ ፓርቲ፣ መንግሥት ህንድን በተቃርኖ የተሞላች አድርጓታል ይላል፡፡

አክራሪ ሂንዱ እምነትን ዋና ማጠንጠኛው ያደረገው መንግሥት ህንድ ሙስሊሞች በመሠረቱት የሙንጋል ሥርወ መንግሥት ከ16ኛው ክፍል ዘመን ጀምሮ በቅኝ ተገዝታ ኖራለች የሚል ትርክት ያቀነቅናል፡፡ መንግሥት ህንድን ከሙንጋል ሥርዓትና ከቅኝ ገዥዎች ተፅዕኖ ማላቀቅ አለብኝ በማለት አዲስ ታሪክ መጻፍ መጀመሩንም ይናገራል፡፡ በህንድ ዛሬ 200 ሚሊዮን የሆኑ ሙስሊሞች፣ 28 ሚሊዮን ክርስቲያኖችና ሌሎች የሃይማኖት ማኅበረሰቦች መጤ ሰፋሪዎችና መብታቸው የማይከበር አናሳዎች ተደርገው መቆጠር መጀመራቸውን በመጥቀስ ሥርዓቱ ከሲክ፣ በቡዲዝምና ከሂንዱዝም ውጪ ያሉ የሃይማኖት ተከታዮች ከህንድ መጥፋት አለባቸው የሚል ፖለቲካዊ ስሜት ማንፀባረቅ መጀመሩን ዶክመንተሪው ይተርካል፡፡

‹‹ሳፍሮናይዜሽን›› በሚል ፖሊሲ የሙስሊሞቹ ሙንጋሎች ታሪክ ተዘሎ የሂንዱዎች ታሪክ ብቻ በትምህርት ፖሊሲው ትውልዱ እንዲማር ይደረጋል፡፡ የሙንጋል ነገሥታት ጥንታዊ የሂንዱ ቤተ መቅደሶችን አፍርሰው መስጊዶችን መገንባታቸው፣ ሲኮችንና ሂንዱዎችን መጨፍጨፋቸው በስፋት ይነገራል፡፡ እንደ ኦራንግዜብ ያሉ ነገሥታት የገነቧቸውን መስጊዶች አፍርሶ በቦታው የሂንዱ ቤተ መቅደሶችን መትከል፣ በህንድ ታላቅ የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ የታሪክ ፖለቲካ ሆኗል፡፡

በንጉሥ ኦራንግዜብ ስም የተሰየመ ጎዳናን ስም በመቀየር በህንድ የኑክሌር ፕሮግራም አባት በኤፒጄ አብዱል ከላም (ዶ/ር) ስም ይሰይማሉ፡፡ ሁለቱም ሰዎች ሙስሊም ቢሆኑም ጥሩና መጥፎ ሙስሊምን የሚበይኑት ግን ፖለቲከኞቹ ሆነዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለህንድ በዓለም መታወቂያዋ የሆነውን ታላቁን የታጅ ማሀል የገነባው ሙስሊሙ የሙንጋል ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ሻህ ጃሀን መሆኑን ረስተውታል በማለት የሚተርከው ዶክመንተሪው፣ የህንድን የታሪክ ፖለቲካ ተቃርኖ በሰፊው ዳሶታል፡፡ 

ኢትዮጵያ በሰሜን ያሉ ደገኞችና በደቡብ ያሉ ሕዝቦች ሲዋጉና ሲፋተጉ ኖረው የተፈጠረች አገር ናት የሚል የታሪክ ትርክት ሲቀርብ ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያ አለፍ ሲልም የአቢሲኒያ ኢምፓየር ውጤት ናት የሚል ትርክት ይቀርባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ የኩሽ ሕዝቦች አገር ናት የሚል የነገድ ትርክትን የሚያራግቡ ኃይሎች እየበረከቱ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ በእስልምናና በክርስቲያን ሃይማኖቶች መካከል የተደረገ የረዥም ጊዜ ግጭትና ፉክክር በወለደው የሕዝቦች ስብጥር የተፈጠረች አገር ናት ብለው የሚደመድሙ አሉ፡፡ ላጲሶ ጌታሁን ዴሌቦ (ፕሮፌሰር) ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን የመነሻና የማንነት ግንዛቤ›› በሚል ርዕስ በ2010 ዓ.ም. ያቀረቡት መጽሐፍ ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች መፋተግ ውጤት መሆኗን ለማሳየት ይሞክራል፡፡ የታሪክ ምሁሩ በኢትዮጵያ ሃይማኖቶች አንዱ ሌላውን በፈቃድ ተቀብሎ ጎን ለጎን የመኖራቸውን አስደናቂ ታሪክ ሳይሆን፣ በመካከላቸው ያለውን ቁርሾ በሰፊው ማንሳታቸው የሚያስገርም መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡    

ከንግሥተ ሳባና ከሰለሞን ግንኙነት ጀመረ የሚባለውን የኢትዮጵያ ምሥረታ ትርክት ማረጋገጫ የሌለውና አፈ ታሪክ ብሎ የሚያጣጥሉ እየተሰሙ ናቸው፡፡ ይህ ጥንታዊ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ትርክት ብቻ ሳይሆን፣ በየዘመኑ ስለተከሰቱ ዓበይት የታሪክ አጋጣሚዎችም በኢትዮጵያ መግባባት የሚባል ነገር ብዙም የለም፡፡

የዮዲት ጉዲት የጦርነት ታሪክን በተመለከተ ያለው አተያይ በየጊዜው እየተቀያየረና የውዝግብ መነሻ እየሆነ ነው፡፡ የግራኝ አህመድ ጦርነትን በተመለከተ የሚቀርበው የታሪክ መረጃም በየጊዜው ሲቀያየርና የውዝግብ መነሻ ሲሆን ይታያል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ መነሻና ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የመስፋፋት ታሪክም እንዲሁ የታሪክ ፖለቲካ ውዝግብ ምንጭ ከሆኑ አጀንዳዎች አንዱ ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያደረጉት ፍልሰት፣ መሰባሰብና መሠራጨት መነታረኪያ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን ነው አልያም ከሰሜን ወደ ምዕራብ ነው የሚል የሚራራቅ መላምት የሚሰጥበት የታሪክ መወዛገቢያ ነው፡፡ 

ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተፈጠረችበት የታሪክ አጋጣሚ ደግሞ ከሁሉም በተለየ ሁኔታ የፖለቲካ መወዛገቢያ ሲሆን ይታያል፡፡ በጦርነት፣ በግጭትና በኃይል ኢትዮጵያ ወደ አንድነት የመጣች አገር ናት በሚለው ላይ የጋራ መግባባት ያለ ቢመስልም፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አመሠራረትን በተመለከተ ያለው ብይን ግን ፍፁም የተቃረነ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አንዱ ቅኝ ገዥ ሌላው ቅኝ ተገዥ ሆነው የፈጠሯት አገር ናት የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መመሥረት ከሁሉም ሕዝቦች የወጡ መሪዎችና የጦር አበጋዞች መሳተፋቸውንና የራሳቸውን አሻራ ማሳረፋቸውን የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡

የጋራ ታሪክና የጋራ ጀግና የለንም የሚባለው የሚመነጨው እርካታ በማጣትና ተስፋ ቢስ በመሆን እንደሆነ የሚናገሩት ፖለቲከኛው አቶ ጥሩነህ፣ ‹‹አንዳንዴ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ምን አገኘሁ በሚል ተስፋ ቢስነትና እርካታ ማጣት ይፈጠራል፡፡ በወቅቱ ባለው ሁኔታ ተቆጥተውና ተስፋ ቆርጠው ሰዎች የጋራ ታሪክ ወይም የጋራ ጀግና የለንም ቢሉ ብዙም አይፈረድባቸውም፤›› ይላሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አንድነት ወይም የኢትዮጵያዊያን አብሮነት የሚባለው ነገር በኃይል የተገነባ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ላለፉት መቶ ዓመታት አሁን ያለውን ሁኔታ ይዘው አብረው ኖረዋል፡፡ ይህን የኢትዮጵያ መልክ ማስቀጠል ይቻላል ወይ ከተባለ መልሴ አዎን ይቻላል ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ የሚሆኑበት አዲስ ሶሻል ኮንትራክት በመፍጠር ማስቀጠል ይቻላል፡፡ አንዱ የሌላውን ቁስል መውጋት አቁሞ መተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ የምናደንቀው ታሪክ ወይ የታሪክ ሰው በሌላው ላይ ምን ያስከትላል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ብሔረ መንግሥት ሳይሆን አገረ መንግሥቱ ራሱ በኢትዮጵያ በትክክል ተገንብቶ አላለቀም፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን የሚያጠቃልሉት፡፡

የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው የታሪክ አረዳድ ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ‹‹የታሪክ ሊቃውንቱ እንደሚሉትም ታሪክ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ ነው፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ግን ታሪክ የትውልዱ የልዩነት ማስመሪያ ቀለም ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለዘውግ ፖለቲካ ማፋፋሚያ ዓይነተኛ ማገዶ ነው፡፡ ታሪክ ለየዘውጉ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ተለውሶ እየቀረበ እንጂ የአገር ውህደትና አንድነት መፍጠሪያ ሲሆን አይታይም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ከገባችበት አዙሪት እንድትወጣ ከተፈለገ ፖለቲከኞቿ ከታሪክ ፖለቲካ መውጣት አለባቸው። ለአገራዊ አንድነት ትርክት መሠረት በሚሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ላይ መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ የታሪክ ምርኮኞች ኢትዮጵያን ወደ ነበር እንዳይቀይሯት ሥጋት አለኝ፤›› ሲሉ በኢትዮጵያ አፈጣጠር ላይ የሚቀርበው የልዩነት ትርክት የደቀነውን አደጋ ያስረዳሉ፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ የጋራ ነገን ካለማለም መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ይጠቅሳሉ፡፡

የታሪክ ምሁሩ ሺመት (ፕሮፌሰር) ግን የኢትዮጵያን አመሠራረት ሒደት ልክ እንደ ታላቁ ዓባይ ወንዝ አፈጣጠር ነው የሚመስሉት፡፡ ‹‹ዓባይ ሰከላ ላይ እረኞች የሚዘሉት ምንጭ ነው፡፡ ሰከላን ተሻግሮ ብዙ አካባቢዎችን እያቆራረጠ ሲሄድ ግን በየቦታው በርካታ ጅረቶችና ምንጮች እየተቀላቀሉት ታላቁን የዓባይ ወንዝ በሒደት ይፈጥራል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

‹‹የኢትዮጵያም ታሪክ እንደዚያው ነው፡፡ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ እየሰፋ ሲሄድ ብዙ ሕዝቦችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችንና ግዛቶችን እያቀፈ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ የደረሰ የታሪክ ፍሰት ያለው ነው፡፡ ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ ኅብረ ብሔራዊ የሆነ መንግሥት  ነው፡፡ በድንጋይ ላይ የተጻፉ ማስረጃዎች ሞልተዋል፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገር  አልነበረም፣ ኅብረ ብሔራዊ ነበር፤›› በማለትም ከዚያ ተነስቶ የዛሬይቱ ቅይጥ ማንነት ያላት ታላቅ አገር ኢትዮጵያ መፈጠሯን ያብራራሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -