Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ የሆነው የሆርቲካልቸር ዘርፍ ምን ድጋፍ ይሻል?

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከሌሎች የወጪ ንግድ ዘርፎች በተለየ ከዕቅድ በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት አገሪቱን ይጠቅማል ተብለው ከተለዩ ዘርፎች ተጠቃሹ ነው፡፡

አገሪቱ ሥርዓት ባለው መንገድ ዘርፉ ያፈራቸውን ምርቶች መላክ ከጀመረች ከሁለት አሠርት ዓመታት ያልዘዘለ ጊዜ ቢቆጠርም፣ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት ዘርፍ መሆን ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ምናልባትም ለሌሎች ዘርፎች የተሰጠውን ያህል ክትትልና ድጋፍ ቢያገኝ በዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የዕድገት ምጣኔው ደግሞ ከቡና የበለጠ እንደሚሆን ይነገራል፡፡

ለማሳያ ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና ተጓዳኝ እክሎቹ የተለያዩ ምርቶች ገበያን ክፉኛ በጎዳበት ወቅት፣ ከኢትዮጵያ አንፃር በተለይ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ወረርሽኙ እንደታሰበው ተፅዕኖ ሳያደርስበት ከዕቅድ በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለዘርፉም ለአገሪቱ ኢኮኖሚም ትርጉም ያለው ድጋፍ አስገኝቷል።

ከሰሞኑ በተካሄደው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር የንግድ ትርዒት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነጋ መኳንንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል የማይባል ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ አንፃር በተለይ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ወረርሽኙ እንደታሰበው ተፅዕኖ ሳያሳድርበት ከዕቅድ በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል፡፡ ይህም የሆነው መንግሥት፣ አምራቾችና የላኪዎች ማኅበር እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሩን ወደ ዕድል በመቀየራቸው ነው፡፡

አቶ ነጋ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረትና ይህንንም ወደ ውጭ ለመላክ የሚሆን ምቹ ዕድል አላት፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አገሪቱ በዝቅተኛ ወጪ ቢዝነስ መሥራት የሚቻልባት በመሆኗ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የአግሮሎጂስቲክስ በተለይም የአየር በረራ በመኖሩ፣ እንዲሁም ለባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች የሚሰጥ ሥርዓት መንግሥት መዘርጋቱ ተጠቃሾች ናቸው።

የሆርቲካልቸር ዘርፉ በዚህ ወቅት ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ዘርፎች በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ትርጉም ባለው መልኩ ከዘርፉ ለመጠቀም እየተሠራና አገሪቱ ያላትን አቅም እየተጠቀመች እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

በቅርቡ የግብርና ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በተደራጀ ሁኔታ የሆርቲካልቸር ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ከጀመረች 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ዘርፎች መካከል ሆርቲካልቸር ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዓብነትም ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከሆርቲካልቸር ምርቶች ኤክስፖርት ከ414 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

ከዚህ ዘርፍ ሊገኝ ይገባ የነበረው የውጭ ምንዛሪ አሁን እየተገኘ ካለው በላይ መሆን እንደነበረበት ይጠቀሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አገሪቱ ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚሆን ምቹ ሁኔታና ተስማሚ ተፈጥሮን የታደለች በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ዕድል በአግባቡ ገና እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡ 

በተለይም በዚህ ወቅት የዓለም ገበያ ፍላጎት የሆነውን የፍራፍሬና አትክልት ምርት በሚጠበቅበት ልክ ገቢ እንዲያመጣ ወቅታዊ የምግብ ቴክኖሎጂዎችን ማስረፅና ዘርፉን መደገፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ያስረዳሉ፡፡

በተለይም ከአበባው የበለጠ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከፊቷ መልካም ዕድል እንዳላት የሚገለጽ ሲሆን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የሚገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ከፍ ለማድረግም ሆነ ወደ ውጭ የሚላከውን የአበባ ምርት ለመጨመር ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡

የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች እንደሚገልጹት፣ ዘርፉን የሚደግፉ የሕግ ማዕቀፎች በትክክል የሚተገበሩ ከሆነ ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል መፍጠርን ጨምሮ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከዚህ በላይ ማሳደግና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲበረክት ማድረግ ይቻላል።

በተለይም የዘርፉን ወቅታዊ ችግሮች ማለትም አምራቾች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ አቅርበው ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ መጠቀም እንዳይችሉ የሚከለክለው የብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ ከመሬት ጋር በተያያዘ ያልተመለሱ ጥያቄዎች፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ፈጣን መፍትሔ ሊየበጅላቸው የሚገባቸው እንደሆኑ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅና በአግሮ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን በማቅረብ የሚታወቁት መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስን የግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ ኤክስፖርት አድራጊ አገር ናት፡፡ ቡናን አስቀድሞ በመቀጠል ከሚጠቀሱ ምርቶች የሆርቲካልቸር ውጤቶች ተጠቃሾቹ እንደሆነና ከዚያም ውስጥ አብዛኛው ገቢ የሚገኘው ከአበባ እንደሆነ መንግሥቱ (ፕሮፌሰር) ይገልጻሉ፡፡ 

አገሪቱ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዳላት መገለጫ ከሆኑት ዘርፎች መካከል የአትክልትና ፍራፍሬ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆኑን የሚናገሩት ምሁሩ፣ በተለይም ለፍራፍሬ ምርት የሚሰጠው ትኩረት እጅጉን አናሳ በመሆኑ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መታጣቱን ያስረዳሉ፡፡

ሆርቲካልቸር በትናንሽ አልሚዎች በተበጣጠሰ የእርሻ መሬት እንዲሁም በሰፋፊ ማሳ የሚሠራ (ኮሜርሻላይዜሽን) እንደሆነና በተለይም በተበጣጠሰ መልኩ የሚመረተው ምርት ዝቅተኛ ስለሆነ ወደ ገበያ ይቅረብ ቢባልም ብዙ አቅም የሌለው መሆኑን ምሁሩ ይገልፃሉ፡፡ 

መንግሥቱ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ከግብርና ምርት በተለየ የሆርቲካልቸር ምርቶች ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም የምርት አቅርቦቱ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአገሪቱ ምርቱንም ሆነ ሥርጭቱን፣ ክምችቱን እንዲሁም ኤክስፖርቱን የሚደግፍ ቴክኖሎጂ አለ ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል። ምርቱ ለብልሽት ተጋላጭ እንደመሆኑ መጠን ሳይበላሽ ለማቆየት የሚያስችሉ የጥንቃቄ ቴክኖሎጂዎችን የሚፈልግ ነው ፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ማግኘት የዘርፉ ፈተና መሆኑን አስረድተዋል።

በሆርቲካልቸር ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ሆነ አርሶ አደሩ ከሚያጋጥሟቸው አውራ ችግሮች መካከል የካፒታል እጥረት አንዱ መሆኑን ያስረዱት ተመራማሪው፣ ይህም ለዘርፉ ተፈላጊ ናቸው የሚባሉት ግብዓቶች እንዳያሟሉ እንቅፋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ 

በሌላ በኩል ዘርፉ በምርምሮች በበቂ ሁኔታ የተደገፈ ነው ለማለት አያስደፍርም የሚባል ሲሆን በምርጥ ዘር፣ በአመራረት ዘዴ ላይ እንደሚደረጉት ምርምሮች ለሆርቲካልቸር ምርቶች የተደረጉት ምርምሮች ትኩረት ያላገኙና እምብዛም ያልተተኮረባቸው ተብለው ሊገለጹ የሚችሉ መሆናቸው ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ 

ሆርቲካልቸር በምርትና በድህረ ምርቱ ሒደት ላይ ከፍተኛ ብክነት ያለበት፣ ገበያውም ውስብስብ ችግሮች ያሉት፣ በደላሎች ጣልቃ ገብነት የታጨቀ፣ የገበያ መዋዠቅ ያለበት፣ የገበያ መሠረተ ልማት ችግር ያለበት እንዲሁም ከአምራቹ እስከ ነጋዴውና ኤክስፖርተሩ ድረስ ያለው ትስስር የላላበት እንደሆነ በዘርፉ ላይ ጥናትና ምርምሮች ያደረጉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ 

የመሠረተ ልማት ዓይነቶች የሚባሉትን በተለይም የማከማቻ፣ የትራንስፖርት የአስተሻሸግ (ፓኬጂንግ) ሥራዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሊሆን እንደሚገባ፣ ይህም ውድ የሆነ ቴክኖሎጂ ወጪ ስለሚጠይቅ በዚህ ላይ ለዘርፉ ተዋንያን ብድር የሚያገኙበት አሠራር ቢዘጋጅ ወደ ዘርፉ ለሚገቡትም የሚያበረታታ ይሆናል የሚሉት መንግስቱ (ፕሮፌሰር)፣ ለዘርፉ ተዋንያን የታክስ እፎይታ መስጠትም ማንም ደፍሮ የማይገባበትን ዘርፍ እንደማበረታቻ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አገሪቱ ከሆርቲካልቸር ዘርፉ ለምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች እንደሚገልፁት አትክልትና ፍራፍሬ ሰፋፊ መሬት ይፈልጋል፡፡ ለሆርቲካልቸር መሬት መቅረብ አለበት፡፡

በመሬት አቅርቦት ላይ ትልቅ ማነቆ ነው ያለው፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ኢንቨስትመንት በሚፈለገው ልክ እየገባ አይደለም የሚሉት የዘርፉ ተዋንያን፣ ኢንቨስትመንቱን ለመቀላቀል ፍላጎት ቢኖርም፣ የመሬት አቅርቦቱ ግን እንደሌለ፣ አሁን በማልማት ላይ ያሉት ባለሀብቶች እርሻቸውን ማስፋፋት ቢፈልጉም፣ መሬት አቅርቦቱ ግን ችግር እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡

የአገር ውስጥ አልሚዎችንም አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በማበረታታት ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲመጡ የማድረግ ሥራ በመንግሥት በኩል መሠራት አለበት የሚለውን የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎቹ አፅንኦት ይሰጡበታል፡፡

ብዙዎቹ በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጥያቄያቸው ከውጭ ምንዛሪና ከማስፋፊያ ቦታ ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚናገሩት ግርማ (ዶ/ር)፣ በተለይም የማስፋፊያ ጥያቄን መመለስ ጥቅሙ ለመንግሥት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ 

የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሀቶች ጥሩ ገበያ ያላቸው ሲሆኑ ዋነኛ ጥያቄያቸው የሆነው የማስፋፊያ እርሻ ቦታ ጥያቄ እንደሆነና ይህንን ጉዳይ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ቶሎ መፍታት በቤት ሥራ መልክ የያዙት ጉዳይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

‹‹በኤግዚብሽኑ የአነጋገርኳቸው አልሚዎች በሙሉ ማስፋፊያ ለመሥራት መሬት እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል፡፡ እየሠሩ ላሉት ኩባንያዎች ማስፋፊያ ለሚፈልጉት፣ አዲስ ለሚገቡትም መሬት ማዘጋጀት ይፈልጋል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የመብራትና የትራንስፖርት ችግሮችም እንዳሉና ሊፈቱ እንደሚገባ አክለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በዘርፉ ከተሰማሩ ባላሀብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ያነሱት ጥያቄ ከላይ ከተገለጸው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነና በዚህም መፈታት ያለበት ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ በሌላ በኩል መንግሥት ያዘጋጃቸውና የአሌክትሪክ ኃይል ሳይዳረስባቸው በቀሩ ለአብነትም በአማራ ክልል ባህርዳር ዙሪያ ቁንፅላ የሚባል እርሻ እንዳለና ከዘር ምርት ቦታ ተወስዶ ለአበባ ምርት የተሰጠውን ቦታ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኘ በመሆኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋጋር ባላሀብቱን ማስተናገድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

ግርማ (ዶ/ር) እንደሚስረዱት፣ አትክልትና ፍራፍሬው እንደ አበባው ያላደገ ሲሆን፣ ይህም ሰፊ መሬት የሚፈልግ በመሆኑ ተጨማሪ መሬት አዘጋጅቶ ለአልሚዎች መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በተጠናቀቀው ሳምንት ለሦስት ቀናት ያህል በሚሊንየም አዳራሽ በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ኤግዚቢሽን ከ90 በላይ የአገር ውስጥና የውጪ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እንዲሁም የተለያዩ ግብዓት አምራቾች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በሁነቱ ከኤግዚቢሽን ውጪ የሆርቲካልቸር ዘርፉ ያለውን ዕድልና እያጋጠሙት ያሉ ችግሮች እንዴት ይፈቱ? በሚለው ላይ የዘርፉ ተዋንያንና የሚመለከታቸው ተቋማት በሰፊው መክረውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች