Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቻይና ጥቅም ላይ ባለመዋሉ የመለሰችውን የአዲስ አበባ ግዙፍ የውኃ ፕሮጀክት ብድር በድጋሚ ፈቀደች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውኃ ችግርን ለመቅረፍ የታሰበው ግዙፉ የገርቢ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በቻይና መንግሥት ተፈቅዶ ጥቅም ላይ ሳይውል በመቅረቱ፣ ተመላሽ የተደረገውን ብድር የቻይና መንግሥት ሰሞኑን ድጋሚ መፍቀዱ ተገለጸ።

በየካቲት ወር መገባደጃ ወደ ቻይና የተጓዘው በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ ከቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት በሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ዙሪያ ተመካክሮ የተለያዩ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርሞ መመለሱ ይታወቃል። 

በዚህ ጉብኝት ውጤቶች ዙሪያ ለመንግሥት ሚዲያዎች ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረሰ ስምምነት መሠረት ለገርቢ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ቀደም ሲል ተፈቅዶ፣ ኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ባለማዋሏ ተመላሽ የተደረገው ብድር በድጋሚ መፈቀዱን ተናግረዋል።

የገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን ጨምሮ ለ14 ፕሮጀክቶች ግንባታ በቻይና ኤግዚም ባንክ የተፈቀደው አጠቃላይ ብድር 622 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ገልጸዋል።

የቻይና ኤግዚም ባንክ የፈቀደው ብድር የገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን ጨምሮ ለ14 ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የመቀሌ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ የሐዋሳ የፍጥነት መንገድ፣ የድሬዳዋ ደወሌ (ጂቡቲ ጠረፍ) የባቡር መስመር ግንባታ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከተፈቀደው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ግን ወደ 50 በመቶ የሚጠጋው ለገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል።

ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ ከእንጦጦ ተራራ ጀርባ የሚገኘውን የገርቢ ወንዝ በማልማት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግርን ትርጉም ባለው መልኩ ይቀርፋል ተብሎ ከ15 ዓመት በፊት የታቀደ ነው።

ይህንን ፕሮጀክት ለማስጀመር የሚያስፈልግውን ፋይናንስ ለማፈላለግ ብዙ ጥረት ተደርጎ፣ በስተመጨሻም የቻይና መንግሥት ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውል ብድር በ2009 ዓ.ም. ተፈቅዶ በቻይና ኤግዚም ባንክ በኩል እንዲለቀቅ መወሰኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው ሰነዶች ያስረዳሉ።

ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘው ብድር 242 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ብድሩንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አፅድቆት ነበር።

ከቻይና ተገኝቶ የነበረው ይኼ ብድር የአዲስ አበባ የመጠጥ ውኃ ፍላጎትን 80 በመቶ ያሟላል ለተባለው የገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንደሚውል የብድር ስምምነቱ ያስረዳል፡፡

የገርቢ የውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት በአማካይ በየቀኑ 76,000 ሜትር ኪዩብ ውኃ ማቅረብ እንደሚችልና በከተማዋ ለአምስት ክፍላተ ከተሞች፣ በተለይም በሰሜን አዲስ አበባና ሱሉልታና አካባቢው ለሚገኙ 800 ሺሕ ሰዎች በቂ የውኃ አቅርቦት እንደሚሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ነበር። ተገኝቶ የነበረው ብድርም ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍን በወቅቱ የፀደቀው የብድር ስምምነት መግለጫ ያስረዳል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ መንግሥታዊው የውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን በ72 ሚሊዮን ብር ለመሥራት የተስማማ ሲሆን፣ ግንባታውን ደግሞ የቻይናው ሲጂሲኦሲ በሦስት ቢሊዮን ብር ለማካሄድ ስምምነት ተፈራርሞ ነበር፡፡

ነገር ግን ለ20 ዓመታት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል የተባለውን ይህንን ፕሮጀክት ሙሉ የግንባታ ወጪው መሸፈኛ ብድር ተገኝቶም በወቅቱ መጀመር አልተቻለም። 

ምክንያቱ ደግሞ የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አስፈላጊው ጥናት በሙሉ ከተካሄደ በኋላ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ግንባታ፣ ውኃው ለሚተኛበት፣ የውኃ ማጣሪያ ጣቢያ ለሚገነባበት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ለውኃ ተፋሰስ የሚሆን መሬት ከሰው ንክኪ ነፃ አድርጎ ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው።

በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሰጠው ምክንያትም የክልሉና የአካባቢው ሕዝብ ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት የሚገልጽ ነበር። በዚህም ሳቢያ የክልሉ መንግሥት ለገርቢ ግዙፍ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሳያቀርብ በመቅረቱ ለፕሮጀክቱ የተፈቀደው ብድር መጠቀሚያ ጊዜ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ተጠናቆ ብድሩ ቀሪ ሆኗል።

በጉዳዩ ላይ ለመንግሥት ሚዲያዎች አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥዩም ቶላ፣ ፕሮጀክቱ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በመሬት ካሳ ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት መቋረጡን ገልጸዋል። ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት 1,800 ሔክታር የመሬት ይዞታ ላይ ለነበሩ 1,850 ባለይዞታዎች 750 ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን ጠቁመዋል።

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የቻይና ኤግዚም ባንክ ለመልቀቅ በመወሰኑ፣ የፕሮጀክቱን ግንባታ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ለመጀመር እንደሚችሉ አቶ ሥዩም ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት በቅርቡ የተቋቋመው የሸገር ከተማ ከንቲባ አቶ ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፣ የውኃ ፕሮጀክቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች