Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበልባዊ ዕርቅ አዲስ ችቦ ለማውለብለብ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን?

በልባዊ ዕርቅ አዲስ ችቦ ለማውለብለብ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በእስከ ዛሬ ጥቅል ኑሯችን፣ የተወሰነ ዕሳቤን ሐሳቤ ብለን የምንይዘው ወይም ለሆነ ነገር ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ የምንሰጠው፣ በሐሳብ ፍጭት መድረክ ውስጥ የንፅፅርና የማብላላት ልሂቃዊ ዕገዛ ተደርጎልን የሚበጀን ይኼ ነው በማለት መርጠን አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹ልክ›› እና ‹‹ልክ ያልሆነው›› በሌሎች እየተወሰነልን ምርጫ የለሽ ‹‹ምርጫ›› እየተቀበልን ለረዥም ጊዜ ኖረናል፡፡ አመለካከቶች ትክክለኛ እምነትን የጠበቁ አለዚያም የመናፍቃንና የተጠራጣሪ ተብለው ሲፈረጁ ኖረዋል፡፡

ፀረ አብዮትና አብዮት፣ አድሃሪና ተራማጅ፣ ፀረ ሰላምና ሰላም ወዳድ፣ ወዘተ በሚል ተጣማጅ (ባይነሪ) አስተሳሰብ ውስጥ እየተሽከረከረን መኖር ከጀመርን ይኼው 50 ዓመት ልንደፍን ነው፡፡ ተጣማጅ አስተሳሰብ ሦስተኛ ምርጫ አይሰጥምና ቀንበርን ይመስላል፡፡ አንዱን ጥግ ያልያዘ አቋምና ሠልፍ ቢወድም ባይወድም የሌላው ጥግ ሠልፈኛ ሆኖ ይፈረጃል፡፡ ጥጎቹ የማይቻቻሉ ሆነው የተወጠሩ ናቸው፡፡ አንዱ ጥግ ተወዳሽ/ተሞጋሽ ሲሆን፣ ሌላው ተኮናኝ/ተወጋዥ ነው፡፡ ይህ አፈራረጅ ለለውጥ እንታገላለን በሚሉ ቡድኖች ውስጥ ገብቶ እርስ በርስ እንዳናጨ ሁሉ፣ የመንግሥት ፖለቲካና የተቃዋሚ ፖለቲካ መለያ ሆኖም አጨብጭቦ ማደርን ለአገር ከማሰብ ጋር፣ መቃወምን ደግሞ ለአገር ጠንቅ ከመሆን ጋር ለማዛመድ አስችሏል፡፡ እናም ፍረጃው ራሱ በቁሙ የመወንጀልና የመታሰር ዕድል የት ጋ እንዳለ እየነገረ ሠልፋችንን ‹‹እንድንመርጥ›› ሲያዝ ኖሯል፡፡

አጠቃላዩ የኩነናና የውዳሴ ፍረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በወገኛ ዴሞክራሲ ከተወዳሹ ፓርቲና ከተኮናኞቹ ፓርቲዎች  በድምፅ ‹‹የምንመርጥበት›› ተውኔት ሲመጣ ደግሞ፣ በሥውርም ሆነ ዓይን ባወጣ ሸፍጥ የድምፅ ውጤት ውሉን እንዳይስት የሚደረግበት መንገድ አብሮ መጥቷል፡፡ ሰዎች የሚሰጡትን ድምፅ በተለያየ የአፈና ቅንብር ከመቆጣጠር ባሻገር ተቃዋሚዎችን በፀረ ሰላምነት፣ በፀረ ሕዝብነት/በውጭ ተላላኪነት ማጠልሸት የሕዝብን የፖለቲካ ድጋፍ መግዣ ዋና አሉታዊ መሣሪያ ሆኖ (እነሱን አለመደገፍ የእነሱን ‹‹ኃጢያት›› ያለ መጋራት ማረጋገጫ) ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያ ባሻገር የብሔር ዝምድናና የአካባቢ ልጅነት ሌላው ትልቁ የድጋፍ መግዣ መሣሪያ ሆኖ ሠርቷል፡፡

የዕርዳታ ጥቅም፣ በመንግሥት ታግዞ በሥራ ፈጠራ የመቋቋም ዕድል፣ በግብር ፋታ የመታገዝ ዕድል፣ በመንግሥት ቤት የመቀጠር/ዕድገትና ሹመት የማግኘት ዕድሎች፣ የውጭ ትምህርት ዕድል፣ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ የሥልጠናና የማሠልጠን ዕድል፣ ወዘተ ሁሉ መንግሥታዊ ፖለቲካ ድጋፍን ለመግዣነት ሲገለገልባቸው ኖሯል፡፡ የምርጫ ውድድር መዳረሻ ላይ ሕገወጥ የመሬት ይዞታን ሕጋዊ የሚያደርግ ውሳኔ ማድረግም የድምፅ መግዣ ሆኖ ተሠርቶበታል፡፡ የገንዘብ ጉርሻ ረጨት ማድረግም ሆነ አጓጊ ተስፋ አንጠልጥሎ ጉጉትን መማረክም በድምፅ ግብይይት ውስጥ ሲሠራበት ታይቷል፡፡ መንግሥታዊው ፖለቲካ የሚኮንናቸው ቡድኖችም በፖለቲካ ንግድ ውድድሩ ውስጥ አልቦዘኑም፡፡ በተቃዋሚነት ያለ ብሔርተኝነት በሥልጣን ላይ ካለው ብሔርተኛ ቡድን ይበልጥ ለብሔሩ ‹‹አሳቢ›› መሆኑን ለማሳየት ብዙ በደል የመተረክና ብዙ ጥያቄ የመደርደር ሥራ ሠርቷል፡፡ አገራዊ ዕይታ አለኝ ባይ ቡድኖች ብዙ ድጋፍ ያስገኝልናል፣ ገዥውንም ቡድን ለማስኮነን ይመቻሉ ባሏቸው አቋሞች ነግደዋል፡፡ ‹‹ገዥው ቡድን ማርክሲስት፣ በነፃ ገበያ የማያምን፣ በሥውር ሶሻሊዝም መገንባት የሚፈልግ፣ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት የሚከተል፣ ሊብራል ዴሞክራሲን የማይቀበል… እኛ ግን የሊበራል ዴሞክራሲ መርሐ ግብር ያለን፣ የግል መብትን የሁሉ መብቶች መፍቻ አድርገን የያዝን…›› በሚል ዓይነት ከውስጥም ከውጭም የምዕራባውያንን ድጋፍ ለመግዛት የፖለቲካ ንግድ ሲያጣጡፉ ቆይተዋል፡፡

የመንግሥትንም ሆነ የፖለቲካ ቡድኖችን የፖለቲካ አቋም በገንዘብ ድጋፍ የመቃኘትና የመቆጣጠር ጫና፣ በውጭ ካሉ የኢትዮጵያ ተወላጆች በኩል በተደጋጋሚ ተሰንዝሯል፡፡ ታላላቅ አገሮች በዕርዳታና በብድር ልዋጭ፣ በማዕቀብ ልምጭ ኢትዮጵያን በፍላጎታቸው ውስጥ አዳሪ የማድረግ ተግባራቸው በተደጋጋሚ የተፈተንበት ነው፡፡ ለአገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች የተለያየ ዓይነት ድጋፍ በመስጠት ኢትዮጵያን በልጓም ውስጥ የማቆየት፣ ካልሆነም የመቅጣት ሙከራዎችንም ኖረንባቸዋል፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ገዥነት ጊዜ በዓለም አቀፍ ግንኙነታችንና ዲፕሎማሲያዊ መረባችን የተፈጠረ የአንድ ቡድን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ላይ የተመሠረተ (ለአገርና ለዲፕሎማሲ ሙያ በመታመን ላይ ያልታነፀ) ቋጠሮ፣ በኋላ ከሥልጣን ሸርተት ሲባል ኢትዮጵያን በኃያላን መዳፍና ጡጫ ለማጎሳቆል መሣሪያ ተደርጎ የተሠራበት መሆኑም ለኢትዮጵያ አዲስ ልምድ ነው፡፡

ከዚህ የከፋ (በደም የነገደ) ልምድም አይተናል፡፡ በተለይ 2011 ዓ.ም. ይዞ ነባሩን  የፖለቲካ ንግድ ያኮሰሰ ወፈፌ ንግድ ተከስቷል፡፡ በመንገድ ላይ ከዓይኖቹ ዕንባ እየጨመቀ (ዕንባ እየሸጠ) ምፅዋትን የሚገዛ ችግርተኛ ልናይ እንደምንችል ሁሉ በፖለቲካው ግብግብ ውስጥም በሐሳዊ መረጃ፣ በጥላቻና በበቀል ክትባት የሰዎችን ሕይወት ወኔያቸውን፣ እልሃቸውንና ቁጣቸውን ለጥፋት ጦርነት የሚገዙና የሚማግዱ የግፍ ነጋዴዎችንም አየን፡፡ በዚህ በመጨረሻው ንግድ የደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ የሁለት ወገን ከመሆኑ ሌላ፣ ነጋዴዎቹ ሕዝብን እየማገዱ ባደረሱት ዕልቂትና ውድመት አንዳች ትርፍ አለማግኘታቸው ነው፡፡ ሕዝብ የማባላትና አገር የመበታተን አጀንዳቸውም የገዛ ጆሮ ግንድ ላይ ተኩሶ የራስን ነፍስ ከማጥፋት የተለየ አልነበረም፡፡ የዚህ ክንውን አሳዛኙና አሸማቃቂው ፈርጅ ደግሞ፣ የሕዝብን ደምና ኑሮ የበላውን ይህንን ተግባር የቀየሱትና ያመላለሱት ሰዎች፣ ‹‹ተራማጅነት/ለሕዝብ መታገል ዓላማዬ›› ሲሉ የነበሩት የ1960ዎች ትውልድ ሙጣጮች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ጉድ፣ ያንን ዘመን የምንጋራ ሁሉ እንደ እኔ የምንሸማቀቅ ይመስለኛል፡፡ ለሕዝብ የተሻለ ሕይወት እናመጣለን ብለው ከአፈና ኃይል ጋር እየተናነቁ የተሰው ባልንጀሮቻችን ከመቃብር ተነስተው ይህንን ጉድ ለማየት ቢችሉ ኖሮም በቁማቸው ወደ ድንጋይነት የሚለወጡ ይመስለኛል፡፡ አውሬያዊ ግፍ መሠራቱ ካሸማቀቀን በላይ ያሸማቀቀን ደግሞ፣ ፀፀትና ሕዝብን ይቅርታ የመጠየቅ ስሜት ሰዎቹን ሲያንሸቀሸቅ አለማየታችን ነው፡፡

በእኔ ዕይታ ከሕዝብ ፊት ለይቅርታ መንበርክክ የቃላት ጉዳይ አይደለም፡፡ የምር መግለጫዎቹ ከቃላት የላቁ ናቸው፡፡ ‹‹ጦርነቱን እኛ አልከፈትንም›› የሚል ቅጥፈት ዛሬም አጥብቆ መድረቅ፣ በኃጢያት ጭቃ ተለውሶ ንፁህ ነኝ ማለት፣ ወጣቱን አንካሳ ባንካሳ፣ እናቶችን ሐዘን ልብስ በሐዘን ልብስ አድርጎና የአሳር ኑሮን አባዝቶ ‹‹ለሕዝብ ታገልን፣ ታግለንም ሰላምን አመጣን›› ብሎ ማለት ከፀፀት ስሜት ጋር አይሄድም፡፡ ርቃነ-ሥጋውን በሕዝብ ፊት እየተቆነነ ‹‹ለማንም የማይታይ ልብስ ለብሻለሁ›› ብሎ እንዳመነው የተረት ንጉሥ መሆን፣ እውነታንና ስህተትን ከመቀበል ጋር የመጣላት ከፍተኛ ደረጃ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን የደገፉ ሰዎችንና በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ውስጥ ተሳትፏቸው ጊዜ ለሕወሓት ያልተገዙ ሰዎችን አስሮ እስከ ዛሬ ማቆየት፣ ከተለያዩ ሥፍራዎች የተጋዙ ሰዎች የት እንደ ደረሱ አለመናገር (በሕይወት ካሉ  አለመልቀቅ)፣ ከአፋርና ከአማራ አካባቢ በሙያተኛ ተነቃቅለው የተወሰዱ የሥራ መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን ለመመለስ ፍላጎት አለማሳየት (እንዲያውም ወሬው እውነት ከሆነ መቀወር)፣ ወደ ፀፀትና ዕርቅ ከመሄድ ጋር ይጋጫል፡፡

አሁን ትግራይ ውስጥ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር መንግሥት ከዚህ ቀደም ሕወሓቶች በከፈቱት ወረራ በተሸንፉ ጊዜ ተቋቁሞ ከነበረውና በሕወሓታዊ ሰርጎ ገብነት ከከሸፈው በባህርይው የተለየ ነው፡፡ ጊዜያዊው መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የሚዋቀር ከሆነ፣ ከሁሉ በፊት የስብሰቡን ወሳኝ ጥንቅር በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ውስጥ የሚያስቡ ሰዎች የተቆጣጠሩ መሆናቸው ግድ ነው፡፡ የድርድሩ አንዱ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድር አለመቅረቡ ነውና፡፡ ጊዜያዊ መንግሥቱ የሥልጣን ሽሚያ መድረክ ከመሆን ይልቅ፣ የትግራይን ሕዝብ የመካስ ተልዕኮን ማዘልም ይፈለግበታል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከአንድ ቡድን ይዞታነት ወጥቶ የተለያዩ አስተሳሰቦችን መስማት መቻል፣ የህሊና ነፃነት ማግኘትና አንደበቱን ፈትቶ የልቡን ለመናገር መብቃት፣ ሥውርና ግልጽ አፈናን ሳይፈሩ ማሰብና መንቀሳቀስ የአንድ ሰሞን ጉዳይ አለመሆን (ከቡድን ታማኝነት የወጣ ሕግና ሥርዓት አስከባሪ ተቋም የመገንባት ሒደት ውስጥ መግባት)፣ የተጎዱ የኑሮ ፈርጆችንና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን መልሶ ወደ ማነፅ ውስጥ መግባት ሁሉ የተልዕኮዎቹ አካላት ናቸው፡፡ የእነዚህን ተልዕኮዎች መቃናት ያለ ሸፍጥ ማገዝ፣ ተፀፅቶ የሕዝብ ይቅርታን ለመማፀን/‹‹ለሽግግር ፍትሕ›› ከመዘጋጀት ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በበቀልና በጥላቻ ይሰግሩ የነበሩ ኃይሎች ሁሉ በንስሐና በጦረኝነት መሀል መፈተናቸው አይቀርም፡፡ ምንም ሆነ ምን ግን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ሆነ በኋላ የሚመጣው የሽግግር ፍትሕ የብልጣ ብልጦች መሙለጭለጪያ አይሆንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የትግራይ ተሃድሶ ሕወሓታውያንንም ያድሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የትናንት ሕወሓቶች በአዲሲቷ ትግራይና በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ በፖለቲካ ጭምር የመሳተፋቸው ዕድል ክፍት ነው፡፡ ይህ ግን ‹‹በአሮጌ በሬ›› የሚሆን አይደለም፡፡ ስም ቀይሮም ሆነ ሳይቀይሩ የትግራይ ሕዝብ የትግል ቅርስ ወካይ እኔ ነኝ ሌላው ባንዳ ነው የሚል አመለካከት በአዲሲቷ ትግራይ ቦታ የለውም፡፡ ወልቃይትና ራያን በውድ ባይሆን በግድ እስከ መጨረሻው ድረስ መስዋዕትነት ከፍለን የትግራይ አካል እናደርጋለን የሚል የጉልበት መንገድም፣ የሕዝብ ለሕዝብ ሰላምና ልማትን ይቃረናልና ለነገዋ ትግራይ አይበጅም፡፡ የራስን ህሊናና ልቦና ለየትኛውም ቀጣፊ ፍላጎት ከመሸጥ አልፎ፣ የሕዝብን ህልውና ከጉርስ እስከ ደምና አጥንት ድረስ/ከወንዜ ስሜት እስከ ሃይማኖት ድረስ ለጠባብ ጦረኛ ዓላማ መቆመሪያ ማድረግ፣ ከእንግዲህ የሚቀልል አይመስለኝም፡፡ ሸርን፣ መሰሪነትንና ውንጀላን እየፈበረኩ በተቀናቃኝ ላይ መለጠፍንና በቀልን የሚያፈቅር የፖለቲካ ባህል፣ በታደሰች ትግራይና ኢትዮጵያ ውስጥ ወሳኝ ቦታ አይኖረውም፡፡ የዚህ ዓይነት ፖለቲካ ምን ያህል ዱርዬና ርኅራኄ ቢስ እንደሆነ፣ ምን ያህል የሕዝብ ሕይወትና ኑሮ እንደሚበላ ባለፉት ጊዜያት ከሚበቃ በላይ ታይቷል፡፡ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በቆየንባቸው የጦርነት ጊዜያት፣ ጦረኞች ፖለቲካ እንደ ሞተባቸው አስመስክረዋል፡፡

ከአሁን በኋላ፣ በአዛውንትነት የሰነበቱም ሆነ በጎረምሳ መልክ ብቅ ያሉ አሮጌዎች የሐሰት ትርክት፣ የዓይነ ደረቅነት፣ የመሰሪነትና ስም የማጠልሸት የፖለቲካ ባህላቸውን ይዘው ሕዝብን ለማደናገር ከቻሉ (ሌሎች ቡድኖች፣ አሮጌዎቹ በአስከሬናቸው መቅረታቸውን ለሕዝብ ማሳየት ከከበዳቸው)፣ ከአሮጌ ቡድን የተሻለ የአዲስ ብርሃን ቡድን የትግራይ ሕዝብ ካጣ፣ ትግራይ ውስጥ አማራጭ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሞቷል ማለት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሲያይ የነበረው መከራና ግፍ ጌጥና ምርቃት ሆኗል፣ የትግራይ ሕዝብ እንደ ታዳጊ ልጆቹ ህሊናውንም ተነጥቋል ያሰኛል፡፡ ይህ ይሆናል ተብሎ ማሰብ ለእኔ ቆሎ ይበቅላል የማለት ያህል የማይታመን ነው፡፡ በጥላቻና በሐሳዊ መረጃ ህሊና እየተወሰወሰ ሕዝብ የተማገደበት የጦርነት ልምድ ትኩስ ነው፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ስንቱን የሆነውን የሰሜን ዕዝ ለመምታትና የትግራይን ለጋ ወጣት ለመማገድ የጨከነ ጦረኝነት ራሱን በራሱ ውድቅ አድርጓል፡፡ በዚህና በሌሎች ነውረኛ ተግባራቱ ቡድኑ ራሱን ከሕዝብ ከበሬታ ውጪ አድርጓል፡፡ ቅጥፈት፣ ጥላቻና በቀለኝነት ሕዝብ መገነዣና ማስከሪያ መሣሪያው መሆኑንም በተግባሩ አስመስክሯል፡፡ እንዲህ ያለ አሮጌ አቋም ከአፋር፣ ከአማራና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ተሳስቦ በሰላም ለመልማት የማያስችል ደንቃራ መሆኑም ቁልጭ ያለ እውነት ነው፡፡ ይህን ያህል አገራዊ እውነታችን የሻረውን አሮጌነት ከሥራ ውጪ አድርጎ አዲስ ሙሽራ የሚወልድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አንቅስቃሴ እንደምን ይጠፋል?

ይህንን ጥያቄ መመለስ ለእኔ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፖለቲካ እውነታ ቆሎ ማብቀልም የሚቻለው መሳይ ነው፡፡ በትግራይ ውስጥ ስላለው ትክክለኛ እውነታ ጥርት ያለ መረጃ ማግኘት ችግር ነው፡፡ ሁሉ ነገር ድብስብስ ነው፡፡ ሕወሓት ትጥቅ ስለመፍታቱ የሰማ ጆሯችን ሕወሓት አሁንም ፀጥታ ማስከበርን በመሰለ ሚና ታጥቆ እንደሚገኝ እንሰማለን፡፡ የትግራይ መገናኛ ብዙኃን የእሱ ልሳን እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ አዲስ መዋቅር ስለመዘርጋት የሚያወራልንም እሱ ነው፡፡ እነ ጌታቸው ረዳ ተዓምራዊ የተሃድሶ ፈውስ አግኝተው ገለልተኛ የፀጥታ ኃይል ሊያደረጁና ሁሉም ዓይነት የፖለቲካ ቡድንና ሕዝብ በማይሸማቅቅ ነፃነት የሚንቀሳቀስበት ድባብ ሊፈጥሩ ነው? በታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ ወደ መቀሌ ሄዶ በነበረበት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ አንድ ጳጳስ (መሰሉኝ) ‹‹…ሸፍተን ነበር እኛ፣ እንኳን መጣችሁ›› መሳይ ቃል ሲናገሩ ሰምተን ነበር፡፡ አፈንግጠው የነበሩ የኦርቶዶክስ አባቶች በኦሮሚያ የኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናትን በጉልበት የመቆጣጠር እንቅስቃሴ ያደርጉ በነበረበትና ኦሮቶዶክሳውያን ነነዌ ፆምን የተመረኮዘ ቅዋሜን ጥቁር በመልበስና ፀሎት/ምህላ በማካሄድ ይገልጹ በነበረበት ወቅት፣ ከወደ ትግራይ ደግሞ በጦርነቱ ጊዜ ከአዲስ አበባ ሲኖዶስ ተነጥያለሁ ባዩ አካል ባለበት እንደሚቀጥል የሚገልጽ ጳጳሳዊ ድምፅ ተሰማ፡፡ ይህንን ያሳወቁን የሃይማኖት መሪ የሰጡት ምክንያት (በቁንፅል እንደሰማሁት) ‹‹የትግራይ ሕዝብ ከምድረ ገፅ እንድንጠፋ ሲታወጅብን ከአዲስ አበባ ሲኖዶስ በኩል ጩኸታችንን አልተጋሩም›› የሚል መሳይ ነበር፡፡

ጦርነቱን የከፈተው፣ አከታትሎም ሌሎች ሁለት ወረራዎች ያካሄደው የሕወሓት ጦር መሆኑ በግልጽ በታየበት ምድር፣ በሰሜን ዕዝ ላይ የተካሄደው ባለ ብዙ ሥልት ፍጅት ሌትና ቀናትን ያገናኘ ሆኖ ሳለ፣ እንዲያውም የቀሳውስት ልብስን በለበሱ ሰዎች አማካይነት የሰሜን ዕዝን ሠራዊት ትጥቅ ለማስፈታት እምነት ማሞኛ ሆኖ በሠራበት ምድር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከትግራይ ከወጣ በኋላም በሌላ ወረራ አፋርና አማራን በዘረፋና በውድመት እየመነጠረ ሸዋ የዘለቀው ሕወሓታዊው ጦር ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ገልብጦ ‹‹የትግራይን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት›› የሚል ኡኡታ ከሃይማኖት መሪ ከመጣ፣ ዛሬም የሕወሓት ሐሳዊ ፕሮፓጋንዳ በቤተ ክርስቲያን በኩል እየተረጨ ነው ያሰኛል፡፡ ሕዝብ የጳጳሱን ግንዛቤ የሚጋራው ከሆነም የትግራይ ሕዝብ የህሊና ነፃነት ገና ብዙ ሥራ ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የእስራት ገመድ በአምስት ለአንድ መዋቅርና በመገናኛ ብዙኃን ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን በእምነቱ በኩልም ገብቷል ያሰኛል፡፡ ሕወሓታዊ የህሊና እስራት ታድሶ ከቀጠለ ደግሞ ለትግራይም ለኢትዮጵያም መርዶ ነው፡፡

እንዲህ ያለውን መርዶ እውነት ብሎ ለመቀበልም አይቻለንም፡፡ የፈለገ ቢሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ሰዎች ጋር ግጥምጥሞሹ ሲደጋገም፣ ያንን ሁሉ ተጋድሏዊ ድል አስመነተፈው ብለን አንጠረጥረውም፡፡ በያዝነው የካቲት ወር ውስጥ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረትንና አፍሪካዊ አደራዳሪዎችን ከማመሥገን ጋር የሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ አፈታት ምሳሌያዊ ስለመሆኑ መናገሩ የሚሰጠን መልዕክት በጣም አዎንታዊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ትልሙን አልሳተም ብሎ ለመተማመንም የሚያደፋፍር ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ጦርነቱ በነበረበት ጊዜ ስለጦርነቱ አረማመድ እናገኛቸው የነበረውን ብናኝ ፍንጮች ያህል ስለሰላም ስምምነቱ የአተገባበር ዕርምጃ እያገኘን አይደለም፡፡ አደራዳሪዎቹ የፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት የፖለቲካ ውይይት እንዲያካሂዱ ስለመግለጣቸው ከሰማንም በኋላ እንኳ ከድንግዝግዝ ያለፈ ነገር ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከሕወሓታዊያኑ ቡድኖች ውጪ የሆኑት ትግራይ ነክ የፖለቲካ ቡድኖች ምን እየሠሩ እንዳሉ፣ እየሆነ ያለው ይሙቃቸው ይብረዳቸው አይታወቅም፡፡

በበኩሌ አሮጌው ሕወሓታዊነት ከእነ ፖለቲካ ባህሉ እንዲሰረዝ እፈልጋለሁ፡፡ እንዲሰርዝልኝ የምጠብቀው ግን በሕግ፣ በአዋጅ ወይም በምርጫ ቦርድ ውሳኔ አይደለም፡፡ ኤክስ በኤክስ አድርጎ እንዲሰርዘው የምጠብቀው ትግራይ ውስጥ በሚመሠረት የሽግግር አስተዳደር ጥላ ውስጥ የሚላወስ የአዲስ ሕይወት ፖለቲካና የሕዝብ ነፃ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የሕወሓትና የሕወሓታውያን ሰዎች በዚህ የአዲስ ሕይወት ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ መቻል፣ በአዲስ አመለካከትና የፖለቲካ ዘይቤ ከመወለድ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ራሱን ‹‹ሕዝብ›› ብሎ ከመሾም ወጥቶ በሕዝብ አስተዳደር ሥር ለማዳር ያልቆረጠና ዴሞክራሲን፣ ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ መልካም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማስፈንም ሆነ ከቡድን ታማኝነት ነፃ ለሆኑ ተቋማት ግንባታ ከወዲሁ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በትብብር ለመሥራት ያልተዘጋጀ፣ የትግራይን ጥሬ የልማት አቅም የማሻሻል ጉዳይ ከዱሮው ዓይን አውጣና ዕብሪተኛ የመሬት ስርቆት መንገድ ይልቅ በዕርቅ በሚገኝ የሕዝብ ለሕዝብ መተሳሰብ መፍትሔ መሻትን የሚጠይቅ መሆኑን ያልተረዳ አዕምሮ አዲስ ውልደት ውስጥ ነው ሊባል አይችልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሰላምና የልማት ግስጋሴ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት ውስጥ ከቀሪው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና ከኤርትራ ኅብረተሰብ ጋር በፅኑ የተሳሰረ መሆኑን የተረዳ አመለካከት መቆናጠጥ የሚተናነቀው ህሊና አዲስ ውልደት ነው ሊባል አይችልም፡፡

በአዲስ አመለካከትና የፖለቲካ ዘይቤ መወለድ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ የዱሮ አቋሜንና ስሜን ቀይሬያለሁ የማለት ወይም በአሮጌ ‹‹መሪዎች›› ሥር ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ እያካሄድኩ ነው›› የማለት ጉዳይ አይደለም፡፡ አሮጌ ቀፎ ሰብሮ የመውጣትን (አሮጌ አመለካከትን/አስተሳሰብን ገፎ የመጣል) ምጥን በነፃ እንቅስቃሴ ውስጥ ማካሄድን፣ ለሕዝብ ይቅርታ መንበርከክን፣ ከሌሎች አዲስ ኃይሎች ጋር መሳሰብን/መዋሃድን፣ በሒደትም አዲስ አቋሞችንና መሪዎችን የማጎልበት ጉዞን ይፈልጋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ይህንንና ይህንን የመሰሉ የአዲስ ሕይወት ጉዞዎች እንዲያብቡበት እንጓጓለን፡፡ ከአንድ ቡድን ርዕዮተ ዓለማዊ እስረኝነት ነፃ የሆኑ ልሂቃንና ምሁራን የሚያብቡት፣ ለሚዛናዊነት፣ ለሕዝብና ለሀቅ የሚታመኑ ጋዜጠኞችንም ትግራይ የምታገኘው በዚህ ሒደት ውስጥ ነው፡፡ ማናህሎኝ ባይ ዕብሪትና ጎጠኛ/ብሔርተኛ ፅንፈኝነት ሄዶ ሄዶ ታገልኩለት ያለውን ሕዝብ በጥላቻና በበቀል እሳት እንደሚበሉ ከትግራይ ሕዝብ በላይ ያየ የለም፡፡ ይህንን መራራ ልምድ የትግራይ ሕዝብም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ኅብረተሰበብ እንዳይረሳና ለዚህ ዓይነት የጉልቤ ቡድኖች ፊት እንዳይሰጥ እኔም ጊዜውም እንማፀናለን፡፡

ይህ ተማፅኖ የድርሰት ቄንጥ አይደለም፡፡ 2016 ዓ.ም. የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት 50ኛ ዓመት ነው፡፡ ይህ ወር ሁላችንም ለፍርድ የምንቆምበት ወር ነው፡፡ ኅብረተሰባችን በሙሉ ከትናንትናና ከትናንት ወዲያ ወላጆቻችሁ መሠረታዊ የጉርስ ፍላጎቶች፣ መሠረታዊ የፖለቲካ መብቶችና የፍትሕ ጥያቄዎች ምን ያህል ፈቀቅ አላችሁ ተብሎ ይጠየቃል፡፡ በዚህ የታሪክ ፍርድ ፊት ቆመን የትናንትናና የዛሬ ልሂቃን በትውልድ ቅብብሎሽ ምን ያህል ፍሬማ ውጤት አመጣችሁ ተብለን እንጠየቃለን፡፡ የትናንትናና የዛሬ ፖለቲከኞች ምን ያህል ከጥፋት ተምራችሁ ሕዝብ የሚክስ ሥራ ሠራችሁ ተብለን እንጠየቃለን፡፡ ይህ ጥያቄ ወደ ትናንትና ኅብረ ብሔራዊ ትግል ርዝራዦች ይመጣል፡፡ ከትናንት አንስቶ በብሔርተኛነት ውስጥ ደፋ ቀና እያልን እዚህ ለደረስንም ሆነ፣ ከአንዱ ፖለቲካ ሠፈር ወደ ሌላው ሠፈር ለተፈናጠርን ሁሉ ጥያቄው አይቀርልንም፡፡ ጥያቄዎቹ በየፊና የተሰነጣጠሩ ሳይሆኑ የሁላችንንም የአስተዋፅኦ ድምር ውጤት የሚመለከቱ እንደ መሆናቸው ምን የሚያኮራ የጋራ መልስ ይኖረን ይሆን? ቢያንስ ቢያንስ በአያያዙ የሚያምር የአዲስ ሕይወት ልምላሜ ቤታችንን አቆናጠን ብሩህ የወርቅ እዮቤልዩ ለማክበር እንበቃ ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...