በሞገስ ዘውዱ
በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ጥናት ውስጥ በጣም አወዛጋቢ ከሆኑት መካከል ብሔርተኝነት አንዱ መሆኑ ዕሙን ነው። የውዝግብ ምንጭ በተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች መካከል ያለው ያልጠራ ብያኔ፣ የብሔርተኝነት ምንነትና ባህሪ፣ እንዲሁም ብሔርተኝነት የሚፈጠርበት፣ የሚፋፋበትና የሚደበዝዝበት ሁኔታ በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እኔም ይህንን የብሔርተኝነት ተለዋዋጭና አወዛጋቢ አረዳድ መኖሩን ዕውቅና የምሰጥ ቢሆንም፣ በጉዳዩ ላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች አሉ።
በመጀመርያ ሊታወቅ የሚገባው በብያኔ (Definition) ደረጃ የብሔርተኝነት ግማሽ፣ ቡራቡሬና ጉራማይሌ መልክ የለውም። አንድ እንቅስቃሴ ወይ ብሔርተኛ ይባላል አሊያም አይባልም። ሁሉም የመብት ጥያቄና ትግል ግን ብሔርተኝነት አይደለም። በተመሳሳይ በአፈጣጠርና መገለጫ ብሔርተኝነት የተለያዩ ሒደቶችን ያልፋል። በዚህ ክፍል የንዑስ ብሔርተኝነት ምንነት (አፈጣጠርና ባህሪ)፣ መገለጫዎች (Manifestations) እና የፖለቲካ ግብ ይዳሰሳሉ። ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ በክፍል ሁለት የሚቀርብ ይሆናል። ከዚህ በኋላ በሌላ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር ብሔርተኝነት የሚለው ቃል “Ethnic Nationalism”ን ለመግለጽ ሥራ ላይ ይውላል።
፩ ብሔርተኝነት ምንድነው?
ብሔርተኝነት ከመኖሩ በፊት ሕዝብ፣ ነገድ (Ethnic Groups) እና ብሔር (Nation) ይኖራሉ (Through Dynamic Social Transformation Process)። በጋራ ማንነት ዙርያ ያልተሰባሰበና ከሌሎች ጋር ተሰባጥሮ የሚኖር ቡድን ሕዝብ ይባላል። ሕዝብ በራሱ ማንነት ዙርያ ተሰባስብቦ ሲገለጽ ወደ ነገድ ከፍ ይላል (Ethnic Group Based On Distinct Culture)። ነገድ የፖለቲካ ህልም ሳይኖረው የባህል ማኅበረሰብ ሆኖ ለዘመናት ይኖራል፡፡ የብሔር ጥያቄም አይነሳም (The National Question)። ነገር ግን በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ (National Consciousness) ሒደት የጋራ የፖለቲካ ግብ ሲኖር የፖለቲካ ማኅበረሰብ ይፈጠራል። ይኼም ማለት፣ በጋራ የባህል ማንነት ላይ የጋራ ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ሲጨመር የፖለቲካ ማኅበረሰብ (Nation) ይወለዳል። የጋራ ግቡ (Political Demands) ማንነት ዕውቅና እንዲያገኝ ጀምሮ በአንድ አገር ውስጥ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ የራስ አገር መመሥረት ይሄዳል። በመሆኑም፣ ብሔርተኛ ለመባል የራስ አገር ግንባታ ግዴታ አይደለም (It Is Not A Mandatory Definitional Element)።
በኅብረ ብሔራዊ አገሮች ውስጥ አገረ መንግሥት (State) እና ብሔር (Nation) አንድ ዓይነት አይደሉም (Dominant Ethnic Group or Groups ቢኖሩም)። ኢትዮጵያም በ(Plurinational State) ውስጥ ትመደባለች። ከዚህ ተነስተው ምሁራን ብሔርተኝነትን እንደሚከተለው ይገልጹታል (Definition Of Ethnic Nationalism)፡፡
ከአገር (State) ይልቅ ለብሔራቸው ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጡ፣ የሚታገሉና ታማኝነት ያላቸው ቡድንና ይኼንን ለማስፈጸም የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ከአገር ጋር ያለው ግንኙትና ታማኝነት (Civic Allegiance) ቀጥሎ የሚመጣ (Derivative Loyalty) ይሆናል። የዚህ (Typical Example) ግልጽ መገለጫ ቅድሚያ ለብሔር ማንነቴ የሚል እንቅስቃሴ ነው። ለምሳሌ “I am Oromo First” እዚህ ውስጥ ሊመደብ ይችላል።
፪ የብሔርተኝነት መልኩ መገለጫዎች ምንድን ናቸው?
ብሔርተኝነት ግቡ ከላይ የተመላከተው (ከለዘብተኛ ጥያቄ እስከ አገር ምሥረታ የሚሄድ) ሲሆን፣ በሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ የሚታወቀው የብሔርተኝነት ውልደት ካለው አገረ መንግሥት ጋር ራስን በመነጠል (Nationalism By Disassociation) ነው። ሁለተኛውና ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ካለው አገረ መንግሥት ጋር ጠንካራ ቁርጠኝነት በመፍጠር (Nationalism by Sense of Exceptionalism) እና ለሌሎች ብሔርተኞች የመልስ ምት (Reactionary Movement) ነው። የመጀመርያዎቹ ጎራ በአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ በቂ ሚና አልነበረኝም፣ ቢኖረኝም አገር (State) የእኔን ማንነት በሚገባ አላንፀባረቀችም፣ ከዚያም አልፎ ተጨቁኛለሁ (ወይ በሥርዓቱ አሊያም በሌላ ብሔር) የሚል ሲሆን፣ በሒደት የሚነሱ ጥያቄዎች ካልተመለሱለት ጉዞው የመንገንጠልና አገር ግንባታ (Secessionist Movement) ይሆናል።
ሁለተኛው ጎራ ደግሞ በአገረ መንግሥቱ ውስጥ ታሪካዊ ድርሻ አለኝ፣ ማንነትቴ ካለው አገረ መንግሥት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፣ የገነባሁትን አገር ከአፍራሾች የመጠበቅ ኃላፊነት አለብኝ፣ ከፍ ሲል አገሩ የእኛ ስለሆነ ሌሎች በሚናቸው ልክ ይንቀሳቀሱ ይላል። አንዳንዴ ደግሞ የመጠቃት ስሜት የብሔርተኝነቱ እርሾ ከሆነ፣ ከአጥቂዎች ራሳችንን የመጠበቅ እንቅስቃሴ (ብዙውን ጊዜ ብሔርተኝነት ብለው አይጠሩትም!) ይጀምርና ጉዳዩ ወደ ፍጥጫ (Security Dilemma) ያመራል። ‹‹Security Dilemma›› በዋናነት የሚፈጠረው አንዱ ቡድን ሌላው እያጠቃኝ ነው፣ የሚታጠቀው እኛን ለማጥፋት ነው ብሎ ይወስናል (Threat Perceptions)፣ ቀጥሎ ለራሱ ተመጣጣኝ ቢቻል ደግሞ የተሻለ ኃይል ወደ መገንባት ይሄዳል። ሌላው ቡድን ይኼን እንደ ጥቃት ያየዋል፣ የራሱን ኃይል ያጠናክራል። እንዲህ እያለ ወደ የማያባራ ግብረ መልስ ያመራል። የዚህ ሁሉ ማደራጃ ፍልስፍና ደግሞ “እኛ” ጥሩዎችና “እነሱ” ጠላቶች ከሚል የሚቀዳ ነው። ያለ እኛና እነሱ ብሔርተኝነት ፈጽሞ አይኖርምና፡፡
አገር የእኔ አይደለችም (አትመስልም) በሚል የተመሠረተ ብሔርተኝነት ወደ ጥርጣሬ፣ ለቅሶና መገንጠል ፖለቲካ ሲያመራ፣ በአንፃሩ አገረ መንግሥቱ እኔን ይመስላል፣ እንዲሁም ጥቃት ደርሶብኛል መመከት አለብኝ ብሎ የሚፈጠረው ደግሞ ወደ ጡዘት (Polarization) እና ፋሺዝም (Fascism) ያመራል። በሌላም ዓለም ይኼንን ሁኔታ አልፎ አልፎ (Right Wing Nationalism) ብለው ይበይኑታል። የዚህ ብሔርተኝነት ምሳሌ በየአገሩ ቢኖርም፣ ትልቅ ምሳሌ የሚሆነው የዩጎዝላቪያ ሰርቦች እንቅስቃሴ ነው።
ዋናው ቁምነገር የሁለቱም እንቅስቃሴ በብሔር ላይ እንጂ በአገር (Civic Nationalism) (ሕግ፣ ተቋምና የዜግነት እኩልነት) ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ሁለቱም ስማቸው ብሔርተኝነት ተብሎ ይጠራል፡፡ ስለሆነም ብሔርተኝነት ከአንዱ ብሔር ወደ ሌላው፣ ከወንዝ ወንዝ ትርጓሜው አይቀያየርም። ምናልባት መገለጫዎቹ ጎልተው እንዲወጡ (Everyday Manifestations) በየአገሩ የፖለቲካ ሁኔታ (Conducive Environment) ሊወስን ይችላል። ለምሳሌ መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ፣ የብሔርተኞቹ የፖለቲካ ኃይልና የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል አካሄዱን ሊቀርፁት ይችላሉ።
፫ የትግል ሥልቶች ምን ዓይነት ናቸው?
ለብሔርተኝነት እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲ ግዴታ አይደለም። እንዲያውም ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ በጨቅላ ዕድሜው ላይ ሲሆን በዋናነት በሲቪክ ማኅበረሰብ መልክ፣ በሚዲያ ትግል፣ በባህል ዘመቻ (Cultural Renaissance)፣ ነባር ተቋማትን (የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ) መጠቀምና በልሂቃን ድርድር ሒደት ይገለጻል። ይኼ ደረጃ (National Consciousness) የሚፋፋምበት ነው። የጋራ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ሳይፈጠር ብሔርተኝነት ስለማይኖር፣ ቢሞከርም ስለማያብብ።
የፖለቲካ ፓርቲ ከተመሠረተ በኋላ ግን ሥልጣን መያዝ ግዴታው ነው። በተባታተነ መልኩ የሚነሱ የብሔር ጥያቄዎች (Political Demands) በዋናነት በተቋም በኩል ይሆናል ማለት ነው። ይኼ ሒደት (Channelling Grievances Via Party Structure) ተብሎ ይጠራል። በብሔር የተደራጀ ፖርቲ ሥልጣን ፈልጌ አይደለም ማለት ልክ “ትዳር ውስጥ የገባሁት ለመታቀብ ፈልጌ ነው” እንደ ማለት ነው። ለፅድቅ የሚቋቋም የፖለቲካ ፓርቲ የለም፣ ለሥልጣን እንጂ፡፡
በሁለተኛው መንገድ የተወለደው ብሔርተኝነት ተደራቢ የቤት ሥራ አለበት። ይኼም የሆነው የብሔር ማንነቱ ከአገራዊ ማንነቱ ጋር በእጅጉ የመጀመርያዎቹ (Minimal Overlapping Values) ነው የሚኖራቸው፡፡ ተመጋጋቢ ከሆነ ሁለቱን ማንነት (Decouple) ማድረግ ወይም ራስን (ብሔርተኝነቱን) በአገራዊ ማንነት መቅረፅ ይጠይቃል። “እኔ የአገረ መንግሥቱ ጠባቂ ነኝ” የሚል ስሜት እንዲንፀባረቅ ያደርጋል። አንዳንዴ (In Rare Situations) አገራዊ ማንነትና ንዑስ ብሔርተኝነቱን ለማስማማት (Synthesis) የሚሞክሩ አሉ። ይኼ ትግል ከተሳካ የንዑስ ማንነቱ መገለጫዎች ዋና የጋራ እሴት (Dominant Culture) ይሆናል። ካልሆነ ግን በብሔረ መንግሥት ግንባታ (Nation Building) ሒደት አገራዊ ማንነቱ ይቃኝና የተለየ ባለቤት ነኝ (Exclusive Sense Of Belongingness) እየከሰመ ይሄዳል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየውም ሽኩቻ በመጠኑ የዚህ (Dialectic Tension) ነው።
፬ እንደ መውጫ
የብሔርተኝነት ትርጉምና መገለጫ በየወንዙና አደረጃጀት የሚቀያየር ጽንሰ ሐሳብ አይደለም። ብሔርተኛ ሳይኮንም የመብት፣ ፍትሕና እኩልነት ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን አንዴ ብሔርተኛ ነኝ ብሎ ራሱን ከጠራ ወይም የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ መሥፈርት ካሟላ በኋላ፣ ‹‹የእኔ ብሔርተኝነት ልዩና ጉዳት አልባ (Innocuous Nationalism) ነው ማለት (By Definition) አይቻልም። የብሔርተኝነት ነዳጅ ደግሞ እኛና እነሱ ፖለቲካ (Politics of Othering) ነው። በዚህ ረገድ “ኢትዮጵያን እናድን” የሚለው ቃል ራሱ በአግባቡ ካልተገለጸ በብሔርተኝነት ቋንቋ ሲመዘን፣ “ለመሆኑ ከማነው የምታድናት?” የሚል ጥያቄ ይዞ ይመጣል።
ክፍል ሁለት (የአማራ ብሔርተኝነትን ጨምሮ) ይቀጥላል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ mogeszewdu2013@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡