Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አገራችን አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ በስክነት የሚታዘብ ማንም ጤነኛ ዜጋ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› በሚባል አዘናጊ አባባል የሚታለል አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ አብዛኛው የታሪኳ አካል ከእርስ በርስ መገፋፋቶችና መሳሳቦች፣ ከግጭቶች፣ ከፋ ሲልም ከለየላቸው ጦርነቶች ጋር የተያያዘ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ በዕድሜዬ ከማስታውሳቸው አስደንጋጭ ጊዜያት አንዱ 1969 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሕዝባዊው አብዮት በወታደሮች ተጠልፎ አኩራፊዎች የበዙበት፣ የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጠልቆ የገባበት ነበር፡፡

ከውስጥ ኢሕአፓ፣ ሻዕቢያና ጀበሃ፣ ሕወሓት፣ ኢዲዩና ሌሎች በየአቅጣጫው ነፍጥ አንስተው ከቀጥታ ጦርነት እስከ ከተማ ግድያ በመሰማራት ኢትዮጵያ ተቀስፋ ተይዛ ነበር፡፡ ከውጭ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት በዘመኑ በሚገባ የሠለጠኑ በርካታ እግረኛና ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮችን፣ እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉ ከባድ መሣሪያዎች ጋር በማቀናጀት ወረራ በመፈጸም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተዳፍሮ ነበር፡፡ በዚያ አስፈሪ ጊዜ አንድ ተስፋ የነበረው አገሩን የሚወደው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ቅሌን ጨርቄን ሳይል ወራሪውን ለመመከት በአንድ ልብ ተነስቶ መክተቱ መቼም የማይረሳ ታሪክ ነው፡፡

አብዮቱ በደም ጨቅይቶ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ቢፋጁም፣ ከጥቂቶቹ በስተቀር ብዙኃኑ ሕዝብ አገሩን ከወራሪው ጠላት ነፃ ለማድረግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ታጠቅ ጦር ሠፈር በከፍተኛ ወኔ የከተተው ሦስት መቶ ሺሕ ሚሊሻ በሦስት ወራት ሥልጠና ታላቅ ገድል በመፈጸም ኢትዮጵያን አኩርቷል፡፡ ቀሪው ሕዝብም ስንቅ በማዘጋጀት፣ በጉልበትና በገንዘብ በመደገፍ፣ ያልቻሉ ደግሞ በፀሎታቸው አገራቸውን ታድገዋል፡፡ ያንን የመሰለ ታላቅ አገራዊ ትብብር በመጀመሪያ ለታሪካዊው የካራማራ ድል ሲያበቃ፣ በመቀጠል ደግሞ የሶማሊያ ሠራዊት አከርካሪው ተመቶ ከኢትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ እንዲወጣ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የካራማራን ድል ስንዘክር ይህንን የመሰለ አገራዊ ፍቅር ጭምር እያስታወስን ነው፡፡

የካራማራ ድል የታላቁ ዓድዋ ድል ማጠናከሪያ ታሪካችን አካል በመሆኑም፣ በዚያ በጨለማ ዘመን የደረሰብንን ቁስል ጭምር ጠገግ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን በቀይና በነጭ ሽብር ዕልቂት፣ እስር፣ ሥቃይ፣ ስደትና አንገት መድፋት ያደፈው ታሪካችንም አይረሳም፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ የቅርብ ዘመዶቼን በነጭና በቀይ ሽብር ዕልቂት ከማጣቴም በላይ፣ ብዙዎቹ በሥቃይና በስደት ያሳለፉት አሳዛኝ ጊዜ አይረሳኝም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ያለፈውን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ በመዝጋት ኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት አገር በጋራ መገንባት እንችላለን ባይ ነኝ፡፡ ይሁንና ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው ታሪካችን ያጋጠሙ ስህተቶችን አሁንም አንላቀቅም ብለው፣ አገርን እያደር ወደ ቁልቁለት የሚነዱ ሰዎች ጉዳይ ደግሞ ያሳስበኛል፡፡

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በሕዝባዊ እንቢተኝነት ተገዶ ከመንበሩ ገለል ሲደረግ፣ ያንን አስከፊ ሥርዓት የማይቀበል አዲስ የለውጥ ጉዞ ሲጀመርና ብዙኃኑ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የተስፋ ብርሃን ሊወጣ ነው ብሎ በሙሉ ልብ ለውጡን ሲደግፍ የነበረው ሁኔታ አይረሳም፡፡ የለውጡ መሪዎች እየተሞካሹ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ሲደረግላቸው፣ እነሱም ለውጡን የሚያጠናክሩ ዕርምጃዎችን ሲወስዱ፣ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱና በስደት የነበሩት አገር ቤት ሲገቡ የነበረው ደስታና እርካታ ወደር አልነበረውም፡፡

ያ ደስ የሚል ጊዜ ግን እያደር መወየብ ሲጀምር በቡራዩ የወገኖቻችን የጅምላ ግድያና ማፈናቀል ተጀመረ፡፡ በምዕራብ ጉጂና በጌዴኦ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለ ግድያ ተከተለ፡፡ እያለ እያለ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻኑጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ አፋር… በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከሚፈጸም ጥቃት እስከ ቀጥተኛ ግጭት ብዙዎች ተፈጁ፣ ተፈናቀሉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በትግራይ ክልል በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመ ጥቃት መነሻ የለየለት ጦርነት ተጀምሮ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ያጠቃለለ ዕልቂትና ውድመት ደረሰ፡፡ ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭቶች ታሪክ ውስጥ ታላቁን ጥፋት አደረሰ፡፡ ምናልባትም በወደፊቱ ትውልድ ጭምር ይቅር የማይባል ወንጀል ሊሆንም ይችላል፡፡

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት በአንፃራዊነት በመውጣት ሰላም የሰፈነ ቢመስልም፣ አሁንም ያልተቋጩ ጉዳዮች በመኖራቸውና መተማመኑም ያን ያህል ስላልሆነ ሥጋት አለ፡፡ ከዚህ ሥጋት ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጠረው ችግር፣ በአማራና በኦሮሚያ አመራሮች መካከል ተፈጠረ የሚባለው ሽኩቻና ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የማያስችለው የፀጥታ መታወክ፣ እንደ ሰደድ እሳት እየተባባሰ ያለው አደገኛ የኑሮ ውድነትና ሌሎች አሳዛኝ ክስተቶች ያሳስባሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓድዋ ድል አከባበር ወቅት የታየው አንገት አስደፊ ድርጊትና የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ዕርምጃ ወቅቱን አስፈሪ አድርገውታል፡፡

እነዚህንና ሌሎች የጊዜያችንን አሳሳቢ ጉዳዮች በአዕምሮዬ እያነሳሁ ስጥል አንድ ነገር ሰቅዞ ያዘኝ፡፡ በፊት ቢሆን ኖሮ የእኛ ሰው የከፋ ችግር ቢገጥመው እንኳ ከራሱ ይልቅ አገር ያስቀድም ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከአገር በላይ ምንም ነገር ቅድሚያ ስለማይሰጠው ነው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያ ከአማራነቱ፣ ከትግሬነቱ፣ ከኦሮሞነቱ፣ ከወላይታነቱ፣ ከአፋርነቱ፣ ከሶማሌነቱ፣ ከጋምቤላነቱ ወይም ከየትኛውም ብሔር ተወላጅነቱ በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ይበልጥበት ነበር፡፡ ነፍሱን ይማረውና ታዋቂው ጸሐፊና ፖለቲከኛ አቶ አሰፋ ጫቦ፣ ‹‹እኔ ጋሞነቴም ሆነ ኢትዮጵያዊነቴ ተጋጭተውብኝ አያውቁም›› ያለው ታሪካዊ አባባል ብዙዎች የሚጋሩት አስተሳሰብ ነበር፡፡

ዛሬስ የተገላቢጦሽ እየሆነ ይመስለኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ድሮ እፈራው ከነበረው 1969 ዓ.ም. ይልቅ የዘንድሮው 2015 ዓ.ም. እያስፈራኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የጎሳ ከረጢታቸው ውስጥ የሚያደፍጡ እየበዙ ስለሆነ ነው፡፡ በአንድ ነገር ግን ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በዚህ ዘመን ራቅና ሰፋ ያለ ዕይታ ያላቸው ወገኖቼ ከአድፋጮቹ የተሻለ የበላይነት አግኝተው፣ ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርባትና ለመጪው ትውልድ ታሪክ የምናስቀምጥባት ታላቋን ኢትዮጵያን እንደሚገነቡ ይታየኛል፡፡ ፈጣሪ ሲጨመርበት ደግሞ ችግራችን ሁሉ ይቀረፍና ዘላቄታዊ ሰላም ይሰፍን ይሆናል፡፡ ፈጣሪ ይርዳን፡፡

(ጥላሁን ገብረ ሚካኤል፣ ከጀሞ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...