Thursday, March 23, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ተስፋ እንደ ጉም እንዳይበተን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው የተማፅኖ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ፀንታ የምትቆመው ሁሉም ልጆቿ በነፃነትና በእኩልነት ሊያኖራቸው የሚችል ሥርዓት ሲገነባ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ የዘመኑ ትውልድ የራሱን የሚያኮራ ታሪክ መሥራት ሲገባው፣ በአያቶቹና በቅድመ አያቶቹ ዘመን ስለተፈጸሙ ድርጊቶች እየተወዛገበ አገር እንዳያፈርስ ማሳሰቢያ እየተሰጠው ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ ለሥልጣን የሚፎካከሩ የፖለቲካ ልሂቃን ካለፉት ስህተቶች እንዲማሩ ሲነገራቸው፣ ምክረ ሐሳብም ሆነ ማሳሰቢያ ለማዳመጥ ፍላጎት የላቸውም እየተባሉ እየተተቹ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አገርን የመምራት ኃላፊነት ትከሻቸው ላይ የወደቀ ወገኖች ከማንም በላይ ተጠያቂነት ስላለባቸው፣ ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውትወታው በርትቶባቸዋል፡፡ አገር ተስፋዋ የሚያብበውና ሰላም ሰፍኖ ዕድገት የሚገኘው ለመከባበር፣ ለመነጋገር፣ ለመደማመጥና አብሮ ለመሥራት ፈቃደኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ትከሻ ለትከሻ እየተለካኩ በምን ታመጣላችሁ ስሜት የሚመራ ፖለቲካ አገርን ለውድቀት ነው የሚዳርገው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጀብደኝነት የአገርን ተስፋ ያጨፈግጋል፡፡

የአገር ተስፋ የሚለመልመው ልጆቿ ለልዩነቶቻቸው ዕውቅና ተሰጣጥተው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ አብረው ሲሠሩ ነው፡፡ ልዩነትን ይዞ ተከባብሮና ተባብሮ መሥራት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም፣ የዘመኑ አብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ይህ ክቡር ተግባር የገባቸው አይመስሉም፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በታሪክ አረዳድና በሌሎች ጉዳዮች ልዩነት መኖሩ ሊያስገርም አይገባም፡፡ ልዩነት በአግባቡ ከተያዘ ሐሳብ ለመለዋወጥና ዕውቀት ለመገብየት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ፣ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ፍትሕና እኩልነት እንዲኖሩና ሰዎች ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ነፃነታቸውን እንዲያጣጥሙ ይረዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የዘለቀው የፖለቲካ ባህል ግን ሐሳብን ከመድፈቅና ጉልበትን ከመተማመን ውጪ አላሳይ ብሎ፣ በእኩልነትና በነፃነት አብሮ መኖርና መሥራትን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳች ችግር ሲያጋጥም ተቀምጦ ከመነጋገር ይልቅ ጦር መስበቅና መፋጀት ተለምዶ፣ አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ የመልማትና የማደግ ተስፋዋ እንደ ጉም እየበነነ ነው፡፡ ከጋራ አገር ይልቅ የብሔር ጎጆ መቀለስ ልማድ ሆኗል፡፡

በታላቁ የዓድዋ ድል ሳቢያ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጀመር ዋነኛ ምክንያት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ከነበረችበት ከፍታ ወርዳ የብሔር ፖለቲካ መሻኮቻ ምድር ስትሆን ከማየት በላይ የሚያሳቅቅ ነገር የለም፡፡ ለዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊ አንድነት በመናድ የብሔር የበላይነት ፉክክር ውስጥ ሲገባ፣ በመጪው ትውልድ ሳይቀር የሚያስረግም የታሪክ ጠባሳ እየተፈጠረ ነው፡፡ ሥልጣን ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው በተሸጋገረ ቁጥር የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘመን ተሻጋሪ መስተጋብር ወደ ጎን በማለት፣ ለብሔር የበላይነት የሚደረገው ትንቅንቅ በማየሉ ኢትዮጵያ የቁልቁለቱን መንገድ እንድትያያዘው ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የዛሬው ትውልድ የራሱን አኩሪ ታሪክ ሠርቶ አገር በጋራ ከመገንባት ይልቅ፣ በድሮ ታሪክ ላይ ተቸንክሮ እየተወዛገበ አገሩን ኪሳራ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ለዘመናት የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙ ታሪካዊ ጠላቶች መልካም አጋጣሚ እየተፈጠረላቸው፣ በግራም በቀኝም እርስ በርስ ለሚተናነቁ ኢትዮጵያውያን ክብሪትና ጋዝ እያቀበሉ ናቸው፡፡ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ጭምር ታላቅ አርዓያ የነበረች አገር፣ እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች ሰላም አጥታ የታሪካዊ ጠላቶቿ መጠቋቆሚያ እየሆነች ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የሚያስከብሯት የታላላቅ ገድሎች ባለቤት ነበረች፡፡ ለዘመናት ሲያናጥሩባት ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ በላይ የምትኮራባቸው ታሪኮች የተከናወኑባት አገር ናት፡፡ የሕዝቡን አንገት ሲያስደፉ ከቆዩት መከራዎች በላይ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትነትዋ የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ መርግ ይከብዱ ከነበሩ ቀንበሮቿ በላይ፣ ታሪኮቿና ገድሎቿ አንፀባራቂ ናቸው፡፡ በዚህም ክብር የሚገባት ታላቅ አገር ናት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በውስጡ ያሉትን ልዩነቶች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይዟቸው በእርስ በርስ መስተጋብሩ ተምሳሌታዊ አንድነቱን ይዞ በመቆየቱ፣ ለዘመናት የዘለቀው ይኼው አስደሳች አብሮነት ዛሬም ቢቀጥልም ሥጋት ግን አለ፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነትን አጉልቶ በማውጣት በደስታውም ሆነ በሐዘን አብሮ ቢኖርም፣ በአሁኑ ጊዜ ከባድ ፈተናዎች ከፊቱ ተጋርጠዋል፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝባችን በደስታውም ሆነ በመከራው ጊዜ አብሮ በሰላም መኖሩ በታሪክ የተመሰከረ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ግን ይህንን አስመሥጋኝ ልምዱን የሚገዳደሩ እየበዙ ነው፡፡

የሕዝቡን ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች የማስከበር ኃላፊነት ወር ተራው የዚህ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያለበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በርካታ ተስፋ የሚፈነጥቁ አጋጣሚዎችም አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በተለይ በፖለቲካው ከባቢ ውስጥ የሚገኙ እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ ከምንም ነገር በፊት የአገሪቱና የሕዝቧ ጥቅም መቅደም አለበት፡፡ ይህ ጥቅም መቅደም የሚችለው ደግሞ በመከባበርና በወዳጅነት መንፈስ ለዓመታት የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የመፈራረጅና የመጠላላት ፖለቲካ ለአገሪቱ ፋይዳ እንደሌለውና የሕዝቡን ሥነ ልቦና እንደማይገልጸው እየታየ ነው፡፡ ‹‹ከእኔ በላይ ለአሳር›› የሚለው የጀብደኝነት አካሄድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅምና የአገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ ስለሚከት፣ ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ከአሉታዊ ድርጊቶች ይታቀቡ፡፡ የዚህን ኩሩ ሕዝብ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተና ለዘመናት የኖረውን አንፀባራቂ አርዓያነት በመከተል፣ በአገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት መኖር አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚያግባባው እየተግባቡ፣ ልዩነቶችን ደግሞ እያቻቻሉ የኢትዮጵያዊነትን ከፍታ መጨመር የግድ መሆን አለበት፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚባለው ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ናት፡፡ የሚያስተዳድራት መንግሥትም ተጠሪ መሆን ያለበት ለሕዝቡ ነው፡፡ ለሕዝብ ተጠሪ የሆነ መንግሥት ደግሞ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን በሚገባ መወጣት ይችላል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምሰሶ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ተሟልተው በማይገኙበት ሁኔታ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ሲጣስና የፕሬስ ነፃነት ሳይከበር ሲቀር፣ በርካታ ጩኸቶችና አቤቱታዎች ቢቀርቡ ሊያስገርም አይገባም፡፡ ይልቁንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የሠፈሩትን የሰው ልጆች መብቶች የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎችን ተቀብላ ባፀደቀች አገር ውስጥ ሕግ ካልተከበረ፣ በውስጥና በውጭ ግፊት የሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ይቀጥላሉ፡፡ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይም አደጋ ይደቅናሉ፡፡ በሰብዓዊ መብት ምክንያት የሚነሳው ተቃውሞ መርገብ የሚችለው ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት አገር አንገቷን አትድፋ፡፡ ለሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ፡፡ አፋጣኝ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ለአገር ልማትና ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ለህልውናዋ ጭምር ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአገር ተስፋ እንደ ጉም እንዳይበን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

መንግሥት በግማሽ ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ያህል ቀጥታ ብድር መውሰዱ ታወቀ

የአገር ውስጥ ብድር ከ1.6 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል የብሔራዊ ባንክ...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...