በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትምባሆ ማጨስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተለያዩ ሕጎችና መመርያዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው ለውጥ ቢያሳይም፣ ዛሬም በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ እንደሚሉት፣ ችግሩን ለመቅረፍ በቅድሚያ መሠራት ካለባቸው ሥራዎችም በትምባሆ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን አጠናክሮ ለሕግ አውጪዎችና ለማኅበረሰቡ ማዳረስ ብሎም ግንዛቤ መፍጠር አንዱ ነው፡፡
በመሆኑም የትምባሆ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ምርቶች ሙሉ ለመሉ መረጃን መሠረት ያደረገና የተለያዩ የቁጥጥር ዕርምጃዎችን ለመውሰድና ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችል የኢትዮጵያ የትምባሆ ቁጥጥር ድረገጽ ይፋ ሆኗል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት፣ ከዴቨሎፕመንት ጌት ዌይና ከጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ጋር በመተባበር ከ2021 ጀምሮ ሲዘጋጅ የቆየው ድረገጽም፣ ለሕግ አውጪዎች፣ ለውሳኔ ሰጪዎች፣ የቁጥጥር ሥራ ለሚሠሩ፣ ለተመራማሪዎችና ለማኅበረሰቡ በትምባሆ የቁጥጥር ሥራዎች ላይ ተጨባጭና የተረጋገጡ መረጃዎች ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በዓመት ከ16,000 በላይ ሰዎች ከትምባሆ ማጨስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች እንደሚሞቱ በማስታወስም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአጫሾች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ውስጥ እየጨመረ በመሆኑ፣ ጠንካራ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ማውጣትና መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳሳበዋል፡፡ የመረጃ ሥርጭትና ግንዛቤ መፍጠር ደግሞ ወሳኝ መሆኑን አክለዋል፡፡
ጠንካራ ሕጎች እንዳይወጡ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት መኖሩን፣ ሕግ እንዳይወጣ እንቅፋት ከመሆን ባለፈም፣ ከወጣ በኋላ እንዳይተገበርና ደካማ አፈጻጸም እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) እና የኡራጋዩ ፕሬዚዳንት ታባሬ ራም በ2018 በፕሮጀክት ሲንድኬት ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች የበለፀጉ አገሮችንም ጭምር መፈተናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ አገሮችም ይህንን ለመከላከል ጠንካራ ሕጎችን በማውጣትና በማስፈጸም ያለውን ተፅዕኖ ለመገደብ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በ2011 የወጣው የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ በውስጡ ጠንካራ ድንጋጌዎችን መያዙን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ሕጎችና ስምምነቶች አንፃር ጠንካራ ቢባልም፣ አተገባበሩ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ለሕዝቡ ግንዛቤ መፍጠርና ትክክለኛ መረጃ ማተላለፍ ዋነኛ ሥራ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ የመረጃ ፍላጎቶች ባለሥልጣኑ የትምባሆ ቁጥጥር መረጃ ማዕከልን በመጠቀም ሁሉንም መረጃ ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ፣ ኃላፊነቱን ለመወጣትና የመረጃ ክፍተቱን ለመሸፈን እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስለትምባሆ አጫሾች ቁጥሮች ምን ያሳያሉ?
ዳይሬክተሯ እንደገለጹት፣ ትምባሆ በዓለምም በአገርም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ትምባሆ ከሚያጨሱ መካከልም ግማሽ ያህሉ በትምባሆ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች የሚሞቱ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ምክንያት ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ያህሉ ሁለተኛ አጫሾች ወይም የማያጨሱ ሆነው ከሚያጨሱ ሰዎች በሚለቀቀው ጭስ ምክንያት የሚሞቱ ናቸው፡፡
በዓለም ትምባሆ ከሚያጨሱት መካከል 80 በመቶ ያህሉ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሚኖሩ ሕዝቦች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያም ከዚሁ የምትመደብ በመሆኗ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ያስገድዳል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ አጫሹ ማኅበረሰብ ሁለት ዓይነት የትምባሆ ምርቶችን ማለትም በፋብሪካ የተመረተ ወይም በእጅ የሚጠቀለል ሲጋራ፣ ሲጋራዎች፣ የቱቦ ትምባሆ፣ ጋያና ሺሻ እንዲሁም ጭስ አልባ የሆነ ትምባሆ በማሽተትና በማኘክ ይጠቀማል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሰራው የአዋቂዎች ትምባሆ የመጠቀም ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አምስት በመቶ አዋቂዎች የትምባሆ ምርቶችን ይጠቀማሉ፡፡
የትምባሆ ዓይነቶችን በተመለከተ፣ 2.7 በመቶነ አዋቂዎች በፋብሪካ የተመረቱ ሲጋራዎች ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ 1.7 በመቶ ያህሉ ጭስ አልባ ትምባሆ ተቃሚዎች ናቸው፡፡
የትምባሆ አጠቃቀም ከዕድሜ አንጻር ሲታይ 2.4 በመቶ በመያዝ በዝቅተኛው እርከን የተቀመጡት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ 8.9 በመቶ በመያዝ ከፍተኛው የትምባሆ ጠተቃሚዎች ደግሞ ዕድሜያቸው ከ45 እስከ 64 የሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ናቸው፡፡
የትምባሆ አጠቃቀም በክልሎች ልዩነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር በምሥራቅ አካባቢ ያሉት አፋር፣ ሶማሌና ሐረሪ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ አዋቂዎች በብዛት ትምባሆ ይጠቀማሉ፡፡
በኢትዮጵያ የትምባሆ አጠቃቀም ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር በአንፃራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሄራን፣ ሆኖም ከሕዝቡ ቁጥር አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ሊባል እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡
ቶባኮ ኮንትሮል ዳታ ኢንሽየቲቭ እንደሚለውም፣ ከትንባሆ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በሳምንት 259 ወንዶችና 65 ሴቶች፣ በዓመት ደግሞ 16,800 ሰዎች ይሞታሉ፡፡
ትምባሆ ማጨስ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
ትምባሆ ማጨስ ከመገለል አንስቶ እስከ ከፍተኛ የጤና መታወክ ለሚያደርሱ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ የበሽታዎች መቆጣጠርና መከታተል ድርጅት (ሲዲሲ) ይገልጻል፡፡
እንደ ድርጅቱ፣ ማጨስ በተለይ የሴቶችን የመፀነስ ዕድል ይቀንሳል፡፡ ቢፀንሱ እንኳን ጊዜው ያልደረሰ ልጅ እንዲወልዱ፣ ፅንሱ እንዲጨናገፍ፣ ከክብደት በታች የሆኑ፣ የፊት ገጽታቸው ያልተስተካከለና በጨቅላነት ለድንገተኛ ሞት የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ የሆነ ልጅ ሊወልዱም ይችላሉ፡፡
የጥርስ፣ የምላስ፣ የከንፈር፣ የጣትና የቆዳ ቀለም ከመቀየር ባለፈም ትምባሆ የሚፈጥረው ጠረን ከሰዎች እንዲገለሉ ያደርጋል፡፡ ካንሰርን ጨምሮ የመተንፈሻ አካላት፣ ለልብና ለደም ትቦ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ ማጨስ በአንጀት፣ በኩላሊትና በሁሉም የአካል ክፍሎች ላይ ካንሰር ሊያስከትል እንደሚችልም የሲዲሲ መረጃ ያሳያል፡፡
አንድ ሰው የመጨረሻውን ካጨሰበት ከ20 ደቂቃ ጀምሮ እስከ 15 ዓመታት ባያጨስ ምን የጤና ጥቅም ያገኛል?
ትምባሆ የሚያጨሱ ሰዎች ለማቆም የሚቸገሩ መሆኑ ብዙ ጊዜ ይሰማል፡፡ በሠለጠኑ አገሮች ትምባሆ የሚያጨሱ ሰዎችን ከሱሳቸው ቀስ በቀስ እንዲወጡ ለማስቻል ሕክምናዎች ቢኖሩም፣ ይህ በኢትዮጵያ ብዙም አልተለመደም፡፡
በተለይ በድህነትና በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አጫሽ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ከአጫሽነት ለማውጣት ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳን፣ በቂ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት የሉም፡፡
ከትምባሆ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ በጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር፣ በማቴዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲና በሌሎች ተቋማት በተዘጋጁ መድረኮችም ከትምባሆ ሱስ ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች በቂ የሕክምና ድጋፍ የሚያገኙበት ዕድል አለመኖሩ በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ አንድ ሰው ሲጋራ ማጨስን ባቆመ ከመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች በኋላ የልብ ምትና የደም ግፊቱ ይቀንሳል፣ በ12 ሰዓታት ውስጥ በደም ውስጥ ያለው የካርቦን ሞኖክሳይድ (የተቃጠለ አየር) ወደ መደበኛው ይወርዳል፣ በሁለት ሳምንታት ውስጥ የደም ዝውውር ሲሻሻል የሳንባ ሥራውን የመሥራት አቅምም ይጨምራል፡፡
አንድ አጫሽ ጠንክሮ አንድ ወር ድረስ ባያጨስ ከማጨስ ጋር የሚያያዙት የአፍንጫ መጠቅጠቅ፣ የትንፋሽ ማጠርና የመተንፈሻ አካል ችግሮች ይቀንሳሉ፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ በተለይ የሴቶች የመፀነስ ዕድል የሚሰፋ ሲሆን፣ ጊዜው ያልደረሰ ልጅ የመውለድ ዕድልም ይጨምራል፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ የሳንባ ጥንካሬና የመሥራት አቅም በጣም ይሻሻላል፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ በልብ ሕመም የመጠቃት ዕድል እንደማያጨሱት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡
ከአሥር ዓመታት በኋላ በሳንባ ካንሰር የመያዝ ዕድል ከማያጨሱ ሰዎች ጋር ሲመጣጠን፣ ከ15 ዓመታት በኋላ ደግሞ በልብ ሕመም የመጠቃት ዕድል ምንም አጭሰው ከማያውቁ ሰዎች እኩል ይሆናል፡፡
ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የትምባሆ ቁጥጥር ድረ ገጽ
ይህ ቁጥጥርን የሚመለከቱ ሰባት ርዕሰ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፣ የትምባሆ ቁጥጥር ሕግ፣ የትምባሆ አጠቃቀም ሥርጭት፣ የትምባሆ ሕገ ወጥ ንግድ፣ የቁጥጥር ሕጎች አተገባበር፣ የትምባሆ ጉዳትና ተያያዥ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው፡፡