Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያሰቡበት መዋልና ማደር ሲያቅትስ!

ሰላም! ሰላም! ሰላም ለአገራችን፣ ሰላም ለአፍሪካችን፣ ሰላም ለዓለማችን ይሁን፡፡ ሰላም የሚነሱን የሰላም አምላክ ይቅር ይበላቸው እላለሁ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ‹‹አገሬ ብሎ ነገር ውኃ ሊበላው ነው አሉ…›› ብዬ ነገር ማማንዠክ ስጀምር፣ ‹‹ውኃ ምን አደረገህ? እን እንቶኔ ሊበሉት ነው አትልም?›› ያሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ደግሞ ብለን ብለን እሳቸውን የምሳሌያዊ አነጋገር ማስታወሻ እናድርጋቸው? ጉድ እኮ ነው እናንተ። መቼስ አገርን መውደድ፣ አገርን በሙሉ ሐሳብና ኃይል ማገልገልን የመሰለ ነገር ያለ አይመስለኝም። ግን ግርም የሚለኝ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አገር አጥሮ፣ አስሮ፣ አሳስሮና አደናግሮ አገሬን አገሬን ባይ ሐሳዊ ነፍሶች መኖራቸው ድንቅ ይለኛል። አንድ የእኔ ቢጤ ደላላ በአንድ ወቅት፣ ‹‹አቶ አንበርብር ሁሌ ኢትዮጵያ… ኢትዮጵያ ስትል እሰማሃለሁ፡፡ ነገር ግን ግራ ግብት የሚለኝ አፍህ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ልብህ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፡፡ አንተስ ይህንን አብራራ ብትባል ወኔው ኖረህ ልታብራራ የምትሞክር አይመስለኝም…›› ካለኝ ወዲህ፣ ራሴን በራሴ ኦዲት ለማድረግ ጥረት እያደረግኩ ነው። እውነቴን እኮ ነው። ምሁሩ የባሻዬ ልጅም፣ ‹‹ወዳጄ አንተ እኮ በየዋህነት ነው ራስህን የምታስጨንቀው፣ ሌላው ግን ባላየ ባልሰማ እያለፈ የልቡን ይሠራል….›› ብሎኝ አሳረፈኝ። አንዳንዴ እኮ ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው ሲባል፣ መርዛማዎች ቢኖሩም እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አይቀርም ነው ያልኩት!

በቀደም ዕለት ከአንድ ደንበኛዬ ጋር ቀጠሮ ስለነበረኝ ተገናኝተን ስናወራ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር እባክህ እስቲ ከጎረቤት አገሮች የት ሄጄ ኢንቨስት ባደርግ ትመክረኛለህ…›› ዓይነት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔ ደግሞ ያው እንደምታውቁት የአገሬ ነገር አይሆንልኝምና ተናድጄ፣ ‹‹ወንድሜ ምን ሆነህ ነው ኢትዮጵያን የመሰለች ቅድስት አገርህን ትተህ ጎረቤት አገር የሚያስኮበልልህ…›› በማለት አፈጠጥኩበት፡፡ ደንበኛዬ ግን የሚበገር አልሆነም፡፡ ‹‹ወዳጄ በአገር ተስፋ አይቆረጥም ተብዬ ያደግኩ ሰው ነኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ግን በቃኝ፡፡ በገዛ አገሬ እንደ ባይተዋር እየታየሁ ከመኖርና ከመሥራት ሁሉንም ነገር ጣል አድርጎ መውጣት ነው ያለብኝ፡፡ ልጆቼ ይህንን ሁሉ ትርምስ እያዩ ከሚሳቀቁና ከዛሬ ነገ ምን ልንሆን ነው ብለው ከሚደናገጡ ራቅ ብለው ቢማሩ የተሻለ መሆኑን አምኜያለሁ፡፡ እኔ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ በቅቶኛል…›› ብሎ ሲንገፈገፍ የበለጠ ደነገጥኩ፡፡ በዚህም በዚያም ብዬ ባለችኝ የደላላ ዕውቀት ተስፋ እንዳይቆርጥ ላስረዳው ብሞክርም፣ ‹‹ለምን ኤርትራ አይሆንም ሄጄ ዕድሌን እሞክራለሁ…›› ብሎ ከዚህ በላይ ማሳሰቢያ እንደማይፈልግ ሲነግረኝ፣ ተስፋ መቁረጥ ምን ያህል አደገኛ ነገር መሆኑን ተረዳሁ፡፡ የተስፋ ያለህ ያስብላል እኮ!

አንድ በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ለሠፈራችን ሕፃናት መዋያ ያከራየውን ግቢውን ወደ ስፖርት ቁማር ቤትነት ማሸጋገሩን በሩ ላይ የቆመው ጥበቃ ነገረኝ። መዋዕለ ሕፃናቱ ሲዘጋ ግን የነገረኝ አንድ ሰው የለም። ሕፃን አዋቂው ቁማርተኛ በሆነበት ጊዜ አንተስ ምንቆርጦህ የሰው ልጅ ታማለህ አትሉኝም? ከደላላነት የሚብስብኝ ነገር ዘልዛይነቴ መስሎኝ። ይኼም ኑሮ፣ ያም ኑሮ ተባለ አሉ። ልዩነቱ የእኔ የሥጋት፣ የዚያኛው የአምሮት መሆኑ መሰለኝ። ካላመናችሁ ላመሳክርላችሁ። እኔ ሠፈር የተዘጋው መዋለ ሕፃናት ነው። የተከፈተው ደግሞ ቁማር ቤት ነው። እንግዲህ የእናንተን ሠፈር አላውቅም። ግን ልገምት። ትናንትና መለስተኛ ክሊኒክ የነበረው ምናልባት ስጠረጥር ዛሬ ጫት ቤት ሆኗል። ወይም ደግሞ መለስተኛ መጻሕፍት አከፋፋይ የነበረ ከሆነም ዛሬ ወይ መጠጥ ቤት ነው ወይም ማሳጅ ቤት ሆኗል። ባይሆን እንኳ በዚህ አያያዛችን ከቀጠልን እመኑኝ ይሆናል። ‘ሳያዩ የሚያምኑ መልካም ዜጎች ናቸው’ እንዳልላችሁ፣ እኔም እንደ እናንተው በሚመጣ በሚሄደው ስም ያጠረው ነገር ተገዥ ነኝ። ታዲያ ሌላ ምን እላለሁ? ብቻ እንዲያው ሲገርመኝ ሰነበተ። ‹‹ኤድያ ያንተ ግርምት ነው እኔን ያስቸገረኝ…›› ይለኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ምን ያድርግ!

ነገሩ ከንክኖኝ፣‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ምን አገባኝ ብለህ ነው እንዲህ የምትብሰከሰከው? ሥልጣን የለህ፣ ድምፅ የለህ፣ ወይ ጉልበት የለህ። ምን ብትጠግብ ነው በዚህ የኑሮ ውድነት ላይ የትም ለፍተህ የምትቆርሰው እንጀራ አንጀትህ ሳይደርስ የምታበነው?›› ይለኛል። ቆይ ግን ልክ አይደለም ወይም ኧረ ይኼ ነገር ሲል አድማጭ ቢጠፋ ቢያንስ የመገረም መብቱን ይገፈፋል? ሌላው ሁሉ ቢቀር የተገራሚ ታዛቢ ለመሆን ሲባል ብቻ በሥጋ ተሟሽቶ፣ በቅጠል ተብላልቶ፣ በገብስ የሚታጠብ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤ ከተማችንን አገራችንን ማኖ ሲያስነካ ኧረ “ፋውል” ነው የሚል ይጥፋ? ለስሙ ግን ኳስ ስንተነትን አንደኛ ነን፣ ድንቄም አሉ፡፡ እሺ ግድ የለም። የዓይኑን ተውትና ወደ ጆሮ ልውሰዳችሁ። መቼም በስሚ ስሚ የነገር ሐረጋችንን አንጠራጠርም። ዓይቶ ማመንማ ዘበት ሆኗል። እስኪ ወደ ስልክ ጥሪ ልውሰዳችሁ። አንድ ደንበኛዬ ባሏ ያለ አመሉ መሸታ ቤት ለምዶ አንዷን ለመደና ከቤት እንደ ወጣ ቀረ።  ገና ሁለት ዓመት ያልሞላት ልጅ አለቻቸው። በቀደም ዕለት ስልኬ ሲጠራ ሳየው የእሷ ቁጥር ነው። ‹‹ምን ልትለኝ ነው?›› ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ ‹‹አንተ ደግሞ…›› ብላ ስልኩን አነሳችው። ከላውድ ስፒከሩ የምሰማው ድምፅ ጩኸት ነው። ‹‹ገደልኳት… ገደልኳት…›› እያለች እሪ። ኋላ አንድ የተረጋጋ ሰው ስልኳን ነጥቆ ሲነግረን፣ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ እያየች ዓይኗን ሳትነቅል፣ ለሕፃኗ በጡጦ ወተት ስታቀብላት ሕፃኗ ፀጥ። ምን ሆኖ መሰላችሁ? ወተቱን ከእነ ጡጦው ለብ አድርጋ ልትሰጥ የፈላ ውኃ ውስጥ ነክራው እሷ ቀልቧ ድራማው ላይ ነበር። ሙቀቱን ሳትገምት እንደ ወረደ ስታወርድላት ፍግም። ይኼውላችሁ እንግዲህ። ቴሌቪዥን ፍርድ ቤት የምንገትርበት ጊዜ ሊመጣብን ነው? ነው ወይስ ዓይን ሊከሰስ ነው? ያዩት ‘በእኛ ይብቃ’ ሲሉ ያላዩት እንዳልሰሙ ሆነው ሌሎች በሚቀሰፉባት ዓለም ያተረፍነው ተረትና ንግርት ብቻ ሆነ። ጆሮ ለባለቤቱ!

ሁሉ በደጃችን አልሆን እያለ ቢያስቸግረን የምናወራው ነገር መቼም አናጣ። እናላችሁ ብለን ብለን በ‘የምበላው አታሳጣኝ ፈንታ ‘የማወራው አታሳጣኝ’ የምንልበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም። ታዲያ ይኼ ምኑም አይገርምም፣ ምኑ ይገርማልና? በቃ መኖር ካቃተን መኖር ስለቻሉት ማውራቱ፣ ሌላው ቢቀር አኗኗሪነታችንን ሲያረጋግጥልን በዓይናችን በብረቱ ዓይተናል (አባባል ስለሆነ እንጂ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብረት ይሁን አይሁን፣ ደረቅ ይሁን እርጥብ የተረጋገጠ አይመስለኝም)፡፡ መብላት ሲያቅተን ወይ በግላጭ ወይ በድብቅ በልተው ስላደሩት ሆድ ባይሞላም ጨዋታ ሲደምቅ ታዝበናል። ‹‹እሱ የለመኑትን የማይነሳ የምንጎርሰው ስናጣ የምናወራው ነገር ይለቅብናል። መፍጠር አይታክተው እሱ…›› የሚለኝ አንድ የሠፈሬ ጫት ነጋዴ ነው። ለጫት ካለው የተለየ ፍቅር የተነሳ በማይቅሙ ሰዎች ይናደዳል። ‹‹ሰው እንዴት ኑሮን በምርቃና መፎረፍ ሲችል አበሳ ያያል?›› ይለኛል ባገኘኝ ቁጥር። እሱ ሕይወትን አታሎ ለማለፍ የሚፈልገው በምርቃና፣ እኔ ደግሞ ተግዳሮትን አሸንፌ ማለፍ የምፈልገው በመጋፈጥ ነው፡፡ ግና አፍና ልብ አልገጥም ብለውኝ ይኸው እወዛገባለሁ፡፡ ዘመነ ወዝጋባ!

ስለዚህ ያሉብኝን ማኅበራዊ ግዴታዎች እየሸዋወድኩ አንድ ቪላ ላከራይ ብዙ ዋተትኩ። የዋተትኩት ተከራይ አጥቶ ወይ ጠፍቶ እንዳይመስላችሁ። እኮ እንዴት ተብሎ? ይልቅ ወገኔ እንኳን ቪላ ኮንዶሚኒየም ቤትም ተከራይቶ መኖር እንዴት እንዳጎበጠው ስለማውቅ፣ ከሐበሻ ተከራይ ይልቅ የውጭ ዜጋ ልፈልግ ብዬ ነው። በለስ ቀንቶኝ አንድ ስደተኛ ሶሪያዊ አገኘሁ።  ቤቱን ልየው ብሎኝ ወስጄ ሳሳየው ታዲያ፣ ‹‹ጥሩ ነው፣ ይበቃ ይሆናል…›› ሳይል ዝም ብሎ በሌባ ጣቱ ሐሳባዊ መስመር እያሰመረ ይቆጥራል። ‹‹ቤቱ ሙሉውን ነው የሚከራየው በካሬ ሜትር አይደለም…›› አልኩት በአስተርጓሚ። እሱም፣ ‹‹አውቃለሁ መኝታ ክፍሎቹን ሳይጨምር ሳሎኑ ስንት ፍራሽ ይወጣዋል የሚለውን እየቆጠርኩ ነው…›› አለኝ። ‹‹የምን ፍራሽ?›› ብዬ ልጠይቅ ብፈልግም ተውኩት። ችግሩ ገባኝ፡፡ ሶሪያዊው ቆጥሮ ሲጨርስ የሸሪኮቹን ብዛት ለማወቅ፣ ‹‹ስንት?›› አልኩት። ‹‹ሳታጠጋጋው ሰላሳ…›› አይለኝ መሰላችሁ? ነገሩ አስገርሞኝ አፍጥጬ ሳየው፣ ‹‹ወዳጄ ቤት የእግዚአብሔር ነው፣ አገር አለኝ ብለህ ድንገት ሳታስበው ራስህን ሜዳ ላይ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ከእኛ ከሶሪያውያን ተማሩ፣ ካልተማራችሁ ልክ እንደ እኔ አንተም ጎረቤት አገር ለሰላሳና ለሃምሳ ሰዎች ማደሪያ መፈለግህ አይቀርም፡፡ እሱም ፈጣሪ ረድቶህ ሕይወትህ ከተረፈ ነው…›› እያለ በተኮላተፈ አማርኛ ሲነግረኝ ደነገጥኩ፡፡ በጣም ያስደነግጣል!

እንዲያው በነገራችን ላይ አንድ ጉዳይ ላስታውሳችሁ መሰል፡፡ አንዳንዱን ነገር በራሳችን ዓውድ ውስጥ ሆነን ስንመለከተው ጉዳዩ ይገባናል፡፡ ከዓውዱ ውጭ ስናየው ደግሞ ግራ እንደተጋባን ኖረን እናልፋለን፡፡ ለማንኛውም ይህንን ዓለም የሰማውን ጉድ እስቲ እናንተም ስሙት፡፡ የቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በደረሰ ሰሞን የሰማውን አስገራሚ ዜና የነገረኝ ምሁሩ ወዳጄ ቢሆንም፣ እኔ ደግሞ እንዲህ አድርጌ ልንገራችሁ፡፡ ሰውዬው አደጋው ከመድረሱ 48 ሰዓት በፊት ቤት አከራዩ ኪራይ ክፍያ አዘገየህ ብሎ ከቤቱ ያስወጣዋል፡፡ አደጋው ደርሶ በሕይወት የተረፉት ጊዜያዊ መጠለያ በድንኳን ተዘጋጅቶላቸው እንዲያርፉ ይደረጋሉ፡፡ ይህንን አጋጣሚ ሰውዬው ሲተርከው፣ ‹‹እኔም ከምኖርበት ቤት ተባርሬ ሕይወቴ ተርፎ፣ አባራሪዬም ቤቱ በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ወደ ፍርስራሽነት ተለውጦ መጠለያ ውስጥ ተገናኘን፡፡ አሁን ያ ሁሉ አልፎ አብረን ከሰል እየሞቅን ነው…›› ነበር ያለው፡፡ አባራሪና ተባራሪ ሆነን በማንዘልቅበት ምድር ላይ አንዳችን ሌላችንን እየጠላንና እየተራገምን መጨረሻችን ምን ይሆን የሚለው ይጨንቀኛል፡፡ በጣም እንጂ!

በሉ እንሰነባበት። ተፍ ተፍ ብዬ ያጋለኝን ትዝብትና የፀሐይ ንዳድ በንፋስ ሽውታ፣ ደግሞም መቋጫ ያልተገኘለት የነገር ምኅዳራችን ባንቦረቀቀው ስሜት ውስጥ ሆኜ የመረጥኩትን አዝዤ ውስጤን ባላበው ቢራ ላበርድ ግሮሰሪ ስደርስ፣ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ተገናኘን። ቢራችንን አዘን ወግ መጠረቅ ስንጀምር የባሻዬ ልጅ ንግግር ጀመረ፡፡ ‹‹ሰሞኑን ስብሰባ የሚጠሩኝ በዝተዋል። ድግስ እጠራለሁ ሄጄ እበላለሁ እጠጣለሁ፣ የታመመ ጠይቅ ይሉኛል እሄዳለሁ ለሞልቃቃው ሕመምተኛ የመጣው ድግስ ቀረሽ ምግብ አይቀረኝም። ብዙኃኑ ይለፋሉ ጥቂቶች እንዳለ ይዘርፉታል፡፡ ወደ ጭቁኖቹ ሠፈር ዞር ስል ደግሞ የአካባቢውን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራና እዚያም እሄዳለሁ። ድንቅ የሚለኝ ቆሻሻ ለማስወገድ ስንሰበሰብ ቆሻሻ አራግፈን መሆን እንዳለበት የሚናገር ዓይቼ አለማወቄ ነው። ምነው? ቆሻሻ እኮ ብዙ ዓይነት ነው። ሐሳብም እኮ ቆሽሾ ይሰነፍጣል፡፡ ካላመናችሁኝ ቆሽሸው ዓለምን ያቆሸሹ ሰዎችን ታሪክ አንብቡ። በአቋራጭ የመክበር፣ በአቋራጭ የመደለብና በአቋራጭ የመንገሥ የዘመኑ አካሄድ ስንቱን ጤናማ ተፈጥሯዊ በረከት አበላሸው መሰለህ? ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ ዕብሪትና ትዕቢት የተጋመዱበት ጥፋት ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፍራ…›› እያለ ሲያስፈራራኝ አመሸሁ። እንደ አገርም እንደ ግለሰብም ምነው ባሰብንበት መዋልና ማደር አቃተን አያሰኝም? መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት