Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእናቶችና ልጆቻቸውን ከጎዳና ሕይወት የመታደጉ መንገድ

እናቶችና ልጆቻቸውን ከጎዳና ሕይወት የመታደጉ መንገድ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በሚፈጠሩ ጦርነትና ግጭቶች የተነሳ በአብዛኛው እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ሊወጡ ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ባለመስማማት የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑም አልጠፉም፡፡ ይህም ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ልጆቻቸውን ይዘው አላፊ አግዳሚውን ምፅዋት የሚጠይቁ እናቶች ቁጥር በርክቷል፡፡

ጎዳና ወጥተው ምፅዋት ከሚጠይቁት መካከል ወ/ሮ ጀሚላ ሙራድ ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ጀሚላ አንድ ልጃቸውን ይዘው ጎዳና ላይ ከወጡ ሁለት ዓመት አስቆጥረዋል፡፡  ልጃቸውን ለማሳደግ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማየታቸውን የሚናገሩት እኚህ እናት፣ ባለቤታቸው የአምስት ወር ነፍሰ ጡር እያሉ ትቷቸው በመሄዱ ምነው እንዲወጡ ያደረጋቸው፡፡

የሰውን እጅ ማየት በጣም ከባድ እንደሆነ፣ በተለይም ልጅ ለያዘ የማይመከር መሆኑን የገለጹት እናት፣ ከዚህ በፊት ከባለቤታቸው ጋር ቤት ተከራይተው የተሻለ ኑሮ ይኖሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ባለቤታቸው በአንድ አጋጣሚ ጥሏቸው በመጥፋቱ ነው ልጃቸውን ይዘው ጎዳና መውጣትን አማራጭ ያደረጉት፡፡

ወደ ጎዳና ሲወጡ ምንም ዓይነት ጥሪት እንዳልያዙ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት በመጨመሩ የተነሳ ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

ሁለት ዓመታት ያህል ከልጃቸው ጋር በጎዳና ሲኖሩ የቅርብ ዘመድም ሆነ የሚመለከተው አካል ከጎዳና የሚነሱበትን ነገር መፍትሔ ባያበጅላቸውም፣ በአንድ አጋጣሚ ግን የአይኬር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ከጎዳና ሕይወት እንደታደጋቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ዘይት፣ ጤፍ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ ፓስታና ሌሎች መሰል ነገሮችን ከመደገፍ ባለፈ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጣቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በላይ ልጃቸውን ድርጅት ውስጥ በማስቀመጥ አሁን ላይ የተለያየ ሥራ እንደሚሠሩና ከጎዳና ሕይወትም ሊወጡ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባም በርካታ እናቶች ልጃቸውን ይዘው ጎዳና ላይ መውደቃቸውን፣ መንግሥት ለእነዚህ እናቶች መፍትሔ በመስጠት ከጎዳና የሚነሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚህ ነገር ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ዘሐራ ከባለቤታቸው ሦስት ልጆችን በማፍራት የተሻለ ኑሮ ይኖሩ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚም ባለቤታቸው እኩለ ሌሊት ላይ ሦስቱንም ልጆቻቸውን ጥሎባቸው እንደሄደ የሚናገሩት እኚህ እናት፣ ለልጆቻቸው የሚያበሉት ምግብ ስለሌለ ጎዳናን አማራጭ ማድረጋቸውን ያወሳሉ፡፡

በጎዳና ያገኙትን አላፊና አግዳሚውን ምፅዋት ጠይቀው በሚያገኙት ገንዘብ የልጆቻቸውን የዕለት ተዕለት ጉርስ ከመሙላት ባለፈ ትንሽ የምትባል ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ለምነው የሚያገኙት ምፅዋት በሕይወታቸው ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳላመጣላቸውና ልጆቻቸውንም ትምህርት ቤት ለማስገባት መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የሰው እጅ አይቶ ልጅ ማሳደግ በጣም ከባድ እንደሆነ፣ ባለቤታቸውም ትቷቸው ከሄደ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ነገር ውስጥ ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተለይ ሦስት ልጆችን ይዞ ጎዳና ላይ መውጣት ይከብዳል የሚሉት እኚህ እናት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ አማካይነት ወደ አይኬር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት መላካቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ድርጅቱም ከገቡ በኋላ የተለያዩ ድጋፎችን እያገኙ መሆኑን፣ ለትምህርት የደረሱትን ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡ ድርጅቱም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጣቸው እንደሆነ፣ ለልጆቻቸውም ሆነ ለእሳቸው በቂ የሚባል ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛው ሰው ወደ ጎዳና የሚወጣው የሚላስ የሚቀመስ በማጣቱ ምክንያት ነው የሚሉት እኚህ እናት፣ መንግሥት ይህንንም ችግር ታሳቢ በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የአይኬር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሕረተአብ አባተ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ልጅ ይዘው ጎዳና ላይ የሚለምኑ እናቶችን ለመታደግ ድርጅቱ እየሠራ ነው፡፡   

በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናውን ሙጥኝ ብለው ላይ ወጥተው ለሚለምኑ እናቶች ትኩረት አለመሰጠቱን፣ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ገንዘብ ወይም የዕለት ጉርስ ከመስጠት ውጪ ወጥ የሆነ ድጋፍ ሲያደርግ አለመታየቱ፣ የችግሩን መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከየካ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር ስምምነት በመፍጠር 15 እናቶችን ከእነ ልጆቻቸው ከጎዳና በማንሳት ሥራ መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከ64 በላይ እናቶችና 68 ልጆች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን፣ ይህንን ተፈጻሚ ሲያደርግ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር የሚሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱም ለእናቶች የተለያዩ ሥልጠናዎች፣ እንዲሁም የወር አስቤዛዎችን ተደራሽ እያደረገ ሲሆን፣ ለሕፃናቱ ደግሞ ልብስ፣ ጫማና የሕክምና አገልግሎት፣ እንዲሁም የዕለት ከዕለት ምገባ በማከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከጎዳና የተነሱ እናቶችን ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ራሳቸው እንዲችሉ በማድረግ ላይ መሆኑን፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወርም 25 እናቶች ሥልጠናውን ወስደው የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይም የመንግሥት ተቋማት ድጋፍ ማነስ፣ የኑሮ ውድነት፣ የቦታ ችግር ድርጅቱን እንደፈተነው የተናገሩት አቶ ምሕረተአብ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡  

በቀጣይ በክልሎች ተደራሽ ለመሆን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...