Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቃል ከተገባለት ከ130 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ቢያንስ...

ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቃል ከተገባለት ከ130 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ቢያንስ አብዛኛው እንዲሰጠው ጠየቀ

ቀን:

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚያካሂደው መሠረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃል ከገባለት 130 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ አብዛኛው እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ በአስተዳደሩ ቃል የተገባለት ቦታ በአሁኑ ወቅት ለሌሎች አገልግሎት እንደሚውል መታሰቡንም ኮሌጁ ገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል ‹‹ጥቁር አንበሳ ለሀገር ከታሪክ እስከ ብሩህ ተስፋ!›› በሚል መሪ ቃል የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከበረበት ሥነ ሥርዓት የኮሌጁና የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ደነቀ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ቦታው ለሆስፒታሉ ካለው ቅርበትና ሆስፒታሉም ከሚሰጠው የጤና አገልግሎት፣ ከሕሙማን ብዛት፣ ከሚያስተምረው የተማሪዎች ቁጥር አንጻር አሁንም ቦታው ለኮሌጁ ይገባዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

‹‹በቅርቡም አዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በመተባበር ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ለውይይት ይቀርባል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይባልም አብዛኛው ቦታ ለኮሌጁ  ይፈቀዳል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባባል፣ በቅርቡ በሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ ‹‹ራስ ገዝ አመራርም›› ኮሌጁና ሆስፒታሉ የራሳቸውን ሪፎርም በማድረግና በማዘጋጀት ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የራስ ገዝ የሪፎርም ቡድን አቋቁመዋል፡፡

የገቢ ማስገኛ መስኮችን በመለየትና መመርያዎችን በመቅረጽ ላይ እንደሚገኝ፣ አንዳንዶቹ መስኮችም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ፣ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ፋርማሲ እንደተከፈተ፣ በቅርብ ወራትም የማኅበረሰብ አቀፍ ላብራቶሪ አገልግሎት፣ በቀጣይም የክሊኒካል ሰርቪስ የመሳሰሉትን በግል የአገልግሎት ዘርፍ እንደሚጀምርም አመልክተዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዓመት ከ500 ሺህ በላይ ተመላላሽና ከ25 ሺህ በላይ ተኝቶ ታካሚዎችን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ አመራርም ኮሌጁና ሆስፒታሉ ራሳቸውን ሪፎርም በማድረግና በማዘጋጀት ወደተሻለ እንቅስቃሴ በመግባት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ኮሌጁ አሁንም ተመራጭና የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ለማራመድ እንደ ቀድሞው ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዩኒቨርሲቲው አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ በኅብረተሰብ ዘንድ ተመራጭ ሊሆን የቻለው በአገሪቱ ታዋቂና ስመ ጥር የሆኑ ስፔሻሊስቶችና ሰብ ስፔሻሊስቶች ስለሚገኙበት መሆኑን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲውም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሀብቱን ለኮሌጁ እንዲውል ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የመሆን ጥያቄ ያቀረበው በደርግ ሥርዓት ነበር፣ ሲመሠረትም በቻርተር ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ነው፡፡ ያ ጥያቄ ዕውን ሆኖና አሁን መንግሥት ፈቃደኛ ሆኖ ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሷል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ አኳያ የሚያገኘውን ራስ ገዝነት ይዞ ወደ ኮሌጆች፣ ወደ ትምህርት ክፍሎችና እስከ ፕሮፌሰር ደረጃ ድረስ ማውረድ እንዳለበት፣ የሚሰጠውን የመማርና ማስተማር፣ እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብን አገልግሎት የላቀ ማድረግ የሚቻለው በዚህ መንፈስ ሲኬድ ብቻ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አሁን ዘመኑ እንደተቀየረ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም እየተከተለ ያለው አቅጣጫ በጥሩ መንገድ ላይ እንዳለ፣ በዚህ አቅጣጫ መሠረት ተማሪዎችን በፍላጎት መቀበል እንደተጀመረና የትምህርት ክፍሎችም ራሳቸውን ለተማሪ አገልግሎት ዘመናዊ እንደሚያደርጉ ነው ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ምሕረት ደበበ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቻርተር ቢቋቋምም በመሀል ነጻነቱን አጥቶ እንደከረመና አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞው ቦታው የሚመለስበት ታሪካዊ ጉዞ ላይ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላለፉት ግማሽ ምዕት ዓመትን ለተሻገረ ጊዜ ለመላው ኢትዮጵያውያን የሕክምና አገልግሎት በመስጠት፣ በመማር ማስተማርና በምርምር መስኮች የሚያስመሰግን ሥራ ሠርቷል ያሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ ሆስፒታሉ ያሉበትን የቦታ፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይል ችግር በመቅረፍ የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሄዱ ዜጎችን በአገር ውስጥ ሕክምና ማግኘት እንዲችሉ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሆኖ እንዲተዳደር እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን የተለየ ተፈጥሮ ግምት ውስጥ በማስገባት ራስ ገዝ ሆኖ ይቋቋማልም ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸው፣ ከጠቀሜታዎቹም መካከልም ሥርዓተ ትምህርታቸውን የመቅረፅ፣ የምርምር ፖሊሲ የማውጣት፣ የተማሪዎች መቀበያ መስፈርት የመወሰን፣ እንዲሁም በጀታቸውን የመወሰንና የማስፈጸም መብት ያገኙበታል ብለዋል፡፡

‹‹ጥቁር አንበሳ ለሀገር! ከታሪክ እስከ ብሩህ ተስፋ!›› በሚል መሪ ቃል በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ በእንግዶች የተጎበኘ ሲሆን፣ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጣቸው አምስት የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰሮች ከዕለቱ የክብር እንግዳ  ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ ከተሸላሚዎቹም ፕሮፌሰሮች መካከል ሦስቱ ሴቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...