በኢትዮጵያ አንድም ከአገሪቱ የፖለቲካ ሥሪት በሌላ በኩል ደግሞ ከቆየ የታሪክ ቁርሾና ትርክት በመነጨ ችግር የአገረ መንግሥት ግንባታው አጠያያቂና አድካሚ እየሆነ ከዛሬ ነገ ይሻላል ቢባልም፣ ከተስፋ ያለፈ አስታራቂ የሆነ ሒደት ላይ መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህም እምብዛም መፍትሔ በራቀው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምና ዕርቅን ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ለተጎጂዎች ተገቢውን መፍትሔ ለመስጠት የሚሆን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማውጣት ሒደት ተጀምሯል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር ይፋ በተደረገው የፖሊሲ ግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነድ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ቁርሾዎችን አግባብነት ባለው ሁለንተናዊ፣ አሳታፊና በተቀናጀ መንገድ፣ ሳይፈቱ ሲንከባለሉ የመጡ የሚባሉ በደሎችና ቁርሾዎች እንዲጠገኑና ወደ ተሻለ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ካስፈለገ፣ የሽግግር ፍትሕ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የሚረዳውን ፖሊሲ ለማደራጀትና ለማዘጋጀት የሚረዱ የመነሻ የጥናት ሰነዶች ከሕገ መንግሥቱ፣ አገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና አገራዊ ልምዶች በማካተት በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል በተዋቀረ አንድ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች ቡድን ተዘጋጅተው ይፋ ተደርገዋል፡፡
በመጪዎቹ 13 ሳምንታት በፖሊሲ ሰነዱ ላይ በተመረጡ 59 የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን ያሳተፈ ውይይት በማካሄድ ፖሊሲው እንዴት ይዘጋጅና እንዴት ይተግበር ተብሎ ውይይት ተደርጎበት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በሚቀጥለው 2016 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተዘጋጀው የግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነድ ላይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ተመሳሳይ የዓላማ አንድነትና አረዳድ ለመፍጠር ያለመ የምክክር ማስጀመሪያ መድረክ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተከናወኑ ኢፍትሐዊ የሆኑና በቁርሾ የተሞሉ ታሪኮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት፣ አዲሲቱን ኢትዮጵያ በአዲስና በተሻለ እሴት ለመገንባት ያሰበ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በውይይቱ ወቅት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ ይህ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እውነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ፍትሕንና ይቅር መባባልን መዳረሻው ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፖሊሲ ግብዓት ለመሰብሰብ በተዘጋጀውና የአማራጭ አቅጣጫዎችን የያዘው ይህ የሽግግር ፖለሲ ሰነድ፣ የሽግግር ፍትሕ ሒደት ከየትኛው ጊዜ ይጀምር የሚል የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን የያዘ ነው፡፡ ሒደቱ የሚሸፍናቸውን የጊዜ መነሻና መድረሻ ስለመወሰንም ያብራራል፡፡ በዚህም ሒደቱ ‹‹ከ1983 ዓ.ም. በፊት፣ ወይም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ወይም ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ያለው፣ ወይም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ይሁን›› የሚሉ የተለያዩ አማራጮችን ከፋፍሎ አስቀምጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚነሱት የታሪክ ቁርሾዎች ወደ ኋላ በርካታ ዓመታትን ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በቅርቡ ከተከሰተው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ የግብዓት መሰብሰቢያ ሰነድ ውስጥ ዜጎች ሒደቱ ከየት ይጀመር የሚለውንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡
ታዲያ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተካሄደው ውይይት አስተያየት የሰጡት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የተሻለ ዛሬንና ነገን ለማየት አዲስ ምዕራፍ በሚጀመርበት ጊዜ ውይይቱ ዜጎችን ሊያቀራርብ እንጂ የባሰ ሊያራርቅ የሚችል እንዳይሆን አካሄዱ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
ወደ ውይይት ሲገባ በፖሊሲው የተመላከቱ ጉዳዮች ተፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡ በግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነዱ በቀረቡ አማራጮች ውስጥ፣ ‹‹ጉልህ›› የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በፈጸሙ አካላት ላይ ክስ እንደሚመሠረትና የችግሩ ዋነኛ ጠንሳሽ የሆኑትን እንመልከት የሚል አማራጭ ሐሳብ መቅረቡ አሻሚ የሆነና ለትግበራ አመቺ ያልሆነ አሠራር ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡
‹‹ጉልህ›› የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚለውን ጉዳይ ትርጉም ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን በማብራራት፣ በዚህ ሒደት ይኼኛው ጉልህ ያኛው ቀላል ነው ብሎ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ ወቅታዊ አስፈላጊና ለአገሪቱ የተሻለ ተስፋ ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሽግግር ፍትሕ ውስጥ ሊታዩ ከታቀዱት ጉዳዮች መካከል አንዳንዱ ታሪካዊ ኢፍትሐዊነት ላይ በዳይም ተበዳይ በሕይወት የማይኖርበት፣ የትርክት አለመጣጣም የሚታይበትና ማኅበረሰብን ከፋፋይ የሆነ ትርክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከቀደሙት ነገሥታት ጀምሮ ያለው ሁኔታ እገሌ እንደዚህ አድርጓል፣ ይህ ማኅበረሰብ ተበድሏል፣ ያኛው አልተበደለም የሚለው ታሪክ ከሞላ ጎደል ከፋፋይና የማኅበረሰብ ምሬት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን በመግለጽ፣ ይኼኛው ጉዳይ በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ቢታይ የተሻለ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚያያቸው ጉዳዮች በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው መታየት ካለባቸው ጉዳዮች በጥልቀትም፣ በይዘትም የሚለያዩ በመሆናቸው የጊዜ መነሻቸው በግልጽ መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራው ተጎጂዎች ከነበሩበት ቁስል ወጥተው፣ አገርም ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንድትል መሆኑን በመጥቀስ፣ የሽግግር ፖሊሲ ትግበራው ጊዜ መነሻ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ካልሆነ ጉዳዩ ሰፊና ከፍተኛ የሆነ ሀብት የሚጠይቅ እንዳይሆን ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ቆየት ያሉና ለአገራዊ ግንባታው የሚጠቅሙ ሒደቶችን በብሔራዊ ምክክር፣ አሁናዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ክስተቶች ደግሞ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ቢታዩ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ምሕረትን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ በሽግግር ፖሊሲው በተቀመጠው መሠረት አንድ ግለሰብ ወንጀል ፈጽሞና አምኖ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሳይታይ ሊሰጥ የሚችል ምሕረት ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ የምሕረት አሰጣጥ የተበዳዩን ቁስል ሊያክም ሳይሆን የፖለቲካ ምሕረት ይሆናል ብለዋል፡፡ ይህም ዓይነቱ የምረት አሰጣጥ ለወደፊቱ ያልተገባ አካሄድ ከማሳየቱ ባሻገር እንቢተኝነትን ያስፋፋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንትና የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስኪያጅ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ይህንን ትልቅ የሆነና አገሪቱ ልትወጣ የማትችለው ዓይነት ተግባር ይቻላል በማለት እንዲያው ቀለል አድርጋችሁ በማቅረባችሁ በጣም ገምቼያችኋለሁ፤›› በማለት፣ ኢትዮጵያን አረጋግቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማካይነት ይቻላል መባሉ፣ እንደገና የማትወጣበት ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከታት ይችላል ብለዋል፡፡
ለዚህ ሥጋት እንደ ምክንያት ያቀረቡት፣ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ዓውዱ የሰፋ መሆኑን ነው፡፡ የሺዎች ዓመታት ታሪክ አላት የምትባል አገርን ወደኋላ በመሄድ የነበሩት ቅሬታወች ታሪካዊ ቁርሾዎች አንስቶ መነጋገር ይቻላል፣ መስማማት ይቻላል የሚል ሐሳብ በጣም አስፈሪ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ግዙፍ አጀንዳዎች ያሉባት አገር ይዞ በ59 ውይይት ብቻ አይደለም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መድረኮች ቢዘጋጁ ለመግባባት ከባድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሒደቱን ዓውዶች በማናበብ በቅርብ ጊዜ የነበሩ ክስተቶች ላይ ቢተኮር የተሻለ መሆኑን የተናገሩት በየነ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ያለበለዚያ እንዲያው ኳስ አበደች ነው፣ ይህችን አገር የማይሆን ነገር ውስጥ ከተን መሰብሰብ ያቅተናል፡፡ ስለዚህ እኔ ይህንን ሳልናገር ብሔድ ከህሊናዬ ጋር መኖር ስለማልችል እንዲያው ልተንፍስ ብዬ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ሁልጊዜ እንደሚደረገው የልሂቃን ውይይት ሳይሆን፣ ከምሁራን ውይይት ወጥቶ ወደ ሕዝቡ መውረድ ካልቻለ ሒደቱ ተንሳፎ እንደሚቀርና ለስሙ ጉዳዩ ተነስቶ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስቦ ምግብ በልቶ መለያየት ይሆናል ያሉት ደግሞ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
‹‹ትርክቶቹ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሁሉ መቋጫ የሚሆን ያለፈውን ሁሉ በይቅርታ እንለፈው የሚል ዓውድ መፈጠር አለበት እንጂ፣ ከዚህ በፊት ስንቱ ጉድ ተደርጓል፤›› ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ‹‹ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሕጎችና አካሄዶችን መዘየድ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ መንገዱ ውስብስብ ቢሆንም ተቸክለን መቀጠል የለብንም፣ ከችካሉ መውጣትና ቋሚ መፍትሔ ቀይሶ በመፍትሔው ላይ መረባረብ ላይ ይጠይቃል፤›› ሲሉም አክለው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወይም ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ወይም ደግሞ ለውጡ ከመጣበት በሚል ከመሀል ቆርጦ በተወሰነ ደረጃ ብቻ መፍትሔ ለመስጠት መሞከሩ፣ ትክክል አለመሆኑንና አሁን በኢትዮጵያ እንደሚታየው ሁሉም ነገር አከራካሪና አነጋጋሪ በሆነበት ልክ የቅርቡን ብቻ መርጦ መፍትሔ ለመውሰድ መሞከር በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም መልካም የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥያቄ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በሰፊው በማየትና በመዳሰስ መፍትሔ በሚሰጥ መንገድ፣ ሕዝብን በሰፊው በማሳተፍ ካለፈው በመማር በቀጣዩ ላይ በማተኮር የወደፊቱን ማጠንጠን ይሻላል ብለዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕፎፌሰር) በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያነሱት የነበረን ሐሳብ በማውሳት፣ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክርና የዕርቅ ኮሚሽን ቢባል ኖሮ ሁለቱንም ሥራዎች አጠናክሮ መሄድ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በየቀኑ ኮሚሽኖችን ከምናቋቁም የአገራዊ ምክክር ማቋቋሚያ አዋጅን እንደገና በማየት እንደ አዲስ ሁለቱን በአንድ ማቋቋም ይሻላል የሚል ሐሳብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርቦ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
‹‹አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወደ ኅብረተሰቡ ለውይይት እየገባሁ ነው በሚልበት ጊዜ፣ የሽግግር ፍትሕ ትግበራውም በዚያው ወደ ሕዝቡ መግባቱ ይህ አካሄድ ኮሚሽኑ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮት ይፈጥርብን ይሆን የሚል የራሴ የሆነ ሥጋት ፈጥሮብኛል፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በመሆኑም ‹‹ወደፊት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አዘጋጆች ከኮሚሽኑ ጋር በመሆን ምክክር በማድረግ ለይተን መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ሰነድ ላይ የቀረቡት የመፍትሔ አማራጮች በጣም የተለጠጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ይህንን አባባላቸውን ሲያብራሩ፣ ‹‹በሰነዱ እንደተቀመጠው ተጠያቂነት መስፈን አለበት፣ ይቅርታ መደረግ አለበት የሚሉ ጉዳዮች ተካተዋል፤›› በማለት በተለይም ከ1950ዎቹ ጀምሮ ወደኋላ ይጀመር ሲባል ግን ማን ጠያቂ ተጠያቂ ማን ሊሆን ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹የሚጠየቀው አካል በሕይወትስ አለ ወይ? በመሆኑም ይህንን ጉዳይ ታሪክ እንድናውቅና አንብበን እንድንረዳ ካልሆነ በስተቀር አባት ባጠፋው ልጅ መጠየቅ አለበትስ ወይ? ወደኋላ ስንመለስ የነበሩ ነገሥታቶችና መሪዎችን ጭምር ለመጠየቅ የቀረበው ይህ ሰነድ እነሱን የሚያካትት አይደለም፡፡ እንዴት ነው ታዲያ መጠያየቅ የሚመጣው፤›› ሲሉ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
ቀደም በነበሩ መንግሥታት የተፈጸሙ ግፎችስ ብለው፣ የአሁኑ መንግሥት በቀደሙ መንግሥታት ድርጊቶች ሊጠየቅ ይችላል ወይ የሚለው ሁኔታ በደንብ ግልጽ ሆኖ መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡ በመሆኑም አካሄዱ የተረሳን ቁስል መቀስቀስ ሊሆን እንደሚችልና በሰላም አብሮ እየኖረ ያለውን ማኅበረሰብ ማራራቅ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ እየኖረ ያለውን ማኅበረሰብ እንደገና ወደ ማፋታትና ወደ ማለያየት ነው የሚኬደው ያሉት የድሬዳዋ ከንቲባ፣ ሥራው በትክክል ይከናወን ከተባለ መደረግ ያለበት የጊዜ ገደቡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን እንዴት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ልናይ ይገባል የሚለውን ቢሆን ይሻላል ብለዋል፡፡
በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ የሚፈጠር የጥንቃቄ ጉድለት የተኛውን መቀስቀስ እንደሚሆን፣ በተለይም ደግሞ ለካ እኔም ተበድዬያለሁ የሚል ቅሬታ ፈጥሮ ከይቅርታ ይልቅ መበጣበጥን ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹አሁን መጠያየቅ ይምጣ፣ እንጠይቅ ካልን ያለፉት ነገሥታት ላጠፉት ጥፋት በሕይወት በሌሉበት ልንጠይቃቸው ነው ወይ? እንዴትስ ሊጠየቁ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም በቀደሙት ጊዜያት የነበረው ትውልድ በሕይወት የለም፡፡ ስለዚህ መጠየቅ የማንችለው ጉዳይ ላይ ለጥያቄ ጠረጴዛ ላይ መቅረብ በራሱ ስህተት ነው፤›› አክለዋል፡፡
‹‹በዚህ መድረክና በከተማ ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ሊያገናዝብ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ወዴት ሊሄድ እንደሚችል በማመዛዘን አስቀምጦ መናገር ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ከማይችለው አንዳንዱ ያልተማረ፣ ሌላው ደግሞ መበደሉን የማያውቅ፣ ቂም ያልያዘ ማኅበረሰብ ላይ አዲስ ነገር አውርደን የመድረክ ላይ ጦርነት መፍጠርና በሰላም የሚኖሩ ዜጎች እንዲቀያየሙና እንዲኮራረፉ ከማድረግ በስተቀር መፍትሔው ሩቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት በበኩላቸው፣ በሰነዱ እንደ አማራጭ ከቀረቡት አንዱ የተጠያቂነት አሠራር ውስጥ የልዩ ፍርድ ቤት መቋቋም የሚለው ነጥብ በጥንቃቄ እንዲታይ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ካነሷቸው ችግሮች ውስጥ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ልዩ ፍርድ ቤት ይቋቋም መባሉን ጠቅሰው፣ ይህ አማራጭ ሕገ መንግሥቱን ተርጉሞ ልዩ ፍርድ ቤት ለማቋቋም አሁን ባለው ሁኔታ የሚያስኬድ አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹በሌላ በኩል አንድ ችግር ለመፍታት ተብሎ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር እሠጋለሁ፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም ከተጀመረ መጨረሻው የት ይሆናል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ከመድረክ ለተነሱት ሐሳቦች ማብራሪያ የሰጡት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር)፣ የታሰበው ትልቅ ሥራ በመሆኑና የሰላም ግንባታ ከግድብ ግንባታ የበለጠ ውድ ፕሮጀክት መሆኑን፣ ነገር ግን ግድቡን ሊያፈርሱና የተገነባውንም ሊያወድሙ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳይደገሙ ለማድረግ የሚችሉ የዋስትና የእርምት ዕርምጃዎች የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ጉዳዮች አማራጭ የላቸውም፣ ያለፈውን ጉዳይ መዳሰስና ማየት አማራጭ አይደለም ግዴታም ነው ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታም ይህንን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ አስፈላጊነት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት የነበሩን በርካታ ችግሮችና ውጣ ውረዶች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ አነሳሱ አገራዊ በመሆኑ ሰፋ ተደርጎ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡