Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል አራት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

አንተማ የመጣህበትን ብላ”

ሰውዬው የጤፍ ነዶውን ወደ ውድማ በአህያ እየጫነ ለመውሰድ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል አራት ወይም አምስት አህያዎች፣ በአህያዎቹ ቁጥር ልክ የሆነ መጫኛ (ከከብት ቆዳ የተሠራ ገመድ) እና የሚያጫጭን አንድ ወይ ሁለት ሰው፡፡

በዚሁ መሠረት ወደ አንድ ቤት ጎራ ይላል መጫኛ ሊዋስ፡፡ ለሰላምታው ምላሽ ከሰጡት በኋላ፣ “ግባ፣ ግባ!” ሲሉት፣ ትንሽ እንኳን ሳያመነታ፣ ወደ ቤት ዘው ብሎ ገባ፡፡

“ና ቁጭ በል፣ እንብላ፡፡”

“እንብላ” የሚለው ቃል፣ ገና ከአባዋርዬው አፍ ወጥቶ ሳያበቃ ከማዕዱ አጠገብ ቁጭ አለና አብሮ መብላት ያዘ… ከንጋት ጀምሮ በባዶ አንጀቱ እዚያም እዚህም ሲሮጥ ነው የቆየው፡፡ ገና ከቤቱ በር ላይ እንደቆመ፣ የቀረበውን ምግብ ሲያይ ነው ወስፋቱ መላወስ የጀመረው….

ብዙም ሳይቆይ፣ ሌላ ገበሬ ከውጭ፣ “ቤቶች እንዴት አደራችሁ?” አለ፡፡

አባወርዬው ለሰላምታው መልስ ከሰጠው በኋላ፣ “ግባ፣ ቁርስ ላይ ደርሰሃል፡፡”

“እቸኩላለሁ፡፡ መጫኛ ስጡኝ፣ መጫኛ ልዋስ ነው የመጣሁት፡፡”

ይኼኔ ቀደም ብሎ የመጣውና ከቤተሰቡ ጋር ቁርስ በመብላት ላይ ያለው ገበሬ፣ “ኧረ እኔም መጫኛ ልዋስ ነው የመጣሁት” ይላል፡፡

በዚህን ጊዜ አባወርዬው፣ “በሉ መጫኛውን ከደጅ ለቆመው ስጡት” ይላል፡፡

ቀድሞ የመጣው ገበሬም፣ “ቀድሜ የመጣሁት እኔ እያለሁ” በማለት ቅሬታ ያቀርባል፡፡

አባወርዬውም፣ “አንተማ የመጣህበትን ብላ” ብሎት ዕርፍ…

ይህ ገበሬ ሁለት ዓይናቸውን ያፈጠጡ ስህተቶችን ሠርቷል፡፡ አንድ በጧቱ ወደ ሰው ቤት የመጣበትን ጉዳይ አልተናገረም፡፡ ያንኛው ገበሬ እስከሚመጣ ድረስ፣ የመጀመርያም የመጨረሻም ዓላማው ያደረገው ቢያንስ በተግባር ደረጃ ሆዱን ነው፡፡ ሁለት “ና ቁጭ በል፣ እንብላ” ሲሉት፣ ቢያንስ ቢያንስ ትንሽ እንኳን አልተግደረደረም፡፡ ምን ማለቱ ነው? በመጠኑም ቢሆን በመግደርደር የወጉን ግብር ማድረስ ነበረበት፡፡ እሱ ግን ይህን አላደረገም፡፡ እናም ክፉኛ “ማኖ” ነክቷል፡፡

“አንተማ የመጣህበትን ብላ” የሚለው አነጋገር በእነዚህ በተጠቀሱት ሁለት ጉዳዮች ላይ ሰውዬው የሠራውን “ፋወል” (“ይቅር” የማይባል ስህተት) በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ የሚተች ነው፡፡ እንበልና ሰውዬው የመጣበትን ጉዳይ (ማለትም መጫኛ ለመዋስ መምጣቱን) ባይናገር እንኳን፣ “… ቁጭ በል፣ እንብላ” ሲባል፣ በወጉ መሠረት አሳምሮ ቢግደረደር ኖሮ፣ ይኼን ያህል የሰላ ትችት ላይደርስበት የመቻል ዕድል ነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ አባዋርዬው ትችቱን ፍፁም ከምግብ (“አንተማ የመጣህበትን ብላ” ከሚለው) ጋር ሳያገናኝ፣ “ሞትም የቀደመውን ነው የሚወስደው” በማለት፣ በኋላ ለመጣው ሰውዬ መጫኛቸውን ሊሰጥ ይችል ነበር በኋላ ቢመጣም ጉዳዩን ቀድሞ ተናግሯልና…

በሐበሻ ባህል ውስጥ ምግብ መጋበዝ፣ ማብላትና ማጠጣት ያለውን ያህል፣ መግደርደርም አለ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈላጊም ነው፡፡ ረሃብ ሆዱን እየሞረሞረው ያለ ሰው፣ ምግብ እንዲቀርብለት ሲጠየቅ፣ “በአንድ አፍ” “እሺ” ከማለቱ በፊት በትንሹም ቢሆን መግደርደር (ለምሳሌ፣ “ኧረ አትቸገሩ”፣ “በልቻለሁ”… በማለት) ወይም ያ ቢቀር ቢያንስ በተዛዋሪ የመግደርደር ምልክት ማሳየት ይኖርበታል፡፡ አዎ፣ የሚፈልጉትን ምግብ ለማግኘት መግደርደር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡

እርግጥ ነው፣ ይህን ጥያቄ ለአንድ የገጠር ሰው ብናቀርብለት፣ “እንዴት ዘሎ ከሰው ማ’ድ ቁጭ ይባላል?” ወይም “እንዴት ዝም ብሎ ከአፋቸው እንደወጣ ‘እሺ’ ይባላል?” ሊለን ይችላል፡፡ ነገሩን ጠለቅ ብለን ስናየው፣ በተጠያቂ ሥነ ልቦና ውስጥ ትንሽም ቢሆን መግደርደር በ”ተገቢነት” መርህ ደረጃ የተያዘ ቢሆንም፣ ጥያቄያችን ወደ ፊት ሰርስሮ በመሄድ በ”እንዴት” የቀረበውን “ወግ አጥባቂ” አቋም (“እንዴት ዘሎ ከሰው ማ’ድ ቁጭ ይባላል?” የሚለውን) መሞገት ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመብላት ፍላጎቱ ያለው ሰው “ና እንብላ” ወይም “ነይ እንብላ” ሲባል ወይም ምግብ እንዲቀርብለት ሲጠየቅ ያለምንም መግደርደር ወይም ማመንታት ወደ ማዕዱ ቢቀርብ ወይም እንዲቀርብለት “እሺ” ቢል ችግሩ ምንድነው?

በሌላ አነጋገር አንድ ሰው ወደ ቀረበው ማዕድ ጠጋ ብሎ እንዲበላ ወይም ምግብ እንዲቀርብለት ሲጠየቅ፣ የሚግደረደረው ልማድ ስለሆነበት ብቻ ነው ወይስ በጠያቂውም በተጠያቂውም ዘንድ መግደርደር ይፈለጋል? በኅብረተሰብ የተግባቦት ሥርዓት ውስጥ አንድ የባህል ክንውን ሁለቱን የመስተጋብር አካላት በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ የማይጠቅም ከሆነ፣ ለረጅም ጊዜ ህልውና ሊኖረው አይችልም፡፡ የመግደርደርና የማግደርደር ባህል ስንት ትውልድ ያሳለፈ ዕድሜ ጠገብ አዛውንት መሆኑን አስቡት? በሁለቱ ወገን በኩል ተፈላጊነት ሳይኖረው ይህን ሁሉ ዘመን መኖርማ እንዴት ይቻለዋል?

ከተጋባዡ አንፃር ካየነው፣ መግደርደር የጋባዡን የመጋበዝ ቁርጠኝነት መለኪያ መንገድ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አቶ ተጋባዥ “አልፈልግም” ወይም “አልበላም” ብሎ በደንብ ሲግደረደር፣ መጋበዝ የፈለገው ሰው በበኩሉ “ካልበላህ” ወይም “ካልጋበዝኩህ” በሚል ሐሳቡ ከፀና ወይም ችክ ወደ ማለቱ ካዘነበለ (ማለትም በደንብ ካግደረደረው) ከልቡ ሊጋብዘው የፈለገ መሆኑን ተጋባዡ ይረዳል፡፡

ከጋባዡ አንፃርስ፣ የተጋባዡ መግደርደር ያለው ፋይዳ ምን ይሆን? ተጋባዥ ምግብ እንዲቀርብለት ሲጠየቅ፣ ያለ ምንም ማቅማማት “እሺ” ቢል፣ ጋባዡን ቅር ሊለው ይችላል በሁለት ምክንያት፡፡ በባህሉ ውስጥ ያልተለመደ ነውና ያልተዘጋጀበት ነገር ስለሚያጋጥመው በመጠኑም ቢሆን ሊደነግጥ ወይም ቅር ሊለው ይችላል፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ ሰውዬውን ከማብላት የሚያገኘውን እርካታ ሊያጣ ወይም እርካታው ሊቀንስበት ይችላል፡፡ መግደርደር በትህትናና በምሥጋና የተሞሉ ቃላዊና አካላዊ ክንውኖችን የያዘ ነው፡፡ ይህ ክንውን የሚፈጸመው ደግሞ “ለጋባዡ” ነው ምግብ ለመስጠት መልካም ፈቃዱን በመግለጹ ምክንያት፡፡ ስለዚህ “ተጋባዥ” መግደርደርን “ሰጪ” ሲሆን፣ “ጋባዥ” ደግሞ መግደርደርን ተቀባይ ነው፡፡ መግደርደር በረጅም ጊዜ ሒደት ውስጥ፣ ቢያንስ በተዛዋሪ መንገድ፣ “ለጋባዡ” ውስጣዊ እርካታን የሚፈጥር ክንውን ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ሰውን ለመጋበዝ ወይም ለማብላት ፍላጎቱ ሳይኖራቸው፣ ማግደርደር የሚፈልጉ ሰዎችም አሉ፡፡ ማለትም አንድ ሰው እንዲግደረደር ግን እንዳይበላ! ለምን? ምክንያታቸው ወዲህ ነው፡፡ “‘ላፏ እንኳ'” ወይም “‘ላፉ እንኳ ምግብ ብሉ’ አላሉንም” ተብለው እንዳይተቹ በመፍራት ወይም ከዚህ ከፍ ያለ ግብም ሊኖራቸው ይችላል “እሱማ አባ ስጠው ነው”፣ “እሷማ እማ ስጪው ናት” ተብለው እንዲሞገሱ በመሻት፡፡ በአጭሩ ተግደርዳሪ ብቻ ሳይሆን አግደርዳሪም አለ ለማለት ነው፡፡

ከአግደርዳሪዎች (የእንግዳን መግደርደር ከሚፈልጉት መካከል) ለማብላት ምንም ፍላጎት ወይም የተዘጋጀ ምግብ ሳይኖራቸው፣ ከልክ በላይ የሚያግደረድሩ ሰዎች፣ “በሞቴ፣ አፈር ስሆን ምሳ ብላ” ብለው የሚማፀኑ እናቶች ጭምር አሉ፡፡ ይኼኔ ተለማኙ ሰውዬ የመብላት ፍላጎት እንኳን ባይኖረው፣ የተማፀኑትን ሰዎች ለማስደሰት በማሰብ ደጅ ከሆነ ያለው ወደ ቤት ይገባል፡፡ ከቤት ወጥቶ ለመሄድ ተነስቶ ከሆነ ተደላድሎ ይቀመጣል፡፡ በዚህን ጊዜ፣ በተለይ በቤት ውስጥ የበሰለ ምግብ ከሌለ፣ ጉድ ፈላ ማለት ነው፡፡ ከጎረቤት እንጀራ እስከ መበደር የሚደርሱ ሁሉ አሉ…

ከዚህ የምንረዳው፣ መግደርደርና ማግደርደር የመጠን ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ ከበዛ ያልተፈለገን ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የመብላት ፍላጎት ያለው ሰው፣ የወጉን ላድርስ ብሎ የመግደርደሩን ኪኒን ከ”ትክክለኛው” መጠን ካበለጠው መብላት እንዳማረው፣ ወስፋቱ እንደ ጮኸ ይቀራታል:: ለዚህም ሂሳዊ የሆነ ምሳሌያዊ አባባል አለ “የሆድ ምቀኛው አፍ ነው” የሚል፡፡ በሆድ ላይ ያልተተረተ (ያልተተረበ) ምን አለ ብላችሁ?

 በአንፃሩ የማብላት ፍላጎት የሌለው ሰው፣ የወጉን ላድርስ ብሎ የማግደርደሩን ኪኒን ከ”ትክክለኛው” መጠን በላይ ከሰጠ፣ በገዛ እጁ ያፍራታል በተለይ የተዘጋጀ ምግብ ከሌለ፡፡ ማብሰል የራሱን ጊዜ ስለሚፈልግ፣ “ምሳ” ወይም “ምግብ ካልበላህ” የሚለው ያ ሁሉ ፉከራ (ያ ሁሉ ኪኒን) አግደርድሮ የመሸኘት እንጂ፣ ከልብ የሆነ የመጋበዝ ፍላጎት እንዳልነበረ፣ ለተግደርዳሪ ግልጽ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዶች ለተጋባዡ የተሻለ ምግብ ለማቅረብ ሲሉ፣ አዲስ ምግብ ማብሰልን የሚመርጡበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ በዚህም በኩል ቢሆን፣ ተጋባዡ አዲስ ተበስሎ የቀረበለትን የምግብ ዓይነትና ደረጃ በማየት፣ “ምሳ” ወይም “ምግብ ካልበላህ” የሚለው ያ ሁሉ ውትወታ ከልብ ወይም ለይስሙላ የተባለ መሆኑን መገመት ላያዳግተው ይችላል፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ፣ ‹‹የመግደርደርም ሆነ የማግደርደር መጠኑ ወይም ኪኒኑ ምን ያህል መሆን አለበት?›› የሚለው ነው፡፡ የመጠኑ ነገር እንደየ ባህሉና አካባቢው ሊለያይ ይችላል፡፡ ለአንድ አካባቢ ወይም ንዑስ ባህል (Subculture) በቂ የሆነው፣ ለሌላው አካባቢ ወይም ንዑስ ባህል ሊያንስ ወይም ሊበዛ ይችላል፡፡ በአጭሩ የጨዋታው ሕግ ይኼ ነው ‹‹አለቅጥ አትግደርደር/አታግደርድር ወይም የምታደርገው ከሆነ በንዑስ ባህሉ ውስጥ ያለውን አተገባበር እወቅ››፡፡

ይህን የጨዋታ ሕግ ባለማወቅ፣ አንዳንድ ሰዎች የመብላት ፍላጎቱ እያላቸው (ርቧቸውም እያለ ጭምር) የመግደርደር ኪኒኑን አብዝተው በማቅረብ የመብላት ዕድላቸውን የሚገድሉ አሉ፡፡ እኔ ራሴ በልጅነቴ የመግደርደርን ኪኒን ከሚያበዙት ሰዎች አንዱ ነበርኩ ወግ አጥብቄ ሙቼ! ነገሩ “አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ደሴ፣ ዓረብ ገንዳ ያለችውን ፋጢመት አደምን (የእህቶቼ እህት ናት) ግን ምን ጊዜም አልረሳትም፡፡ ተልኬ ወደ ቤቷ በሄድኩ ቁጥር፣ የመግደርደር ኪኒን እንደማበዛ ስላወቀችብኝ፣ እኔን ለማብላት የምትጠቀመው ዘዴ ምን ነበር መሰላችሁ? ወደ ቤት እንደ ገባሁ፣ “ቁጭ በል” ትለኝና ፈጠን ብላ ወደ ማዕድ ቤት ትሄዳለች፡፡ የተላኩበትን ጉዳይ ሳትሰማኝ፣ ምግቡን ታቀርበዋለች፡፡ አለቀ ነገሩ… አይ ጥፍጥናው!.. አይ ቅልጥሙ!…    

በተለይ ከምግብና ከመግደርደር አንፃር ንዑስ ባህልን አለማወቅ የሚያመጣውን ጣጣ ለመረዳት፣ ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ የሄደ ሰው ምሳሌ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የደረሰባቸው ሰዎች ለሰው አውርተው ከሰማሁት ላጫውታችሁ፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ሰዎች፣ የክፍለ ሀገር ሰው ከመንገድ እንደ ገባ ወደ ቤታቸው ሲሄድ፣ ምግብ እንዲቀርብለት ይጠይቁታል ወቅቱ የምሳ ሰዓት ከሆነ “ምሳ ይቅረብ”፣ ምሽትም ከሆነ “ራት ይቅረብ” በማለት፡፡

ራት ወይም ምሳ ያልበላ ሆኖ እያለ፣ የሐበሻ ወጉን ሊያደርስ፣ በማንኛውም መንገድ አንዴ አሉታዊ መልስ ከሰጠ (“ግዴለም”፣ “በቃኝ” ወይም “አያስፈልግም…” ካለ)፣ ደግሞ መጠየቅ (ማግደርደር) የሚባል ነገር የለም፡፡ በቃ! የምግብ ፋይል ተዘጋ፡፡ (የጨዋታ ፋይል ግን አሳምሮ ሊከፈት ይችላል፣ በጫዋታው ውስጥ የሚያግደረድር ነገር ከተገኘ፣ መግደርደር ነዋ!)

የአዲስ አበባ ወይም የሌላ አካባቢ ሰው ወደ ክፍለ ሀገር ከተማ እንደ ሄደ አድርገን ነገሩን ገልብጠን ብናየው፣ ከዚህ እጅግ የተለየ ክንውንን እናገኛለን፡፡ ምግብ የማቅረብ ጥያቄ ጭራሽም አይቀርብ፡፡ እንግዳው እቤታቸው እንደ ገባ የእጅ ውኃና ምግብ አከታትለው ነው የሚያቀርቡት፡፡ የተዘጋጀ ምግብ ከሌለ ደግሞ በቀጥታ ወደ ማብሰል ሥራ ነው የሚገቡት፡፡ እርግጥ ነው የእጅ ውኃ ሲቀርብ፣ “በልቻለሁ”፣ “አሁን መብላት አልፈልግም”፣ ወዘተ. በማለት ሊግደረደር ይችላል፣ ይግደርደር፣ ችግር የለም እነሱም አሳምረው ያግደረድሩታል፡፡ 

ከፍ ሲል ካየነውና የክፍለ ሀገር ሰዎችን ከአዲስ አበቤዎች ቤት ስለገጠማቸው ለይስሙላ ያህል የተነገረ ከመሰለው የ”ራት ይቅረብ” ገጠመኝ የከፋ ትርክት በቅርቡ ሰምቻለሁ፣ አንዳንዶቻችሁም ሰምታችሁት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሩ ቀልድም ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ላካፍላችሁ… አቶ የክፍለ እንግዳ ገና መሸት እንዳለ፣ ከአዲሳቤዎቹ ቤት ከች ይላል፡፡ ትንሽ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ አቶ አባወራ “ራት ይምጣልህ?” በማለት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ወ/ሮ ሚስት ፈጠን ብላ (አቶ እንግዳ ከመናገሩ በፊት) “ወይስ ስለደከመህ አረፍ ትል” ብላው እርፍ!… (ይኼ ትርክት ልቦለዳዊም ቢሆን፣ ለመፈጠሩ ዋናው ሰበብ የኑሮ ውድነት ጣሪያ መንካቱ መሆኑ ብዙም አያጠራጥርም፡፡ የኑሮ ውድነት ያላመጣብን ጣጣ አለ ብላችሁ?)

እስካሁን ያለውን ለመተንተን የበቃነው፣ ራሱ መጫኛ ሊዋስ ሄዶ የሆድ ነገር ለዚያውም መግደርደርን እስከሚረሳ ድረስ ጠልፎ ስለጣለው ገበሬ ነው፡፡ ልጁን የላከ ገበሬ ማለትም “ሲበሉ የላኩት” የሚባለው ምሳሌያዊ አነጋገር ጉዳይስ? ኢንሻ አላህ በሚቀጥለው ጽሑፍ የምናየው ይሆናል…

(በክፍል አምስት እንገናኝ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...