Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየዓድዋ ድል ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት ሽግግር በአውሮፓውያን ጋዜጠኞች ዓይን

የዓድዋ ድል ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት ሽግግር በአውሮፓውያን ጋዜጠኞች ዓይን

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በያሬድ ኃይለ መስቀል

የዳርዊን ዝንጀሮ ሰው ሆኖ ተገኘ

ዓድዋን የሚያቃልሉ ፖለቲከኛች ምኒልክ ተሸንፎ ቢሆን እነሱም ዛሬ በምዕራባውያን ከተሞች የመኖር፣ የመሥራትና የመማር ዕድል አይኖራቸውም ነበር። ፈረንጆቹ ትንሽ ዕውቀት አደገኛ ነው ይላሉ። ዛሬ የፈረንጅን ፕሮፓጋንዳና ጥምቀት የተቀበሉ የዳርዊን ዝንጀሮዎች በምኒልክና በዓድዋ ድል ላይ የማጣጣል ዘመቻ ሲያካሂዱና አዲሱን ትውልድ ወደ ቅድመ ዓድዋ የዳርዊን ገመሬ ዝንጀሮነት ለመመለስ ሲጥሩ ሳይ አዝናለሁ። አንዳንዴ ሰው ያደረገውን ድል የሚያጣጥል ሳይ ምናልባት ቻርልስ ዳርዊን ትክክል ይሆን እንዴ ብዬም እስቃለሁ።

ለማንኛውም 1988 ዓ.ም. ከዓድዋ ውጊያ በፊትና ከዓድዋ ሽንፈት በኋላ የተጻፉትን ጋዜጦች እናያለን። በመጀመርያ እነዚህ ዝንጀሮዎች ጠግበው የውጫሌን ማታለያ ውል አንቀበልም አሉ፣ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከነጭ እኩል ነን ስላሉ 5‚000 ፈረንጅ ሄዶ ልካቸውን ሊያሳያቸው ይገባል ብለው ነበር። ከዚያ የቻርልስ ዳርዊን ዝንጀሮ ቱባ ነጩን ደመሰሰው። 4‚000 ሺውን ማረከው፣ ሦስቱን ጄኔራሎች ገደለ የሚለው ዜና ሲደርሳቸው ሳይንሱ ስህተት ነበር ብለው ለመቀበል አልደፈሩም፡፡ ይልቁንም ምኒልክ ነጭ ነው ብለው ማሰብ ቀለላቸው። ስለዚህ ምኒልክ ትንሽ ከከንፈሩ መወፈርና ከመጠየሙ በላይ የካውኬዥያን ዝርያ ነው፣ ነጭ ነው። ሚስቱም እቴጌ ጣይቱ ትንሽ ጥርሷ ወጣ ከማለቱ በስተቀር የፈረንሣዩን ናፖሊዮን ሚስት የምትመስል ናት ብለው ሽምጥጥ አድርገው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ነጭ አደረጉ።

ይህ በሁለት በኩል የሚቆርጥ ስለት ነበር። አንደኛው ዳርዊንና ተከታዮቹ ያሳተሙት ሳይንስ ትክክል ነው። ጣልያን የተሸነፈው በዝንጀሮ ሳይሆን በሌላ ነጭ ጦር ነው የሚለውን ማፅናት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቻይናውና ህንዱ ለካ ነጭም ይሸነፋል እንዴ የሚል ሐሳብ በአዕምሮው እንዳይሰርፅ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከዓድዋ በፊት የተጻፉትንና ከዓድዋ በኋላ የተጻፉትን እየጠቀስኩ ለማሳየት እሞክራለሁ።

ከዓድዋ በፊት የነበሩት ጽሑፎች

ማንም የአውሮፓ ጋዜጣና ተንታኝ ታላቋን ሮም ገጥሞ ጥቁር ያሸንፋል ብለው አላሰቡም ነበር። ያው እንደተለመደው በዘመናዊ መሣሪያ ሲያዩ ኢትዮጵያውያን ደንብረው ይጠፋሉ አሉ። ዝንጀሮ ይሁን አንበሳ የጥይት ድምፅ እንደሚያስደነብረው፣ ኢትዮጵያውያንም የጣልያንን መድፍ ሲሰሙ ይበተናሉ ብለው ቀምረው ነበር።

በዚህ ምክንያት ጄኔራል ባራቴሪም ምኒልክን በፍግርግር ብረት ውስጥ አድርጎ ወደ ሮም እንደሚያመጣ እርግጠኛ ነበር። ካርቱን ሠዓሊዎችም ጥቁሩን ምኒልክ ከንፈሩን አግዝፈው፣ እግሩን አንሻፈው፣ ሆዱን አንዘርጥጠው ራቁቱን እንደ ዝንጀሮ በፍግርግር ብረት ውስጥ አስረው አሳቁ።

ጄኔራል ባራቴሪ በኢቮሊሽነሪ (በዝግመተ ለውጥ) ሳይንስ የበላይነት በመተማመን ወደ ጦር ከመዝመቱ በፊት፣ ምኒልክ የውጫሌንን አፈርሳለሁ ብሎ በማስቸገሩ ‹‹ምኒልክን በፍግርግር ብረት ውስጥ አስገብቶ እንደሚያመጣው›› ለተሰብሳቢው መንጋ ተናግሮ አስጨበጨበ (Baratieri Promised Crowds “To Bring Back Menelik in a Cage” 1895)፡፡

የዳርዊንን የሐሰት ትንቢት አምነው ጄኔራል ባራቴሪ ታበየ። ንቀቱም ከልክ አለፈ። ከዚህ ጥበብና ብልጠት ከሌለው ዝንጀሮ ጋር እንደሚዋጉ አምነው ወደ ጦርነት ገባ። በዚያም የተሳሳተ እምነት ተሸነፈ። ጄኔራል ባራቴሪም ሸሽቶ ነፍሱን ቢያተርፍም፣ ከሥልጣኑ ተወግዶ በኃፍረት ሕይወቱን ጨረሰ። የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒም በደረሰው ውርደት የተቀሰቀሰ ቁጣ ከሥልጣኑ ተባረረ።

ጋዜጦቹም ጣልያን የነጩ ዘር ሁሉ ሽንፈት በማምጣቷ ከኢሮፕያውያን ዝቅ ተደርገው ታዩ። አንድ ጋዜጣ  “The crushing defeat the Italian forces have sustained at the hands of a half savage people will imperil her position among the nations of Europe” ብሎ ጻፈ። የሚኮሩባት የነጭ ሥልጣኔ እንብርት ሮም ከነጭነትም ወረደች። በግማሽ አረመኔ ሰዎች በመሸነፏ የአውሮፓን ክብር አዋረደች፣ ከአሁን ወዲያ የጣሊያን ክብር ወርዷል አሉ። በዚህ በኩል ደግሞ ዝንጀሮ የመጠቀ አዕምሮ ያለው ሰው ሆኖ ተገኝ።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያውያን ከነጭ እኩል ነን ብለው በማሰባቸው የተናደደ ጋዜጠኛ፣ ኢትዮጵያውያን ከነጭ እኩል ነን ብለው በማሰባቸው 5‚000 የነጭ ጦር ለመቅጣት በቂ ነው ብሎ ጽፎ ነበር “5‚000 European soldiers are enough to punish Ethiopians for believing themselves equal to white men”፡፡

ይህ የዳርዊንና የስፔንሰር ሳይንስ ዓድዋ ላይ ተቀበረ። ችግሩ የኢትዮጵያ ምሁራንና የታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝን አሸነፈች ብለው ያቆማሉ። ከቅኝ ግዛት ጀርባ የነበረውን የሳይንስና የፍልስፍና መሠረት የተረዱና ያብራሩ የሉም።   ይህም ድል የስሎቫኪያም፣ የቻይናም፣ የቬትናምም፣ የአፍሪካም የሰውነት ትግል መሆኑ እስካሁን አልተዘከረም። ጦርነቱ በሰውነትና በኢቮሌሽነሪ ሳይንስ መካከል መሆኑን በርካታ መረጃ እያለ ይህንን አቀናብሮ የተረከው የለም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማው ይህንን የጥናት ዘርፍ ለማመላከትና ሌሎች ባለሙያዎች እንዲያጎለብቱት ነው።  ፍሬዲሪክ ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል እኛ ነን ያለነው” ያለው በዓድዋ ላይ ተቀበረ። ነጭ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ጥቁሩ ምኒልክ አሳየው።

ምኒልክ ሰው አደረገን የምለው ለዚህ ነው። ዛሬ በየዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ተብሎ የጭንቅላት ሥራ እንዲሠራ የተፈቀደለት በምኒልክ፣ በጣይቱ፣ ለአሉላ፣ በአውአሎም፣ በሀብተ ጊዮርጊስ፣ በመኮንን፣ ወዘተ. የአዕምሮ ምጥቀት ምክንያት ነው። እነዚህን ሰው ያደረጉንን ጠዋት ባንዲራ ሲሰቀል በመዘመር ማክበር ሲገባን ሐውልታቸውን ካላፈረስን ብለን እንጋበዛለን። የዓድዋ መሠረታዊ ድል የፍልስፍና ፍልሚያ እንጂ የባሩድና የጎራዴ አጠቃቀም የበላይነት አይደለም። የማሰብ፣ የማቀድና ወደ ተግባር የማውረድ የአዕምሮ ጥንካሬ የበላይነት እንጂ። የምኒልክ፣ የባልቻ፣ የገበየሁ፣ የአሉላ፣ የራስ መኮንን፣ የጣይቱ የማሰብ ችሎታ ከእነ ባራቴሪ ስለበለጠ ነው ያሸነፉት። ይህንን በማድረግ የረቀቀ ሐሳብ የመቀበል አዕምሮ ስላላቸው ዓይተው ዳርዊንን ፉርሽ አደረጉት።

ከዓድዋ ማግሥት

ከዓድዋ የባራቴሪ ሽንፈት በኋላ ዜናው በቴሌግራም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሲደርስ፣ የዳሪዊን ተከታዮች ግንብ መናዱን ሲያዩ የዳርዊንን ግንብ ለመጠገን ተሯሯጡ። የመጀመርያው የነጩ ጦር መሸነፍ የሚያመጣውን መዘዝ አብጠለጠሉ። ከዚያ ማምለጫ ያሉት ኢትዮጵያውያን ነጭ ናቸው ብለው ለማሳመን ተሯሯጡ። አሶሼትድ ፕሬስ እ.ኤ.አ. ማርች 7 ቀን 1896፣ ‹‹የጄኔራል ባራቴሪ መሸነፍ በአፍሪካውያን ሞራል ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሲኖረው፣ የአውሮፓ አገሮችን ክብር ደግሞ ያዋረደ ነው፤›› አለ፡፡ “General Oreste Baratieri’s defeat must have an enormous moral effect in Africa and diminish considerably the prestige of European troops of all Nationalities.”

ምኒልክን ጥቁር አይደለም ለማለትና ዓለምን ለማሳመን ተሯሯጡ፡፡ ‹‹ከከንፈሩ መወፈር በስተቀር ኔግሮ የሚመስል ነገር አለበት ብለው ጻፉ፡፡ “He was not a Nigroid but a Caucasian’ አስፋፍተውም ኢትዮጵያዊያን ምንም የኔግሮ ነገር የለባቸውም፣ ይስባሉ፣ ባህሪያቸው የተረጋጋ ነው አሉን። “The characteristic African features are almost wholly missing among the Abyssinia. They have intelligence, stability of character, courage, skill, and qualities of endurance not found in any of the races of pure Negroes.”

ከዚያ እውነታውን መካድ ብዙም አላራመደም። ምኒልክን ነጭ ማድረግ እንዲህ ቀላል አልሆነላቸውም። ስለዚህ እውነታውና ሰውነቱን ለመቀበል ግድ ሆነባቸው። “The first African of modern times to show fighting qualities of a high order and true military skill in handling large masses of men” New York Journal፡፡ ከዚያም አልፈው ሕዝባዊ ነገር የመቀበል አዕምሮ የለውም ካሉት ዝንጀሮነት አስፈንጥረው እኛን ሁሉ በክርስትናችን ይንቁናል አሉ። “Their national pride is unlimited and they look down upon all other nations of the world as inferior to them in Christianity.” ምኒልክ ጀግና ተዋጊ ብቻ ሳይሆን የተሳካለትም ዲፕሎማት ነው ለማለት ተገደዱ። “The Nigus of Abyssinia is Evidently not Only a Valiant Warrior and Sherwd Diplomat.”

ከዚያ ሁሉም ወደ አዲስ አበባ መልዕክተኛ እየላከ ገጸ በረከት ይዘው ከምኒልክ ፊት እጅ መንሳት ግድ ሆነባቸው። ትልቁ የሮም ጳጳስ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ምኒልክን ተማፀኑ። በሚወዳቸው ስም እማፀንዎታለሁ እባክዎን እስረኞችን ይፍቱ ብለው ዝቅ ብለው ለመኑ። “June 11, 1896 Italian pope wrote to” in the name of all that dearest to you, please release the prisoners.”

ከዚያ በጥቅምት ወር ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያን ዝንጀሮነት ሳይሆን፣ በእኩል ሰዎች መሆናቸው አምነው ለመቀበል ተገደደ። ጥቅምት ላይ የኢትዮጵያውያን የማይከሰስና የማይገሰስ ነፃ ሕዝብ መሆኑን እንቀበላለን አሉ። October 20, 1896 “Recognizes the Absolute Independence of Ethiopia and Abrogate Uchally Treaty” New York Herald.” ከዚያ ሙገሳው ቀጠለ። ምኒልክን ከናፖሊዮን ጋር ጣይቱን ደግሞ ከፈረንሣይ ልዕልት ጋር አወዳደሩ። ጣይቱም ‹‹ሰውነቷ የተመጣጠነ፣ ጠይሙም ቀለም፣ የፀዳ፣ የሚያበራ ጥቁር ዓይን ያላት ሲሆን ትንሽ ጥርሷ ጋ ብቻ ነው ጉድለት ቢኖርባትም እሱንም ስታወራ ሸፈን ታደርገዋለች፤›› አሉ። Tayetu is “Well formed, with regular features, except little defect of the mouth, which she endeavours to council when she speaks,. Her skin is a clean brown. Her eyes are black.”

ጥቁርነቷንና ማማሯን ለመመስከር ተገደዱ። የኢትዮጵያዊያን ጀግንነትም አለማድነቅ የማይቻል ነበር። ከተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ፍርኃት ያልፈጠረባቸው ግድያን በግድያ የሚጋፈጡ ናቸው አሉ። “Of all the pity wars of the past few months the Abyssinian struggle is the most interesting for the reason that the people are fearless and capable of meeting slaughter after slaughter.” ተድላ ደስታ (ዶ/ር) የተባሉ ጸሐፊ በዚህ ዙርያ ከበርካታ ጋዜጦች በማሰባሰብና ከጦርነቱ በፊትና በኋላ የታተሙትን ቆንጆ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የዚህን ጽሑፍ ጽንሰ ሐሳብ ለመመርመር ለሚፈልግ ሥራውን ቀላል ያደርግለታል።  

መደምደሚያ

ዓድዋ የጎራዴና የጦር አጠቃቀም ወይም አልሞ ከመተኮስ በላይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሰው ልጆች ሰው ሆኖ የመታየትና የእኩልነት ትግል ነበር።  የማሰብ ችሎታ፣ የማቀድ፣ ጠላትን የማታለል፣ ኃይል ማሰባሰብ፣ ወታደራዊ ንቅናቄና በፈጣን ዕርምጃ የመውሰድ ትግል ነበር። ይህ ጥቁሩ ውስጥ ገና አልተፈጠረም፣ አዕምሯቸውም እንዲህ ዓይነት ሐሳባዊ (Abstract Knowledge) የመቀበልና የማስተናገድ አቅም የለውም ብሎ ዳርዊን ጽፎ ባሳመነ ማግሥት ጥቁር ማሰብ የሚችል ሰው እንደሆነ ያስመሰከረበት ትግል ነው። የእነ አውአሎም የረቀቀ የስለላ ሥራ፣ ሁሉም ሰው ንግሥ ለማክበር እንደሄደ ለጣሊያን ጦር እንዲደርስና ይህንንም አምኖ እንዲቀበል የተደረገበት መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሚስጥር የመያዝ ችሎታ፣ ጦርነቱ ሲጀመር ፈጥኖ ቦታ የመያዝ፣ ፈጥኖ ሥምሪት፣ ፈጥኖ ማጥቃት፣ ከሌሎች ክፍሎች ጋር የሬዲዮ ኮሙዩኒኬሽን ባልነበረበት ጊዜ ተማምኖና ተናቦ መሥራት የሚያስገርም የማሰብና የማቀድ ችሎታን ነው ያስመሰከረው። ዳርዊን ያዘመተው ሐሳብ ዓድዋ ላይ ሞቶ ተቀበረ። ጃፓኖች እኛም አያቅተንም አሉ፣ ቻይናዎችም ተነቃቁ፣ ቬትናሞችም ሲዋጉ ኢትዮጵያን እያሰብን ነው አሉ።

ነጮቹ እንደፈሩት ኢትዮጵያኒዝም የጥቁር ሕዝብ እንደ ማርክሲዝም ዕርዮት ሆነ። በአሜሪካ የባብቲስት አቢሲንያ ቸርች ተመሠረተ፣ እነ ማርቆስ ገብሬል የጥቁርን ሕዝብ ንቅናቄ ዓድዋን ጠቅሰው ቀሰቀሱ፣ እነ ማንዴላ በድካማቸው ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያንና እነ ምኒልክን አሰቡ። የጥቁር ሕዝብ አርነት ንቅናቄ ተቀሰቀሰ። በባርነት ያሉ የአፍሪካ አሜሪካዎች እኛም ኢትዮጵያውያን ነን፣ ኢትዮጵያ እጇን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች የሚለውን ተስፋ ሙጥኝ ብለው ያዙ። መንገዱ ቢከብድም ፈተናው ቢበዛም በመጨረሻ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ አንድ ቀን ነፃነታችንን እንቀዳጃለን ብለው አመኑ። እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ የኢትዮጵያን ተስፋ ጠበቁ።

ክብር ለእምዬ ምኒልክ፣ ክብር ለእቴጌ ጣይቱ፣ ክብር ለራስ መኮንን፣ ክብር ለባልቻ አባ ነፍሶ፣ ክብር ለአሉላ አባ ነጋ፣ ክብር ለገበየሁና ክብር ለኢትዮጵያ ጀግኖች ከዝንጀሮ ምድብ አውጥተው ሰው አስባሉን። ስለዚህ ክብር ለዓድዋ ጀግኖች፣ ክብር ለምኒልክ፣ ለጣይቱ፣ ለገበየሁ፣ ለባልቻ፣ ለአሉላ፣ ለመኮንንና ለሌሎችም የጦር መሪዎች። ክብር ለአዕምሮ ምጥቀት በዓድዋ ላይ ላስመሰከሩ ሁሉ ይገባል። በአስተሳሰባቸው ጥልቀትና ስትራቴጂ የዳርዊንን አስተምህሮ ፉርሽ ስላደረጉ።

የ127ኛውን የዓድዋ ድል ስናከብር ባራቴሪ አሸንፎና ምኒልክን ማርኮ በፍግርግር ብረት እንዳለው ሮም ወስዶት ቢሆን ኖሮ የዳርዊን አስተምህሮ እውነት ይሆን ነበር። እሱ እንደተነበየውም የበላዩ ነጩ ሰው ጥቁሩን አጥፍቶ ምድርን ይወርስ ነበር። የጥቁርም እኩልነት ሌላ ምኒልክ እስከሚወለድ መቶ ዓመት ይፈጅ ነበር። በማሰብ፣ በዕቅድ ድክመት፣ በስትራቴጂ ስህተት ተሸንፈው ባራቴሪ እንዳቀደው ምኒልክን በፍግርግር ብረት ውስጥ አስሮ በሮም አደባባይ ለተመልካቾች አቅርቦት ቢሆን ኖሮ የዛሬዋ ነፃ ቻይና፣ ጃፓን፣ ቬትናም፣ ስሎቫኪያና የእኛው አገርም አትኖርም ነበር።

ለዚህ ነው ዓድዋ ሰው አደረገን፡፡ ምኒልክ ሰው ሆኖ ባያስነሳ ጋሻ የዓለምን ነጭ ያልሆነ ዘር ሁሉ ሰው ለመባል ብዙ ጊዜ ይፈጅ ነበር። አንዳንድ ያላነበቡ ወይም ያልተማሩ እነ አቶ በረከት ስምኦን በካድሬ ሥልጠና ያስታጠቋቸውን እንደ እውነት ወስደው የሚፍጨረጨሩ አሉ። ይቅር ይበላቸው። መጽሐፍ ቅዱስም ራስህን እንደ ጎረቤትህ ውደድ ነው የሚለው። ራሱን የጠላና የናቀ ሰው ሌላውን ሊወድ አይችልምና።

ክብር ለዓድዋ አያቶቻችን!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢንቨስትመንት አማካሪ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ችግሮችና ታሪክ ላይ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው yaredhm.yhm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...