Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየካራማራ ጎዳና

የካራማራ ጎዳና

ቀን:

‹‹ለአንድነቱ

ድሉ እንዲሰምር የነፃነቱ

ወጣ ወረደ ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አለኝ አደራ

የተቀበልኩት ከጀግኖቹ አውራ

እንድትኖር ሀገሬ ታፍራና ተከብራ

ብሎ ተነሳ ሕዝባዊ ሠራዊት

ጉዞ ጀመረ እየዘመረ

እያበራ

የነፃነት ድል ያንድነት ጮራ

አውለበለበ ቀዩን ባንዲራ እንዲያበራ…››

ከአርባ አምስት ዓመታት በፊት ነበር  በ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› ቅዠት የተለከፈው በፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ይመራ የነበረው የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት፣ በ1969 ዓ.ም. በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቆ በተቆጣጠረ ጊዜ ወረራውን ለመቀልበስ የተሠለፈው፣ በወቅቱ አጠራር አብዮታዊ ሠራዊት ይባል የነበረው የመከላከያ ኃይል፣ እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የተመለመለውና ሚሊሺያ የተሰኘው ሕዝባዊ ሠራዊት ይዘምረው የነበረ ወኔ ቀስቃሽ መዝሙር ነበር፡፡

ይህ በታዋቂው ገጣሚ የሠራዊቱ አባል ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በወቅቱ እንደ ሕዝብ መዝሙር ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያሉት ከአንደበታቸው አይለዩትም ነበር፡፡ 

የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታሪካዊውን የእናት አገር ጥሪ ያቀረቡት ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. ነበር፡፡ እንዲህም ብለው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለአገራዊው ጥሪ ሁሉም ይክተት አሉ፡፡

‹‹…ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአብዮታዊት እናት አገራችን ዳር ድንበርና የማይገሰሰው አንድነታችን በውጭ ኃይል እየተደፈረ ነው፡፡ በአብዮታችንና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ህልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራና ድፍረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል… ለብዙ ሺሕ ዘመናት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ክብርንና ነፃነትህን ለመድፈር፣ አገርህን ለመቁረስ… የተጀመረውን ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሠልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ! ዝመት! ተዋጋ! እናሸንፋለን!!››

የጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተነስ ታጠቅ ዝመትን ተከትሎ ቀድሞ ሥጋ ሜዳ ይባል በነበረውና በክተቱ አዋጅ መሠረት ታጠቅ የጦር ሠፈር በተባለው ቦታ ለሦስት ወራት የሠለጠነው 300 ሺሕ ሚሊሺያ (ሕዝባዊ ሠራዊት) ከመደበኛው ጦር ጋር ሆኖ በአብዮት አደባባይ ታላቅ ሠልፍ አሳየ፡፡ በዘመኑ አጠራርዋ ከአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጎን በሶቭየት ኅብረት አማካይነት ሶሻሊስት አገሮች ከጎኗ ሲቆሙ በተለይም ኩባ እና ደቡብ የመን እግረኛ ሠራዊት፣ ታንከኞችና መድፈኞችን በመላክ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እኛና አብዮቱ ታሪካዊ ክንውኑን እንዲህ ዘክሮታል፡፡

‹‹ኦጋዴንን ተቆጣጥሮ የያዘውን የሶማሊያን ጦር በተባበረ ኃይል ወግቶ ለማስወጣት ኩባ በጄኔራል ኦቸዋ የሚመራ ከሠላሳ ሺሕ በላይ ወታደሮች አሠልፋ ወሳኝ ውጊያ አካሂዳለች፡፡ የሶማሊያን ጦር ለመውጋት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር የሚሠለፉ የደቡብ የመን የታንከኛና የመድፈኛ ክፍሎችን ልካለች፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራዊትና የውጭ መንግሥት ወታደሮችን አስተባብሮ በበላይነት የሚመራና የሚዋጋ የጦር አዛዥ ሶቪዬት ኅብረት ጄኔራል ፔትሮቭ የሚባሉ ታዋቂ የጦር ጄኔራል ላከች፡፡ በጦር ክፍሎችም አማካሪ መኰንኖች መደበች፡፡ በዚህ አኳኋን የተደራጀ ግዙፍ ጦር በሊቀመንበር መንግሥቱ ጠቅላይ አዛዥነት እየተመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሶማሊያን ጦር አንኮታኩቶ ብዙውን ገድሎና ማርኮ በሽሽት ያመለጠውን ቀሪ ጦር ከግዛታችን በማባረር የኢትዮጵያን አንድነት አስጠበቀ፡፡ ድንበራችንንም አስከበረ፡፡

‹‹የሶማሊያ ጦር የቆሬን የመከላከያ ቀጣና በጎን በማለፍ በጃርሶና በኮምቦልቻ በኩል አድርጎ ድሬዳዋን፣ በፌዲስና ሐኪም ጋራ በኩል ሐረርን ለመያዝ ከታኅሣሥ 15 ቀን 1970 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ ማጥቃት ሰነዘረ፡፡ የኢትዮጵያና የኩባ ሠራዊትም ወደ ሐረር በመገስገስ ላይ የነበረውን ፌዲስ ላይ፣ ድሬዳዋን ለመያዝ በመገስገስ ላይ የነበረውን ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው አጠገብ እንደደረሰ ሁለት ከፍተኛ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዎችን አካሄደ፡፡ በዚህ መልሶ ማጥቃትም ኮሎኔል ፋንታ በላይና (በኋላ ሜጀር ጄኔራል) የአየር ኃይል ባልደረቦች እንደ አንድ እግረኛ ወታደር ጠበንጃ ይዘው በግንባር ተሠልፈው በጀግንነት ተፋልመዋል፡፡ በዚህ ቀውጢ ሰዓትም ለራሳቸው ሳይሳሱ የጠላትን ጦር በአየር ደብድበዋል፡፡

ከጠላት ወገንም ወደ ሦስት ሺሕ የሚሆን ሠራዊት ደመሰሱ፡፡ ጠላት በተለይ በድሬዳዋ አካባቢ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ታንኮች ብዛት ያላቸው መድፎች የተለያዩ ቀላልና ከባድ መሣሪያዎች በከፊል ሲወድምበት ከፊሉን ደግሞ ጥሎ በመሸሹ ከፍተኛ የንብረት ኪሳራ ደረሰበት፡፡ በዚህ ሽሽት ገና ከእሽግ ያልወጡ የኔቶ መሣሪያዎችም ተማርከዋል፡፡ የሶማሊያ ጦር ከዚህ ሽንፈት በኋላ ዋናው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ባልተጠበቀና ባልታሰበ ፍጥነት ይዞታውን በመልቀቅ መፈርጠጡን ተያያዘው፡፡

‹‹ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና የኩባ ሠራዊት ቀደም ብሎ በታቀደው መሠረት በየካቲት ወር 1970 ዓ.ም. ዋናውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻቸውን ጀመሩ፡፡ አብዛኛውን ምሥራቃዊ ደጋ ክፍል ነፃ በማውጣት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. እጅግ ስትራቴጂካዊ የሆነውን የካራማራን ኮረብታና አካባቢ ከወራሪው ጠላት አስለቀቀ፡፡ የካቲት 27 ቀን 1970 ዓ.ም. የጅጅጋ ከተማና አካባቢዋን በቁጥጥር ስር አውሎ ሰንደቅ ዓላማችን በነፃነት እንድትውለበለብ አደረገ፡፡

‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ

ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ፤

ረዥሙን ጉዞ ጥንቱን አውቄ 

ተነስቻለሁ ትጥቄን አጥብቄ፤

መብት ነፃነት እስኪሆን አቻ

ተነስቻለሁ ለድል ዘመቻ፤

ልሙት ልሰዋ ደስ ብሎኝ ስቄ

ለአገሬ ክብር እኔ ወድቄ፡፡›› የሚለው ዝማሬም በኢትዮጵያ ሰማይ ተስተጋባ፡፡

የዚህን ታሪካዊ የካራማራ ድል 45ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ዋናው ፖስታ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የትግላችን ሐውልትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የሚል ታካይ ስያሜ ባገኘው ሥፍራ እሑድ፣ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡

በመታሰቢያ በዓሉ በጦርነቱ የዋሉ ጄኔራል መኰንኖች፣ የቀድሞው ሠራዊት መኰንኖችና ባለ ሌላ ማዕረጎች፣ የካራማራና በሌሎቹም ዓውደ ውጊያዎች የተሰዉ ቤተሰቦች ተገኝተውበታል፡፡ በጦርነቱ እስከ መስዋዕት የከፈሉ ወታደሮቿን በመላክ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ያሳየችው የኩባ አምባሳደርም ታዳሚ ነበሩ፡፡  የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በሥነ በዓሉ ላይ ከተገኙት ሹማምንት አንዷ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሶማሊያ ጋር እንዲሁም በሰሜን ግንባር ሲዋጉ ለተሰዉና ለተጎዱ፣ ለተካፈሉም ሁሉ መታሰቢያ እንዲሆን በጥቁር አንበሳና በዋናው ፖስታ ቤት መካከል የቆመውና ንድፉ በቀራፂና ሠዓሊ ታደሰ ማመጫ የተሠራው ‹‹ትግላችን ሐውልት››፣ የ10ኛው አብዮት በዓል መስከረም 2 ቀን 1977 ዓ.ም. ሲከበር በዋዜማው መመረቁ፣ በወቅቱም የአብዮቱን የአሥር ዓመታት የትግልና የድል ጉዞ በሦስት ዓበይት ምዕራፎች የታየበት ‹‹ድላችን ኤክስፖ›› (የአሁኑ የኤግዚቢሽን ማዕከል) መከፈቱ ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...