የአሜሪካዊ አርተር ሚለር ‹‹ዴዝ ኦቭ ኤ ሴልስማን›› (Death of the salesman) የተሰኘው ተውኔት ‹‹የአባወራ ጉዞ›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እሑድ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀረበ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ፐብሊክ አፌርስ አነስተኛ ፈንድ ፕሮግራም ተውኔቱን የተረጎመው ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ፀሐፌ ተውኔት ዓለማየሁ ገብረሕይወት ሲሆን፣ ያዘጋጀው ደግሞ ታዋቂው ሥነ ጥበበኛ ተክሌ ደስታ ነው፡፡ ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን የቴአትር ደራሲዎች፣ ዳይሬክተሮችና የብሔራዊ ቴአትር አርቲስቶች ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ተውኔቱ ተርጉሞ እንዲቀርብ በማድረጉ ኤምባሲው መደሰቱን ገልጿል። የአርተር ሚለር የአባወራ ጉዞ ተውኔት የማንነት መጥፋትና አንድ ሰው በራሱና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ለውጥ መቀበል አለመቻሉን ይናገራል። ተውኔቱ የትዝታ፣ የህልሞች፣ የግጭቶችና የክርክር ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጓዞች በገጸ ባሕርዩ የዊሊ ሎማን የመጨረሻ 24 ሰዓታት ዓውደ ሕይወት ውስጥ የሚታዩ ናቸው። ተዋናዮቹ ተስፋዬ ገብረሃና፣ አዳነች ወልደገብርኤል፣ ሱራፌል ተካ፣ ሚካኤል ታምሬ ብሩክ ምናሴ፣ ገነት አሰፋ፣ ትዕግሥት ባዩ፣ ሔኖክ በሪሁን፣ አሳዬ ገነነና ሮዛ አየነው ናቸው፡፡ ተውኔቱ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለሁለተኛ ደረጃና ለኮሌጅ ተማሪዎች እንዲሁም ለመምህራን ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ከተሞች እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡በኤምባሲው መግለጫ፣ የተውኔቱ ፕሮጀክት ዓላማ የአሜሪካን ተውኔት ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች በማስተዋወቅ በአሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ነው፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ተውኔቱ በብሔራዊ ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርብ የአሜሪካ ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሩት አን ስቲቨንስ ክሊትዝ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ከያንያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም የዝግጅቱ አካል ነበሩ። ከዚህ ቀደም ጥቂት የአሜሪካ ተውኔቶች በኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ ተተርጉመው ቀርበዋል፡፡ ከእነሱም መካከል የኤድዋርድ አልቢ ‹‹አንበሳ ግቢ›› (Zoo Story) እና የዩጂን ኦኔይልስ፣ ‹‹አንድ ለአንድ›› (ዌልድ) ይጠቀሳሉ።ስቲቨንስ ክሊትዝ ከትርዒቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኤምባሲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋር በመተባበር ተውኔቱን በማቅረቡና በሁለቱ አገሮች መካከል ለባህላዊ ግንኙነት መንገድ ከፋች ወጣት ከያኒያንም ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን በደስታ ገልጸዋል፡፡