Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበደቡብ ኦሞ ለተከሰተው ድርቅ ዕርዳታ በመዘግየቱ 338 ሺሕ ሰዎች ለከባድ ምግብ ዕጦት...

በደቡብ ኦሞ ለተከሰተው ድርቅ ዕርዳታ በመዘግየቱ 338 ሺሕ ሰዎች ለከባድ ምግብ ዕጦት መጋለጣቸው ተሰማ

ቀን:

  • ከ15 ሺሕ በላይ ከብቶች መሞታቸው ተገልጿል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ስድስት ወረዳዎች ለተከታታይ አምስት ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ከ338 ሺሕ ሰዎች በላይ ለከባድ የምግብ ዕጦት መጋለጣቸው ተነገረ፡፡ የዕርዳታ ሥርጭቱም በታኅሳስ ወር ለአጭር ጊዜ ከቀረበ በኋላ መቋረጡን የዞኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በድርቁ ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ከብቶች ለከፍተኛ የውኃና የመኖ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን፣ እስካሁን ከ15 ሺሕ በላይ ከብቶች መሞታቸው ተጠቁሟል፡፡ ከቦረና ዞን ጋር አዋሳኝ የሆነው የደቡብ ኦሞ ዞን ከቦረናው ድርቅ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ውስጥ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ዱባ ያራ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹የሚዲያ ትኩረት ማጣት ካልሆነ በስተቀር እዚህ ያለው ችግር ቦረና ከደረሰው ድርቅ ጋር እኩል ነው፤›› ሲሉ አቶ ዱባ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለችግሩ ዋነኛ መንስዔ ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች የዝናብ አለመጣል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተለይ ደግሞ ከደቡብ ኦሞ ዞን አሌ ወረዳ ተነስቶ ቦረናን፣ ኮንሶን፣ ሐመርንና ሌሎች አካባቢዎችንም የሚያዳርሰው ትልቁ የወይጦ ወንዝ ሙሉ በሙሉ መድረቅ ትልቁ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

‹‹በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ትልቁ የወይጦ ወንዝ ሙሉ በሙሉ ደርቋል፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ እየሸሸ ስለሆነ በቴክኖሎጂ መሳብ አልቻልንም፡፡ ድርቅ በተደጋጋሚ እየመጣ ይሄድ ነበር፡፡ አሁኑ ግን ሁሉም የተፈጥሮ የውኃ ምንጮች ጠፍተዋል፤›› በማለት አቶ ዱባ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ሕዝብ ቁጥሩ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑን፣ 70 በመቶው የሚኖረው ግን አሁን በድርቅ  በተጠቁ ስድስቱ ወረዳዎች ውስጥ እንደሆኑ፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለም የዞኑ ሕዝብ በሙሉ ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

‹‹የኦሞ ሕዝብ አርብቶ አደር ነው፡፡ ከብቶቹ ከሞቱ ለዘለዓለም ተረጂ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ አሁን እየሞከርን ያለነው ቢያንስ ለዘር የሚሆኑ ከብቶች እንዲተርፉ ነው፡፡ ከፍተኛ የውኃና የመኖ እጥረት አለ፤›› ሲሉ አቶ ዱባ ገልጸዋል፡፡

ለተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ ዕርዳታን በተመለከተም ከፍተኛ የአቅርቦት ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት መንግሥት ዕርዳታ ማቅረብ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን አሟልቶ ማቅረብ ስላልተቻለ ከሦስት ወራት በኋላ ተቋረጠ፡፡ ከዚያ መንግሥት ከወርልድ ቪዥን ጋር ተነጋግሮ እሱም ከአንድ ዙር በላይ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ከታኅሳስ ወዲህ የቀረበ ዕርዳታ የለም፤›› ሲሉ አቶ ዱባ ተናግረዋል፡፡

ምሥራቅ አፍሪካን ለተከታታይ ዓመታት እየጎዳ ባለው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት ደቡብ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ ክልልና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዕርዳታ ጠባቂዎች ሆነው ችግሩ ከተባባሰ በኋላ ትኩረት እያገኙ ቢሆንም፣ የዕርዳታ ምላሹ ግን አናሳ ነው እየተባለ ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...