- ብሔራዊ ባንክ የላከው አምስት ቢሊዮን ብር በአንድ ሳምንት ማለቁ ተነግሯል
በትግራይ ክልል በድጋሚ ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮች፣ በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ለደንበኞቻቸው በቂ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ተገለጸ።
ተገልጋዮች ወደ ተለያዩ የባንክ ከቅርንጫፎች ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ቢሄዱም፣ ጥቂት ባንኮች የሚያስተዳድሯቸው ውስን ቁጥር ያላቸው ቅርንጫፎች ከሚሰጧቸው አነስተኛ ገንዘብ በስተቀር ተጨማሪ ማግኘት እንዳልቻሉ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎችና ደንበኞች ለመረዳት ተችሏል።
ከአንድ ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር አድርገውት ከነበረው ውይይት በኋላ በተወሰነው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል ልኮ የነበረ ቢሆንም፣ ገንዘቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ወጪ ሆኖ እንዳለቀ ለማወቅ ተችሏል።
ባንኮቹ ባላቸው የደንበኛ አገልግሎት ስፋትና በብሔራዊ ባንክ ክፍፍል መሠረት፣ ወደ ትግራይ ከተላከው የአምስት ቢሊዮን ብር ጥሬ ገንዘን ለወጋገንና ለአንበሳ ባንኮች አንድ ቢሊዮን ብር በነፍስ ወከፍ የተሰጠ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ቀሪው ሦስት ቢሊዮን ብር ተሰጥቶት ነበር።
ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የትግራይ ዲስትሪክቶች የአንደኛው ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብ እንደገለጹት፣ ማኅበረሰቡ በችግር ላይ የነበረ እንደመሆኑ፣ ገንዘቡ በተፈቀደ ጊዜ እርሳቸው የሚመሩት ባንክ ተጨማሪ ገደብ ሳይጥል በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ብቻ በቀን ለአንድ ግለሰብ እስከ 50,000 ብር ወጪ ሲያደርግ ነበር።
ኅብረተሰቡ ተገበያይቶበት ገንዘቡ ወደ ባንኩ ተመልሶ እንደሚመጣም በማሰብ ይህን እንዳደረጉ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ የንግድ ሥርዓቱን እንዳላስተካከለውና ገንዘቡም ተመልሶ ወደ ባንክ እየገባ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት። አክለውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ብቻ ካሉት 24 ቅርንጫፎች ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም እርስ በእርስ በኔትወርክ ተሳስረው እየሠሩ መሆናቸውን፣ አብዛኞቹ ቅርንጫፎችም በገንዘብ እጥረት ምክንያት መክፈል እንዳቆሙ ገልጸዋል።
‹‹በጣም ጥቂት ቅርንጫፎች ናቸው አሁን ሁለትና ሦስት ሺሕ ብር እየሰጡ ያሉት፡፡ እነሱም ግዴታ ሆኖባቸው ገንዘብ ወደ ባንክ ከሚያስገቡ ኩባንያዎች ከሚሰበስቡት እያወጡ ነው፤›› በማለት፣ ቅርንጫፎቹ ከብሔራዊ ባንክ የተሰጣቸውን ገንዘብ ጨርሰው ከገበያው የሚያገኙትን ጥቂት ገንዘብ ብቻ እየከፈሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሽያጭ ገንዘብ ወደ ባንክ እያስገቡ ካሉት ጥቂት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የተወሰኑ የቶታል ኢነርጂ ማደያዎች ብቻ መሆናቸውና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፣ ከእነዚህ ውጪ ሌላ የሚገባላቸው ገንዘብ እንደሌለ ተናግረዋል። ‹‹ጥሬ ገንዘብ አሁንም እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ ነው ከተማ ውስጥ፣ ይኼንን የሚመለከተው አካል ካላስቆመው ለእኛ በጣም ፈታኝ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመድቦለት የነበረውን ሦስት ቢሊዮን ብር ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አከፋፍሎ የጨረሰ መሆኑን፣ ከመንግሥትና ከግል ሽያጮች የሚገኘው ገንዘብ ካለመምጣቱም በተጨማሪ፣ ኅብረተሰቡ በእምነት ማጣት ጥሬ ገንዘቡን አውጥቶ እንደያዘ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ‹‹የጥሬ ገንዘብ አያያዝና የንግድ ሥርዓቱ ቢስተካከል አምስት ቢሊዮን ብር በቂ ይሆን ነበር፤›› ብለዋል።
የወጋገን ባንክ ሀብት ማሰባሰብና ቅርንጫፍ ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእሳቸው ባንክ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ ሌሎች ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ጫናው እነሱም ላይ እንዳለ ነው። የወጋገን ባንክ በሥሩ የታቀፉ ትልልቅ የገንዘብ ዝውውር ያላቸውን ድርጅቶች እንደ መያዙ፣ ከብሔራዊ ባንክም የተቀበለው ገንዘብ እንደ መኖሩና አሠራሩን በማስተካከሉ ብዙም ችግር እንዳልገጠመው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የደንበኞች ከባንክ ገንዘብ አወጣጥን በሚመለከት ወጋገን ባንክ የብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትሎ እየሠራ እንደሆነና ባንኩ ለብቻው የሚመለከታቸው ሁኔታዎች እንዳሉም የገለጹት አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹ጥሬ ገንዘብ ለማውጣት ብቻ በሚል ወዲያው ገቢ ተደርጎላቸው፣ ወዲያው የሚያወጡ ደንበኞች ካሉ፣ ገንዘቡን በጥሬ ብቻ ፈልገው እንደ መተላለፊያ ከሌላ ባንክም እያዞሩ የሚጠቀሙብን ካሉም እሱንም አናበረታታም፤›› ብለዋል።
ወጋገን ባንክ የአማራና የአፋር ክልሎችን ጨምሮ ከጦርነቱ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ፣ ነገር ግን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው 122 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ በአማራ ክልል ያሉት ዘጠኝ ቅርንጫፎች አሁን አገልግሎት መጀመራቸው ተገልጿል፡፡ በአፋር ክልል ያለው አንድ ቅርንጫፍ ግን አገልግሎት መስጠት አልጀመረም ተብሏል፡፡ በትግራይ ከነበሩት 112 ቅርንጫፎች አሁን ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 87 መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አይደር ሆስፒታል መምህር የሆኑትና ላለፉት 21 ወራት ደመወዝ እንዳላገኙ የተናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አምሐ ካህሳይ የታዘቡትን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አምስት ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል የተላከ ጊዜ ባንኮች በቀን 50,000 ብር እየሰጡ ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ የሚሰጡትን የገንዘብ መጠን መቀነሳቸውን፣ በአሁኑ ጊዜም ብዙዎቹ የባንኮች ቅርንጫፎች ጥሬ ገንዘብ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ደመወዝ ባለመከፈሉ እሳቸው ገንዘብ ለማውጣት እንግልት ባይገጥማቸውም፣ በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው እንዳዩት ሁለት ሺሕ ብር ብቻ ከተወሰነ ቅርንጫፍ እየወጣ ነው። ‹‹ጓደኛዬ ከውጭ አገር ሊልክልኝ ፈልጎ የባንክ ሒሳቤ በመዘጋቱ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ሒሳቤ ቢከፈትም ወረፋ ደርሶኝ ዕድል ካለኝ ከሁለት ሺሕ ብር በላይ ልቀበል ስለማልችልም ዋጋ የለውም፤›› ብለዋል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ።
‹‹በየጊዜው ሰው እየሞተ ስለሆነ ገንዘብ አሁን ሕይወት የሚያድን ነው፣ መድኃኒትና ምግብም የሚገዛ ነው። እንደ ስንዴው ዕርዳታና ልመና ሳይሆን ኅብረተሰቡ የራሱን ገንዘብ ነው የባንክ ደጅ እያየ የሚጠብቀው፤›› ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምንም ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ የተናገሩት ሪፖርተር ያናገራቸው በትግራይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ፣ እስካሁን የመንግሥት ሠራተኞችና ጡረተኞች ደመወዝ መከፈል እንዳልጀመሩና በዚህ ሁኔታ ለእነሱም መከፈል እንዲጀመር ቢታዘዝ ችግሩ የባሰ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በመቀሌ ከተማ በተለምዶ ‘ትልቁ ቅርንጫፍ’ የሚባለው ብቻ አገልግሎት ሳያቋርጥ እየሰጠ ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቅርንጫፍ ማውጣት የሚቻለው የገንዘብ መጠንም ሦስት ሺሕ ብር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እዚህ ቅርንጫፍ ወረፋው በጣም ረዥም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ ጥሬ ገንዘብ እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ እንደሆነና ከመሃል አገር ሳይቀር ሰዎች ገንዘብ ወደ ሌላቸው ሰዎች እያስተላለፉ በኮሚሽን እያስወጡ እንደነበር ገልጸው፣ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ‹‹ዋጋ ያስከፍላል›› ሲሉ ተናግረዋል።