Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ በየዓመቱ 90 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሕዝብ እ.ኤ.አ በ2030 ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል የሚለውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ፣ በየዓመቱ እስከ 90 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙት 16,652 አጠቃላይ ከተሞች (የገጠር ከተሞችን ጨምሮ) የአሌክትሪክ አገልግሎት የተዳረሰው 7,962 ለሚሆኑት እንደሆነና ቀሪዎቹ 8,679 ከተሞች እስካሁን ኤሌክትሪክ እንዳላገኙ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከትናንት በስቲያ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል ‹‹ዋና ደንበኞች ከሚባሉትና ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገሮች ተሰባስበው ከቀረፁዋቸው ዘላቂ የልማት ግቦች እንዱ የሆነው እ.ኤ.አ በ2030 ሁሉም አገሮች ለሁለም ዜጎቻቸው ተመጣጣኝና አረንጓዴ ኃይል ያቀርባሉ የሚለው የሚገኝበት ሲሆን፣ ይህንን ተስማምተው ከፈረሙ አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ዕቅዱን ዕውን ለማድረግ በየዓመቱ እስከ 90 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ለዘርፉ ማግኘት እንደሚያስፈልጋት ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን ባለው አካሄዷ ብትቀጥል ሁሉም ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት 20 ዓመታት ይፈጅባቸዋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ገለጻ፣ ዘርፉ በየዓመቱ እስከ 90 ቢሊዮን ብር በጀት ካላገኘ እ.ኤ.አ በ2030 ኤሌክትሪክ ለሁሉም ዜጎች የሚለው ግብ አይሳካም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የዋጋ ንረቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ከፍ እያለ የሚሄድ ከሆነ ወጪውን የባሰ እያናረው እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ያህል አባወራዎች ቢኖሩም እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘው ኅብረተሰብ ቁጥር 4.5 ሚሊዮን መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ዕቅዱን በታቀደው ልክ እንዳታሳካ የበጀትና የግብዓት እጥረቶች ችግሮች ተጠቃሾች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የዓለም ባንክን ጥናት መሠረት በማድረግ እንደተገለጸው፣ በዓለም ላይ የአሌክትሪክ ኃይል ካላገኘው 733 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አራት በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ አጠቃላይ ሕዝቡ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ከተፈለገ 640 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ አባወራዎች እ.ኤ.አ በ2030 በኤሌክትሪክ ለማገናኘት በአማካይ ለአንድ አባወራ 650 ዶላር ሲያስፈልግ፣ በአጠቃላይ 13 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ዕቅድ በሚፈለገው ፍጥነት ማስኬድ ስላልቻለች በዕቅዱ መሠረት ለመተግበር፣ አዲስ የሦስት ዓመታት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡፡

የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ ልማት፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና የሰው ሀብት አቅም ግንባታ፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት፣ እንዲሁም አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም መገንባት ተቋሙ ይፋ ያደረገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የተካተቱ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተብራርቷል፡፡

ተቋሙ በተያዘው ዓመት መጨረሻ የጠቅላላ ደንበኞቹን ቁጥር 5.5 ሚሊዮን ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሦስት ዓመታት ዕቅዱ መጨረሻ ይህ ቁጥር 7.9 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለመተግበር የያዘውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለማስፈጸም የሚያስፈልገው የ‹‹ካፒታልና ኦፕሬሽናል›› በጀት 2.76 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2014 ዓ.ም. ከኃይል ሽያጭ ያገኘው ገቢ 20.94 ቢሊዮን ብር መሆኑንና በተያዘው ዓመት ይህንን ገቢ 33.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እንዳቀደ፣ የሦስት ዓመት ዕቀዱ በሚጠናቀቅበት 2017 ዓ.ም. ከኃይል ሽያጭ ሊሰበሰብ የታሰበው ገቢ 40.2 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሏል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ደንበኞች በሰጡት አስተያየት የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ፣ የሠራተኞች ሥነ ምግባር ችግር፣ የመሠረተ ልማት ስርቆት፣ የአስቸኳይ ጥገና አገልግሎት መዘግየት፣ የንባብ ችግር፣ ለኢንዱስትሪ ደንበኞች ተገቢው ትኩረት አለመስጠትና የማከፋፈያ ጣቢዎች አቅም መዳከም በተቋሙ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገው በሚገኘው የሦስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለመስጠት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሽፈራው ተሊላ ያስታወቁ ሲሆን፣ በዚህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር፣ አገልግሎቱን ማስፋፋት፣ መሠረተ ልማት ማሻሻልና የመሳሰሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. የሦስት ዓመት ስትራቴጂውን አስመልክቶ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለድርሻ አካላት ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ሽፈራው፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የኃይል ፍላጎት እንዳለ፣ ያንን ፍላጎት ማሳካት የሚችል መሠረተ ልማት መገንባት አስፈላጊነቱን አስረድተው፣ በአገሪቱ ከማመንጫ ጣቢያዎች የኃይል አቅርቦት ውስንነት ችግር ባይኖርም፣ የመነጨውን ኃይል ደንበኞች ዘንድ ማድረስና የኔትወርክ አቅም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የፋይናንስ ውስንነት እንዳለበትና ይኼ ደግሞ በዋናነት ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳን ከአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማትና ተቋሙ በራሱ ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ተጠቅሞ እየሠራ ቢገኝም፣ በሚፈለገው ፍጥነት መሥራት አለመቻሉ በውይይቱ ላይ ተገልጾ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች