እናት ፓርቲ ሆን ተብሎ በመንግሥት የማፍረስ ሴራ እየተሸረበበት እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ከሰሞኑ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳያካሂድ በመንግሥት መከልከሉና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ማስፈራሪያና ዛቻ መከፈቱ፣ የማፍረስ ሴራ አካል መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡
የተፎካካሪ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ለጽሕፈት ቤት የሚሆን ቢሮ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በኩል ሲመቻችላቸው፣ እናት ፓርቲ ግን ሆን ተብሎ ለረዥም ጊዜ እንዳያገኝ ተደርጓል ብሏል፡፡
ይህ ሳያንስ ደግሞ ከሰሞኑ የጠራው ጠቅላላ ጉባዔ በመንግሥት ውሳኔ እንዳይካሄድ መደረጉ፣ እናት ፓርቲ ህልውናው እንዳይቀጥል ወይም እንዲፈርስ ከመፈለግ የመነጨ ነው ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡
የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ግርማ ፓርቲያቸው ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ላቀረበው ጥያቄ፣ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኩል ስድስት ኪሎ የሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ እንደተፈቀደላቸው ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የተቃውሞ ሠልፍ ሊጠራ ይችላል የሚል ሥጋት በመፈጠሩና የፀጥታ ሥጋት ሊያጋጥም እንደሚችል በመገመቱ፣ የጉባዔውን ቀን ለማራዘም እንደተገደዱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በተለምዶ እስጢፋኖስ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስብሰባ አዳራሽ ጉባዔውን ለማካሄድ ተፈቀደልን፡፡ ለእሑድ ጉባዔ እየተዘጋጀን ባለንበትና የምርጫ ቁሳቁስ ወደ አዳራሹ እያስገባን ሳለን ግን፣ ዓርብ ከረፈደ በኋላ አዳራሹ በመንግሥት ይፈለጋል ተብሎ ተከለከልን፤›› ሲሉ የቅሬታቸውን መነሻ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው የጉባዔ ቀኑ ስለተቃረበ ወደ 700 የሚሆኑ አባላቱን ከመላው አገሪቱ ጠርቶ እንደነበር አቶ ጌትነት ይገልጻሉ፡፡ ጉባዔው ሊሰረዝ የማይችል በመሆኑ በብዙ ፍለጋ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ስብሰባ አዳራሽን በክፍያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹በዚህ አዳራሽ ጉባዔው እንደሚደረግ ይፋ ስናደርግ ግን ‹የኦርቶዶክስ ፓርቲ የሆነው በሥላሴ አዳራሽ ጉባዔ ሊያደርግ ነው› የሚሉና ሌሎችም የስም ማጥፋት ዘመቻዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ዘመቻ ይደረጉብን ጀመር፡፡ ዛቻዎችም ይደርሱን ጀመር፡፡ በስተመጨረሻ እሑድ ከማለዳው 12፡30 ሰዓት ቶሎ ድረሱ ተብሎ በአዳራሹ ሰዎች ተጠራን፡፡ በቦታው ስንደርስም በፖሊሶች ጉባዔውን ማካሄድ አትችሉም ተባልን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ብዙ ወጪ ወጥቶና አባላቱን ከረዥም ርቀት ጠርተው ሊያካሂዱት ቀጠሮ የያዙበትን ስብሰባ በመጨረሻ ሰዓት መንግሥት ማገዱ፣ ፓርቲውን ሆን ብሎ ለማዳከም የተደረገ ጥረት ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርቲው በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ቀውሶችን በተመለከተ ጠንካራ ትችቶችን ማቅረቡና የመንግሥትን ስህተቶች ማጋለጡ እንዳልተወደደለትና ጥርስ ውስጥ እንዳስገባው ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ፓርቲውን ለማዳከምና ለማፍረስ ሆን ተብሎ በመንግሥት ሴራ እየተሸረበብን ነው የሚል ስሜት እንደተፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግሩ እንዲሰምር፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በሚል ምርጫ በተካሄደ ወቅት ከእነ ችግሮቹ ሒደቱን ደግፈናል፡፡ አገሪቱ በጦርነት ስትፈተን የህልውና ዘመቻውን ደግፈናል፡፡ የውጭ ጫና አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ሲከት የበኩላችንን ተወጥተናል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጌትነት፣ ይህ ሁሉ ተረስቶ መንግሥት ፓርቲውን ለማፍረስ መነሳቱ ካለፈው ሥርዓት ያልተማረና አለፍ ሲልም የባሰ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡