በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ በነበረው የሲኖዶስ ግልበጣ ሙከራ ጋር በተያያዘ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ሁከት ለመፍጠርና ሌላ አጀንዳ ከሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩት ፓስተር ቢኒያም ሽታዬ፣ ከፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሰው ዋስትና ቢፈቀድላቸውም፣ ሳይፈቱ ከርመው በከተማ ሰበር ሰሚች ችሎት ይግባኝ ከተጠየቀባቸው በኋላ፣ ትናንት ምሽት ከ12፡00 ሰዓት በኋላ ፖሊስ ለቋቸዋል፡፡
ፓስተሩ ከእስር የተፈቱት ጠበቆቻቸው መጀመርያ የክስ መዝገብ ተከፍቶባቸው ለነበረው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቤቱታ አቅርበው፣ ፍርድ ቤቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስለሁኔታው ዛሬ ረቡዕ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ነው፡፡
ጠበቆቻቸው ይግባኝ አቅርበው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን እንደማይከበር ሲጠይቁ፣ የአራዳ ፖሊስ ለንፋስ ስልክ ፖሊስ አሳልፎ እንደሰጣቸው ቢያስረዳም፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ እንደለቀቃቸውና የልደታ ፖሊስ በሌላ ወንጀል ጠርጥሯቸው እንዳሰራቸው ሲያስረዳ፣ ጠበቆች ደንበኛቸው (ፓስተር ቢኒያም) የትኛውም ፖሊስ ጣቢያ ቢያስራቸውም፣ የሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲጠይቅላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የኮሚሽኑ ኃላፊ ከንጋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ቀርቦ እንዲያስረዳ ቀጠሮ ሰጥቶ እያለ፣ ምሽት ላይ ፖሊስ እንደለቀቃቸው ጠበቃቸው አቶ ብሩክ ተፈራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ፓስተር ቢኒያም የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠቱን፣ ፖሊስ ይግባኝ ቢልም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ማፅናቱንና ወደ ሰበር ቢሄድም የሕግ ጥሰት እንደሌለ ገልጾ፣ መዝገቡን ከዘጋው በኋላ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ከተማ ፍርድ ቤት መውሰዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡