Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአወዛጋቢነቱ የቀጠለው የነዋሪዎች ቤት ፈረሳ

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የነዋሪዎች ቤት ፈረሳ

ቀን:

ወ/ሮ መስከረም ለማ  ፈረንሣይ ለጋሲዮን ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከፍ ብሎ በሚገኘው ጉራራ ሠፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ ሰባት ዓመት በዓረብ አገር ለፍተው ያገኙትን ጥሪት በማሟጠጥ፣ መንግሥት የአርሶ አደር ልጆች ናችሁ ብሎ በሰጣቸው መሬት ላይ ቤት ሠርተው መኖር ከጀመሩ ስምንት ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ቤት ሠርተው መኖር ከጀመሩ በኋላ በየዓመቱ ለመንግሥት ግብር በመክፈል ይኖራሉ፡፡

ከዚህ በፊት እዚያው አካባቢ ከቤተሰቦች ጋር ይኖሩ እንደነበር የሚያስታውሱት ወ/ሮ መስከረም፣ በሠሩ ቤት እየኖሩ ከባለቤታቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ለዓመታት በቀለሱት ጎጆ ላይ ያለ ሥጋት ይኖሩ የነበሩት እኚህ እናት ባልታሰበ ጊዜ ‹‹ሕገወጥ ቦታ ነው የያዛችሁት›› ተብለው ቤታቸው በላያቸው ላይ መፍረሱን ይናገራሉ፡፡

‹‹ሰባት ዓመት ለፍቼ ባገኘሁት ጥሪት የሠራሁትን ቤት፣ መንግሥት በአንድ ጀንበር ልዩ ኃይሎችን ይዞ በመምጣት በዶዘር ሙሉ ለሙሉ ማፍረሱ ትንግርት ፈጥሮብኛል፤›› ያሉት ወ/ሮ መስከረም፣ የእሳቸውን ጨምሮ በርካታ ቤቶችም በአካባቢው እየፈረሱ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የነዋሪዎች ቤት ፈረሳ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በተለይም ከበፊት ጀምሮ የነበሩ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ከእነ ልጆቻቸው ጎዳና ላይ መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ካርታ ያላቸው ነዋሪዎችም ጭምር ቤቶቻቸው እየፈረሰ መሆኑን የሚናገሩት እኚህ እናት፣ የፈረሰባቸውም አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች መሸሸጊያ አጥተው ጎዳና መውጣታቸውን ዕንባ በተሞላበት ድምፀት ተናግረዋል፡፡

እየፈረሱ ያሉ ቤቶች የቆዩና ሕጋዊ ካርታ ያላቸው ጭምር እንደሆኑ፣ እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ለምን ቤቶቸው እንደፈረሰባቸው ለማወቅ የሚመለከታቸውን አካላት ቢጠይቁም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታችን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹እየፈረሱ ያሉ ቤቶች ሕገወጥ ናቸው ቢባል እንኳን፣ ቤቶቹ ገና በመሠራት ላይ እያሉ መንግሥት ማፍረስ ነበረበት፤›› የሚሉት ወ/ሮ መስከረም፣ አሁንም ቢሆን ችግሩ ያለው ማኅበረሰቡ ጋ ሳይሆን መንግሥት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚያው አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ወ/ሮ ፍሬ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፈረንሣይ ለጋሲዮን ከፍ ብሎ የሚገኘው ጉራራ ሠፈር ለበርካታ ዓመታት ቤተሰብ መሥርተው ይኖሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቤታቸው እየፈረሰባቸው ነው፡፡

ቤታቸውም ከፈረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት እኚህ እናት እንደገለጹት ከሆነ፣ ደንብ አስከባሪዎች ከልዩ ኃይል ጋር በመኪና በመምጣት ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ሰዉ በተኛበት ቤቶቹን አፍርሰዋል፡፡

የፈረሰባቸው ሰዎች መጠለያ አጥተው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከጎረቤት ተጠግተው እየኖሩ እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅት እየፈረሱ የሚገኙ ቤቶች ሕገወጥ ይሁኑ አይሁኑ የሚለውንም ሳያጣሩ ማፍረሳቸውን ገልጸዋል፡፡  

በተለይ ‹ለምን ቤታችን ይፈርሳል?› የሚለውን ጥያቄ አፍራሾቹን ሲጠይቁ፣ የጠየቀውን እስር ቤት እንደሚወረውሩ ገልጸው፣ ወንድማቸውም ይህንን በመጠየቁ ለእስር መዳረጉን ተናግረዋል፡፡

እሳቸውም በዚያው ቤት ሠርተው መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት ማስቆጠራቸውና የአካባቢውም ተወላጅ መሆናቸውንን፣ እስካሁን የቤተሰቦቻቸው ቤት ግን አለመፍረሱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ቤቶች እየፈረሱ መሆናቸውን በተለይም ሕጋዊ ቦታ ይዞታ ያላቸው ቤቶች ጭምር እየፈረሱ መሆኑ፣ ነገሩ ፖለቲካዊ ቅርፅ እንዲይዝ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ቤት የፈረሰባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ውልደትና ዕድገታቸው እዚያው አካባቢ መሆኑን፣ ቤት ሠርተው ሊኖሩ የቻሉትም ከቤተሰቦች ባገኙት ቁራሽ መሬት እንደሆነ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እናት እንደገለጹት፣ መንግሥት ሰጠኝ ከሚል ግለሰብ ላይ 1.2 ሚሊዮን ብር በማውጣት መሬት ገዝተው ቤት ከሠሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡፡ ከዚህ በፊት ይኖሩ የነበሩት ቡራዩ አካባቢ መሆኑን፣ እዚያም ያለው ቤት ሕጋዊ ካርታ ያለው እንደነበርና እሱን ሸጠው ወደ እዚህ ሊገቡ እንደቻሉ  ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፈረሰባቸውን ቤት ሲገዙት የአየር ካርታ አለው ተብሎ እንደተሸጠላቸው፣ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የሠሩት ቤት ሕገወጥ ነው ተብሎ ሊፈርስባቸው እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

በተለይ የገዙት ቦታ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ በመሆኑ ሲገዙትም ሆነ ቤቱን ሲሠሩ ምንም ዓይነት ሥጋት እንዳልነበራቸው፣ ይሁን እንጂ ደንብ አስከባሪዎችና የክልል ልዩ ኃይል ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ መጥተው ጊዜና ገደብ ሳይሰጣቸው ቤታቸውን እንዳፈረሰው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቦታውንም የሸጠላቸው ግለሰብ የት እንደገባ እንደማያውቁ፣ እንደ እሳቸው ዓይነት ቦታ ገዝተው ቤት የሠሩ ሰዎችም የሸጡላቸውን ሰዎች አግኝተው ገንዘባቸውን እንዳስመለሱ ተናግረዋል፡፡

ከቡራዩ አካባቢ ካርታ ያለውን ቦታቸውን ሸጠው እዚህ ሲገቡ ከባለቤታቸው ጋር መጋጨታቸው ያስረዱት እኚህ እናት፣ አሁን ላይ አራት ልጆቻቸውን ይዘው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን እንዲሁም ትዳራቸው መፍረሱን አክለው ገለጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በሠፈራ አካባቢ ከአርሶ አደር ላይ ቦታ ገዝተው ቤት ሠርተው ከአሥር ዓመት በላይ የኖሩት አቶ ደምሴ ቶላ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ወጪ አውጥተው ቦታ የገዙ ሰዎች ቤታቸው ያላግባብ እየፈረሰ ነው፡፡

‹‹በቅርቡም በአካባቢው ላይ የመንግሥት አካላት ቤት እያፈረሱ ነው፤››  የሚሉት አቶ ደምሴ፣ በዚህ አካባቢ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለመንግሥት በየዓመቱ ለቦታው ግብር በመክፈል ሲኖሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሁን ወቅት ቤተሰቦቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ይዘው ዘመድ ተጠግተው እየኖሩ መሆኑን የሚናገሩት እኚህ አባት፣ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ሲሰጥ ሕገወጥና ሕገወጥ ያልሆኑ ቦታዎች መለየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ቤት የፈረሰባቸው ዜጎች ያላቸውን ጥሪት በማሟጠጥ ቤት መሥራታቸውን ከዚህ በፊትም መንግሥት በአካባቢው ላይ ቤት ሲያፈርስ የእሳቸውን ቤት ተዘሎ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

በእርግጥ በአካባቢው አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቤት የሠሩት ከአርሶ አደር በገዙት ቦታ ላይ መሆኑን፣ ሕጋዊ ካርታም የሌላቸው ነዋሪዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ ቢሆንም ከሥር መሠረቱ ይህን አሠራር ቢከተል ይህ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እዚያው አካባቢ ኑሯቸውን ያደረጉ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ንጉሤ እንደተናገሩት፣ እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በአካባቢ ላይ ብዙ ዓመት ኖረዋል፡፡

በአካባቢው ቤተሰብ መሥርተው መኖር ከጀመሩ አሥራ አራት ዓመት ማስቆጠራቸውን የተናገሩት እኚህ እናት፣ ደንብ አስከባሪዎች ከፖሊሶች ጋር በመምጣት ሕገወጥ ነው ብለው ቤታቸውን እንዳፈረሱባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹በከፍተኛ ወጪ የሠራሁን ቤት በአንድ ቀን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሲፈርስ ማየት ያማል፤›› የሚሉት እኚህ እናት፣ በአሁኑ ወቅት አንድ ልጃቸውን ይዘው ቤተሰቦቻቸው ጋ መቀመጣቸውን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ባለበት አገር እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም ማየት አዲስ አለመሆኑን፣ ችግሩም ከዚህ በፊት የነበረና በርካታ ዜጎችን ያማረረ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢውም በርካታ ቤቶች እየተለዩ እያፈረሱ መሆኑን፣ ነዋሪዎቹም ‹‹ለምን ቤታችን ይፈርሳል?›› የሚለውን ለማወቅ የመንግሥት ተቋማትን በር ቢያንኳኩም ምላሽ እንዳላገኙ ተናገግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅም በአዲስ አበባ ከተማና በቅርቡ በተመሠረተችው በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቤቶቻቸው እየፈረሰባቸው መሆኑን ሪፖርተር በቦታው በመገኘት ለመመልከት ችሏል፡፡  

ጉዳዩን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሕገወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ ከተማው ሕጋዊ ባህሪን እንዲይዝ ይደረጋል፡፡

ከዚህ በፊት ጠንከራ የሆነ አስተዳደር ባለመኖሩ በርካታ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ መሥፈራቸውን የተናገሩት ከንቲባው፣ በተለይም ፈቃድ ሳይኖር መብራትና ውኃ በማስገባት ይጠቀሙ የነበሩ ዜጎች ችግሩን አባብሰውታል ብለዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች በማስወገድ አንድ ሰው ሕጋዊ በሆነ መልኩ ካርታ መውሰድ እንዳለበት ገልጸው፣ በዚህ መሠረት ሁሉን ነገሮች ሳያሟሉ መብራት ወይም ውኃ ስለገባ ሕጋዊ ነው ማለት አይቻልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተቋሙ በኩል ባሉ ክፍተቶች የተነሳ መብራት፣ ውኃና ሌሎች ነገሮችን አውጥተው መኖር የጀመሩ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነና ይህንንም አሠራር ለመቀልበስ ተቋሙ እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በክልል ደረጃም ሆነ በከተማ ትልልቅ ፕሮግራሞችን በማውጣት አሁን ላይ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ችግር የሚታየው በሚዘረጋው አሠራር መሆኑን ተሾመ (ዶ/ር) ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እየፈረሱ ያሉ ቤቶች ብሔርን ተኮር ያደረጉ አለመሆናቸውን፣ ሰዎቹ ቤታቸው ከመፍረሱ በፊት ተቋሙ ነዋሪዎችን ማነጋገሩንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ቤት የፈረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ተቋሙ ሰፊ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውሰዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...