በአበበ ፍቅር
ትምህርት መሠረታዊና ሰብዓዊ መብት ከመሆኑ ባሻገር ዘላቂነት ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እውን ለማድረግ የሚያስችልም ትክየለሽ መሣሪያ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳትም መንግሥት በፆታ፣ በአካላዊ ሁኔታ፣ በቋንቋ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ እንዲሁም በሃይማኖት ያልተገደበ ትምህርት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ተናግሯል፡፡
መንግሥት እየሠራ ከሚገኝባቸው ውስጥ አካል ጉዳተኞች እንደ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ሥልጠና አገልግሎት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሕግና የፖሊስ ማዕቀፎች ቀርፆ ሥራ ላይ ማዋሉ ይገኝበታል፡፡
ኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት አንቀጽ 41 እና 91 መንግሥት የመልሶ ማቋቋሚያና የድጋፍ አገልግሎቶችን ለአካል ጉዳተኞች የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
ከዚህም በላይ መንግሥት ለአካቶ ትምህርት አግባብነት ያላቸውን ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች፣ ኮንቬንሽኖችና ደንቦች በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ትኩረት የሰጠውን የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ኮንቬንሽንን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ2006 በማፅደቅ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ በ1986 ዓ.ም. ፀድቆ በተግባር ላይ የዋለው የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ ጥራት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ የመብት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ልማትን የማረጋገጫ ዋስትና መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡
የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርትን ልዩ ፍላጎት ላለቸው ሕፃናትና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራም ስትራቴጂ በ1998 ዓ.ም. ቀርፆ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ስትራቴጂው በሥራ ላይ ባዋለባቸው አምስት ተከታታይ ዓመታት ከተገኙ ውጤቶች መካከልም የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራሞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መጀመራቸው ይገኝበታል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአርብቶ አደርና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዲስክ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት በቀለ እንደነሩን፣ በትግበራ ወቅት በገጠሙ ችግሮች ምክንያት የታለመለትን ግብ ማሳካት ባለመቻሉ በ2004 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ1998ቱን ስትራቴጂ በማሻሻል የተጠናከረ የአካቶ ትምህርት በመንደፍ ሥራ ላይ አውሎ ነበር፡፡
ይህ ስትራቴጂ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ከአዲሱ የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ ጋር ለማስማማት እየተሻሻለ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በዓለም 15 በመቶ በኢትዮጵያ ደግሞ 17.6 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል አካል ጉዳተኞች ናቸው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2011 ያወጣው ጥናት ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል በዓለም ላይ 258 ሚሊዮን የሚጠጉ የልዩ ፍላጎት ለትምህርት ዕድልን ያላገኙ ወጣቶች፣ ሕፃናትና ጎልማሶች ይኖራሉ ሲል ግሎባል ኤዱኬሽን ሞኒተሪንግ በ2020 ላይ ሪፖርቱ አስነብቧል፡፡
በኢትዮጵያ የጎላውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከሚሠራው በተጨማሪ የአገር ውስጠና የውጭ ድርጅቶች የመንግሥትን ሥራ ይደግፋሉ፡፡
ከነዚህም አንዱ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት ከመንግስት ጋር በመተባበር የአካቶ ትምህርትን በመላ ኢትዮጵያ ሲሰጥ የቆየው ቴክኒካል ሰፖርት ፎር ኢንክሉሲቭ ኤዱኬሽን በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡
የፕሮጀክቱ ኃላፊዎችም ከችግሩ ስፋት አንፃር መንግሥት ብቻውን ለውጥ ማምጣት ስለማይችል፣ በጥናት ላይ ተመርኩዘው ባለፉት አራት ዓመታት ውጤት ማስመዝገባቸውን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ1.4 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ወደሥራ ሲገባ፣ አካል ጉዳት ያለባቸውና የሌለባቸው ተቀላቅለው የሚማሩ በመሆኑ፣ ወላጆችና መምህራን ‹አካል ጉዳተኞች ለብቻቸው መማር አለባቸው፣ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ ተማሪዎች ጋር መማር አይችሉም› ብለው ሞግተውባቸው እንደነበር የፕሮጀክቱ ዋና አማካሪ ጥበቡ ቦጋለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ከወላጆችና ከመምህራን ጋር ቀርበው በመወያየትና ሥልጠና በመስጠት ከሞላ ጎደል አምነውበትና ግንዛቤ ይዘው ተሳትፎ በማድረጋቸው ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ጥበቡ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
24 ሺሕ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ለማስተማር አቅደው ወደ ሥራ እንደገቡ የገለጹት ዋና አማካሪው፣ በተፈጠረው የኅብረተሰብ የግንዛቤ ለውጥና መማር ማስተማሩ በመሻሻሉ ከ90 ሺሕ በላይ ተማሪዎች የልዩ ፍላጎት (የአካቶ) ትምህርት ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ለእነዚህ ተማሪዎች ትግራይ ክልልን ሳይጨምር በመላ ኢትዮጵያ 800 ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና 9,000 መምህራንን በማሠልጠን ላለፉት አራት ዓመታት መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡
10 ሚሊዮን የሚጠጉ የአካቶ ትምህርት የሚሹ ሕፃናትና ወጣቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ጥበቡ (ዶ/ር)፣ ሁሉንም የልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎችን በአካቶ ትምህርት ማስተማሩ ተደራሽነቱን ያሰፋዋል ብለዋል፡፡
የአካቶ ትምህርት ፍላጎት ካለው ስፋት የተነሳ ለአካል ጉዳተኞች ተለይቶ ትምህርት ቤትን መገንባትና ማስተማር የመንግሥትን አቅም የሚፈትን ስለሆነ፣ መደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው አብረው እንዲማሩ ማድረግ ተገቢ ነው ያሉት ዋና አማካሪው፣ ለዚህም ከፕሮጀክታቸው ጥንካሬና ድክመት ልምድ በመውሰድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የአራት ዓመት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰው ፕሮጀክቱ፣ የአካቶ ትምህርት ፕሮግራምን ለማስቀጠል ሌሎች ረጂ ድርጅቶች በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ጥበቡ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በግጭት ላይ ከቆዩ አካባቢዎች ውጭ ባሉ አካባቢዎች በርካታ መልካም ጅማሮን አሳይቷል ሲሉም ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል፡፡
ለአካቶ ትምህርት ድጋፍ ሰጪዎችና ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ለውጥ በማምጣት፣ ለተማሪዎች የሚደረጉ ድጋፎችን በአግባቡ እንዲደርሳቸው በማድረግ ረገድ ፕሮጀክቱ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት 113 የድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንደነበሩ አንስተው፣ የነበረውን አኃዝ ወደ 800 ከፍ በማድረግ የትምህርት መስጫ ተቋሞች እንዲስፋፉ ማድረጋቸውን ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡
3 ሺሕ አካል ጉዳተኞች ብቻ የትምህርት ዕድልን ያገኙ እንደነበር ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ላለፉት አራት ዓመታት ተማሪዎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ከመንግሥት አቅጣጫ ተሰጥቶት ቢነሳም በተሠሩ ሥራዎች ከ80 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡
ከታየው ለውጥ በመነሳት ለዘንድሮ ለቀጣይ ዓመት የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ ስድስት መቶ ተጨማሪ የድጋፍ መስጫ ማዕከላት ለማቋቋም መታሰቡን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡