Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፕላስቲክ ጠርሙስ ሰብሳቢ ማህበራትን ችግር ያቃልላል የተባለው ድጋፍ

የፕላስቲክ ጠርሙስ ሰብሳቢ ማህበራትን ችግር ያቃልላል የተባለው ድጋፍ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በዓለም ላይ በየዓመቱ እስከ አምስት ትሪሊዮን ፕላስቲክ ለዕቃ መያዣነት ጥቅም ላይ እንደሚውል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2018 ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ሆኖም ፕላስቲኮችን መልሶ ቅጥም ላይ ለማዋል ጥረቶች ቢኖሩም፣ ከፕላስቲክ ከተሠሩ ዕቃዎች 79 በመቶ የሚሆነው እንዲሁ የሚጣል ነው፡፡ ከሚጣሉት የፕላስቲክ ዕቃዎች ውስጥ ደግሞ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ የተለያዩ ፈሳሾችን የሚይዙ ይገኙበታል፡፡

ያደጉ አገሮች ይህንን ችግር ለመቅረፍ የውኃና ከአልኮል ነፃ የሆኑ መጠጦች መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን፣ ተጠቃሚዎች ከተጠቀሙ በኋላ መልሰው እንዲሰጡ ለማድረግ ተጠቃሚች ገንዘብ የሚያገኙበትን መመርያ አውጥተው መሥራት ጀምረዋል፡፡ የተመለሱ የፕላስቲክ ጠርሙሶችም ደግሞ ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡

ጀርመን ይኼንን የፕላስቲክ ምርት ደግሞ ሥራ ላይ ከሚያውሉት አገሮች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡

የችግሩ ሰለባ በሆነችው ኢትዮጵያም የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች በየቦታው መጣል በሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በዕፅዋት ጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለይዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡

በአዲስ አበባም በርካታ ወጣቶች በጋራም ሆነ በግል የፕላስቲክና ሌሎች ተረፈ የደረቅ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብና ለፋብሪካዎች በማስረከብ ይሠራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ሥራው አድካሚና ብዙ ጉልበትን የሚጠይቅ በመሆኑ በሥራው ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሚሰበስቡት ፕላስቲክና የሚከፈላቸው ገንዘብ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

አጋጣሚው ለወጣቶቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለከተማዋ ፅዳት ትልቅ መሣሪያ ቢሆንም፣ እነዚህን ወጣቶች መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ኮካ ኮላ ቤቨሬጅ አፍሪካም በአዲስ አበባ ፕላስቲክ በመሰብሰብ በማኅበር የተደራጁትን እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

ኮካ ኮላ ቤቬሬጅስ አፍሪካ፣ (ሲሲቢኤ)፣ በከተማዋ በማኅበር ተደራጅተው የፕላስቲክ ጠርሙስ ለሚሰበስቡ ወጣቶች የመሰብሰብ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለውን የድጎማ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡

ፕሮግራሙ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን፣ አሥር ሚሊዮን ብር በመበጀት ወደ ሥራ መግባቱን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ለ30 ማኅበራት ድጎማ እንደሚያደርግ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ማኔጄኒግ ዳይሬክተር ዳሪል ዋልሰን ተናግረዋል፡፡

ድጎማው ለማኅበሮቹ በአፈጻጸማቸው መሠረት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሲሲቢኤ ኢትዮጵያ በአንድ ወር ውስጥ አንድ ቶን ፕላስቲክ ለሚሰበስቡ ማኅበር 15,000 ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሮቹ በግል እየሰበሰቡ ለሚያስረክቧቸው ሰዎች ከዚህ በፊት ሲረከቡበት ከነበረው ላይ በኪሎ ሁለት ብር እየጨመሩ እንዲገዟቸው ያሳሰቡ ሲሆን፣ ጭማሪውንም ድርጅቱ እንደሚከፍል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በዓለም ላይ ያለውን የፕላስቲክ መጠን ለመቀነስና ችግሩን ታሪክ ለማድረግ ኩባንያው በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ያነሱት ሚስተር ዳሪል፣ እ.ኤ.አ. በ2030 በፋብሪካዎቹ የሚመረተውን የፕላስቲክ ጠርሙስ መቶ በመቶ ለመሰብሰብና እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል ዕቅድ መያዛቸውን አብራርተዋል፡፡

በተለይ ካለፉት አሥርት ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የፕላስቲክ ቆሻሻ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የከተማ ደረቅ ቆሻሻና የሕግ ትግበራና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እስከ 420 የሚደርሱ ድርጅቶች ምርታቸውን በፕላስቲክ ጠርሙስ አሽገው ለገበያ እንደሚያቀርቡ አንስተው፣ እነዚህ ድርጅቶች ያሸጉበትን ፕላስቲክ መልሰው እንዲሰበስቡ የሚያደስገድድ ሕግ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የፕላስቲክ መጠንን ከዓለም ዙሪያ ለመቀነስ በርካታ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም፣ አሥር በመቶ የሚሆነው ብቻ እየተሰበሰበ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ አምስት በመቶ ብቻ የሆነው የፕላስቲክ ቆሻሻ መሰብሰቡን አቶ ግርማ አንስተዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለል የአጋር ድርጅቶችንና የወጣቶችን እንቅስቃሴ ማበረታታትና የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት ኃላፊነታቸውን አንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቆሻሻን በአግባቡ ከያዙት ትልቅ ሀብት ነው፣ ካልሆነ ግን ለከፋ ችግር ያጋልጣል፤›› ያሉት የአዲስ አበባ የፅዳት ማኔጅመንት ኤጀንሲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ግርማ ናቸው፡፡

በቀን ከ250 ቶን በላይ ቆሻሻን የምታመነጨው አዲስ አበባ ከጉያዋ የሚወጣውን ቆሻሻ በወቅቱ ማስወገድ ካልተቻለ፣ ኅብረተሰቡ ለበሽታ ከመጋለጡም ባሻገር የጎርፍ መውረጃ ቱቦዎችን በመዝጋት በዝናብ ወቅት ለከፋ የጎርፍ አደጋ ያጋልጣል ብለዋል፡፡

የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ለመሰብሰብ የኤጀንሲው ዋና ትኩረት መሆኑን ያነሱት አቶ ካሳሁን፣ ከተማዋን ከማፅዳት በተጨማሪ ለወጣቶችም ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ኩባንያው ውስጥ ባለፉት 64 ዓመታት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እየሠራ ነው ያሉት ሚስተር ዳሪል፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋና በባህር ዳር ከሚገኙ ፋብሪካዎች በተጨማሪም በቅርቡ በሰበታ ከተማ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ግዙፍ ፋብሪካ ማስመረቁን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ለ3,500 ሰዎች ቀጥታ የሥራ ዕድልን የፈጠረ ሲሆን፣ ከ75,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የእሴት ሰንሰለት ተጠቃሚ ማድረጉንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...