የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) 6.5 ሚሊዮን ብር (120 ሺሕ ዶላር) የሚገመቱ የሕግ መጻሕፍትን ለሕግ ትምህርት ቤቶች መማርያ እንዲውሉ ለገሰ። እነዚህ የመማሪያ መጻሕፍት ኢትዮጵያውያን የሕግ ምሁራንና ጠበቆች ያዘጋጁት በአሜሪካው የተራድዖ ድርጅት በኩል በቀረበላቸው የቴክኒክ ድጋፍ አማካይነት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ የኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር እነዚህን የመማሪያ መጻሕፍት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ አርባ የሕግ ትምህርት ቤቶች በማደል ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ ዲግሪ የሕግ ተማሪዎችን ለማሠልጠን ይሠራል።በኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር አማካይነት ለየተቋማቱ የሚታደሉት እነዚህ የመማሪያ መጻሕፍት በተለይ የሚያገለግሉት የሕግ ትምህርት ለሚከታተሉ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ትምህርት ቤቶች ያሏቸው አርባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ፣ እነዚህም ትምህርት ቤቶች የቅድመና የድኅረ ምረቃ ኮርሶች እንዳላቸው፣ ይህም ሆኖ ግን ደረጃውን የጠበቀና በሚገባ የተጠና፣ አጠቃላይና ወቅታዊ የሆነ የሕግ መጻሕፍት እጥረት እንዳለባቸው፣ ይህንንም ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ለቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የሚውሉ መጻሕፍትን ማበርከት እንደቻለ ነው ዓለም አቀፍ ድርጅቱ የገለጸው፡፡
የተበረከቱትም መጻሕፍት የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ (የተሻሻለው እትም)፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት (የተሻሻለው እትም)፣ የኢትዮጵያ የታክስ ሕግና የአሠሪና ሠራተኛ ሕግን ያካተቱ መሆናቸውን ድርጅቱ አመልክቶ፣ ኢትዮጵያን በዳኝነትና በዓቃቤ ሕግነት፣ በጥብቅናና በፖሊሲ አማካሪነት ማገልገል የሚችሉ 2,000 የቅድመ ምረቃ የሕግ ተማሪዎች የመጻሕፍቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙና መጻሕፍቱ ለማንበብ የሚፈልጉ በማኅበሩ ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚችሉ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡
የሕግ መማርያ መጻሕፍቱን በአዲስ አበባ ኤሊሊ ኢንተርናሽናል የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት፣ የዩኤስኤአይዲ/የኢትዮጵያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አደም ሽሚት ለሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ለደረሶልኝ የኔአባት አስረክበዋል፡፡በዕለቱም ከተለያዩ የሕግ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ የተማሪዎች ተወካዮች፣ ዲኖችና መምህራን ከሲቪክ ማኅበራትና የፍትሕ ተቋማት ጋር ተገኝተዋል።ዩኤስኤአይዲ እ.ኤ.አ በ2022 ብቻ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ መስጠቱንም ጠቁሟል።