እንደሆነው ቀርቶ – እንዳልሆነው አርገው
ቀጥቅጠው፣ በጥብጠው – ቀይጠው ከጠጡት
ታሪክ ግራዋ ነው – ከትናጋ አይወርድም – አይችሉም ሊውጡት፤
የሆነውን አምነው – ያልሆነውን ትተው
መርገው ሳይሆን ፈልጠው
ጠርበው ሳይሆን ጓጉጠው – ታዛ ካስደገፉት
ታሪክ ወይራ እንጨት ነው
ዘመንና አገርን – ከሕዝብ ጎጆ ጋር
ሽሕ ዕድሜ ያኖራል – የቤት ምሶሶ ነው – አይችሉም ሊጥሉት፤
ዓድዋም እንዲያ ነው – ግራዋና ወይራ
ድልና ሽንፈት ነው – ጣፋጭ ከመራራ፡፡
* * *
ተቀበል አዝማሪ…
‹‹እንዴው ዘ ራ ፌ ዋ…
ያልተጻፈ አንባቢ – በሞላበት አገር
ታሪክ ያበላሻል – ታሪክን መናገር፤››
ይህንን አዝማሪ…
በል ግጠም ይለዋል – የዚህ ዘመን ግጥም
ከቶ እንዴት ይቀበል – ታሪክ ሳያጣጥም?!
(ከማራራቅ ተምኔት – ከዘር አቡጊዳ
እንደ ህያው ጥበብ – ጥላቻ ሲቀዳ
በል ያለው ጊዜ ነው – የሆነው ባለዕዳ!)
* * *
አዝማሪ ቀጠለ…
‹‹ነይ ነይ ዘ መ ድ ዬ…
እልፎች አንድ ሆነው – በሞቱበት አገር
ይኸው ነውር ሆኗል – ታሪክን መናገር፤››
ይህንን አዝማሪ..
የሄደ፣ የመጣ – ‹‹ታሪክ›› ተናጋሪ – ሐተታ መንዛሪ
ከአገር ታሪክ ላይ – የጎጥ አፅምና – አጥንት ዘርዛሪ
ድንገት አመሻሽ ላይ – ጠጪ እንደደከመ – ሰው እንደዛለ አይቶ
በል ይለው ጀመረ – ከሕዝቦች ታሪክ ላይ – ግለሰብ ለይቶ፤
ይህንን እያየሁ
እኔ እንዲህ እላለሁ፤
‹‹ምኔ ነው ዓድዋ?
ምኔ ነው ሶሎዳ?
ምኔ ነው ምኒልክ?
ምኔ ናት ጣይቱ?
ምኔ ነው አሉላ?
ምኔ ነው ዲነግዴ?
ምኔ ነው ጎበና?
ምኔ ነው ገበየሁ?
ምንድኔስ ነው ባልቻ?
ለሚል ጥያቄያችሁ – በታሪክ ስልቻ
አንድ ነው ምላሹ – ሺሕ ጊዜ አንድ ብቻ!!
ምክንያት፤
ግራዋ ነው ሲባል – ቅጠሉ መራራ
በታሪኩ ኮርቶ – ታሪክ ለሚሠራ
ዓድዋ ባላ ነው – ትልቅ የአገር ወይራ!!
* * *
በል አሁን ተቀበል – በል አዚም አዝማሪ
ታሪክ አይበርዝም – ድሮም ታሪክ ሠሪ፤
‹‹እንዴው ዘ ራ ፌ ዋ…
ዓድዋና ወይራ – ከፍ ካሉ በአገር
ከታሪክ በላይ ነው – ታሪክን መዘከር – ታሪክን መናገር!!››
– (ደመቀ ከበደ – ዓድዋ ድልድይ፤ አዲስ አበባ)