Thursday, March 23, 2023

የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ተቃርኖ የደቀነው አገራዊ ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በታሪክ አጋጣሚ የሺሕ ዓመታት አገረ መንግሥት ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊነት በእጁ ላይ የወደቀው ብልፅግና ፓርቲ፣ ይህን ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣቱ ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ በተለይ በፓርቲው ውስጥ በየጊዜው የሚያገረሸው ተቃርኖና ቁርቁዝ ከራሱ አልፎ ለአገር የሚተርፍ ቀውስ እንዳይፈጥር የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡

‹‹የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል›› እንደሚባለው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርቲው ውስጣዊ ችግሮቹን ለመፍታትና ለማጥራት ተወያየ እየተባለ፣ መልሶ በሚታይ ደረጃ በውስጡ ሽኩቻ መስተዋሉ የተለመደ እየሆነ መጥቷል ተብሎ እየተተቸ ነው፡፡

ብልፅግና ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለሦስት ጊዜ ያህል የውስጥ ችግሮችን ለማጥራት ስብሰባ ተቀመጠ መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ፓርቲው የፓርቲነት ተክለ ቁመና አለው ወይ? የሚል ጥያቄ ሁሉ እያስነሳ ነው፡፡ በተለይ ዛሬ ታረቁ ተብሎ በማግሥቱ የሚቆራቆዙት የአማራና ኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች ሁኔታ አሥጊነት በሰፊው መነጋገሪያ እየሆነ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች ታርቀው የማይቆዩትና በተቃርኖ በተሞላ ግንኙነት ውስጥ የወደቁት ለምንድነው የሚለው የወቅቱ ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ ለሁለት ቀናት የተደረገው የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች ስብሰባ፣ ከከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የተለየ ውጤት ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ ፈጥሮ ነበር፡፡

ብዙ የተጠበቀው የሁለቱ ኃይሎች ንግግር ሲጠናቀቅ ግን የተሰጠው መግለጫ፣ በመናበብና በጋራ መግባባት ችግሮችን እንፈታለን ከሚል ንግግር የዘለለ አልነበረውም፡፡ በተጠበቀው ልክ አገር አቀፍ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ማብራሪያ ከመግለጫው አለመደመጡ፣ በስብሰባው ላይ የተለያዩ ግምቶችና ሐሜቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ባለሥልጣናት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በትንሹ ከሁለት ጊዜ በላይ መግለጫ ሲሰጡ ነበር፡፡ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል የኦሮሚያና የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊዎች ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ፣ በባህር ዳር ከተማ የተደረገውን የሁለቱን ብልፅግናዎች ስብሰባ ተከትሎ የጋራ መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡

በዚህ የጋራ መግለጫ የሁለቱ ብልፅግና ባለሥልጣናት የጋራ መግባባት ስለመፍጠራቸው ተናግረውም ነበር፡፡ ከወራት ቀደም ብሎ በተደረጉ ምክክሮች ማግሥትም ሆነ በሌሎች የፓርቲ ስብሰባዎች ወቅት የብልፅግና ፓርቲ አባል ድርጅቶች ስለመግባባት ያልተናገሩበት ጊዜ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የብልፅግና አባል ፓርቲዎች በየፊናቸው በሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ በመካከላቸው ያለውን መግባባት ሳይሆን እየሰፈነ ያለውን ልዩነት የሚጠቁም ሲሆን ነው የሚታየው፡፡

ከሰሞኑ በአማራና በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች መካከል ስለሰፈነው ልዩነትና ልዩነቱን ያጠባሉ ተብለው ስተለካሄዱ ውይይቶች አስተያየት የሰጡት አቶ ቹቹ አለባቸው፣ ጉዳዩ በመግባባትና በውይይት ብቻ የሚታለፍበት ደረጃን ስለማለፉ ይናገራሉ፡፡

‹‹ለጉዳዩ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ደግሞ ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መንገድ የሚሰጥ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባል የነበሩትና በሁለቱ ፓርቲዎች ማለትም በኦሮሚያና በአማራ ብልፅግና ፓርቲዎች መካከል ሲካሄዱ የቆዩ የከዚህ ቀደም ምክክሮችን በቅርበት የታዘቡት አቶ ቹቹ፣ ሁለቱ ፓርቲዎች ተስማምተው መቀጠል መቻላቸው ለአገር ወሳኝ ነው ሲሉ ያሰምሩበታል፡፡

‹‹በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል መተማመንና መስማማት ሊደረስባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፤›› በማለት፣ ‹‹ሁለቱ አገሪቱን በመምራት ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ፓርቲዎች ቢስማሙ ለአገራዊ አንድነት ወሳኝ ጠቀሜታ አለው፤›› ሲሉም ያወሳሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅሬታ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ቹቹ፣ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ አትገቡም የሚባሉ መንገደኞች ጉዳይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት፣ እንዲሁም በዙሪያዋ ባለው የሸገር ከተማ አስተዳደር መኖሪያ የማፍረስ ዘመቻ ያስከተለው የዜጎች መፈናቀል ሁለቱን ፓርቲዎች ካላግባቧቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩልም በወለጋና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውና ለጉዳት መዳረጋቸው ፓርቲዎቹን አቃቅሯቸዋል ይላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው ውጥረት፣ የፓርቲዎቹን ልዩነት እያሰፋው መምጣቱን ነው በተለየ ሁኔታ ያነሱት፡፡

የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በአንገብጋቢነት እያነሳው ስላለ ጉዳይ የጠቀሱት አቶ ቹቹ፣ ‹‹የአማራን ሕዝብ ከውርደት መታደግ›› የሚል አጣብቂኝ መሀል መውደቁን ገልጸዋል፡፡ በአማራ ብልፅግና ውስጥ ተክደናል የሚል ስሜት መፈጠሩንም አክለዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ መስፍን አማን በበኩላቸው፣ ‹‹ባህር ዳር፣ አዳማና አዲስ አበባ እየተመላለሱ ስብሰባ በመቀመጥ ብቻ የሁለቱ ብልፅግናዎች ችግር አይፈታም፤›› ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የሁለቱ ብልፅግና መሥራቾች ማለትም የኦሕዴድና የብአዴን ታክቲካዊ አጋርነት ሕወሓትን ከነበረው የሥልጣን የበላይነት ማስወገዱን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹አሁን ግን ያንን ዓይነት አጋርነት ሳይሆን በሁለቱ መካከል ጠንካራ መገፋፋት እያየን ነው፤›› በማለትም ያስረዳሉ፡፡

አቶ መስፍን እንሚናገሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ በመካከላቸው ያሉ ችግሮችን አድበስብሰው ማለፍ አይችሉም፡፡ ‹‹አንፃራዊ መግባባትም ሆነ መለሳለስ በመካከላቸው የተፈጠረውን ከባድ ልዩነት አይፈታውም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ብልፅግናዎች በተለይም የአማራና ኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች በመካከላቸው እንዳለ ለሚነገረውና በተለያዩ መግለጫዎቻቸው ላይም ሲንፀባረቅ ለሚታየው ሽኩቻ መፈታት ያላቸው ፍላጎት አሁን ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ እንደሚገኝ፣ ሁለቱ ወገኖች ችግራቸውን በግልጽ ለመፍታት ከፈለጉ ስብሰባዎቻቸውን በዝግ ማድረግ አልነበረባቸውም የሚል ሙግትም ይሰማል፡፡

በሌላ በኩል የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግናዎች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎች ብልፅግና ፓርቲዎች ሚናም ለመላው ብልፅግናና ለአገራዊ ፖለቲካ ጤናማነት ድርሻው ከፍተኛ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ በአማራና ኦሮሚያ ብልፅግናዎች መካከል የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ጭብጦች በግልጽ አለመታወቃቸው፣ ችግራቸው ላይፈታ ይችላል የሚል ግምት ካሳደሩ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡

የሰሞኑን ስብሰባ ተከትሎ የሁለቱ ፓርቲዎች ቁንጮ አመራሮች ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን አልተገኙም መባሉ፣ የውይይቱን ችግር ፈቺነት ጥያቄ ውስጥ የጣለ ነው ተብሏል፡፡

ግንባር ተብሎ ለረዥም ጊዜ የቆየውን ኢሕአዴግ የተካ ብልፅግና ሲመሠረት ሁሉንም ያዋሀደ ድርጅት ይመስል ነበር፡፡ አጋር እየተባሉ ለኖሩ ክልሎች ፓርቲዎች የተሻለ የፖለቲካ ውክልና ማጎናፀፉ በሰፊው ሲነገር ነበር፡፡ የብልፅግና አባል ፓርቲዎች የዓላማም ሆነ የርዕዮተ ዓለም አንድነት ያላቸው ስለመሆኑም ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች የብልፅግና አባል ፓርቲዎች ሰፊ ልዩነት በመካከላቸው መኖሩ ብዙ ሳይዘገይ መታየት ጀምሯል፡፡ አሁን በአማራና በኦሮሚያ ብልፅግና መካከል ያፈጠጠ ልዩነት ቢኖርም፣ በሌሎች የብልፅግና አባል ድርጅቶች ውስጥም ቅራኔ መመልከት የተለመደ መሆኑን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡

የሶማሌ ብልፅግናና የአፋር ብልፅግና በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ የድንበር ይገባኛል ችግሮች ዙሪያ ተቃራኒ አቋም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡

የአማራ ብልፅግናና የቤኒሻንጉል ብልፅግና ፓርቲዎች፣ በተለይ በቤኒሻንጉል አንዳንድ ዞኖች በሚነሱ ግጭቶች የተነሳ ልዩነታቸው ሲሰፋ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

በጋምቤላ ብልፅግናና በኦሮሚያ ብልፅግናዎች በቅርቡ በኦነግ ሸኔና በጋነግ ኃይሎች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች የተለያዩ አቋሞች ሲያንፀባርቁ ነበር፡፡

እነዚህና ሌሎችም ልዩነቶች የሞሉበት ብልፅግና የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግናዎች ስለተወያዩ ብቻ ተቃርኖዎቹን መፍታት እንደማይችል የሚገምቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ከዚህ ተነስተው ይመስላል በተቃርኖ ተሞልቶ ወደ ውህድ ፓርቲነት ተለወጥኩ የሚለው ብልፅግና፣ በሒደት ለአገር የሚተርፍ ቀውስ ምንጭ እንዳይሆን እየሠጉ ያሉት፡፡

ብልፅግና አምና የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ ‹‹ከፈተና ወደ ልዕልና›› በሚል መሪ ቃል ሲያካሂድ ለሕዝብ የተነገረውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ዛሬ ከፓርቲው ራሳቸውን ስለማግለላቸው በሰፊው እየተነገረ የሚገኘው የብልፅግና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብርሃም አለኸኝ፣ አዳማ ከተማ የተደረገውን ቅድመ ጉባዔ የአቋም መግለጫ ሲያቀርቡ ብዙ ጉዳዮችን አውስተው ነበር፡፡

‹‹የአገረ መንግሥት ግንባታ ጉዟችንን በጥልቀት ፈትሸናል፡፡ አገር የማፅናትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የማሻገር ትልማችን ሊሳካ የሚችለው ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በፅኑ ኢትዮጵያዊነት ላይ በመገንባት ነው፤›› ሲሉ ነበር አቶ አብርሃም የገለጹት፡፡ አሁን ግን ብልፅግናዎች በአገረ መንግሥት ግንባታ ተስማምተናል ማለታቸው ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ብልፅግና በአምና ጉባዔው የአቋም መግለጫ ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነትን እንደሚከተል ቃል ገብቶ ነበር፡፡ በጥብቅ የፓርቲ ዲስፒሊን የታነፀ መዋቅር እንደሚገነባና የሚያቀራርቡ አመለካከቶችን በአገር ደረጃ እንደሚፈጥርም ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ በተናገረ በዓመቱ በዋናነት በሁለቱ ጠንካራ አባል ድርጅቶቹ የኦሮሚያና የአማራ ብልፅግናዎች መካከል ሰፊ የልዩነት ገደል የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አገራዊ ቀውስ እንዳይወልድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -