አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ተናኜ ተስፋዬ፣ በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ከአካባቢያቸው የሸማች ማኅበር አምስት ኪሎ ስኳር በኪሎ 41 ብር ከ64 ሳንቲም መግዛታቸውን ይናገራሉ።
በአሁኑ ወር ደግሞ በአንድ ኪሎ 20 ብር ከ61 ሳንቲም እንደተጠየቁ የገለጹት ወ/ሮ ተናኜ፣ የዋጋው ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ተናኜ፣ በአንድ ወር ልዩነት በአንድ ኪሎ ስኳር ላይ ከ20 ብር በላይ ጭማሪ አስደንጋጭ ነው ይላሉ፡፡
በኪሎ ሃያ ብር ዋጋ ከመጨመሩ ባሻገር፣ በወር ለአንድ ሸማች የሚሰጠው መጠን ከሦስት ኪሎ ግራም ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪ ያሳየው ከየካቲት ወር በኋላ መሆኑን የኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ቶሌራ ገልጸው፣ ከመተሃራ የስኳር ፋብሪካ በኪሎ 57 ብር እየገዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት፣ የጫኝና አውራጅ ተጨምሮ ለሸማቾች በኪሎ 62 ብር ከ25 ሳንቲም እየተሸጠ መሆኑን፣ ጥር ወር ላይ በኪሎ 41 ብር ከ64 ሳንቲም ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአንድ ወር ልዩነት የ20 ብር ከ61 ሳንቲም የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ኅብረት ሥራ ዩኒየኑ 992 ኩንታል ከመተሃራ መግዛቱን፣ ለአምስት መሠረታዊ ማኅበራት፣ ለክፍለ ከተማ ሠራተኞችና ለፀጥታ ኃይሎች በኮታ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ በላይ፣ የስኳር ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ጭማሪው ከፋብሪካ ግዥ ጀምሮ የመጣ መሆኑን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ፣ በኢትዮጵያ ያለው የስኳር አቅርቦት ችግር ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ በመጀመርያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረውን የምርት መስተጓጎል ያነሱት አቶ ረታ፣ ይህም በኢንዱስትሪው የስኳር አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማስከተላቸው በተጨማሪ፣ አንዳንድ ፋብሪካዎች በፀጥታ ምክንያት ችግር ውስጥ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ኢንዱስትሪው የሚያቅደው አራትና አምስት ሚሊዮን ቶን የማምረት ዕቅድ እንደነበረ አስታውሰው፣ አሁን ባሉበት ሁኔታ በፊት ከሚታቀደው ከግማሽ ያነሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የስኳር አቅርቦት ለመሙላት ከውጭ የሚገባው ስኳር በወቅቱ አለመድረሱ ሌላኛው ችግር መሆኑን የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነቱ፣ አሁንም ድረስ ወደ አገር ውስጥ እንዳልገባ ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪው የስኳር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ካሉት የስኳር ፋብሪካዎች የተወሰኑት ማምረታቸውን፣ በዚህም 770‚000 ቶን ተመርቶ ለኅብረተሰቡ እየተዳረሰ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እስከ ባለፈው ታኅሳስ ወር ድረስ ከሚፈልጉት መጠን ያነሰ ወይም 25 በመቶ ብቻ እየቀረበላቸው መሆኑን፣ ነገር ግን ከጥር ወር በኋላ 50 በመቶ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ይህም አቅርቦት ከሚፈለገው 100 ከመቶ ግማሹን ብቻ መሆኑን፣ ለዚህም ከላይ የተጠቀሱ አገር አቀፍ ችግሮች ምክንያት እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
ኢንዱስትሪው ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እስከ ጥር ወር ድረስ ስኳር በኪሎ 39 ብር 37 ሳንቲም ሲያቀርብ እንደነበር፣ ነገር ግን ባለው የነገሮች ዋጋ መወደድ ምክንያት ከቅርብ ወራት በኋላ በኪሎ 75 ብር እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን በሸማቾች እየቀረበ ያለው የስኳር ዋጋ በኪሎ እስከ 62 ብር መሆኑን ጠቁመው፣ ጭማሪው በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የዋጋ ንረት ጫና መሆኑን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
አራት የስኳር ፋብሪካዎች ማለትም ወንጂ ሸዋ፣ መተሃራ፣ ፍንጫ፣ ኦሞኩራዝ ሁለት በታኅሳስና በጥር ወራት ላይ ማምረት እንደጀመሩ የገለጹት አቶ ረታ፣ ፋብሪካዎቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ በቀጣይ ከሁለት ሚሊዮን ቶን ስኳር በላይ ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የፍላጎትና የምርት አለመጣጣም በመኖሩ ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 120‚000 ኩንታል ሲቀርብ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን 60‚000 ኩንታል ወይም 50 በመቶ እየቀረበ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የክልሎች የስኳር ኮታ በየ45 ቀናት ልዩነት የሚቀርብ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም 562‚000 ኩንታል ይቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ኢንዱስትሪው ካለበት ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት በፊት ከማያቀርበው ምርት 50 በመቶውን ብቻ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከውጭ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለት ሚሊዮን ቶን ስኳር፣ አሁን ያለውን የአቅርቦት ችግር ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡