Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየገበሬ ነፃነት ከስንዴ ፖለቲካና ከዋጋ ፖሊሲ አኳያ

የገበሬ ነፃነት ከስንዴ ፖለቲካና ከዋጋ ፖሊሲ አኳያ

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

ይህ አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ በቅርቡ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ለቃለ መጠይቅ ተጋብዤ ስለግብርና አብዮት ለኢትዮጵያ አስፈላጊነት ለቀረበልኝ ጥያቄ የሰጠሁትን ምላሽ፣ ከእኔ ከረም ካለ በኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬዎች (አርሶና አርብቶ አደሮች) እንደ ግል ኢኮኖሚ ተዋናይነት ከተነፈጋቸው ነፃነት ጋር ተቀናጅቶ የቀረበ ማስገንዘቢያ ጽሑፍ ነው፡፡ አጀማመሩ በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ኢንስትቲዩሽን (ፖስፕኢ) ቀረፃና ትግበራ ዙሪያ፣ ከሰሞንኛው የስንዴ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ከማሳ ዝግጅት ወቅት እሰከ ሰሞንኛው ምርት አለ፡፡ ኤክስፖርት እየተደረገ ነው፡፡ በአገር የውስጥ ገበያ ላይ አቅርቦት እጥረት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት በኮንትሮባንድ ከባሌ፣ አርሲ፣ ወዘተ. እየገዛን ዱቄት እያመረትን ስለሆነ የስንዴ ዱቄት ዋጋ ጨምሯል፡፡ ተያይዞም የዳቦ፣ የማካሮኒና የመሳሰሉት ሸቀጦች ዋጋም ጨመረ፣ ወዘተ. ከሚል በስንዴ ፖለቲካ፣ በዋጋ እሰጥ አገባና በኑሮ ውድነት ዙሪያ ላሉ ትርክቶችና ዲስኩሮች፣ እንዲሁም ከተለያዩ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች፣ በተለያየ ሥፍራ ከሰዎች ጋር በማደርጋቸው ውይይቶችና መረጃ ጥየቃ ያገኘሁትን ሐሳብና የውይይቶች ይዘት ለሚመለከታቸው የኢኮኖሚውና የፖለቲካ ተዋንያን ለማሳወቅ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው፡፡ 

የማምረት፣ የገበያና የዋጋ ፖሊሲ

በ2014 ዓ.ም. የመኸር እርሻ ማሳ ዝግጅትና የእህል መዝሪያ ሰሞን፣ ከተለያዩ ሚዲያ አካላት ስለማዳበሪያ ዋጋ መወደድ፣ በዚህ ምክንያትም ገበሬው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ለሚመለከታቸው ተቋማት የበላይ አመራር አካላት የማዳበሪያ ዋጋ ተወደደብን፣ አንድ ነገር አድርጉልን ብሎ እየጠየቀ እንደሆነ ገልጸው፣ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ምክር እንደምሰጥ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ በተለይ መንግሥት ለምን የማዳበሪያ ዋጋ ድጎማን በተገቢ መጠን አያደርግም ብለው ጠይቀውኛል፡፡ በወቅቱ ጎልቶ ይነሳ የነበረ ከስንዴ ማምረት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነበር፡፡

ምላሼ የማዳበሪያ ዋጋ ድጎማን አላስፈላጊነት የሚገልጽ ነበር፡፡ ለገበሬው የሚያስፈልገው የማዳበሪያ ዋጋ ድጎማ ሳይሆን፣ አምራቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምርት ዋጋ ፖሊሲን ማዘጋጀት ነው ብዬ ነበር፡፡ ገበሬው ባለው አቅም ማዳበሪያንም ሆነ ሌሎች ግብዓቶችን ለምሳሌ ምርጥ ዘር ገዝቶ አምርቶ፣ የፈጣሪ ፈቃድ ታክሎበት ምርቱን ሲሰበስብና ለሽያጭ ሲያቀርብ፣ ቢያንስ ያወጣውን የማምረቻ ወጪ ሸፍኖለት፣ በተጨማሪም ለእሱ ልፋት ተመጣጣኝ ትርፍ የሚያስገኝ የምርት ዋጋ እንዲኖር ማስቻል አንደኛው የመንግሥት የፖስፕኢ ቀረፃና ትገበራ ሚና ነው ብዬ መልሻለሁ፡፡

 ምላሼ ቢያንስ አምስት የፖሊሲ ጉዳዮችን ያካተተ የመንግሥትን ዝግጅት የሚሻ ስለመሆኑም ማብራሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ አምስቱ የፖሊሲ ጉዳዮችም አንደኛ የማምረት ፖሊሲ፣ ሁለተኛ የገበያና ንግድ ፖሊሲ፣ ሦስተኛ የዋጋ ፖሊሲ፣ አራተኛ የገቢ ፖሊሲና አምስተኛ የሸመታ ፖሊሲ ናቸው፡፡

በወቅቱ ከነበረው ትኩረት አንፃር፣ ስንዴ ተመርቶ በሚፈለገው መጠን ለምንፈልገው አጠቃቀም ሊበቃ የሚችል ያህል ከተገኘ የመሸጡ ውሳኔ ማለትም ለማን፣ መቼ፣ በምን ዋጋ የሚለው ውሳኔ የገበሬው መሆን አለበት ብያለሁም፡፡

ገበሬው በነፃነት ሊሸጥለት ለሚፈልገው አካል (ግለሰብ ሸማች፣ ነጋዴ፣ ኤክስፖርተር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የዱቄት ፋብሪካዎች፣ የመንግሥት ድርጅቶች)  በሚሸጥበት ሥፍራ (ገበያ) ተገቢውን ዋጋ ማግኘት ከቻለ፣ የዋጋ መቁረጥ ጉዳይ በአቅርቦትና በፍላጎት ሕግ በገበያ እንዲወሰን ይገባል ብያለሁ፡፡ ገበያው ፍትሐዊ  ካልሆነ፣ ለአምራቹ የማምረቻ ወጪውን ሸፍኖ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ዋጋ ካልቆረጠለት፣ በተለይም የበርካታ ኤጀንቶች ተገቢ ያልሆነ የተጠቃሚነት ሴራ ከተስተዋለበት፣  መንግሥት  የገበሬውን የማምረት እንቅስቃሴ በአስተማማኝና በቅቡል የገበያ ሥርዓት ለመምራት በሚያስችል የክትትልና ቁጥጥር አሠራር ጣልቃ እንዲገባ ምክረ ሐሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ ይህ ማለት ከሚነሱ ጥያቄዎች አንፃር ተገቢውን የፖሊሲ ክፍል፣ በተለይም የዋጋ ፖሊሲ ማዕቀፉን ባማከለ እየፈተሸ የምርት ውጤቱን ይጠብቅ ብያለሁ፡፡

የዋጋ ፖሊሲ በጥቅሉ በድጎማ ፖሊሲ ሊገለጹ የሚችሉ ግን በፖሊሲ ቀረፃውም ሆነ በአፈጻጸም የተለያዩ የፖሊሲ መሣሪያዎችን የሚያቅፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ፖሊሲው የወለል ዋጋን የመወሰንና ምርቱ ወደ ገበያ ሲቀርብ የሚፈጠር አሉታዊ ዋጋን ልዩነቱን በመክፈል አምራቹን ተጠቃሚ በማድረግ፣ ወይም የዋጋ ግብ አስቀምጦ የገበሬውን የማምረቻ ወጪ ላይ ተጨማሪ የጥረት ማካካሻ ገቢ ጋር ለማይመጣጠንና ከግቡ በታች ለሚሆን የገበያ ዋጋ መንግሥት በተቀመጠው የዋጋ ግብ ምርቱን በመግዛት፣ ይህንንም በሸማቹ በኩል ለሚከሰት የዋጋ መናር ማስተካከያነትም በመጠቀም፣ ወይም ለገበሬው በምርት መሰብሰቢው ወቅት ከአቅርቦት መጨመር አንፃር ለሚፈጠር የዋጋ መውደቅ ከለላ ለመስጠት፣ ለገበሬው የመጋዘን ሥርዓት ዘርግቶ፣ እህሉን አስይዞ የሚበደርበትንና በተሻለ የዋጋ ወቅት ሸጦ ዕዳውን ከፍሎ አምራቹንም ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ፣ በአጠቃላይ አምራችንም ሸማችንም (መታወቅ ያለበት አምራቹ ሸማች እንደሆነም ነው) በተረጋጋና ተገማች የገበያ ሥርዓት አፈጻጸም ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ በቅርቡ ግን በስንዴም ሆነ በሌሎች የሰብል ምርቶች የመገበያየት ሒደት ውስጥ እየታየ ያለው ሁኔታ ይህ አይደለም፡፡ መንግሥት በስንዴ ዋጋ ረገድ በቂ የፖስፕኢ ዝግጅት ሳያደርግ የዋጋ እሰጥ አገባ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡

የኢኮኖሚ ተዋንያን ሚና ቀጭጮ የፖለቲካ ተዋንያን ሚና በጎለበተበት ኢኮኖሚ ውስጥ፣ በተለይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ፖለቲከኞች፣ በታችኛው መንግሥታዊ አካል፣ ማለትም ለአምራቹ የመጀመርያ ተደራሽ ወይም ደራሽ በሆኑ የወረዳ አስተዳደርና ደንብ አስከባሪዎች የገበሬው ነፃ ኢኮኖሚ ተዋናይነት ተገፎ፣ ከዋጋ አንፃር የስንዴን ምርት የሽያጭ ተጠቃሚነት ከአምራቹም ሆነ ከሸማቹ እጅ ተነጥቆ፣ ለእነዚህ አካለትና ከእነሱ ጋር ለሚሞዳሞዱ ስግብግብና በዝባዥ ግን በጣም ጥቂት ለሆኑ ነጋዴዎች፣ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች፣ ኤክስፖርተሮች እንደተዳረገ በተለያዩ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በግል የማገኛቸው የመረጃ ምንጮች አሳውቀውኛል፡፡

ይህ አካሄድ የገበሬውን ነፃ የኢኮኖሚ ተዋናይነት የደፈጠጠ፣ ገበሬን በዘመናዊ ባርነት አስተሳሰብ የፖለቲካ መሣሪያ ብቻ አድርጎ በመቁጠር የሚመራ የማምረት ፖሊሲን የሚፈቅድ መንግሥታዊ አወቃቀር ነው ያለን የሚል ጥያቄ እንዳነሳም አስገድዶኛል፡፡ ገበሬው ከገበያ ተጠቃሚ ካልሆነ፣ ለቀጣዩ የምርት ዘመን ያን ተጠቃሚ ያላደረገውን ሰብል እንዳያመርት ይገፋፋዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የዚያ ምርት ቀጣይነት ሊረጋገጥ የሚችለው፣ ገበሬን እንደ ቀድሞ የባሪያ ሥርዓት ነፃነቱን ገፍፌ፣ የእኔ የፖለቲካ ፍለጎትን ለማሟላት የምጠቀምበት መሣሪያ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥታዊ አደረጃጀት ካለ ብቻ ነው፡፡

ዛሬ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ለምሳሌ ከስንዴ ዋነኛ አምራች ከሆኑት አካባቢዎች ገበሬን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ በመቁጠር፣ እኔ በምወስንልህ ዋጋ ሽጥ ላልኩህ አካል ሽጥ፣ በቀጣይም ቢሆን አስገድጄ አስመርትሃለሁ የሚል ነውጠኛና  ዘራፊ የተደራጀ ኃይል ያለ እሰከሚመስል ድረስ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአምራቹ፣ የአነስተኛ የእህል ሰብሳቢዎች፣ አከማቾችና ወፍጮ ቤቶች፣ በአጠቃላይ በጥቂት ሸምቶ ለሚኖረው ሰው ምርት አቅራቢዎችና ለሸማቾች ማማረርና ምን ዓይነት መንግሥት መጣ የሚል እሮሮ መሰማት መንስዔ እየሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አንዳንዶች ይህች አገር የግብርና አብዮት ያስፈልጋታልን? ብለው ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት፡፡ ጥያቄው አብዮት የኢትዮጵያን ገበሬ ከዘመናዊ የመንግሥት ባርነት የሚያወጣ ይሆን ብሎ ማሰብም የጀመሩ ዜጎች እንዳሉም ይጠቁማል፡፡

የግብርና አብዮትና የፓርኮች ምረቃ

በቅርቡ በአሻም ቴሌቪዥን ጣቢያ ‹‹ወረት›› በሚል ፕሮግራም ለቃለ መጠይቅ ተጋብዤ ቀርቤ ነበር፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጅ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቦልኝ የተደረገው ቃለ መጠይቅ በሁለት ተከታታይ ክፍል በድምሩ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በፈጀ ቆይታ ለሕዝብ ተላልፏል፡፡ ቀስቃሽና የመንግሥት አካላትን ኢኮኖሚ ዘርፎችን አመራር ለአገር ዘላቂ ልማትና ብልፅግና አይመቼነት በማንሳትና በመተቸት የቀረቡልኝ ጥያቄዎች በርካቶች ነበሩ፡፡

ከተጠየቅኳቸው ጥያቄዎች መሀል አንደኛው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የግብርና አብዮት ያስፈልጋታል ብለህ ታምናለህን?›› የሚል ነበር፡፡ ሌላኛው ደግሞ፣ ‹‹የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን የክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ሊመርቀው በሚችል አዲስ የተገነቡ የመኪና ማቆሚያ ፓርኮችን ለመመረቅ ጊዜ ያጠፋሉ? ከዚያ ይልቅ ግብርናውን በቅጡ ቢመሩትና ገበሬውን በትክክልም ከድህነት አረንቋ ሊያወጣ በሚያስችል ሥራ ላይ ቢያተኩሩ አይሻልምን? ለዚህ ምን አስተያየት አለህ?›› የሚሉ ዓይነትና ሌሎችም የሰሚን ጆሮ የሚኮረኩሩ ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ነበር፡፡   

ከላይ እንዳመላከትኩት ቃለ መጠይቁ ለሕዝብ ተላልፏል፡፡ ከተመለከቱትም መሀል፣ ለምን እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ትቀበላለህ? ጠያቂውን ስቲዲዮው ውስጥ ትተህ ተነስተህ አትወጣም ነበር? በተለይ ክብረ ነክ የሆኑ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቀረፃውን ማስቆም ነበረብህ ያሉኝ ነበሩ፡፡

እኔ ለተነሱልኝ ጥያቄዎች የሰጠኋቸው ምላሾች ሰፋ ባለ መንደርደሪያ ጽንሰ ሐሳባዊም ሆነ የቃላት አጠቃቀም ምንነት ላይ ጭምር ያተኮሩ ነበሩ፡፡ እንዳልኩት ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ የተደረገን ቃለ መጠይቅ በዚች አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ አይቻልም፡፡ ያውም የጽሑፉ ዋነኛ ዓውድ ባልሆነበት ይዘት ውስጥ፡፡ አስቸጋሪ ቢሆንም ግን ቢያንስ ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች የሰጠሁትን ምላሽ በወፍ በረር እንደሚከተለው ላመላክት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን የመኪና ፓርክ ለመመረቅ በመሄዳቸው  ለተነሳው ጉዳይ ምላሼ፣ ይህን የሚያደርጉት በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች፣ በተለይ በወቅቱ ትኩረት ለተደረገበት ግብርናው ዘርፍ ተገቢው የፖስፕኢ ማዕቀፍ ቀረፃ በተገቢው ሙያተኛ፣ አገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀረፅ ካደረጉና ለዚህም ዕውቀቱ፣ ችሎታና ብቃቱ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን በአመራር ቦታዎች ላይ ሾመው፣ ባለ አቅም የሚሠራ ሥራ በውጤታማነት እየተሠራ፣ የሌለን አቅም አቅዶ በመገንባት ለማምረት አስቻይ ሁኔታዎችን ከፈጠሩ በኋላ ከሆነ በእኔ በኩል አንድ ሳይሆን በሺሕዎችም የሚቆጠሩ ፓርኮችን እየዞሩ ቢመርቁ ችግር እንደሌለው ገልጬያለሁ፡፡ መጠየቅና መተቸት ካለበት ካደረጉ ያልኳቸውን ማድረግ አለማድረጋቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና አብዮት ያስፈልጋታልን? ለሚለው ጥያቄ በቅድሚያ ‹‹አብዮት›› የሚለው ቃል በጽንሰ ሐሳብም ሆነ በይዘት ምን ለመጠቆም በጥያቄው ውስጥ እንደተካተተ መላምታዊ ግምትና የማሰላሰያ ሐሳብ ካቀረብኩ በኋላ፣ የሚከተለውን ማብራሪያ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ነባራዊ ሁኔታና ድርጊት ጋር በማዛመድ    አቀረብኩ፡፡

ሁሌም ለማሳሰብ እንደምጥረው፣ በመሠረቱ ግብርና ከእርሻ (የሰብልም ሆነ እንስሳት) በተጨማሪ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የያዘ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ መሆኑን አሳወቅሁ፡፡ ከእርሻው ንዑስ ዘርፍ በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንክብካቤና ልማት (አፈር፣ ውኃና ደንን አካቶ) ምርምር፣ ሥርጭት፣ ቴክኖሎጂ ማፍለቅ፣ ማባዛት፣ ግብይትና ንግድ፣ ክምችት፣ ትራንስፖርት፣ መፈብረክ (አግሮ ፕሮሰሲንግ)፣ ወዘተ. የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ንዑስ ዘርፎች እንዳሉት አስረዳሁ፡፡

ከዚህ ማስገንዘቢያ በኋላ አብዮት የሚለውን ቃል ‹‹ለውጥ›› በሚል ዕሳቤ ገበሬው ነፃ ኢኮኖሚ ተዋንያን መሆኑን (ከዘመናዊ ባርነት ተላቆ)፣ እሱ በሚሰማራበት የእርሻው ንዑስ የግብርና ዘርፍ በማሳ ስፋት ለውጥ በሚመዘን የግብርና ሴክተር ውስጣዊና መዋቅራዊ ለውጥ የሚለካ፣ ለውጡ በትርክት ሳይሆን የገበሬውን ገቢ በመጨመር የእሱንና የቤተሰቡን የኑሮ ደረጃ መሻሻል የሚያመላክትና የሚለካ  ለውጥ መገለጫ ሊሆን ይችላል ብዬ ከአብራራሁ በኋላ፣ በዚህ ዕሳቤና ማብራሪያ መሠረት አዎ ዛሬም ኢትዮጵያ የግብርና አብዮት ያስፈልጋታል አልኩ፡፡ ይህ ማለት ግን አመፃዊ ንቅናቄ ይደረግ ማለት አይደለም፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት አብዮቱ በመነሻው ገበሬን ትክክለኛ ነፃ የግል ክፍለ ኢኮኖሚው ተዋናይ የሚያደርግ፣ ዛሬም ድረስ እንደሚስተዋለው ፖለቲከኞች በሥልጣን ላይ ለመቆየት ለሚያደርጉት ጥረት አንድም ድህነቱን፣ ሌላም የወታደር ምንጭነቱን ተጠቅመው በዘመናዊ ባርነት ቀንበር ውሰጥ ጨምድደው ይዘው የሚንቀሳቀሱ እስከሆነ ድረስ፣ ይህን አስተሳሰብና ድርጊት መንግሎ የሚጥል የግብርና አብዮታዊ እንቀስቃሴ ቅቡልነት ሊኖረው ይችላል የሚል ድምዳሜ ሰጠሁ፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬ (አርሶና አርብቶ አደር) በተፈጥሮ የግል ተዋናይነቱን ይዞ የሚገኝ ቢሆንም፣ ትክክለኛ ነፃ የግል ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋንያን ግን አይደለም ብዬ በተለያዩ መድረኮችና ጽሑፎቼ መሞገት ከጀመርኩ ዋል አደር ይላል፡፡ በተለይ በዚህ ዙሪያ በ2009፣ በ2012፣ እና በ2013 ዓ.ም. በጻፍኳቸው መጻሕፍት ውስጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርቤያለሁና መጻሕፍቶቹን ገዝተው ወይም ተውሰው ቢያነቡ ብዬ እመክራለሁ፡፡ ደውለው ቢጠይቁን፣ ወይም ከጃፋር መጽሐፍ መደብር ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

ገበሬው ዛሬም ነፃ ያልሆነ በመንግሥትና በካድሬዎቹ፣ እንዲሁም በዕርዳታ ሰጪ ብዝኃና ሁለትዮሽ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ አገር መሠረታቸውን ባደረጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ ተደርጎ ይመራል፡፡ ሰፋ ባለ ዕሳቤ ሲቃኝ ገበሬው የፖለቲካ መሣሪያ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ ገበሬው እንደ ማናቸውም የግል ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋንያን በቅድሚያና በዋነኛነት የኢኮኖሚ ተዋናይ መሆኑ ታውቆና ተከብሮ፣ ከፖለቲካ ዘመናዊ ባርነት በአብዮትም ይባል በሕዝባዊ ንቅናቄ ነፃ መውጣት አለበት እላለሁ፡፡

የገበሬው ነፃ መሆን ማመላከቻና መመዘኛዎች አንድም ለእርሻ መሬት ካለው ተደራሽነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ከዛሬው የመሬት የተጠቃሚ መብት ትርክትና ሰርተፊኬት ውዥንብር ተላቆ ነፃነቱ ከመሬት የባለቤትነት፣ የመግዛትና የመሸጥ፣ የማውረስና የመውረስ መብቶች ጋር የተቆራኘ መሆን አለበት፡፡

ገበሬ ትክክለኛ ነፃ የግል ኢኮኖሚ ተዋንያን መሆኑ የሚገለጸው፣ ገበሬና መሬት እንደ ዋነኛ ኢኮኖሚ መሣሪያነት በነፃ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገናኙ ሆነው፣ በተለይ በእርሻው ዘርፍ በመሬቱ ላይ ምን ላምርት? እንዴት ላምርት? ለማን ላምርት? ከየት ግብዓት ልግዛ? ለማን ልሽጥ? ወዘተ. የሚሉትን ውሳኔዎች ራሱ በነፃነት ሲወስን ነው፡፡ በዚህ ሒደት የላቀ ውጤት የሚያገኝ ገበሬም በዚችው አገሩ ውስጥ ዘመናዊና ንግድ ተኮር በሆነ አሠራር ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ከዚያም ሰፋፊ የእርሻና የሌሎች ግብርና ኢንተርፕራይዞች መሥራችና ባለቤት መሆን ሲችል ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ገበሬው በዘመናዊ ባርነት ሥርዓት ውስጥ እንዳለ መቆጠር አለበት፡፡ የግብርና አብዮቱ ጽንሰ ሐሳባዊ ይዘቱም ሆነ ክስተቱ በዚህ ላይ የሚያተኩር መሆን አለበት፡፡

በስንዴ ፖለቲካ ጨዋታ የተለያዩ ተዋንያን ሚና

በማክሮ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ የፖሊሲ ጥናትና ትንተና ክፍት በሆነ ኢኮኖሚ አራት ተዋንያንና ሦስት ዋና ገበያዎች እንዳሉ ይገለጻል፡፡ ተዋንያኑ አምራች፣ ሸማች (የግብዓትም ሆነ የምርትና አገልግሎት)፣ መንግሥትና የውጭ ኃይሎች ናቸው፡፡ በቅርቡ ረቂቁን በጨረስኩት ተጠባቂ መጽሐፌ ውስጥ ሚዲያን (ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ) እንደ አምስተኛ ተዋንያን አቅርቤያለሁ፡፡ መጽሐፉ ታትሞ ሲወጣ ዝርዝር መግለጫውን ያገኙታል፡፡ ገበያዎቹ በጥቅሉ የግብዓት፣ የፋይናንስ፣ የምርትና አገለግሎት ተብለው ይቀርባሉ፣ የፖሊሲ ትንተናም ይደረግባቸዋል፡፡

ገበሬው ነፃ ይሁን ሲባል፣ መንግሥት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ተዋናይነቱ በማምረት ሆነ በገበያ ወይም በገቢ፣ በዋጋ ሆነ በሸመታ ረገድ በኢኮኖሚው ውስጥ የተረጋጋ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሕግና ደንብ አያውጣ፣ አያስፈጽም፣ ቁጥጥርና ክትትል አያድርግ ማለት አይደለም፡፡ መንግሥት እነዚህን ተጠባቂ ሥራዎቹን መሥራት አለበት፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን በተለያየ የመንግሥት አወቃቀሮች (ፌዴራል፣ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ)፣ በተለያዩ ተቋማት በተለያየ የአመራር ሥፍራ ላይ ያሉ፣ ጥቂቶች ቢሆኑ እንኳ ተገቢውን ሥራ ትተው በአቋራጭ ለመክበርና ለመበልፀግ የሚንቀሳቀሱ  ከሆነ ኢኮኖሚው ምስቅልቅሉ ከመውጣቱ በተጨማሪ፣ የዜጎች የመኖር ህልውና ይዛባል፣ የአገር ሰላምና ደኅንነትም በሌቦች፣ በአስገዳዮችና በገዳዮች መበራከት አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የሰሞንኛው የስንዴ ፖለቲካ ይዘትም በከፊል ይህን ያረገዘ ይመስላል፡፡

እንደ አንድ በጉዳዩ ዙሪያ ሲያጠና፣ ሲመክር፣ የግብርና ዘርፍ ሙያተኞችን ለማስተባበር ሲጥር እንደ ከረመ ሙያተኛ፣ በዘንድሮ የስንዴ ምርት ሒደትና ውጤት በጥቅሉ የብልፅግና መንግሥት የተጫወተውን ሚና ሳላመሠግንና አድናቆት ሳልቸር ብቀር ፈጣሪ ለስህተቴ ይቅር የሚለኝ አይመስለኝም፡፡ 

በታሪካችን በጎላ ሁኔታ ኢትዮጵያን በቂ የስንዴ ምርት አምራች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያስፈልገንን ስንዴ (ምግብ ሳይሆን እህሉን) በበቂ ተመርቶ ቀሪው ለኤክስፖርት መዋል በመጀመሩ፣ ለመንግሥት የበላይ አመራር አካላት፣ በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያለኝን አድናቆትና ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡ እኔ ባለኝ የመረጃ ምንጭ በተባለው መጠን ስንዴ የማምረቱ ጉዳይ ዕውን እንዲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩና የእሳቸው ጽሕፈት ሐሕሐሕሐሕሀህሀህቤት የሥራ ባልደረቦች በማምረት ሒደቱ ውስጥ የነበራቸው ያላሰለሰ ቆራጥ አመራር፣ ክትትልና ግምገማ ለውጤቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተረድቼያለሁ፡፡ ካለኝ መረጃ ይህ ባይሆን ኖሮ በማሳ ዝግጅትና በዘር ወቅት ከግብዓት አቅርቦት መዛባትና ለገበሬ የተላከን ማዳበሪያ ለሌሎች በመሸጥ ጭምር ተሰማርቶ የነበረው፣ ዛሬም በምርቱ ግብይት ውስጥ ያልቦዘነው፣ በአብዛኛው በታችኛው እርከን የመንግሥት አመራር ውስጥ በተሰገሰጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ሌቦችና ሙሰኞች፣ በጥቂቱም ቢሆን በከፍተኛ አመራር ድረስ አሉ ከሚባሉ እኩይ ሥራ ሠሪዎች ጋር ይጓዝበት በነበረው አቅጣጫ ሄዶ ቢሆን ኖሮ ይህ የምርታማነትና ምርት ውጤት መመዝገቡ አጠያያቂ ነበር፡፡

ዛሬ ያለው ጥያቄ ምርቱ ተመርቷል ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ግን ማነው የሚለው ነው፡፡ ባለኝ መረጃ አምራቹ (ገበሬም ይሁን ኢንቨስተር) እና ሸማች አይደለም፡፡  ገበሬ ለአመረተው ምርት ማግኘት የሚገባውን ዋጋ እያገኘ እንዳልሆነ፣ ሸማቹም ከኑሮ ውድነት የሚያላቅቀውን፣ በስንዴ ምርት በኩል የሚገኝን የምግብ ግብዓቶች ዋጋ ቅነሳ እያገኘ አይደለም፡፡ እንዲያውም በዱቄት፣ በማካሮኒ ምርቶች፣ ወዘተ. ላይ ለተጨማሪ የዋጋ ማሻቀብ እየተጋለጠ እንዳለ ተገንዝቤያለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ስንዴ በተፈለገው መጠን ተመርቶ፣ ለኤክስፖርትም ውሎ፣ አንዳንድ አደጉ የሚባሉ አገሮች አድርገውታል እንደሚባለው ውቅያኖስ ውስጥ እንኳ ብንደፋው፣ የኢትዮጵያውያን የቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ ፍለጎት ይሟላል ማለት አይደለም፡፡ ስንዴ በራሱ ምግብ አይደለም፣ የምግብ እህል እንጂ፡፡ ወደ ፋብሪካም ሄዶም ዱቄት ሆኖ ሲወጣም ምግብ አይደለም፣ ማካሮኒም ምግብ አይደለም፣ የምግብ ግብዓት እንጂ፡፡ ይህ ትምህርታዊና ቴክኒካዊ መግለጫዬን በዚህ ጽሑፌ አልቀጥልበትም፡፡ ጠቆም ያደረግኩበት ምክንያት የሰሞንኛው የስንዴ ፖለቲካ ሸቀጥነት፣ ስንዴን አምርቶ ለኤክስፖርት ማቅረቡን የቤተሰብ ደረጃን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጫ መመዘኛ ተደርጎ የፖለቲካ ትርክቶች ሲሰጡበት ስለታዘብኩ ነው፡፡

የገበያ ውስጥ ኤጀንቶች የብልጣ ብልጥነት ጨዋታና የሸማቹ ሮሮ

በአንድ እርሻ ምርት (ሸቀጥ) ገበያ ሰንሰለት ውስጥ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሁሉት (አምራችና ሸማች) ኤጀንቶችን ጨምሮ፣ ከአሥር የማያንሱ ኤጀንቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በአብዛኛው በስንዴ ገበያ ሥርዓት ውስጥ በትክክለኛው አሠራር በቀበሌና ገጠር አካባቢ ከአምራቹ ጀምሮ እህል በማሰባሰብ፣ በማከማቸት፣ በአካባቢውና በቅርብ የገጠር ከተሞች ወይም ከዋነና መዳረሻ ገበያዎች እስካለው የግብይትና የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ለተሰማሩ ትንንሽ ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ተዋንያን፣ ይህን ጽሑፍ እስከጻፍኩበት ወቅት ጊዜ ድረስ የዘንድሮው ስንዴ ምርት ተጠቃሚ አላደረጋቸውም፡፡ የእህሉም ሆነ የዱቄቱ፣ የዳቦም ሆነ የማካሮኒ ሸማቹ እሮሮም እየጨመረ መጥቷል፡፡ በቀድሞ ጊዜ ገበያውን ያመሳቅሉታል የሚባሉ ትንንሽ ደላሎችም ሚና እንኳ ቀጭጮ፣ የገበያው አቅርቦት፣ ዋጋና የእህሉ ከሥፍራ ሥፍራ እንቅስቃሴ ከወረዳ ጀምሮ ወደ ላይ ባሉ ጥቂት ግን አደገኛ በሆኑ የፖለቲካ አመራር  ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ሙሰኞችና ሌቦች ቁጥጥር ውስጥ ወድቋል የሚል የመረጃ ፍሰት አለ፡፡

በክላስተር አደራጅቼ፣ ግብዓት አቅርቤልሃለሁና ያመረትከውን እኔ ባዘዝኩህ ቦታ፣ ለማዝለት ሰው፣ በወሰንኩልህ ዋጋ ትሸጣለህ ከማለት አልፈው፣ በራሳችን ግብዓት ግዥ፣ በክላስተር ሳንደራጅ እናመርታለን ብለው ስንዴ ያመረቱ ገበሬዎችን የመሸጥ ነፃነት ነጥቀው፣ ለመንግሥትና መንግሥት ለሚያመላክታችሁ አካላት ሽጡ የሚሉ ጉልበተኛ የአመራር አካላት እየበዙ እንደመጡ በሰፊው ይነገራል፡፡

ከሰሞነኛው ከአሥር ከማያንሱት የገበያ ኤጀንቶች መሀል በአንዱ ክፍል የሚመደቡ፣ ይህም ማኅበራት በሚባለው የኤጀንት ማዕቅፍ ውስጥ የሚካተቱ፣ የዱቄት አምራቾች ማኅበራትም የማደናገሪያና የብልጣ ብልጥነት ጨዋታ፣ ለሚዲያ ባለ አቅርቦታቸው ተጠቅመው የአዞ ዕንባ የተቀላቀለበት ጩኧት እያሰሙን ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ ይህች አገር የጋራችን መጠቀሚያ ትሁን፣ ሁሉን ለእኔ የሚል ዘራፊ ብቻ በወረቀት ብር የሚጫወትባት አትሁን!!

በአምራቹ አቅራቢያ ያሉ ነጋዴዎችና ወፍጮ ቤት ባለቤቶች እንኳ ከገበሬው ሊሸጥ በሚፈልግበት ዋጋ እንዳይገዙ ተደርጎ፣ ጥቂት ነጋዴዎችና ኤክስፖርተሮች ቢሆኑም፣ አንዳንዶቹም የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች የሆኑ በመንግሥት ዋጋ ወሳኝነት ወደ 3,200 ብር በኩንታል የሚያገኙትን ስንዴ በግልጽ ወይ በአገር ውስጥ ከቦታ ቦታ በሚደረግ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ መጋዘናቸው፣ ወይም ዱቄት ፋብሪካቸው ደጃፍ እሰኪያደርስ ድረስ ከ3,600 እሰከ 4,000 ብር በኩንታል ሥሌት አውጥተውለት፣ ለኮንትሮባንዱ ለአንድ የጭነት መኪና ከእነ ተሳቢው ከመከማቻ ሥፍራ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር (100,000) ድረስ ለሙሰኛ የአመራር አካላት እየሰጡ፣ በየኬላውም ከሰላሳ እስከ አርባ ሺሕ ብር (ከ30 እስከ 40,000) ድረስ ለደንብ አስከባሪዎች እያጎረሱ እንደሚንቀሳቀሱ ማዳመጥ ፀሐይ የሞቀው ሚስጥር ሆኗል፡፡

በዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ አንድ የዱቄት ፋብሪካ አጥር ግቢ ውስጥ ማታ የተራገፈ ስንዴ ተፈጭቶ፣ ጠዋት ሲነጋ በሌላ ተጭኖ ከተማ ውስጥ ለተለያዩ አካላት ኩንታል ዱቄት እስከ ሰባት ሺሕ ብር ይሸጣል፡፡ ዳቦ አምራቹ ደግሞ የዱቄት ዋጋ ተወዶብኛል ብሎ የዳቦ ዋጋን ቀን በቀን እያናረው ሄዷል፡፡ የሸማች እሮሮም በዚያው መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡

ኧረ ጎበዝ በዚህ ዓይነት ጨዋታ በዜጎች የኑሮ መወደድ ሥቃይ፣ ጊዜው ለእኛ እርጥብ ነው ለሚሉ በጣም ጥቂት በጣት ይቆጠራሉ ለሚባሉ ኤክስፖርተርና የዱቄት ፋብሪካ ባለሀብቶች ዝርፊያ እንዴት አገር ሲታመስ ይከርማል? ይህ ባለው መንግሥት አመራር አካል ባልሆኑ የሚፈጸም ዝርፊያ ከሆነ ደግሞ፣ ሌላኛው መንግሥት ለሕዝብና ለአገር ቆሜያለሁ የሚለው የት ነው ያለው? ዕርምጃ ይውሰድ የሚሉም ጩኸቶች እየበዙ ነው፡፡

በእንዲህ መሰል የስንዴ ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ በተለያዩ ማኅበራት ስም፣ አንዴ በኤክስፖርተሮች፣ አንዴ በዱቄት አምራቾች፣ ወዘተ. ስም የተለያየ ሽፋን በመስጠት ድሮ ድሮ አገር ተሻግሮ ለሚወጣ ወይም ለሚገባ ሸቀጥ የሚሰጠው ‹‹ኮንትሮባንድ›› የሚባለው መጠሪያ፣ ከባሌ፣ አርሲ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ ተጓጉዞ በጠራራ ፀሐይ በመቶዎቹ ኩንታል ለተጫነና ለሚንቀሳቀስ ስንዴ ‹‹የኮንትሮባንድ›› እየተባለ መሳለቅ ተጀምሯል፡፡ ኧረ ተው ጎበዝ!!

ከላይ ለማጣቀስ እንደሞከርኩት፣ እነዚህ በጣም ጥቂቶች በሙስናና ሌብነት ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ የግብይት፣ የንግድና የፍብረካ ኢኮኖሚ ተዋንያን፣ ጊዜው ለእኛ ‹‹እርጥብ›› ነው የሚል አገላለጽ እንዳላቸው ሰምቼያለሁ፡፡ አምራቹ ዋጋ አሮበት፣ እንደ ሸማችነቱም በኑሮ ውድነት ተቆራፍዶ ያመረተው ምርት የገቢ ተጠቃሚ ሳይሆን፣ አሁንም መንግሥት አለ ብሎ ስለሚያምን ‹‹ኧረ የመንግሥት ያለህ›› እያለ ነው፡፡ መንግሥት የት ነው ያለኸው?

በተለይም የወቅቱን የስንዴ ፖለቲካ የስበት ማዕከል ተንተርሶ፣ ኤክስፖርተሮች የሚባሉት በተለይ በግል ክፍለ ኢኮኖሚው ውስጥ ያሉና የተፈቀደላቸው ከአምራቹ ገበሬ በአነስተኛ ዋጋ ገዝተው ጥቂቱን ኤክስፖርት አድርገው፣ በርከት ያለውን በአገር ውስጥ እያከማቹ ነው የሚል የመረጃ ፍሰትም አለ፡፡ ይህን የሚያደርጉትም ከጥቂት ወራት በኋላ የስንዴ እህል ዋጋ ይጨምራል በማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ እንዲጨምር በማድረግ፣ የበለጠ ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው የሚል ተጓዳኝ ትንተና ይሰጥበታል፡፡ ኧረ ሃይ ባይ ይምጣ፡፡ ሁሉም ተገቢ የተጠቃሚነት ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ሥርዓት ይዘርጋ፡፡ በቅድሚያ ለአምራቹና ለሸማቹ ቀዳሚ ተጠቃሚነት የሚያስከብር ሥርዓት ይዘርጋ፡፡ በተለይ ገበሬ አምራች ብቻ ሳይሆን ከፍተኛው ሸማችም ነውና መንግሥታዊ ከለላና ተገቢው የዋጋና ገቢ ድጋፍ ፖሊሲ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሥራ፡፡

መንግሥት በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ሥራ ካልሠራ በጥቂት የግብርና ሸቀጦች፣ ስንዴን ጨምሮ በሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ እያሻቀበ በሚሄድ ዋጋ፣ እየተጋጋለና ሕዝብን እያማረረ በመጣ የኑሮ ውድነት፣ ኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን የመላው አገሪቱ ሁለንተናዊ ይዘት ቀውስ ውስጥ እስኪገባ በቸልተኝነት ከተመለከተ፣ በኋላ የቀውሱን ሒደት ለመቀልበስ ማጠፊያው ከባድና አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡  ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ በርካታ የገበሬዎች አብዮት ይህንኑ ማጠፊያ የሚያሳጣ ዓይነት ለውጥ እንዳስከተሉ ታሪክ መዝግቦ ይዟልና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የግብርና ኢኮኖሚስት፣ ከ42 ዓመት በላይ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ልምድና ተሞክሮ ያካበቱና የተለያዩ አካዳሚያዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍት የጻፉ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው demesec2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...