በብሔራልባ ሰሎሞን
ልጆች ሆነን በጣም የምንፈራው ፈተና “ባዶ ቦታውን ሙላ” የሚለውን ነበር፡፡ በእንግሊዝኛ ሲነገር ለብዙዎቻችን ትክክለኛውን ትዝታ ስለሚቀሰቅስ እነሆ (Fill in the Blank Space With the Correct Answer)፡፡
ባዶ ቦታውን ካልሞላን ፈተና መውደቅ ነው፡፡ የተሳሳተ መልስ ከሞላንም እንዲሁ፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንድ ትንሽ የበራላቸው መምህራን ምንም ሳይሞላ ከዘለለው ተማሪ ይልቅ የሞከረው ቢሳሳትም የተሻለ ነው በማለት የጥረት ነጥብ ግማሽ ራይት ብለው የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ለዛሬ ላጋራችሁ የምፈልገው ባዶ ቦታውን የመሙላትና ያለ መሙላት ጉዳይ ላይ ከልጅነት ይዘነው የመጣነውን ፈተና የማለፍና የመውደቅ ጉዳይ ነው፡፡ ታድያ ዛሬ የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት በርግጥ ይኼ ስንፈራው የነበረው የመልመጃና የፈተና ዘዴ የዕለት ተዕለት ልምምዳችን ሆኖ ከአሠራሩ መውጣት የተሳነን ይመስለኛል፡፡ ገና በለጋነታችን ባዶ ቦታ ሁሉ መሞላት እንዳለበት ተማርን፡፡ እንግዲህ በልጅነታችን ባዶ ቦታውን ሁሉ ሙሉ ተብለን ስላደግን፣ ባዶ ቦታ አያስፈልግም የሚል አስተሳሰብ በልቦናችን የታተመ ይመስለኛል፡፡
በዚህ የትምህርት ዘይቤ የተቀረፀ ተማሪ በኋላም በሥራ ዓለም ላይ ሆኖ ባዶ ቦታ ሁሉ መሞላት እንዳለበት አድርጎ ያስባል፡፡ በተለይ ደግሞ ቢሳሳትም እንኳን ለሙከራው ጥቂት ነጥብ በማግኘት ያደገ ከሆነ ያ ሰው በሥራ ዓለም ይሁን፣ በቤት ውስጥ ወይም በመዝናኛ ቦታ ባዶ ቦታ ሁሉ መሞላት እንዳለበት ያስባል፡፡ ስለዚህ መኪና ሲያሽከረክር ከፊት ለፊቱ ያለውን ባዶ ቦታ መሙላት እንዳለበት ስለሚያስብ ከፊቱ ካለው መኪና ጋር የሚተወው ርቀት ላለመጋጨት ያህል ይሆናል እንጂ፣ በአጋጣሚ የፊተኛው መኪና ተበላሽቶ ወይም በሆነ አጋጣሚ ቢቆም መሪውን ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ አዙሮ ለማለፍ በቂ ቦታ አይተውም፡፡ በተመሳሳይ ከእሱ ኋላ ያለውም አሽከርካሪ ባዶ ቦታውን ሙላ በሚለው ቀመር የትምህርት ዘይቤ የተቀረፀ ስለሆነ፣ እግረኛ እንኳን በመካከላቸው ለማለፍ በማይችልበት ሁኔታ ተጠግቶት አያሽከረከረ ስለነበር ወደኋላም ሸርተት ብሎ ለመዞር አይቻለውም፡፡ ሦሰተኛውም፣ አራተኛውም፣ አምስተኛውም፣ ወዘተ፡፡ በተመሳሳይ የትምህርት ዘይቤ በታነፁ አሽከርካሪዎች የተያዙ መኪኖች በመሆናቸው ብቸኛው አማራጫቸው የመኪናቸውን ጥሩንባ እያስጮኹ በጩኸት፣ ከፊት ተበላሽቶ የቆመውን መኪና እንዲንቀሳቀስ መሞከር ነው፡፡ ለክፋቱ ደግሞ የመኪና ጥሩንባ የተበላሸ መኪናን አይጠግንም ወይም መንገድም አያስከፍትም፡፡ እንዲያውም የነበራቸውን የፀጥታ ባዶ ቦታ በጥሩንባው ጩኸት ይሞላዋል፡፡
በዚህ ዓይነት በባዶ ቦታውን ሙላ (Fill in the Blank…) የታነፁ አሽከርካሪዎች፣ መስቀለኛ መንገድ ላይ ከዚህ በባሰ ሁኔታ እርስ በርስ መንገድ ይዘጋጋሉ፡፡ በአንደኛው መንገድ የሚሄዱት መኪናዎች በርካታ ስለሆኑ፣ መስቀለኛ መንገዱን አቋርጠው መሄድ እስከማይችሉ ድረስ መንገዱ ተዘጋግቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ከግራ ወይም ከቀኝ መጥቶ መስቀለኛ መንገዱን ለሚያቋርጥ መኪና መስቀለኛ መንገዱ ውስጥ ሳይገቡ በመቆም ቅደሚያ በመስጠት የእንቅስቃሴውን ፍሰት ከማገዝ ይልቅ በተለመደው የባዶ ቦታውን ሙላ (Fill in the Blank…) ተመራቂዎች አካሄድ ወደፊት እንደማይሄድ እያወቀ፣ ወደፊት በመሄድ መስቀለኛ መንገዱ መካከል ሆኖ ከግራና ከቀኝ መሄድ ለሚችለው መኪና መንገድ ይዘጋበታል፡፡ መስቀለኛ መንገዱን አቋርጦ መሄድ እንደማይችል እያወቀ፣ መሻገሪያው ላይ ከቀኙና ከግራው የሚመጡ መኪናዎች በእሱ መሻገሪያው ላይ መቆም ምክንያት መሻገር እንደማይችሉ እያወቀ ባዶ ቦታውን ሞልቶ መሻገሪያ ላይ ይቆማል፡፡ በአጭር ቃል ይህ አስተሳሰብ “እኔ መሄድ ስለማልችል አንተም መሄድ የለብህም” ይባላል፡፡
ሌላው በዚህ ባዶ ቦታውን ሙላ የተቀረፁ ዜጎች በከተማ አስተዳደር ውስጥ ይገቡና የከተማውን ፕላን ሲሠሩ/ሲያሠሩ ባዶ ቦታ ሁሉ መሞላት ስላለበት መናፈሻዎች፣ የኳስ መጫወቻ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የማኅበራዊ አገልግሎት ቦታዎች፣ እንደው በአካባቢው የመንጎራደጃ ባዶ ቦታዎች (በጥሩ አማርኛ Walk ማድረጊያ) ሁሉ በሊዝ ቸብችበው፣ የከተማው አስተዳደር ሪፖርት ላይ ከቦታ ሊዝ ሽያጭ ይህንን ያህል ቢሊዮን ብር የከተማው አስተዳደር አስገብቷል ብለው ያስጨበጭባሉ፡፡ እኛም ከመጠየቅ እጃችን እስኪቀላ እናጨበጭባለን፡፡
እንግዲህ ከተሞቻችንን ስንመለከት በቅርቡ የተስፋፉትም ሆኑ ነባሮቹ በዚህ መሠረት የተከተሙ ለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ፎቆቻችን ከመኪና መንገድ ባለመራቃቸውና ለመኪና ማቆሚያ እንኳን ባዶ ቦታ ባለመተዋቸው “አንቱ” በተባለ ሠፈር እንኳን ደርቦ በማቆም ስልክ ቁጥር ትቶ በመሄድ ነው በሽታውን ለማከም እየተሞከረ ያለው፡፡ መርካቶ እነ ሚሊቴሪ ተራ ፈርሰው ሲሠሩ በጣም ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ነገር ግን በፊት እየተገፋፉ መሬት ላይ ጨርቅ የሚቆርጡት ፎቅ ስላልነበረ ታች ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን 2 እና 3 ፎቅ ላይ ጨርቅ መሬት ላይ ተተርትሮ ይመተራል፡፡ ድሮም የተቀመጡ የባለሱቅ ንብረቶች ተራምደን እናልፍ ነበር፣ ዛሬም እንደዚሁ፡፡ የተሻሻለው ፎቅ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
ብልህ ከሰው ይማራል፡፡ ሞኝ በራሱ ይማራል የሚል ብሂል አለ፡፡ ለእኛ አገር ፖለቲከኞችና ባለሙያዎቸ ግን ብልህም ሞኝም አይደሉም፣ ከሰውም በራሳቸውም አይማሩም፡፡ የሠሩት ስህተት እንደሆነ ሲነገራቸው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ ምክንያቱም ሪፖርት የሚቀርብላቸው ሊሰሙት እንደሚፈልጉት ሆኖ ስለሆነ ነው፡፡ በእርግጥ ገሚሱ ባለማወቅ ሲሆን፣ ገሚሱ ደግሞ ስህተትን መቀበል እንደ ሽንፈት ስለሚቆጥረው ድርቅ ብሎ እያወቀ ይሞግታል፡፡
አስገራሚውና የከፋው ነገር ደግሞ ስህተትን በስህተት የማረም ልምምድ የተለመደ የመንግሥት አሠራር እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ ለዚህ አንድ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልክት፡፡ ከመስቀል አደባባይ ጎተራ የመኪና መንገዱ ሲሠራ፣ በሦስት የተከፈለ መንገድ ሆኖ ተሠራ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የመካከለኛው መንገድ ተቆፈረ፡፡ ለምን? ለቀላል ባቡር፡፡ ታዲያ የመካከለኛው አስፋልት ለምን ያ ሁሉ ሚሊዮን ብር ወጥቶ፣ ያውም በውጭ ምንዛሪ ተሠራ? ተብለው ሲጠየቁ አይ ያነሳነውን አስፋልት እንጠቀምበታለን፣ አይባክንም አሉን፡፡
ቀደም ሲል ከሜክሲኮ ጀሞ መንገዶቹ ሲታደሱ፣ ለአዳዲስ ሕንፃዎች ማሠሪያ ቦታ ሲሸነሸን/ሲቸበቸብ የከተማው አስተዳደር ከሊዝ ያስገባው የገቢ አኃዝ ወይም ስታትስቲክስ ጉዳይ ብቻ ነበር የሚፈልገው፡፡ ምክንያቱም የገቢውን አኃዝ ከፍ ማድረግ የአገርን ጠቅላላ ገቢ ከፍ ያደርጋልና ለዓለም አቀፍም ሆነ ለአገር ውስጥ ብድር ፋይዳው ከፍ ያለ ነውና፡፡ ከዚያስ በቅድሚያ ከሜክሲኮ አንስቶ እስከ ጀሞ ባለሦስቱን ረድፍ መንገድ ከሁለተኛው ረድፍ ትንሽ ቀንሰው የቀኙን ረድፍ ሙሉ ለሙሉ ለአውቶቡስ ብቻ የሚል አሰፈሩበት፡፡ ለሕንፃ ቦታ ሲቸበችቡ የእግረኛ መሄጃ መንገዱ የሚጀመርበት ድረስ ሳንቲ ሜትር እንኳን ሳይተው፣ ለመኪና ማቆሚያ ምንም ዓይነት ቦታ ሳይተው፣ ንፁህ አየር ለመተንፈስ ዛፍና አትክልት መትከያ ቦታ ያልተወ የከተማ አስተዳደር የትራፊክ መጨናነቅና የሕዝብ ትራንስፖርትን ችግር ለመቅረፍ ልብ ይበሉ ለመቅረፍ ነው፡፡ መቅረፍ ከላይ ከላይ ብቻ ማንሳት ነው፡፡ ከሥሩ ከሆነ ያቀለዋል፡፡ ከላይ ከሆነ ግን እንደ ስልባቦት በስሱ ከማንሳት አይዘልቅም፡፡ ለአውቶቡስ አንድ ረድፍ ወስዶ ያውም ከሁለተኛው ረድፍ ቀንሶ ምን ያህል የትራፊክ ፍሰትን እንደሚያሳልጥ መገመት አያዳግትም፡፡ ያ ማለት ደግሞ ከሜክሲኮ እስከ ጀሞ በግራም በቀኝም መኪና ማቆም ምንጊዜም አይቻልም፡፡ ተከፍሎበት እንኳን መኪና የሚቆምበት ቦታ የለም፡፡ ሲሚንቶ በሲሚንቶ ላይ በመደረብ የኮንክሪት ጫካ ብቻ ሆኗል፡፡
ባለ 6፣ ባለ 8 እና ባለ 10 ፎቅ ሕንፃ እንዲሠሩበት በሊዝ ቦታ የቸበቸበ የከተማ አስተዳደር የዛሬ ገቢውን ብቻ እያሰበ፣ የነገውን ቀርቶ የዛሬውንም ትውልድ ከግምት እንዳላስገባና የዕቅድ ችግር እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ እነዚህ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በአብዛኛው ከ10 እና ከ20 መኪና በላይ የሚያስቆም ቦታ የላቸውም፡፡ ባለጉዳይ መኪናውን የት ያቁም? የከተማው አስተዳደርና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የከተማው የትራፊክ ማኔጅመንት ሹማምንትና ባለሙያዎች የትም ያቁም የትም የእኛ ጉዳይ አይደለም? የከተማውን የሕዝብ መጓጓዣ (የአውቶቡስ) እንቅስቃሴ በማሳለጥ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበናል፡፡ የግል፣ የመንግሥት፣ የዕርዳታ ድርጅት፣ ወዘተ መኪና ይዘው በእነኚህ ሕንፃዎች ውስጥ ይሁን በዚህ መንገድ ዳር በሚገኙ ሌሎች ተቋማት ውስጥ ጉዳይ ያላቸው ውስጥ ለውስጥ የቱንም ያህል ርቀው አቁመው በእግር ሄደው ጉዳያቸውን መከታተል ይችላሉ፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ስህተት እንደ አብነት (Model) ተወስዶ በአንዳንድ ቦታዎች ከመኪና መንገድና ማቆሚያ ተቀንሶ ለአውቶቡስ ብቻ መሄጃ መደረጉ ነው፡፡ ከአንበሳ ጋራዥ እስከ ጃክሮስ፣ ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ ፓስተር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በቅርቡ ተሠርቶ ያለቀው ከማዘጋጃ እስከ ለገሐር ያለውም መንገድ ማሻሻያም ከላይ ከዘረዘርኳቸው ስህተትን በስህተት ከማረም የተለየ አይደለም፡፡ የከተማው አስተዳደር በዚህ መንገድ ግራና ቀኝ ከሚገኙ ባለይዞታዎች ጋር ተደራድሬ መንገዱን አሰፋለሁ ብሎ ወሰነ፡፡ ቀደም ሲል በተለይ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ፖስታ ቤት ድረስ ከመኪና ጋር መጋፋት የቀራቸው መንገድ ዳር የተሠሩ ሕንፃዎች የተሠሩት በዚሁ የከተማ አስተዳደር ቦታ ሽያጭና ፕላን የማፅደቅ ውሳኔ ነው፡፡ አሁን ገሚሶቹ ተቦዳድሰዋል፣ ገሚሶቹ ደግሞ በረንዳቸው ጠፍቷል፣ የተወሰኑት ደግሞ የፊት ለፊት ክፍሎቻቸው ተቀንሰው መጠነኛ ጥገና ተደርጎላቸው ጠበው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ማስተር ፕላን አለኝ የሚል የከተማ አስተዳደር ለምን ትናንትና መንገድ ዳር ቦታ በሊዝ ሰጥቶ ለእግረኛም ሆነ ለመኪና አመቺ ባልሆነ መንገድ ሕንፃዎች እንዲሠሩ ፈቀደ? ለምን ዛሬ ገና አሥር ዓመት እንኳን ያልሞላቸውን ሕንፃዎች መሸራረፍ አስፈለገው? ያን ጊዜ ማስተር ፕላኑ የተሠራው በእነ ባዶ ቦታውን ሙላ (Fill in the Blank…) መርህ በተመረቁ ባለሙያዎች ነበረ ማለት ነው? የአሁኖቹ ሹማምንትና ባለሙያዎች የዚያን ጊዜውን አሠራር ለሕንፃዎች ብቻ ያደላ ሆኖ ስላገኙት ለማረም ፈለጉ (Fill in the Blank…)፡፡ መርህ መተካት እንዳለበት ስለታመነ ማስተር ፕላኑ በዚህ መልክ ተከልሶ ሕንፃዎቹን በመቦደስ እንዲሠሩ አደረገ፡፡
በእርግጥ ከስምንትና ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ይህንን አስተያየት ሰጥቼ ቢሆን ፀረ ልማት ተብዬ እፈረጅ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ምናልባት የለውጡን ሒደት እንደምቃወም አድርጎ የሚፈርጀኝ በርካታ ሊሆን እንድሚችል እገምታለሁ፡፡ ፍረጃ አንዱ መለያችን በመሆኑ ቦታ ሳልሰጠው አልፋለሁ፡፡ ምንም ሆነ ምን ኢትዮጵያውያን በሩጫ ብቻ ረዥም ርቀት ጎበዝ መሆናችንን እንጂ በረዥም ዕቅድ አንታማም፡፡ የረዥም ርቀቱም ቢሆን ባለፈው የጃፓን ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሠራው የሚያሸብር ስህተት እምብዛም አልቀናንም፡፡ በሥራ ዕቅድ ግን ረዥም የሚለው ቃል መዝገበ ቃላታችን ውስጥ ያለ አይመስልም፡፡
እርግጠኛ ነኝ የዚህ ሥራም ሆነ የእርምቱ ስህተትነት በአመራር ላይ ላሉት ላይታያቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከብክነት አንፃር፣ ከሥነ ሕንፃ አንፃርና ከሥነ ውበት አንፃር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር የወጣባቸው ሕንፃዎች በረንዳ ወይም የተወሰነ ካሬ ሜትር ከክፍሎቻቸው ሲፈርስ ብክነት ነው፡፡ ከሥነ ሕንፃ አኳያ ደግሞ ባለሙያው አዕምሮውን ጨምቆ የቀረፀው ዲዛይን ሲቦደስ፣ በአደጋ መጠነኛ ይሁን ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንዳጋጠመው ሰው ወይም እንስሳ ነው የሚሆነው፡፡
በምንም ዓይነት በመጀመርያ የሥነ ሕንፃ ባለሙያውና የሕንፃው ባለቤት እንደቀረፁትና እንዳሰቡት አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡ ከሥነ ውበትም አንፃር ስንመለከተው አፍንጫው በተቆረጠ ጀበና ሊመሰል ይችላል፡፡ ምንም እንኳን አፍንጫው የተቆረጠ/የተሰበረ ጀበና ውስጡ ያለውን ቡና የተለየ ዘዴ ተጠቅሞ መቅዳት ቢቻልም፣ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በሙላት እንዳይሰጥ ሆኗል፡፡ ውበቱም ጎድፏል፡፡ ከአየር ብክለትም አኳያ ጥፋቱ ቀላል አይደለም፡፡ አንድም በማፍረስ እንድም በመጥበቡ ምክንያት፡፡ በእርግጥ በዚህ ለውጥ ምክንያት አንድ ትልቅ ጥሩ ነገር ዓይተናል፡፡ ይኸውም እግረኞች ለመጀመርያ ጊዜ የተመቻቸና ሰፊ መሄጃ አገኙ፡፡ ለብስክሌትም ለብቻው ማሽከርከሪያ ተሠራለት፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ዳገታማ መንገድ ላይ ቢሆን፡፡
ወደ ተነሳሁበት ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ይህ የባዶ ቦታውን ሙላ በሃይማኖትና በፖለቲካውም ውስጥ ሥር የሰደደ ጉዳይ ነው፡፡ በሃይማኖት ስንመለከት የራሱን ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ደንብ ይዞ በመገናኛ ብዙኃን፣ በስብከት፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ የሌላ ሃይማኖቶችን በማንቋሸሽ፣ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ቦታ እንዳያገኝ ማድረግ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት የተመሠረተው የራሱን እምነትና የሃይማኖቱን መርሆች ምዕመኖቹ በሚገባ ተረድተው ለሕይወታቸው መመርያ እንዲያደርጉት፣ በመልካም ሥነ ምግባር በማነፅ አርዓያ የሚሆኑ ሕይወታቸው ራሱ ምስክር የሚሆኑ ሰዎችን መፍጠር ነው፡፡ ምናልባትም የራሱን መልካም አስተምህሮ ወደውና አምነውበት ሌሎች እንዲከተሉት ነው፡፡ ይሁንና በቋሚ የስብከትና የትምህርት መርሐ ግብራቸውም ሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በሚለቋቸው አስተምህሮዎች ውስጥ፣ አንድ ሌላ ሃይማኖት የሚከተለውን ትምህርት በዝርዝር በመተንተን ትችት ሲያቀርቡ የሚሰሙ የቤተ እምነት መሪዎችና ሰባኪያን ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንዲያውም ከዚህ ዓይነት አስተምህሮ የተነሳ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ስድብ ቀረሽ ቃላት እየተጠቀሙ የቃላት ጦርነት የሚያደርጉ ታወቂ ሰባኪያንና የቤተ እምነት መሪዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰል የቃላት ጦርነት የሚደረገው ግብግብ ያው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያለውን ባዶ ቦታ በመሙላት ሌላኛው ቦታ እንዳያገኝ የማድረግ ሒደት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በትንሽ ግቢ ውስጥ ከሚጀመሩት ትንንሽ ቤተ ክርስቲያኖች አንስቶ እስከ ትልልቅና ነባር ቤተ ክርስቲያኖች ድረስ በኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚሰማ የድምፅ ማጉልያ በመጠቀም፣ የራሳቸውንም ሆነ የሌላ እምነት ተከታዮችን ነፃ የፀጥታ ቦታ በድምፅ በመሙላት ቦታ ማሳጣት መብት እስኪመስል ድረስ ተለምዷል፡፡ በተለይ ደግሞ በዓላትን ተከትሎ ሌሊት ሁሉ የዜጎች የፀጥታ ቦታ በዚህ ድምፅ መሞላቱ ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ከሌሊቱ በ8 እና 9 ሰዓት እዚያው ቤተ እምነቱ ግቢ ውስጥ ከሚገኘው ምዕመን ውጪ ማን እንዲሰማው ነው ያ ሁሉ ጩኸት? በቀንስ ቢሆን ለምን በግቢውና ከግቢው ዙሪያ ብቻ ለሚገኙ እንዲሰማ ተደርጎ ደምፁ አይመጠንም? በትንንሽ ቤቶች ኪራይ ከ40 እና ከ50 ሰው ጋር በሚደረግ ሥርዓተ አምልኮ ጎረቤትና መንገደኛው ሁሉ በድምፅ የሚረበሸው ለምን ይሆን? እንደ እውነቱ ከሆነ ለዚህች በአንድ ሰው ግቢ ወይም ሳሎን ውስጥ ለምትገኝ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ ማጉልያ አያስፈልግም፡፡ ግን ተከታይ የሚበዛው በመጮኽ ይመስል ለ20 እና 30 ሰው ነቅናቂ ድምፅ ማጉልያ ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የፀጥታ ባዶ ቦታቸውን በድምፅ ተሞልቶ ያገኙታል፣ ቢወዱም ባይወዱም፡፡
እንዳንዴ በዚሁ ጎልቶ በሚሰማው ድምፅ የሚተላለፈው መልዕክት/ስብከት የራሱ እምነት መሠረታዊ አስተምህሮና ሐሳብ ሳይሆን በእሱ እምነት ስህተት ነው ብሎ የሚያመነውን/የሚያስበውን የሌላ ሃይማኖት አስተምህሮና አደራረግ ሆኖ፣ ተከታዮቹ ከዚያኛው ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ጓደኛ እንዳይሆኑ፣ እንዳይቀራረቡ፣ የባሰባቸው ደግሞ በዚያ እምነት ተከታዮች ቤት ሄደው እንዳይሠሩም የሚያስተምሩ አሉ፡፡ ይኼኛው ደግሞ የሌላውን ሃይማኖትና ተከታዮቹን ባዶ ቦታ ከመሙላት አልፎ የራሱ ቤተ እምነት አባላት የአስተሳሰብና የአመለካከት ነፃነትን በመጫን በነፃ የማሰብ ቦታቸውን ይሞላዋል፡፡
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በተለያዩ ሰባኪያንና ምዕመናን የሚወረወሩ መልዕክቶች በጋራ የምንጋራቸውን ባዶ ቦታዎች በመሙላት በራሳቸው እምነትና አመለካከት ለመሙላት የሚደረጉ ጥረቶች በመሆናቸው፣ ተደጋግፎና ተጋግዞ ወደ ከፍታ ከማውጣት ይልቅ በመወነጃጀልና በመጠላለፍ ማናቸውም ወደ ላይ እንዳይወጡ የሚደረግ ሽኩቻ ነው፡፡ ሃይማኖት እንደ እኔ የመቀበል፣ የመቀባበል፣ ሌላውን እንደ ራስ የማየት፣ የሳተውን ደግሞ በትምህርትና በይቅርታ የመመለስ ሕይወት ነው፡፡
በፖለቲካው ዓለም ደግሞ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ ገና ድሮ በተማሪዎች እንቅስቃሴ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነቶች ሲኖሩ በሆደ ሰፊነት ከማስተናገድ ይልቅ፣ በተቻለ መጠን የተለየ አመለካከት ያለው ሰው/ቡድን ቦታ እንዳያገኝ ከመድረኩ እንዲጠፋ ማድረግ ዋነኛ አካሄዱ ነበር (Fill in the Blank Space)፡፡ በፖለቲካ በጣም ሥር መስደድ የጀመረው ከ1966 ዓ.ም. ለውጥ ጀምሮ ነበር፡፡ በለውጡ እጅግ በርካታ የሆኑ የማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች ነን የሚሉ ነገር ግን አንዳቸው ሌላኛቸውን እንደ አንጃ በመቁጠር ሐሳባቸውን ወይም አደራረጋቸውን ባለመጋራቱ ምክንያት ብቻ፣ በራሳቸው ሐሳብ ባዶ ቦታውን ለመሙላት እርስ በርስ መገዳደል ድረስ የደረሱት፡፡ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የባዶ ቦታውን ሙላ ቁንጮ ነበሩ ለማለት ያስደፍራል፡፡
‹‹አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት›› በሚል ሌላ ዓይነት ኢትዮጵያን በማይፈልግና በማይፈቅድ አመራር 17 ዓመት ስንመራ የመናገርና የማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የማሰብ ቦታችንም በኢሠፓአኮ በኋላ በኢሠፓ ተሞልቶ ነበር፡፡ አሳዛኙ ደግሞ ይህንን የተነፈገውን ባዶ ቦታ ለማስመለስ ጥረት የሚያደርጉት አንዳንዶቹ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ከመሪው ርዕዮተ ዓለም በመለየቱ ያንን ለመተካትና የራሳቸውን እንደ ብቸኛው አማራጭ ለማድረግ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት ሳይኖር ራሳቸውን እንደ እውነተኛውና ትክክለኛው የዚያ ርዕዮተ ዓለም አራማጆች ነን በሚል አስተሳሰብና አቋም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ያለውን ሌላ ሰውና ቡድን ቦታ በመንፈግ በራሳቸው ብቻ ያንን የአስተሳሰብ ቦታ መሙላት የሚሹ ናቸው፡፡ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የደርግ፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የኢማሌድኅ፣ የሕወሓት፣ የሰደድ፣ ወዘተ ልዩነቶች ነው፡፡ ሁሉም የማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች ነን የሚሉ ሆነው ሳሉ አንዳቸውም ለሌላኛቸው ቦታ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡:
በፖለቲካው ይህ አካሄድ ባህል ሆኖ በዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ እንደዚሁ የመንግሥት አሠራር ሆነ፡፡ ገና ከጅምሩ ምንም እንኳን ለብዝኃ አስተሳሰብና ለመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ቦታ አለኝ ብሎ ቢተርክ በመጀመርያ ቻርተሩ ሲረቀቅ አንስቶ ከብሔር ተኮር ፖለቲካ የተለየ አመለካከት/አቋም ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ታስቦበት እንዳይካተቱ መደረጉ፣ ቦታን በራስ ሞልቶ ሌላውን የመንፈግ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኋላም ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ በተመሳሳይ መዋቅራዊ በሆነ መልክ ብሔራዊ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ቡድኖች እንዳይካተቱ መደረጉ፣ የባዶ ቦታውን ሙላ አስተሳሰብ አራማጆች ተፅዕኖ ነው፡፡
የዚህ ባዶ ቦታውን ሙላ አራማጆች የመጨረሻ አሳዛኝና አስከፊ አካሄድ ደግሞ ከጅምሩ መነሻ ሐሳቡ ሰህተት የሆነ የብሔር/የዘውግ ፖለቲካ ጋር ተቆራኝቶ፣ እጅግ አስከፊ በሆነ መንገድ ባዶ ቦታን የመሙላት ሥራ መሠራቱ ነው፡፡ ለእኔ በቋንቋ ረገድ ብሔር የሚለው ቃል በምን ሁኔታ አንድን የቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ እንደሚወክል፣ ያው የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች የስታሊን አስተምህሮ ውላጆች በመሆናቸው (Nations, Nationalities, and Peoples) የሚል በተዛባ ትንታኔ ላይ የተመሠረተ አስተሳሳብ ላይ የተቃኘ ነው፡፡ ልብ ይበሉ ውላጅ እንጂ ልጅ አላልኩም፡፡ ልጅ በሕጋዊ ጋብቻ የሚወለድ ነው፣ ውላጅ ግን በሥውር ከአገልጋይ የሚወለድ ነው፡፡ ስታሊናዊ ርዕዮተ ዓለም በራሱ ማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለምን በማዛባት፣ ነገር ግን ማርክሳዊ ነኝ ብሎ የተቀመረ አመለካከት ነው፡፡ ራሱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ ይወስን የሚል ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ብቻ ሳይሆን ጠንሳሽም ነኝ ያለው ስታሊን አርሜንያን፣ አዘርባጃንን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ዩክሬይንን፣ ወዘተ በጉልበት በተባበሩት ሶቭየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ውስጥ ጨፍልቆ ቀላቀላቸው፡፡ ከ50 እና ከ60 ዓመት በኋላ ሶሻሊዝም ቀውስ ውስጥ ገብቶ ሲፍረከረክ እነዚህ ትንንሽ ውርሶች ራሳቸውን የቻሉ አገረ መንግሥታት ሆኑ፡፡
ታዲያ ዛሬም አገራችን በዚህ ባዶ ቦታውን ሙላ በሚል ቀመር የሚያስብ፣ አገር የሚያስተዳድር፣ የሚሰብክ፣ የሚያስተምር፣ መኪና የሚያሽከረክር፣ የከተማ ፕላን የሚቀርፅ፣ የከተማ፣ የክልልና የአገር መሬት የሚያስተዳድርና ፓርቲ የሚመራ ወዘተ ባለሙያና ባለሥልጣን የተሞላች አገር በመሆኗ ለመኖር፣ ለመናገር፣ ለመወያየትና ለመጻፍ ብሎም ለማሰብ ተቸግረናል፡፡
ቆም ብለን እናስብ፡፡ ሆላንድ ከአውሮፓ በካሬ ኪሎ ሜትር ሲሰላ በሕዝብ ብዛት ከፍተኛውን ትይዛለች፡፡ ይህም 508 ሰው በካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አሁን 115 ሰው በካሬ ኪሎ ሜትር ደርሰናል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው በሆላንድ ከተሞች እነ አምስተርዳምንና ሮተርዳምን ጨምሮ በጣም ትልልቅ ፓርኮችና በየመንደሩ ለአካባቢው ነዋሪ መናፈሻ የሚሆኑ የልጆች ነፃ መጫወቻ ያላቸው? እንዴት እንደ ሆላንድ ያሉ አገሮች በየከተማዎቹ በርካታ የአማተር ኳስ ሜዳዎች (ስታዲየም)፣ የአካባቢ የጋራ የጓሮ አትክልት እርሻዎች፣ የወጣቶች ማዕከላት፣ ፓርኮች፣ ወዘተ ሊኖሯቸው ቻለ? የእኛ የቀበሌ ኳስ ሜዳዎች ምን ሆኑ? በየሠፈሩ የነበሩ እንትን ጫካ፣ እንትን ሜዳ ይባሉ የነበሩት ምነ ሆኑ? በባዶ ቦታውን ሙላ አስተሳሰብ ኮንዶሚንየም፣ በሊዝ ተቸብችበው ፎቆች፣ በደምሳሳው የኮንክሪት ጫካ ሆነዋል፡፡ የሕዝብ ብዛት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ቆም ብለን እናስብ፡፡ ምናልባት ባዶ ቦታውን ሙላ (Fill in the blank space) የሚለውን ዘዴ ትተን ባዶ ቦታውን አልማ/አለምልም በሚል መተካት ይኖርብን ይመስለኛል፡፡ የመናፈሻና የኳስ ሜዳዎችን መሥራት መጀመሩ የሚበረታታ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡