Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ስታዲየሞችን ለማስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን...

ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ስታዲየሞችን ለማስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ገለጸ

ቀን:

  • ባለሀብቶች የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲገነቡ የሚያስችል መመርያ ረቋል

በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብተው የሚገኙ እንዲሁም እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞችን ለማስተዳደር ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቦ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምላሽ እንዳላገኘ ተገለጸ፡፡

የከተማዋ ስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ስታዲየምን እንዲሁም የአደይ አበባ ስታዲየምን ለማስተዳደር በ2011 ዓ.ም. ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አቅርቦ የነበረው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል፡፡

በከተማዋ ለረዥም ዓመታት ግልጋሎት ሲሰጥ የቆየውን የአዲስ አበባ ስታዲየም በከተማ ውስጥ ከመገኘቱ አንፃር ለማስተደደርና ለማልማት ይመች ዘንድ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ዕድሳት እየተደረገለት የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም በፌዴራል ደረጃ ግንባታው እየተከናወነ ቢሆንም፣ ከተማ አስተዳደሩ በባለቤትነት ተረክቦ በቅርበት እንዲያስተዳድረው ጥያቄ ሲቀርብ መክረሙ ተጠቁሟል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የአበበ ቢቂላና በአዲስ መልክ እየተገነባ የሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየሞችን እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ አዲስ አበባ ስታዲየምችን ለማስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ ተገንብተው የሚገኙ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና ማዕከላትን በበላይነት እየገነባ፣ እያለማና እያስተዳደረ የሚገኘው ቢሮ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቅጡ የማስተዳደር ችግር በመኖሩ መመርያ ደንብ መረቀቁ ተጠቁሟል፡፡

የመመርያ ደንቡ በከተማዋ የሚገኙ  የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንና የስፖርት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ እንዲሁም ስታዲየሞችን በበላይነት ለማስተዳደር የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር መመርያው ባለሀብቶች የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን እንዲገነቡና እንዲያለሙ የሚያስችል ሲሆን፣ መቆጣጠሩ የቢሮ ኃላፊነት እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ 

መመርያው በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ የተገነቡ ጅምናዚየሞች፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የግል ክብደት ማንሻ ቤቶች፣ ከረምቡላና ፑል ማጫወቻ ቤቶች፣ ሕጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው አገልግሎት መስጠት የሚያስችልበት ሕጋዊ ማዕቀፍ በውስጡ ያቀፈ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ 

በዚህም መሠረት ማንኛውም ግለሰብ በግሉ የሚከፍተውን የስፖርት ማዘውተሪያና ማዕከላት ሕጋዊ ፈቃድ እንዲኖረው ያስገድዳል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በከተማዋ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ጋር ተያይዞ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ችግሮች ሲነሱባቸው የቆዩ ሲሆን፣ በመመርያው መሠረት ችግሩ እንደሚፈታ አቶ በላይ ጠቁመዋል፡፡

 ደንቡ ረቆ ወደ ፍትሕ ቢሮ ማምራቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በጃንሜዳ የአራት ኪሎ የስፖርት ትምህርት ሥልጠና ማዕከል፣ ራስ ኃይሉ ስፖርትና ትምህርት ሥልጠና ማዕከል፣ አበበ ቢቂላ ስታዲየም፣ አቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም፣ አዲስ አበባ ቴኒስ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል፣ እንዲሁም ቆሼ ትምህርትና ስፖርት ማሠልጠኛ ማዕከላትን እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

ከእነዚህም መካከል የአቃቂ ቃሊቲን ስታዲየም ግንባታ በአዲስ መልክ የጀመረ ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ የሆነው ሳር ያለው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ደረጃውን ለመጠበቅ እድሳት እንደሚደርግለት ተጠቁሟል፡፡

በተለይ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ወንበርና ጣሪያ ገጠማ ቢደረግለትም፣ የሜዳው አርተፊሻል ሳር ለእግር ኳስ አመቺ አለመሆኑንና በስታዲየም ውስጥ አትሌቲክስን ማሰናዳት የሚያስችል መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ቅሬታዎች ሲነሱ ከርመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...