በሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን አስተዳደር ባጋጠመው ድርቅ በርካታ እንስሳት መሞታቸውን፣ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉንና ከአቅም በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከኦሮሚያ የቦረና ዞን ጋር የሚዋሰነው ዞኑ፣ በድርቅ የተነሳ ከሚሞቱ እንስሳት አልፎ ሰዎች ለሆስፒታል እየተዳረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሀቢቻ የድርቁ ጉዳት ከዞኑ አቅም በላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዞናችን ከቦረና ጋር በሁለት ወረዳዎች በኩል ይዋሰናል፡፡ ወደ 700 ሺሕ የሚጠጋ አርብቶ አደር ነዋሪ ያለው ሲሆን፣ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የደረሰው ድርቅ ከብቱን በሙሉ ጨርሶበታል፤›› ብለዋል፡፡
በክልሉ አደጋ ሥጋት ቢሮና በተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች ርብርብ ዘንድሮ ለድርቁ ተጎጂዎች ዕርዳታ እየቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዕርዳታው በቂ አለመሆኑንና ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን በመጥቀስ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹በኦሮሚያ ክልል ለሚገኘው ለአጎራባቻችን ቦረና ዞን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንዳለው ሁሉ፣ ለእኛም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይድረሱልን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ዳዋ ዞን በሥሩ ሞያሌ፣ ሙባረክ፣ ካደዱማና ሁደት የተባሉ አራት ወረዳዎች እንዳሉት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡ ዞኑ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለማግኘቱ ትልቁ የዳዋ ወንዝ ጭምር መድረቁን፣ ድርቅ የሚቋቋሙ ግመሎችን ጨምሮ ከብቶችና ፍየሎች በከፍተኛ ቁጥር ማለቃቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕዝቡ የሚኖረው በከብቶቹ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ድርቁ እስከ መቼ እንደሚቀጥል አይታወቅም፡፡ ለሕዝቡ አስቸኳይ ዕርዳታ ካልደረሰለት አደጋው ከአሁኑ ሊብስ ይችላል፤›› በማለትም አሳስበዋል፡፡ የሞተውን የእንስሳት ሀብት ቁጥር ገና እየተጠና መሆኑንና በሰዎች ላይ የደረሰውንም ጉዳት እየተገመገመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ስለጉዳቱ የተጣራ አኃዝ ባይኖራቸውም፣ በምግብ እጥረት ችግር ወደ ሆስፒታል የገቡ ሰዎች መረጃ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ዓምና በሶማሌ ክልል ካሉ 11 ዞኖች በአሥሩ ከባድ የድርቅ አደጋ ደርሶ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ እንስሳትን መግደሉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ አደጋ ገና ያላገገመው ዳዋ ዞን ዘንድሮም ከባድ አደጋ እንደገጠመው ከወዲሁ ይፋ አድርጓል፡፡
ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል ቦረና የደረሰው ከባድ ድርቅ ከ700 ሺሕ በላይ እንስሳትን መግደሉ አሳሳቢ አደጋ እየተባለ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ለቦረና ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የድርቅ አደጋ በቦረና ወይ በዳዋ ዞኖች ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን የተለያዩ መረጃ ምንጮች እየጠቆሙ ነው፡፡ የሀመር አካባቢን ጨምሮ በድርቅ ጉዳት የገጠማቸውና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚሹ ብዙ አካባቢዎች መኖራቸው በአሳሳቢነት እየተነገረ ነው፡፡